Skip to main content
x
ማሪዮት በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሆቴል ለመክፈት ስምምነት ማድረጉን አስታወቀ

ማሪዮት በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሆቴል ለመክፈት ስምምነት ማድረጉን አስታወቀ

  • ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት አገሮች ሰባት አዳዲስ ሆቴሎችን ለመክፈት ተስማምቷል

በሩዋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎርም ወቅት፣ ማሪዮት ኢንተርናሽናል 165 ክፍሎች የሚኖሩትና ፕሮቲያ ሆቴል የተሰኘውን ብራንድ ቸርችል ጎዳና አካባቢ እ.ኤ.አ. በ2021 እንደሚከፈት የሚጠበቀውን ሆቴል በአዲስ አበባ ዕውን ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ማከናወኑን አስታውቋል፡፡

መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረምን የሚያዘጋጀው የእንግሊዙ ቤንች ኤቨንትስ ኩባንያ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ካስተዋወቃቸው ብራንዶች በተጓዳኝ አዲሱ ፕሮቲያ ሆቴል ልዩ ሬስቶራንት፣ የመጠጥና የምግብ ቤት፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የአካል ብቃት ማዕከልና ስፓ እንደሚኖረው የተነገለት የዚህ ሆቴል ባለንብረት፣ ሆቴሉ የሚፈጀው የግንባታ ወጪና መሰል ጉዳዮችን ከመግለጽ የተቆጠበው የማሪዮት ኢንተርናሽናል፣ አዲሱ ብራንድ ከአራት ዓመት በኋላ ሥራ ስለመጀመሩ በማስታወቅ ተገድቧል፡፡

ይህም ሆኖ ከኢትዮጵያ ባሻገር በኮትዲቯር፣ በጋና፣ በናይጄሪያ ዕውን የሚያደርጋቸውን ሰባት ሆቴሎች ጨምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 በጠቅላላው የሚኖሩት ሆቴሎች ብዛት (በግንባታ ላይ የሚገኙና ሥራ የሚጀምሩ) 37 ሺሕ ክፍሎች የሚኖሯቸው 200 ሆቴሎች እንደሚኖሩት አስታውቋል፡፡ ለእነዚህ ሆቴል እስካሁን የወጣውን ጨምሮ በጠቅላላው የ8.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቁትም ማሪዮት አስታውቋል፡፡ ፕሮቲያ ሆቴልን እ.ኤ.አ. በ2014 ከሌላ ኩባንያ የጠቀለለው ማሪዮት በአፍሪካ በተለይ በደቡብ አፍሪካ ታዋቂ የሆነ ብራንዱ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ የጀመረውና በ35.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባውን ማሪዮት ኤክዚኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴልን ጨምሮ በቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ተጨማሪ ብራንድ ለመክፈት ከሰንሻይን ቢዝነስ ግሩፕ ጋር መስማማቱ ይታወቃል፡፡ ከ100 በላይ ክፍሎች ያሉት ማሪዮት ኤክዚኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴል፣ ሁለት ፕሬዚዴንሺያል ክፍሎች ያሉትና የተሟላ የወጥ ቤት መገልገያዎችን ያካተተ ዓለም አቀፍ ብራንድ ሆቴል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማሪዮት ኮርት ያርድ የተባለው ብራንድ ሆቴልን በ76 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በመገንባት የኮንትራት ስምምነት የፈረመው ሰንሻይን ቢዝነስ ግሩፕ፣ ከዚህ በተጨማሪም በሐዋሳ ከተማ በ42 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሒልተን ብራንድ የሆነውን ሆቴል ለመገንባትና ለማስተዳደር ውል ያሰረው ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡

እንዲህ ያሉ የሆቴል ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ መንገዱን እያመቻቸ የሚገኘው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም ምንም እንኳ በየዓመቱ በአፍሪካ የሚታየው የሆቴል ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱ ቢታይም፣ አሁንም ድረስ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት እንደሚታይ አስታውቋል፡፡ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚታየው የሆቴል ኢንቨስትመንት ከሌሎች የአፍሪካ አካባቢዎች ይልቅ ዝቅተኛ መሆኑን ደብሊው ሆስፒታሊቲ የተሰኘው አማካሪ ኩባንያ ያካሄደውን ጥናት አጣቅሶ አቅርቧል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በኬንያ፣ በታንዛንያ፣ በኡጋንዳ እንዲሁም በሩዋንዳ እየተካሔዱ የሚገኙ የሆቴል ኢንቨስትመንቶች ቢጠቀሱም፣ በሰሜን አፍሪካ ከሚታየው የ41 በመቶና በምዕራብ አፍሪካ ከተመዘገበው የ33 በመቶ የሆቴል ኢንቨስትመንት አኳያ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የ11 በመቶ ኢንቨስትመንት ዝቅተኛው ሆኖ ተመድቧል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በተሰናዳውና ከዚያም ቀደም ብሎ በተካሄደው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ በማሪዮትና በሒልተን ሆቴሎች ከተደረጉት ስምምነቶች ባሻገር ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለሚከፈቱ ሆቴሎች በርካታ ስምምነቶች መካሔዳቸው ይታወሳል፡፡

ከቤንች ኤቨንትስ ጋር በመሆን ፎረሙ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ሲሠራ የነበረው ካሊብራ የተሰኘው አገር በቀል የሆቴል አማካሪዎች ኩባንያ ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመወከል ከውጭ የሆቴል ብራንድ አስተዳዳሪዎች ጋር በሚያደርጋቸው ድርድሮች አማካይነት እስካሁን ሥራ የጀመሩትና በሒደት ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ከ15 በላይ የሆቴል ፕሮጀክቶችን በማማከር መሳተፉን የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡