Skip to main content
x
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በርካታ ታዳሚዎች የተሳተፉበትን ጠቅላላ ጉባዔ አካሔደ

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በርካታ ታዳሚዎች የተሳተፉበትን ጠቅላላ ጉባዔ አካሔደ

ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔዎች ወቅት በርካታ ታዳሚዎች የተገኙበት፣ በዚህ ሳምንት የተካሔደው 13ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከ17 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ 13ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ሲያካሂድ ከ1,257 በላይ አባላት ተገኝተዋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ አወዛጋቢ የነበረውና 500+1 አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ እንደተሟላ ይቆጠራል  የሚለውን ውሳኔ ካሳለፈበትና በዚሁ አሠራር መጓዝ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ይህን ያህል ተሳታፊ ተገኝቶ አያውቅም፡፡

በ2005 ዓ.ም. ንግድ ምክር ቤቱ 10,482 አባላቱን ለስብሰባ ሲጠራ የተገኙት 860 ብቻ ነበሩ፡፡ ይህም ከጠቅላላው አባላት 8.2 በመቶውን እንደሚወክል ያሳያል፡፡ በ2004 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔም 510 አባላት ተሳትፈዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ንግድ ምክር ቤቱ ከ14 ሺሕ በላይ አባላት ለስብሰባ እንዲገኙለት ጠርቶ የታደሙት ግን 889 ነበሩ፡፡ ባለፈው ዓመት ስብሰባ ወቅት ግን 1,220 አባላት ተገኝተው ነበር፡፡ ዘንድሮም ከ17 ሺሕ በላይ አባላት ባሉት የነጋዴዎች ማኅበር፣ በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የተገኙት ግን ከ1,250 በላይ ናቸው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ እንደ አባላቱ መብዛት ሳይሆን፣ 1257 አባላቱ ብቻ በተገኙበት ውሳኔ ማሳለፍ ይቻላል ወይ? የሚለው ጥያቄ እስከ ፍርድ ቤት ማዳረሱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ንግድ ምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ በደረሰበት ቀመር መሠረት ጉባዔውን ማካሄዱን ቀጥሏል፡፡ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባም በዚሁ ቀመር መሠረት የተካሄደ ነው፡፡ ከቀደሙት ጊዜያት ይልቅ የስብሰባው አዳራሽ በታዳሚ ተሞልቶ የታየበት ይህ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከዚህ ቀደም እንደታየው ያለ ጭቅጭቅ ያልተስተናገደበት መሆኑም የተለየ እንዲሆን አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

በዕለቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ  ኤልያስ ገነቲ ያሰሙት ሪፖርት ላይ የቀረበ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎች ሲመደጥ የነበረውም ንግድ ምክር ቤቱ በሪፖርት ያስደመጣቸው ክንውኖችን የሚያደንቁ አስተያየቶች ነበሩ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው በሰላም መካሄዱ፣ እንደቀድሞው ጭቅጭቅ ያልታየበት መሆኑን በማስታወስ ለዚህ መብቃቱን በአወንታ የገለጹ ተሳታፊዎችም ነበሩ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ቦታ መረከቡ፣ የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡና ሌሎችም ሥራዎቹ እንደሚያስመሰግኑት ተሳታፊዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ይህ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ እንደ ትልቅ ተግባር ይታያል እስከማለት የደረሱበት ጠቅላላ ጉባዔ ነበር፡፡ የጠቅላላ ጉባዔው ድባብና በቀረበው ሪፖርት መሠረት የተጠናቀረው ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የከተማ አስተዳደሩና የምክር ቤቱ ወዳጅነት

የንግድ ምክር ቤቱን የ2009 ዓ.ም. የሥራ ክንውን በተመለከተ የንግድ ምክር ቤቱ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርታቸው ውስጥ በጉልህ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ግንኙነቱን እያጠናከረ መምጣቱን የሚያሳየው ይገኝበታል፡፡

በአቶ ኤልያስ ሪፖርት የአዲስ አበባ አስተዳደር ንግድ ምክር ቤቱን በተለየ መንገድ እየደገፈ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡ በዋቢነት የተጠቀሱትም የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የስብሰባና የዓውደ ርዕይ ማዕከል ግንባታ እንዲቀላጠፍ አስተዳደሩ የ650 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን በመግዛት ለግንባታው ያደረገው አስተዋጽኦ ተጠቅሷል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የራሱ ሕንፃ እንዲኖረው በአዲስ አበባ ዳያስፖራ አደባባይ አካባቢ፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ አጠገብ ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በዝቅተኛ የሊዝ ዋጋ እንዲረከብ ማስቻሉም አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ ከሰጣቸው ድጋፎች መካከል ሚዛን የሚያነሳው ነው፡፡

ይህንኑ በተመለከተ አቶ ኤልያስ እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ የሰጠው ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ጠቅላላ የሊዝ ዋጋው 12.14 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከሊዝ ዋጋው 20 በመቶውን ምክር ቤቱ እንደከፈለ በመጠቆም፣ የተረከበው ቦታ በገበያ ዋጋ ቢሰላ ግን በርካታ ሚሊዮን ብር ያወጣ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ለጠቅላላ ጉባዔው የተሰራጨው የንግድ ምክር ቤቱ ዓመታዊ መጽሔት፣ የዚህ ቦታ የገበያ ዋጋ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ይጠቅሳል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታ ለመጀመር እንዳቀደ የገለጹት አቶ ኤልያስ፣ ግንባታውን ለማስጀመር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል፡፡ ለሕንፃው ቀድሞ የተሰናዳው ዲዛይን ለአዲሱ ቦታ በሚስማማ መልክ እንደሚሻሻልም አስታውቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት በዚህ እንደማይወሰን ያመለከቱት አቶ ኤልያስ፣ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ለማስፋፋትና ለማደስ አስተዳደሩ ያደረገውን ድጋፍም ገልጸዋል፡፡

‹‹የከተማ አስተዳደሩ በማስፋፊያው ሥራ እንዲሳተፍ እንዲሁም የማዕከሉን የአዋጭነት ጥናት ለማስጠናት አስተዳደሩ 300 ሺሕ ዩሮ እንዲመድብ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤›› ያሉት አቶ ኤልያስ፣ አስተዳደሩ ለተጨማሪ ማስፋፊያው የሚሆን 8.5 ሔክታር መሬት መፍቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ንግድ ምክር ቤቱ የንግድና የኢንቨስትመንት ምኅዳር እንዲሻሻልና አባላቱ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ አከናውኛለሁ ካላቸው ተግባራት መካከል በተለይ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይ አባሎቹ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀን ገቢ ግምት ስሌት ላይ ያደረባቸውን ቅሬታ ምክር ቤቱ በመቀበል ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገሩ አንዱ ነው፡፡ ይህን በማድረግ ለውጦች እንዲመጡ ማድረጉን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ የግብር ትመናነው እየደሔደበት ያለውን አካሄድ ለማስቀረት ንግድ ምክር ቤቱ ብዙ መሥራት እንዳለበት አባላቱ ተናግረዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ከሚሰጡ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ባሻገር፣ ዓምና ለግልግል ተቋሙ 54 ንግድ ነክ ጉዳዮች ቀርበውለት፣ 28ቱ በግልግል ዳኝነት ሒደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ሌሎች ዘጠኝ ጉዳዮችን አይቶ መፍትሔ እንዲሰጥ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በግልግል ተቋሙ ከታዩ ጉዳዮች ውስጥ 11 ጉዳዮች ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ ሁለቱ ብቻ ለይግባኝ ወደ ፍርድ ቤት ሄደዋል፡፡

በንግድ ሒደት ለሚፈጠሩ ውዝግቦች መፍትሔ የመፈለግና የማግባባት ሥራም ተሠርቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ አምስቱ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከሚገኙ የንግድ ሸሪኮቻቸው በኩል ለገጠማቸው ችግሮች በድርድር መፍትሔ የሰጠባቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ ቻይና፣ ቱርክ፣ ህንድ እንዲሁም እንግሊዝ አገር ካሉ ነጋዴዎች ጋር ለተፈጠሩ አለመግባባቶች ዳኝነት ያስቻለባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ገቢና ወጪው የቀነሰበት ዓመት

የንግድ ምክር ቤቱ የ2009 ዓ.ም. የወጪና ገቢ አፈጻጸም ሪፖርትም ከክንውኑ በተጨማሪ ለተሰብሳቢው ቀርቦ ነበር፡፡ የፋይናንስ ሪፖርቱ እንደቀደሙት ዓመታት የገቢ ጭማሪን አላሳየም፡፡ ከሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው፣ በ2009 ዓ.ም. የነበረው ጠቅላላ ገቢው ባለፉት አሥር ዓመታት ከነበረው አኳያ ዕድገት አላሳየም፡፡ በየዓመቱ እያደገ የነበረው የምክር ቤቱ ጠቅላላ ገቢ፣ በ2009 ዓ.ም. አነስተኛ ሆኗል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ዓምና ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 57.5 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የካቻምና ዓመታዊ ገቢው ግን 65.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም አጠቃላይ ገቢው ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ እንዳሳየ ያመላክታል፡፡

ከ2005 እስከ 2008 ዓ.ም. በነበሩት አራት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ብር ጀምሮ እስከ 16 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ መጠን በየዓመቱ የገቢ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ በ2007 ዓ.ም. 49.5 ሚሊዮን ብር የነበረው ገቢው በ2008 ዓ.ም. ወደ 65.5 ሚሊዮን ብር አድጎ፣ የ16 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየት ችሎ ነበር፡፡ ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው በ2009 ዓ.ም. የመቀነሱ ምክንያት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ለማግኘት ባቀደው ልክ ካለመሥራቱ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡

ከአባላት መዋጮ ማሰባሰብ የቻለው ካቀደው ውስጥ 50 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከአባላት መዋጮ ይጠበቅ የነበረው ገቢ 7.4 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከአባልነት መዋጮው ባሻገር፣ ዓምና ብቻም ሳይሆን ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከንግድ ትርዒቶች ሲያገኝ የቆየው ገቢም እየቀነሰ መምጣቱን የምክር ቤቱ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

በዓመት ውስጥ አራት ቋሚ የንግድ ትርዒቶችን የሚያካሂድ ቢሆንም፣ የንግድ ትርዒቶች ያስገኙት 7.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም. ከንግድ ትርዒቶች የተገኘው ገቢ 7.8 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ ገቢ በ2006 ዓ.ም. ወደ 8.5 ሚሊዮን ብር አድጎ ነበር፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከንግድ ትርዒቶች የተገኘው 9.1 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ግን ገቢው ወደ 8.8 ሚሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን የምክር ቤቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡

ሐሙስ፣ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው 13ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት በአቶ ኤልያስ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያትተው፣ ዓምና ንግድ ምክር ቤቱ ካዘጋጃቸው የንግድ ትርዒቶች ያገኘው ገቢ 7.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም ንግድ ምክር ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከንግድ ትርዒቶች የሚያገኘው ገቢ እየቀነሰ መምጣቱን አሳይቷል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይህ ገቢ ለምን እንደቀነሰ ለቀረበው ጥያቄ በተሰጠው ምላሽ፣ ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ከተከሰተው አለመረጋጋትና ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አኳያ የውጭ ኩባንያዎች ከመቅረታቸው ጋር እንደሚያያዝ፣ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዓምና የተመዘገበው ገቢ ከ2007 ዓ.ም. ከተመዘገበውም ያነሰ ነበር፡፡

በ2009 ዓ.ም. የንግድ ምክር ቤቱ ወጪም መቀነሱን በሪፖርት ተመልክቷል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተው ዓምና የንግድ ምክር ቤቱ ወጪ 43.1 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ ወጪ ከቀደመው ከ2008 ዓ.ም. አኳያ በ9.7 ሚሊዮን ብር ቀንሷል፡፡

ከወጪዎቹ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች ወጪ ሲሆን፣ ይህም ከቀደሙት ዓመታት ያነሰ ሆኗል፡፡ ለደመወዝና ለጥቅማ ጥቅም በ2007 ዓ.ም. 9.2 ሚሊዮን ብር፣ በ2008 ዓ.ም. 10.1 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የሚያሳየው ሪፖርት፣ በ2009 ዓ.ም. ግን 8.6 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያሳያል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ባለመቅረቡ ማብራሪያ አልተሰጠበም፡፡ የአንዳንድ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ እንቅስቃሴ በዚህ ዓመት ስለሚለቀቅ፣ የምክር ቤቱ ገቢ እንደሚጨምር አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡