Skip to main content
x
ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

  • የፋይናንስ ተቋማት ሕግጋት ይከለሳሉ
  • የመንግሥታዊ ተቋማት ክፍያ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ እንዲፈጸም ይደነግጋል
  • የፋይናንስ ተቋማት ከአዲሱ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ አደረጃጀት ይኖራቸዋል

የአገሪቱን የፋይናንስ አገልግሎትና ተደራሽነት ወደ ላቀ ደረጃ ያራምዳል የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ፡፡ ስትራቴጂውን ለመተግበር የፋይናንስ ኢንዱስትሪው የሚመራበት አዳዲስ ሕግጋትና ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ታወቀ፡፡

የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ አጠቃላይ አሠራር ይለውጣል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ስትራቴጂ ሰኞ መስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተፈጻሚ የሚያደርጉት አዲስ ግብ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት ሚና ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን፣ በተለይ የፋይናንስ ተቋማት በአጠቃላይ አገልግሎታቸው ውስጥ መፈጸም ይገባቸዋል የተባሉ ክንዋኔዎችን ያካተተ ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተደራሽነት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲመዘን እንኳን፣ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ይህንን ከፍ ለማድረግ ስትራቴጂው ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡ ስትራቴጂው ሁሉን አቀፍና ዘመናዊ የሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን በ2012 ዓ.ም. ተረጋግጦ ማየት የሚል ራዕይ አለው፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ ድህነት ቅነሳን፣ የፋይናንስና የገንዘብ ሥርዓት መረጋጋትን ለማገዝ በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡ የተለያዩ፣ ተስማሚና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የፋይናንስ ምርቶችና አገልግሎቶች ፈጠራ በታከለባቸውና አመቺ በሆኑ ዘዴዎች ለሁሉም ግለሰቦችና ድርጅቶች ተደራሽ ማድረግ›› ደግሞ የስትራቴጂው ተልዕኮ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ስትራቴጂው የፋይናንስ ተቋማት ለተለያዩ ዘርፎች መሰጠት ያለባቸውን የብድር መጠን ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ካላቸው ጠቀሜታ አንፃር ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለግል ዘርፍ ከሚሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ 15 በመቶውን ለእነርሱ ማበደር እንደልባቸው ይገልጻል፡፡ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በተቀመጠው የስትራቴጂው ዕቅድ ውስጥ፣ አሥር በመቶ የነበረው የጎልማሶች ብድር ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲልም ግብ ተቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ ለግብርና ዘርፍ የሚሰጥ ብድርም በስትራቴጂው ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. ለዘርፉ የሚሰጠው የብድር መጠን ምን ያህል መሆን እንደሚገባው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ግብርና ከአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 38.7 በመቶ፣ ከጠቅላላ የሥራ ሥምሪት ደግሞ 85 በመቶ ድርሻ ቢኖረውም ዘርፉ ከባንክ የሚያገኘው ብድር ድርሻ 10.4 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በአዲሱ ስትራቴጂ መሠረት ግን ለግሉ ዘርፍ ከሚሰጠው ጠቅላላ የባንክ ብድር ውስጥ የግብርና ብድር ድርሻ በስትራቴጂው የዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ ወደ 15 በመቶ ማደግ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎት እንደሚያገኙ ሪፖርት የሚያደርጉ ጎልማሶችን ወደ 60 በመቶ ማሳደግ የሚል ግብ ያስቀመጠው አዲሱ ስትራቴጂ፣ ከፋይናንስ አገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ዙሪያ እንደሚኖሩ ሪፖርት የሚያደርጉ ጎልማሶችን ቁጥር ደግሞ ወደ 80 በመቶ ከፍ ማለት እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡ በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት መቆጠባቸውን ሪፖርት የሚያደርጉ ጎልማሶች በ2012 ዓ.ም. 40 በመቶ ማድረግም ሌላው ግብ ነው፡፡

በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴዎች መጠቀማቸውን የሚያረጋግጡ ጎልማሶች በ2012 ዓ.ም. 40 በመቶ ማድረስ፣ ስለመሠረታዊ የባንክ ሒሳብ አከፋፈት ግንዛቤ ያላቸው ደግሞ 80 በመቶ እንዲሆኑ ማድረግም በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ እንደ ግብ ተቀምጧል፡፡   ከዚህም በተጨማሪ እነዚህን ስትራቴጂዎች ለመተግበር የሚያስችሉ 49 ዋና ዋና ሥራዎች የተቀመጡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ዝርዝር መርሐ ግብር እንደ ተዘጋጀ፣ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚከናወኑ ዋና ዋና ግቦችና ተያያዥ መለኪያዎችም በተመሳሳይ በዝርዝር እንደተዘጋጁ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመንግሥት፣ በግለሰቦችና በድርጅቶች የሚደረጉ ክፍያዎች በአብዛኛው የማፈጸሙት በጥሬ ገንዘብ፣ በቼክና በክፍያ ማዘዣዎች ነው፡፡ ስትራቴጂው በባንክ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲፈጸሙ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ይህም የግብይት ወጪን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመቀነስና የሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነትን ለማሻሻልም ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አቶ ተክለ ወልድ ገልጸው፣ ‹‹የተጠቀሱት ግቦች ሲሳኩ ደግሞ ቁጠባ ይበረታታል፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤›› ብለዋል፡፡ አዳዲስ የማምረቻ ኢንዲስትሪዎችና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እንዲስፋፉና እንዲያድጉ በማስቻል ለሥራ ዕድል ፈጠራ በር እንደሚከፍትም ጠቁመዋል፡፡ ይህም የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር በማድረግ ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደሚወስድም አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ አካታችነት ዝቅተኛ እንዲሆን ያስቻሉ ምክንያቶችን ለመቅረፍ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበሩ አራት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች መነደፋቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም አደረጃጀት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ያላቸው የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ጠንካራ ድጋፍ እንዲሰጡና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እንደሚጠበቅ ያመለከቱት ደግሞ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው፡፡ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በሚኒስቴሩና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ኤጀንሲዎች የሚፈጸሙ ክፍያዎች በባንክ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ በማሳሰብ፣ ተቋማት የክፍያ ሥርዓታቸውን ከአዲሱ አሠራር ጋር ማዛመድ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡

ይህም የደመወዝ፣ የጡረታ፣ የሴፍቲኔትና ሌሎችንም ክፍያዎች ያካተተ ሲሆን፣ የኢትዮ ቴሌኮምና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተንቀሳቃሽ ስልክ ሥርጭትን ማስፋፋትና የኔትወርክ ጥራት ደረጃን ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሚከናወኑ የኤሌክትሮኒክስ የፋይናንስ ልውውጦችን አስተማማኝ እንዲሆኑ ማስቻል በዕቅድ ዘመኑ መፈጸም አለባቸው ከተባሉት ክንውኖች  ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የስትራቴጂውን ሙሉ ትግበራ በዋናነት ከማስፈጸም ጎን ለጎን የቁጥጥርና የሱፐርቪዥን ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ የሚቀርቡ ምርቶች፣ አገልግሎቶችና የአገልግሎት መዳረሻዎች ፈቃድ አሰጣጥ ሒደትን ከስትራቴጂው አቅጣጫ ጋር በማቀናጀትና በማሳለጥ፣ በስትራቴጂው የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ የራሱን ድርሻ እንደሚወስድ አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ መመርያዎችን እንደሚቀርፅና ተግባራዊነታቸውንም እንደሚከታተል ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ስትራቴጂ ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ ለፋይናንስ አካታችነት በተለይ ደግሞ ለአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች፣ የፋይናንስ ምርቶች የአቅርቦት ዘዴዎችና ለመሳሰሉት የሚያስፈልግ መመርያ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለክፍያ ሥርዓት ተዋንያን ለክፍያ መፈጸማያ መሣሪያ አቅራቢዎች መመርያ እንደሚያወጣም ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ሌላ የአገልግሎት አቅራቢዎችን ሚና፣ ቁጥጥርና ክትትል እንደገና እንደሚገመግም የሚያሳየው መረጃ ከወረቀት ሰነድ አያያዝ ጋር የተያያዙ ሕጋዊ ግዴታዎችን፣ እንዲሁም የወኪል ባንኪንግ መመርያን ይከልሳል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግን የሚመለከት መመርያ እንደሚያወጣ፣ እንዲሁም ጤናማ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማበረታታት ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎቶች ፈቃድ አሠራር ሥርዓትን እንደሚከልስ ታውቋል፡፡

አገልግሎች ሰጪ መሥሪያ ቤቶች የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች በባንክ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ እንዲፈጸሙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተገልጿል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ኩባንያዎች ተጨማሪ ኃላፊነት ይኖርቦቸዋል፡፡ አቶ ተክለ ወልድ ከሰሞኑ የተከሰተውን የሞባይል ቅድመ ክፍያ ካርድ ዕጦትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን አገልግሎት ካርድ ከመፋቅ ማውጣት እንደሚቻልና ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዘመናዊ አገልግሎት መጠቀም እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡ የሞባይል ካርድ አገልግሎት በዚህ ዘመናዊ አሠራር መለወጡም ለባንክ አገልግሎት መስፋፋትም ይጠቅማል ብለዋል፡፡

ለዚህ ስትራቴጂ መሳካት እንደባለድርሻ ኃላፊነት አለባቸው ከተባሉት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የፋይናንስ ዕውቀትና ክህሎት በመደበኛ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ፣ ስትራቴጂያዊ ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት ተብሏል፡፡

ስትራቴጂው እንደተመለከተው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ 83 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች እንደ ኤቲኤም ያሉ አገልግሎቶችን አይጠቀሙም፡፡ ከአገሪቱ የባንክ ደንበኞች 9.3 በመቶው ብቻ በኤቲኤም የሚጠቀሙ መሆናቸውን ከስትራቴጂው ጋር የቀረበው ጥናት አሳይቷል፡፡ ይህ የኤቲኤም ተገልጋይ ቁጥር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ለማሳየትም፣ በታንዛኒያ ከባንክ ደንበኞች 62 በመቶ የኤቲኤም ተጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በዛምቢያ ደግሞ 68 በመቶ ይደርሳል፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው ክፍተት በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ለአብነትም በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ላይ ካሉ ኢንዱስትሪዎች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የብድር ጥያቄያቸው አዎንታዊ መልስ አላገኘም፡፡

በተወሰኑ የፋይናንስ አካታችነት አመላካቾች መሠረት ሰኔ 2009 ዓ.ም. የተደረሰበት ዕድገት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ የባንክና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ቁጠባ ሒሳብ ቁጥር የ33 በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 43.8 ሚሊዮን አድጓል፡፡ የባንክ ቅርንጫፎች ቁጥር 34 በመቶ አድጎ 4,227 ደርሷል፡፡  የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች ቁጥር የአራት በመቶ ዕድገት በማሳየት 1,748 መድረሱን አቶ ተክለ ወልድ ገልጸዋል፡፡ የመድን ድርጅት ቅርንጫፎች ቁጥር 492 የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የ15 በመቶ ዕድገት መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡

የክፍያ መፈጸሚያ ነቁጦች (POS) ቁጥር ወደ 8,895 ሲደርስ፣ የክፍያ መፈጸሚያ ማሽኖች (ATM) ቁጥር ደግሞ የ62 በመቶ ዕድገት በማሳየት 2,743 ደርሷል፡፡ የ76 በመቶ ዕድገት አሳይቷል የተባለው የወኪል ባንኪንግ አገልግሎት ደግሞ 10,481 ደርሷል፡፡

የመድን ፖሊሲ ቁጥር ወደ 949 ሺሕ የደረሰ መሆኑን፣ ይህም የ21 በመቶ ዕድገት መኖሩን ያመለክታል፡፡ የባንኮች ቁጠባ የ29.8 በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 568.8 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ብድር ደግሞ በ23.9 በመቶ አድጎ 560.8 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ጠቁመዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የአገሪቱ የፋይናንስ አካታችነት ከሌሎች አዳጊ የአፍሪካ አገሮች አንፃር እንኳ ሲታይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ተክለ ወልድ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሆኑ ጎልማሶች ብዛት 22 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች አማካይ 34 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ ለዚህም ብዙና ተደጋጋፊ ምክንያቶች እንዳሉት የጠቆሙት ገዥው፣ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2014 በተደረገ የዓለም ባንክ የዳሰሳ ጥናት ውስጥ ከተካተቱ ጎልማሶች መካከል 78 በመቶዎቹ አነስተኛ ገንዘብ ለመበደርም ሆነ ለመቆጠብ ወደ መደበኛ ባንክ መሄድ አያስፈልግም የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው፣ 12 በመቶዎቹ ደግሞ የፋይናንስ አገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች ርቀት አገልግሎቱን እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው ጥናቱ ካስቀመጣቸው መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ ዋናዎቹ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ስትራቴጂ ተግባራዊ መሆን ዘርፉ አዳዲስ አሠራሮችን እንዲከተል የሚያስገድደው ይሆናል፡፡ በተለይ የፋይናንስ ተቋማት መተግበር ይገባቸዋል ተብሎ በስትራቴጂው ከተቀመጡት ውስጥ ራሳቸውን በአዲስ አደረጃጀት መገንባት ተጠቃሽ ነው፡፡ በስትራቴጂውም በግልጽ እንደተቀመጠው የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ የፋይናንስ ምርትና የሥርጭት ዘዴዎችን ለማጠናከር፣ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን በብቃት ለማስተዳደር እንዲቻል የሥራ አመራር የመረጃ ሥርዓታቸውን መዘርጋትና ለዚህም መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡  

ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂን ለማስፈጸም ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ካውንስል የተቋቋመ ሲሆን፣ የፋይናንስ አካታችነትን የማስፋፋት ተልዕኮ ያለውና የፖሊሲ አውጪ አካል ይሆናል ተብሏል፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይሆናል፡፡ ራሱን የቻለ የፋይናንስ አካታችነት ጽሕፈት ቤት በብሔራዊ ባንክ ሥር የተቋቋመ ሲሆን፣ በሥሩም የተለያዩ ማስተባበሪያዎች አሉት፡፡