Skip to main content
x
ቴክኖ ሞባይል 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ያለውን ሦስተኛ ፋብሪካ ሥራ እንደሚያስጀምር አስታወቀ

ቴክኖ ሞባይል 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ያለውን ሦስተኛ ፋብሪካ ሥራ እንደሚያስጀምር አስታወቀ

በትራንሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው ቴክኖ ሞባይል የተሰኘው ብራንድ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ሥራ የሚያስጀምረው ፋብሪካ በዓመት የ300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

በቻይና ሼንዜን ከተማ እ.ኤ.አ. በ2007 የተመሠረተው ቴክኖ ሞባይል፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያን በማስቀደም ሁለት ፋብሪካዎችን በመክፈትና የሞባይል ስልኮችን በመገጣጠም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

በወር፣ በአንድ ፈረቃ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስልኮችን የመገጣጠም አቅም ባላቸው፣ በጎፋ አካባቢና በዓለም ገና ከተማ በገነባቸው ሁለት ፋብሪካዎች አማካይነት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ የኩባንያው ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተጠናቀቀው የ2009 ዓ.ም. 60 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡ በዓለም ገና እንዲሁም በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነቡት ሁለቱ ፋብሪካዎች ከ2,000 በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳበረከቱም ጠቅሰዋል፡፡

100ኛውን የቴክኖ ሞባይል ምርቶች መሸጫ መደብር በጉርድ ሾላ፣ ሴንቼሪ ሞል ውስጥ ባስተዋወቀበት ወቅት፣ የሽያጭ መደብሮች ኃላፊ አንድሪው ሊ እንዲሁም የቴክኖ ሞባይል የሽያጭ ክፍል ኃላፊ ሞሐመድ ሐሳኒ እንዳብራሩት፣ ቴክኖ ሞባይል እስካሁን ከነበረው እንቅስቃሴ በይበልጥ በመስፋፋት በቦሌ ለሚ በሚገኘው የኢትዮ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ትልቅ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፋብሪካ በመጪው ዓመት ዕውን ሲሆን፣ በወር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ስልኮችን ለገበያ ማውጣት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለ4,000 ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል የተባለው አዲሱ ፋብሪካ፣ ወደ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሌሎችም አገሮች ሲደረግ የቆየውን የ60 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር በማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተጠቅሷል፡፡ በኢትዮ አይሲቲ መንደር የሚገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ፣ በቻይና ከሚገኘው ፋብሪካ አኳያ ግዙፉ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ የቻይናው የማምረት አቅሙ ሦስት ሚሊዮን ስልኮችን እንደሚያመርት የኩባንያው መረጃ ያሳያል፡፡ በጎፋ ካምፕ አካባቢ የተገነባው የቴክኖ ሞባይል ፋብሪካ ከሰባት ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በወር 425 ሺሕ ስልኮችን ገጣጥሞ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የተገባው የዓለም ገናው ፋብሪካ በበኩሉ በወር 580 ሺሕ ስልኮችን የማምረት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዓለም ከ240 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን ስማርትና መደበኛ የስልክ ቀፎዎችን እንዲሁም ታብሌቶችን በማምረት የሚታወቀው ቴክኖ ሞባይል፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ ከ120 ሚሊዮን በላይ ምርቶችን ለመሸጥ እንደበቃ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ከመገጣጠም ባሻገር በድኅረ ሽያጭ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ መደብሮችን የሚያንቀሳቅሰው ቴክኖ ሞባይል፣ በተለይ የሽያጭ መደብሮችን ከነጋዴዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት መሠረት በሚሰጣቸው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ አማካይት ለመደብሮች ምርቶቹን ያቀርባል፡፡ በኢትዮጵያ የተከፈቱት 100 የሽያጭ መደብሮች በፍራንቻይዝ መልክ የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ፣ በአራት ደረጃዎች እንደሚመደቡም አብድሪው አብራርተዋል፡፡ ስታንዳርድ፣ ስታንዳርድ ኤክስክሉሲቭ፣ ሜጋ ኤክስክሉሲቭ እንዲሁም ፍላግሺፕ የሚባሉ ደረጃዎች ያሏቸውን መደብሮች ለመክፈት የሚስማሙ ነጋዴዎችን ሲያገኝ የምርት ዓይነቶቹም እንደ መደብሮቹ ደረጃና አቅም የተለያየ መጠን እንደሚያቀርብ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመሃል ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኢትዮ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ ቅርብ ጊዜ ድረስ 70 ያህል ኩባንያዎች እንደሚገኙ ማስታወቁ ይታወቃል፡፡ ይሁንና በአሁኑ 170 ኩባንያዎች በፓርኩ ውስጥ የየራሳቸውን ድርጅት ለመክፈት ጥያቄ ማቅረባቸውንና የፓርኩ አስታዳደርም ጥያቄዎቹን እያጠና እንደሚገኝ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

በፓርኩ ውስጥ እንቅስቃሴ ካላቸው ተቋማት መካከል ኢትዮ ቴሌኮም አንዱ ነው፡፡ እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር በሚገመት ወጪ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታን ጨምሮ የአገሪቱን የጥሪ ማዕከል በዚሁ ፓርክ ውስጥ ለማድረግ ግንባታ እያካሄደ እንደሚገኝ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀው የፓርኩ ግንባታ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሔደ ሲሆን፣ የፓርኩ ጠቅላላ የግንባታ ወጪም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስድስት የውጭ ኩባንያዎች ምርት መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ጥያቄ ካረቀቡት 170 ኩባንያዎች መካከል 50 የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፣ የሥራ አቅምና ብቃታቸው ታይቶ በፓርኩ ውስጥ ሥራ ሊጀምሩ እንደሚችሉ የፓርኩ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡