Skip to main content
x
የማይካስ ጉዳት

የማይካስ ጉዳት

መጠነኛ ስፋት ባለው ክፍል ውስጥ ወደ 400 የሚሆኑ የሕግ ታራሚዎች ይኖራሉ፡፡ በክፍሉ ውስጥ የሚገኙት አልጋዎች 100 ሰዎችን ማስተናገድ እንኳ አይችሉም ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ አልጋ ላይ የማደር ዕድል ማግኘት እንደባለፀግነት ወይም እንደ ባለዕድል ሊያስቆጥር ሁሉ ይችላል፡፡

ምሽት ላይ እንደ ግምጃ ቤት ንብረት በጥንቃቄ እየተቆጠሩ ወደ ማደሪያቸው ሲገቡ አልጋ ያለው በየአልጋቸው ላይ ሲወጡ የሌላቸው መሬት ላይ በሚዘረጋው ሰማያዊ ሸራ ላይ ይጋደማሉ፡፡ የኮንትሮባንድ ዕቃ ይመስል በክፍሉ ታጭቀው ከሚኖሩት ታራሚዎች መካከል አቶ የሺጥላ ታደሰ አንዱ ነበሩ፡፡

‹‹አተኛኘታችንን የሚያስተካክሉ አስተኚዎች አሉን፡፡ በጣም ብዙ ከመሆናችን የተነሳ ሁላችንም በአንድ ጎናችን ብቻ ነው መተኛት የምንችለው፡፡ እንደዛም ሆኖ ቦታ ስለማይበቃ ክፍት ቦታ እንዳይኖር በጣም እያጠጋጉን እንድንተኛ ያደርጉናል፡፡ አተኛኛችንን ‹ደቦቃ› እንለዋለን፤›› አሉ አደራደራቸውን በእጃቸው እያሳዩ፡፡ ከአገላለጻቸው ወለሉ ላይ የሚደረደሩት ሰዎች ሳይሆኑ የጣውላ ክምር ነው የሚመስለው፡፡

 እንቅልፋቸውን እረፍት ሳይሆን ሥቃይ ያደረገው ደቦቃ በተባይ የታጀበም ነበር፡፡ ‹‹እጃችንን ወደ ጀርባችን ከላክን ሦስት አራት ቅማል ይዘን ነው የምንወጣው፤›› አሉ ፊታቸውን በሐዘን ቅጭም አድርገው፡፡ በከተማው በሚገኝ አንድ ማረሚያ ቤት  ውስጥ ያሳለፏቸው ሌሎችም ከባድ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ድክድክ ማለት ያልጀመረችን አራስ ልጅ ደፍረው፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሰው ገድለው ከታሰሩ ወንጀለኞች ጋር አንድ መጠለያ መጋራታቸው፣ ሲያልፍም ጎን ለጎን ማደራቸው ሰቀቀን ሆኖባቸው ነበር፡፡ ‹‹ሁሉም ለበጎ ነው፤›› ብለው ወደ ፈጣሪያቸው እንዳይመለሱ ደግሞ ምዕመናንን በማጭበርበር ወንጀል ተፈርዶባቸው ወደ ማረሚያ ቤቱ የሚላኩ የሃይማኖት አባቶችን ሲመለከቱ ነገር ዓለሙ ግራ ይሆንባቸዋል፡፡

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት የ40 ዓመቱ አቶ የሺጥላ፣ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥበቃ ሠራተኛነት ያገለግሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የፐርቼዚንግ ትምህርት በመማራቸውም ከጥበቃ ተነስተው ወደ ስቶር ክፍል ተዛውረው መሥራታቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ያህል በስቶር ውስጥ እንደሠሩም ወደ ሌላ ክፍል ተዛወሩ፡፡

የነበሩበትን የሥራ ክፍል ሲለቁ ፈርመው የተቀበሉትን ፈርመው በማስረከብ ነበር፡፡ ይሁንና ክፍሉን ከለቀቁ ከሁለት ዓመታት በኋላ በቀድሞ የክፍል አለቃቸው፣ በእሳቸውና በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መርታችኋል በሚል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ መሠረተባቸው፡፡ ‹‹በመጀመርያ አለቃዬ ላይ እንድመሰክር ነበር የተጠየቅኩት፣ በጉዳዩ ምንም የማውቀው ነገር ስላልነበር ምንም ብዬ የምስክርነት ቃል መስጠት አልቻልኩም፡፡ ከዚያም ሁላችንም በዚያው ወደ ቤታችን ሳንገባ ቀረን ታሰርን፤›› በማለት ማረሚያ ቤት የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

ከ707 ሺሕ ብር በላይ አጉድላችኋል በሚል መከሰሳቸውን ሲሰሙ ‹‹ሕይወቴን ሙሉ አገኘዋለሁ ብዬ የማላስበው ገንዘብ ነው፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አናግታችኋል የተባልን ነበር መሰለኝ፤›› የሚሉት አቶ የሺጥላ የተከሰሱበትን የገንዘብ መጠንና አቅማቸውን ሲያስተያዩ የሰማይና የምድር ያህል ቢርቅባቸው መፍትሔያቸው ማልቀስ ብቻ ሆነ፡፡ በተለይም በእረፍት ቀናቸው ሊጠይቋቸው የሚመጡ ልጆቻቸውን ሲያዩ ሐዘናቸው ይበረታል፡፡ ሆድ ይብሳቸውና ያለቅሳሉ፡፡

በመጀመርያ የችሎት ውሏቸው ዓቃቤ ሕጉ መረጃ አለማሟላቱንና ገና ያልተያዘ ሌላ ሰው መኖሩን ለፍርድ ቤት ስላስረዳ የአሥር ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲመለሱ ነበር የተደረገው፡፡ የመጀመርያው ቀጠሮ ሌሎች በርካታ ቀጠሮዎችን አከታትሎ ነበረና ጥፋተኛ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ዓመት አለፋቸው፣ ወራትም ተቆጠሩ፡፡

 በማረሚያ ቤቱ በቆዩባቸው በእነዚህ ጊዜያት ካሳለፉት የሥቃይ ኑሮ ባለፈ የቤተሰቦቸው ሁኔታ ያሳስባቸው ነበር፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ ልጆቻቸውን ማስተዳደር ያቃታቸው ባለቤታቸው ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንዲመለሱ መገደዳቸው ደግሞ የተሸናፊነት ስሜት አሳድሮባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ውጣ ወረድና አሥራ ዘጠኝ ወራት በማረሚያ ቤት ከቆዩ በኋሏ የሥር ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲለቀቁ የትዕዛዝ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

 ‹‹ምስክር ሆነው ከቀረቡ ሰዎች መካከል አንዱ እንኳን የሚያውቀኝ አልነበረም፡፡ በዚያ ላይ መረጃ ተብለው በቀረቡት በየትኛውም ሰነድ ላይ የእኔ ስም አልነበረም፤›› የሚሉት አቶ የሺጥላ ዓቃቤ ሕጉ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንዳለና፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዳፀናው ይናገራሉ፡፡ ነፃ መውጣታቸው ትልቅ ዕፎይታን የሰጣቸው ቢሆንም ሕይወታቸው ግን ወደነበረበት ሊመለስ አልቻለም፡፡

ይሁንና ባልፈጸሙት ወንጀል ለእስር መዳረጋቸው ካደረሰባቸው የሞራልና ቁሳቁስ (ማቴሪያል) ጉዳት እስካሁን አላገገሙም፡፡ እንደተፈቱ ከሰው መቀላቀልም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መግባባት ተስኗቸው ነበር፡፡ ወደ ሥራቸው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱም ሁኔታውን አባብሶባቸው ነበር፡፡

ከእስር ከተፈቱ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንኳንስ በእስሩ ለደረሰባቸው ጉዳት መካሻ ይቅርና ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሕይወት መመለስ የዳገት ያህል ከብዷቸዋል፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ለመቀጠር ያደረጉት ሙከራ እስካሁን አልተሳካም፡፡ ቀጣሪ ድርጅቶቹ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለ19 ወራት መታሰራቸውን የሚያሳየውን ማኅደራቸውን ሲመለከቱ ሐሳባቸውን ይቀይራሉ፡፡

‹‹በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በጥበቃ ለመቀጠር አስፈጊላውን ሁሉ አሟልቼ ተመረጥኩኝ፡፡ አሟላ ያሉኝን ሁሉ አሟልቻለሁ፡፡ ዋስ ጠርቻለሁ፡፡ አሻራ ሳይቀር ሰጥቻለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ ክሊራንሴን ሲመለከቱ ደንግጠው አንፈልግህም አሉ፤›› የሚሉት አቶ የሺጥላ መሰል አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በራስ መተማመኔ ጠፍቷል፡፡ ለሥራ ማመልከት ሁሉ መፍራት ጀምሬአለሁ፤›› ይላሉ፡፡

ሕግ ለሰው ልጆች አብሮ መኖር ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሰዎች እርስ በርስ የሚኖራቸው መስተጋብር ማኅበረሰባዊ፣ ዘልማዳዊ፣ አሊያም ዘመናዊና የተፃፉ ሕጎች መሠረት ከሌለው በቅፅበት ጊዜ ውስጥ ምን ሊፈጠር፣ ማን ምን ሊገጥመው እንደሚችል ዋስትና አይኖርም፡፡ ከዚህ አንፃር ሕግ የአብሮነት መሠረት፣ የደኅንነት ዋስትናና መተማመኛ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሕግ አምላክ ሲባል የማይበርድ ፀብ የለም፡፡ አንገቱን የማይደፋ ወንጀለኛ የለም፡፡ ለተበደለ ፍትሕ፣ ለጥፋተኛ ደግሞ ተገቢውን ቅጣት በመጣል የሕይወትን ሚዛን ማስተካከል ዋነኛ የሕግ መገለጫው ነው፡፡

 ሰላምና ፍትሕን የማስፈን ሚና ያለው የሕጉ ሥርዓት በተገቢው መንገድ ተተርጉሞ ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቶ ንፁኃን ያለ ወንጀላቸው የሚቀጡበት፣ ፍትሕ የሚዛባበት፣ ወንጀለኛ ነፃ የሚወጣበት ይሆናል፡፡ ለዚህም የሕግ የበላይነት አለመኖር፣ የዳኞች የነፃነት ጉዳይ አጠያያቂ መሆን በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የሕጉ የአተገባበር ችግር ተጠርጣሪን ከመያዝ ይጀምራል፡፡

በሕጉ መሠረት አንድን ሰው በወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ምክንያታዊ የጥርጣሬ መነሻ ሊኖር፣ በሌላ አገላለጽ ግለሰቡ በእርግጥ ወንጀሉን ሊፈጽም ይችላል የሚል ጥርጣሬ መፍጠር የሚችሉ መረጃዎችን መሰብሰብ ግድ ይላል፡፡ ከመያዙ አስቀድሞም እንደ ወንጀሉ ዓይነት ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው መረጃ መጠናቀር አለበት፡፡ ‹‹አንድ ሰው በቀጥጥር ሥር ሲውል የተለያዩ መብቶቹ ይገደቡበታል፡፡ ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ግለሰቡን በወንጀል ሊያስጠረጥሩ የሚችሉ መረጃዎች አስቀድሞ መሰብሰብ ያለባቸውም በንፁኃን ላይ እነዚህ ገደቦች ጫና እንዳይፈጥሩ ለመከላከል ነው፤›› የሚሉት ጠበቃና የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ አመሀ መኰንን ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ በፖሊስ የግል ውሳኔ አሊያም በሌላ ዓላማ አንድን ግለሰብ በወንጀል ተጠርጥሯል ብሎ መያዝ ሕገ ወጥነት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

በዚህ መንገድ ከታሰረ በኋላ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳያስፈልገው ፖሊስ በሰውዬው ላይ ክስ መመሥረት የሚያስችለው ተጨማሪ መረጃ ከሰውየው ለማግኘት ተጠርጣሪውን ለ48 ሰዓታት ሊያቆየው ይችላል፡፡ ፖሊስ በእነዚህ ሰዓታት ውስጥ የሚፈለገውን መረጃ ማግኘት ካልቻለ ለተጨማሪ ጊዜ የፍርድ ቤት ፈቃድ መጠየቅ ግድ ይለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሚፈቅደው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደ ወንጀሉ ዓይነት የተለያየ ነው፡፡ በመደበኛ የወንጀል ሕግ ለሚታዩ ጉዳዮች በአንድ ጊዜ የሚፈቀደው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 15 ቀን ነው፡፡ ‹‹ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን ክብደትና የተሰበሰበውን የመረጃ መሠረት በማድረግ ከ15 ቀናት ያነሰ ጊዜ አሊያም 15 ቀን ሊፈቅድ ይችላል፤›› ይላሉ አቶ አመሀ፡፡

የተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አልበቃ ካለ ሌላ ማስጨመር ይችላሉ፡፡ ለዚህ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም፡፡ በዚህ ላይ ፖሊስም ለሚጠይቀው፣ ፍርድ ቤቱም ለሚፈቅደው፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ምክንያታዊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ነገር ግን በተግባር ሲታይ ብዙ ችግር አለ፡፡ ፖሊስ በዘፈቀደ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ፍርድ ቤትም እንደዚሁ ላልተወሰነ ጊዜ ሲፈቅድ ይታያል፤›› በማለት አቶ አመሀ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን በተመለከተ ገደብ አለመኖሩ አንቀጹ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል መንገድ መክፈቱን ይናገራሉ፡፡ በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች በተለይም በአንድ ወቅት ብዙ በተሠራበት በአደገኛ ቦዘኔ አዋጅ ፖሊስ የሚጠይቀውን ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በ28 ቀን ገድቦታል፡፡ በፀረ ሽብር አዋጁም በአንዴ ከ28 ቀን በላይ ደግሞ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ አይችልም፡፡ አጠቃላይ የሚጠየቀውን የምርመራ ጊዜም ከአራት ወራት እንዳይበልጥ ተገድቧል፡፡         

በአጠቃላይ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ግን የሚሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በሕግ የተገደበ አለመሆኑ ትልቅ የሕግ ክፍተት ሆኖ ይታያል፡፡ ‹‹ሰዎችም ለረዥም ጊዜ በተጨማሪ የምርመራ ቀን ምክንያት ሲቆዩ እናያለን፡፡ ይህ የቆየ ችግር ነው፤›› ይላሉ አቶ አመሀ፣ ይህ ዋነኛ የሕግ ክፍተት በመሆኑ መረጃ እስኪጠናቀር በሚል ሰዎች ጥፋተኛ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ለወራትና ለዓመታት እንደ ወንጀለኛ ታስረው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል፡፡ አቶ የሺጥላ እንደሚሉት ደግሞ አለጥፋታቸው በስመ ሞክሼ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ያጋጥማሉ፡፡

በምርመራ ላይ ሆነው ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሠረትባቸው ለረዥም ጊዜያት ታስረው፣ ነገር ግን የተሰበሰበው መረጃ ክስ ለመመሥረት በቂ አይደለም በሚል፣ ክስ ተመሥርቶ መከላከል ሳይስፈልጋቸው አሊያም ተከላክለው ከዓመታት እስር በኃላ በነፃ እንዲሰናበቱ የሚደረጉ ጥቂት አይባሉም፡፡

‹‹ሁኔታው እነዚህ ሰዎች ከመታሰራቸው አስቀድሞ ፖሊስ ምክንያታዊ ጥርጣሬ የሚፈጥር መረጃ አላሰባሰበም ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፤ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ መግባትና ክስ ሊመሠረትባቸው ይገባ ነበር ወይ የሚል መሠረታዊ ጥያቄም ያጭራል፤›› የሚሉት አቶ አመሀ፣ በእስር የሚቆዩ ሰዎች በሕይወታቸው ብዙ ዓይነት መመሰቃቀል እንደሚገጥማቸው ታሳቢ በማድረግ ፖሊስ የቤት ሥራውን አስቀድሞ ሊሠራ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታም ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ታስረው ሊቆዩ እንደሚችሉ ያክላሉ፡፡

አቶ አመሀ ተይዘው ከነበሩ መሰል ጉዳዮች መካከል አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ታስረው ዓቃቤ ሕግ ክሱን በማቋረጡ በነፃ የተለቀቁት የአምስቱ ዞን ዘጠኞች ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ‹‹በታሰሩበት ጊዜ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ መክፈል ቀርቶ ይቅርታ የጠየቀ አካል የለም፡፡ ወደ ሥራ ገበታቸውም መመለስ አልቻሉም፤›› ይላሉ አቶ አመሀ፡፡ ሌላው በአቶ አሞት አጎዋ፣ በአቶ አሽኔ አስቲንና በአቶ ጀማል አህመድ በተባሉ ወደ ኬንያ ሲሄዱ በነበሩ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪዎች ላይ ‹‹ሽብርተኛ ድርጅት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነው ወደ ኬንያ የምትሄዱት፤›› በሚል የተመሠረተው ክስ ነው፡፡ አቶ አሽኔ አስቲን የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አባልና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፣ ክሱ የተመሠረተባቸው ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ነበር፡፡

እንደ አቶ አመሀ ገለጻ፣ ሰዎች ለምርመራ በሚል አራት ወራት በማዕከላዊ ቆይተዋል፡፡ በሽብር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸውም ነበር፡፡ ዓመት ከስምንት ወራት ያህል በማረሚያ ቤት ከቆዩ በኋላ አቶ ጀማልና አሽኔ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ዓምና በነፃ እንዲለቀቁ ተደረገ፡፡

በዚህ መንገድ ዓመታት ታስረው በነፃ የተለቀቁ ሰዎች ለደረሰባቸው የሞራልና የቁሳቁስ ጉዳት መንግሥት ካሳ ሊከፍላቸው ይገባል የሚል በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ የለም፡፡ ነገር ግን በ1990ዎቹ መንግሥት ያፀደቀው አንድ የወንጀል ሕግ ፖሊሲ ይህንን የተመለከተ አንቀጽ ማካተቱን አቶ አመሀ ይናገራሉ፡፡

 እሳቸው እንደሚሉት፣ ሕጉ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ወይም በተሳሳተ ማስረጃ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ገብተው ሳይከሰሱ ነፃ ተብለው የተለቀቁና ተከሰው በነፃ የወጡ፣ ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ይህ ወደ ሕግ ተተርጉሞ ገና በሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ምናልባት ተሻሽሎ በሚመጣው የወንጀለኛ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ተካቶ ሊወጣ ይችላል፡፡  

በሌላ በኩል ሕጉ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ ባይኖርም ከውል ውጪ በሚደረስ ኃላፊነት የሚመለከተውን የሕግ አስከባሪ አካል በፍትሐ ብሔር ሕጉ መክሰስ ይቻላል፡፡ ይሁንና ይህ ያልተለመደና ብዙዎች የማያውቁት አማራጭ መሆኑን አቶ አመሀ ይናገራሉ፡፡   

ማንም ሰው በሌላ ሰው ድርጊት ጉዳት ሲደርስበት ካሳ መጠየቅ እንደሚችለው ሁሉ በሕግ አስከባሪው ያልተገባ ዕርምጃ ጉዳት ደርሶብኛል የሚል ክስ መሥርቶ ካሳ ከመጠየቅ የሚያግደው ሕግ የለም፡፡ ነገር ግን እንኳንስ የሕግ ዕውቀት በሌለው ተራ ሰው ቀርቶ፣ እሳት የላሱ ለሚባሉ የሕግ ባለሙያዎች እንኳን ይህ ፈፅሞ የማይታሰብና ድንጋይ የመቀቀል ያህል ነው፡፡ ለዚህም የአቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤልን ጉዳይ በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡

አቶ ዮሐንስ የቀድሞው ፍትሕ ሚኒስቴር የዓቃቤ ሕግ ውክልና ሰጥቷቸው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ ነበር የተከሰሱት፡፡ ተጠሪነታቸው ለወከላቸው የፍትሕ ሚኒስቴር እንደመሆኑ ሊከሳቸውና ሌሎችም አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በእሳቸው ላይ የማሳለፍ ሥልጣን ያለው ሚኒስቴሩ ነበር የሚሉት አቶ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ‹‹በዚህ መካከል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዘሎ መሀል በመግባት ሥልጣንህን ያላግባብ ተጠቅመሃል በሚል ቀጥታ እኔን ከሰሰኝ፡፡ እኔም ለእኔ ኃላፊነት ወስዶ መናገር ያለበት ፍትሕ ሚኒስቴር ነውና ፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጥልኝ ጥያቄ አቀረብኩ፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ሚኒስቴሩ ከሦስት ወራት በኋላ ኮሚሽኑ በእሳቸው ላይ ሥልጣን እንደሌለው የሚገልጽ ደብዳቤ እንደጻፈ፣ ይኸው ደብዳቤ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ግልባጭ እንደገባ፣ ነገር ግን ውድቅ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡

የተከሰሱበት ሁኔታ አግባብነት የሌለው ቢሆንም፣ ተከራክረው ነፃ እስኪወጡ ድረስ ሦስት ዓመታትን በእስር ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡ ከተለቀቁ በኋላም ስማቸውን የማጥራት ሥራውን ሳያቋርጡ ቀጠሉበት፡፡ በእስር ላሳለፉባቸው ዓመታት የደረሰባቸውን የሞራልና የቁሳቁስ ጉዳት ካሳ መጠየቅ እንደሚችሉ ቢያውቁም ‹‹በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ ከማመልከት፣ ‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ መውጣት› ይቀላታል›› በማለት እንደተዉት ይናገራሉ፡፡

በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ተቋማቱንም መክሰስ ቢቻልም፣ ፍርድ ቤቱን አሳምኖ የደረሰበትን ጉዳት ካሳ ማግኘት የሚቻልበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ ክሱ የተመሠረተው ሆን ተብሎ በመነሳሳት መሆኑን ማሳየት ይገባል፡፡ ‹‹ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ በክፉ ልቦና ሆነ ብሎ ሰዎችን አይከስም፡፡ ክፉ ልቦና የሚኖረው ከእነሱ ጀርባ ሆኖ ጥቆማ የሰጣቸው ባለሥልጣን ወይም ሌላ ሰው ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱን ለማሳመን ከእነሱ በስተጀርባ ያለውን ሰው ለይቶ ማውጣትና ሆነ ብሎ የፈጸመው ድርጊት መሆኑን፣ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት በጣም ከባድ ነው፤›› በማለት ትርፉ ልፋት ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በሌላው ዓለም በቂ መረጃ ሳይኖር ክስ መመሥረት ብቻ አይደለም ጉዳዮች አለማሸነፍ በዓቃቤ ሕጉ ላይ የሚያደርሰው የኃላፊነት ወሰን ከሥራ እስከ መታገድ፣ ፈቃድ እስከ መነጠቅ ይደርሳል፡፡ እነዚህ እውነታዎች በሆሊውድ ፊልሞች ላይም ሳይቀር ቁልጭ ብለው ይታያሉ፡፡

‹‹ያላግባብ በቂ ማስረጃ ሳይኖር ወይም አለመኖሩን እያወቀ አንድን ሰው የከሰሰን ዓቃቤ ሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡ በዚህ አግባብ የተጠየቀ ዓቃቤ ሕግም በሕይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም፤›› ያሉት አቶ አመሀ ምናልባት ባልተገባ አኳኋን ሥራን በመምራት በሚለው ወንጀል ሕጉ ድንጋጌ ሊጠየቅ የሚችልበት አግባብ እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ድንጋጌዎች በጣም ሰፊና ፖሊስና ዓቃቤ ሕጎችን በተለየ መነፅር የማያስቀምጡ በመሆናቸው ለመተግበር ሊያስቸግሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ በፕላንና በዕቅድ የመሥራት ባህላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣት ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ወንጀሎችን በራሳቸው ተነሳሽነት ፈልፍሎ ማውጣት ላይ ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በትዕዛዝ ወይም በተንኮል እንዲህ ሆኗል ተብሎ ጥቆማ ሲደርስ ነው ብዙ ወንጀሎቸን ማጣራት የሚጀመረው፡፡ ይህ ለጉዳዩ አዲስ እንዲሆኑ፣ በራሳቸው በቂ መረጃ እንዲያሰባስቡ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህም ተከሳሹን የመረጃ ምንጭ ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡ ይህ ፈፅሞ ሕገወጥ ሲሆን፣ ወንጀለኛ መሆኑ ሳይረጋገጥ ለዓመታት በእስር ላይ እንዲቆይ የሚያደርገው ነው፡፡

‹‹ተከሳሹን በማምታታት፣ በማታለል፣ እያዋከቡ ነው መረጃ የሚወስዱት፡፡ ይህም አብዛኛዎቹ ክሶች በስህተት የተሞሉና ተቋሙንም ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳርጉ ናቸው፤›› ይላሉ አቶ ዮሐንስ፡፡ ይህም እንደ እሳቸውና እንደ አቶ የሺጥላ ያሉ ንፁሃን ውድ ጊዜያቸውን በእስር እንዲያሳልፉ፣ ከሥራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ በስህተት በተመሠረተ ክስ ስማቸው መጉደፉና የሌላም ጉዳት ሰለባ መሆናቸው ሳያንስ ከሥራ ገበታቸው በመነሳታቸው የኢኮኖሚ ጥገኛ የሚሆኑበት አግባብ ደግሞ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ‹‹ወደ ሥራ ገበታ መመለስ ስለማይቻል ያለው ዕድል እጅን አጣጥፎ ወደ ልመና መግባት ነው›› በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ፣ አለበቂ ዕርምጃ ታስረው የሚለቀቁ ዜጎች መኖራቸውንና አቤቱታቸውን ለኮሚሽኑ ያቀረቡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁኔታው ማንም ሰው አለጥፋቱ ዕርምጃ አይወሰድበትም የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚፃረር መሆኑን ተናግረዋል፡፡