Skip to main content
x
ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች መብታቸው እንደሚጣስ በጥናት ተመለከተ

ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች መብታቸው እንደሚጣስ በጥናት ተመለከተ

በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ጎን እየተለጠጡ ከሚገኙ ከተሞች፣ እየተፈናቀሉ የሚገኙ ዜጎች በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ፣ መብታቸው እየተጣሰ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ጉዳይ ላይ ያካሄደውን ጥናት መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ኮሚሽኑ ባካሄደው ጥናት በልማት ምክንያት ከቦታቸው የሚነሱ ዜጎች፣ በተለያዩ መንገዶች የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረት ያደረገው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥናት፣ ተነሺ ዜጎች በቂ ካሳ እንደማይከፈላቸውና በተገቢው መንገድ ምትክ መኖሪያ ቤት አለማግኘታቸው ኑሯቸውን የከፋ እንዳደረገው አመልክቷል፡፡

በአብዛኛው ለተነሺዎች የሚቀርበው ምትክ ቦታም ለኑሮ ምቹ ያልሆነና የመሠረተ ልማት ያልተሟላለት በመሆኑ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዚህ የተነሳም ተፈናቃዮች ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ ቢሆንም፣ ለቅሬታቸው ግን ተገቢውን ምላሽ እያገኙ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ ‹‹የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት ምክንያት ተፅዕኖዎች፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ማካሄዱ ይታወቃል፡፡

በጥናቱ ላይ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ባለው ዕድገት ምክንያት የከተሞች የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ፣ ከዚህ አንፃርም የመሬት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡

ይህ ዕድገትም ለመኖሪያ ቤትና ለአገልግሎት ተቋማት የሚሆን የመሬት ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉ፣ የመሬት ፍላጎት ለማሟላት የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ነባር ቀዬዎች ወደ ከተማ ክልል እንዲቀየሩ ማድረጉን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የከተሞች መጠን (ኧርባናይዜሽን) በ1976 ዓ.ም. 11 በመቶ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 20 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ በ2010 ደግሞ 30 በመቶ ይደርሳል፤›› ሲል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ያካሄደው ጥናት ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ የከተሞች መጠን አሁን ባለው ደረጃ ዝቅተኛ የሚባል ቢሆንም፣ የዕድገት ምጣኔው ግን ከአምስት በመቶ በላይ ነው፡፡

ይህ የዕድገት መጠን በሚቀጥሉት ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለአብነት የስኳር ፕሮጀክቶች ትላልቅ መለስተኛ ከተሞች እንደሚፈጥሩ ጥናቱ ያመላክታል፡፡

ነገር ግን ከቦታቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ተገቢውን ጥቅም ካለማግኘታቸውም በላይ መብታቸውም እየተጣሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተነሺዎች ከነባር ቀዬአቸው የሚነሱበትን ዜና የሚሰሙት በተገቢው መንገድ አይደለም ይላል ጥናቱ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 81 በመቶ የሚሆኑ ተነሺዎች ዜናውን በስብሰባ ይሰማሉ፣ 12 በመቶ በቀበሌ ተሿሚዎች ይሰማሉ፣ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በስሚ ስሚ ይሰማሉ ብሏል፡፡

በጅማ ከተማም እንዲሁ 12 በመቶ በስብሰባ፣ 52 በመቶ በቀበሌ ተሿሚዎች፣ 28 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በስሚ ስሚ ከቀዬአቸው የሚነሱበትን ዜና ይሰማሉ ይላል ጥናቱ፡፡

‹‹ከዚህ መረዳት የሚቻለው ተነሺዎች የሚለቁት መሬት ለምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚውል፣ መቼ እንደሚለቁና ምን ያህል ካሳ እንደሚከፈላቸው በግልጽ እንደማይነገራቸውና ይህንኑ ዜና በጽሑፍ እንዲያውቁት የማይደረግ መሆኑ ነው፤›› ሲል ጥናቱ ያስገነዝባል፡፡

በዚህ ጥናት ላይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ባቀረበው ተቀራራቢ ይዘት ያለው ጥናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብና ውይይት እንደሚደረግበት አስታውቋል፡፡