Skip to main content
x
ድሮ እና ዘንድሮ

ድሮ እና ዘንድሮ

የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ (ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት) አዲስ አበባ ከተገኙና ካከበሩ በኋላ ኢትዮጵያን በይፋ የጎበኙት የሕንዱ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪድ ናቸው፡፡ በሸራተን አዲስ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር በመሆን የንግድ ማኅበረሰቡን አግኝተው ነበር፡፡ ከዘመነ አክሱም በተለይ ከአራተኛው ምዕት ጀምሮ ሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንደነበራቸው ይወሳል፡፡ ከ52 ዓመት በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን (1923-1967) ኢትዮጵያን የጎበኙት ሁለተኛው የሕንድ ፕሬዚዳንት ነርቫፖሊ ራድሃክሪሻን (1954-1959 ዓ.ም.) ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት (ጥቅምት 3 ቀን 1958 ዓ.ም.) ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አግኝተዋል፡፡

***

ወይ ታሪክ!

ታሪክ እነፍሴ ዲብ እየሠራ

ዘመን እልቤ ከምሮ ጋራ

ቀና ቀና ስል ምንም ሳልፈራ

ክብረ ቢስ ችግር ክብሬን ገሶ

ተልኮሰኮስኩኝ ኩራቴ ኮሶ

በልቶ ለማደር አጐነበስኩኝ

ለፍርፋሪ ሞገሴን ሸጥኩኝ፡፡

የአያት ቅድም አያት ያባት እናቴ

የጀግንነቱ ገድሌ ንግርቴ

እልፍ እጥፍ ነበር ዋጋው ግምቱ

ረከሰና ጉርስ ሆነ የዕለቱ

ጊዜ አዘንብሎ ተደፍቶ አንገቴ

ክብሬ ገበያው ሆነ ለዕራቴ

ላብን አፍስሰው በአቅም ሳይጥሩ

ጥሪት ሰብስበው ሠርተው ሳይከብሩ

ወይ ታሪክ እቴ ገድል ቢያወሩ

ኮርቶ ማደር የል ጦም እያደሩ፡፡

  • ተፈሪ ዓለሙ፣ ‹‹የካፊያ ምች›› (2007)

***

‹‹የት አለና ነው አዳኝ?››

ራስን መደለል በእንስሳትም መካከል በጥቂቶች ላይ የተደረገ ሆኖ፤ በምሳሌ ዓይነት እንደ ተረት የሚነገር ቃል እናገኛለን፡፡ ተረቱም እንደሚከተለው ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የተራበች ጦጣ ባንድ የወይን ስፍራ አጠገብ ስታልፍ ቁመቷ ከማይደርስበትና ዘልላም ልታወርደው ከማይቻላት አስቸጋሪ ከሆነ ካንድ ከፍተኛ ስፍራ ላይ በስሎ መልኩ ብቻ እንኳን የሚያስጐመጅ አንድ የወይን ዘለላ ተንዠርጐ ተመለከተች፡፡ ለማውረድም ሞክራ ሳይሆንላት ስለቀረ ልቧ እያወቀ፣ ራሷን በማታለል  ወይኑ እኮ እንደሆን በእውነቱ ገና አልበሰለም፤ ለጊዜው የደረሰ መሰለ እንጂ ጥሬ ነው፡፡ ስለዚህ ላንድ ጥሬ ለሆነ ላልበሰለ ወይን ይህን ያህል ምን ያደክመኛል? የሱን ዓይነት ከሌላስ ስፍራ አጥቼ ነውን? በማለት ራሷን ደልላ ይኸንኑ ቃል በመደጋገም ራሷን እየነቀነቀች ነገሩን አኳስሳ ትታው ሄደች ይባላል፡፡

እንደዚሁም አንዲት ሰጐን አንድ አዳኝ ጠመንጃውን ደግኖ ሊተኩስባት ሲያነፃፅርባት እያየች፤ ሮጣ  ሕይወቷን ለማዳን ከመሞከር ይልቅ፤ እዚያው ሁና ተደፍታ ዓይኖቹዋ እንዳያዩ ወደታች አቀርቅራ፤ የት አለና ነው አዳኝ? ቢኖር ለምን አላየውም? ይኸው ምንም ነገር አላይም እያለች በሐሳቧ ራሷን ደልላ ከዚያው አንገቷን ደፍታ ተቀመጠች ይባላል፡፡    

የቀድሞ አባቶቻችን፤ ሰው ያልኾነውን ነው በማለት ራሱን የሚደልል ከንቱ መኾኑን ተመልክተው ‹‹እርኩምን ሊበሉ፤ ጅግራ ነው አሉ›› ብለው ይተርኩት የነበረ ቃልም ይገኛል፡፡

ስለዚህ ሰው ራሱን በራሱ እንደ ሕፃን  ልጅ በመደለል በሐሳቡ የተመኘውን ነገር ሁሉ ሲፈጽም መታየቱ የቆየ እንጂ፤ አዲስ አይደለም፡፡

  • የማነ ገብረማርያም (ዶ/ር) ‹‹የፍልስፍና ትምህርት›› (1955)

******

ቀይ ወፎች በቀላሉ ጥንዳቸውን ያገኛሉ

በአሜሪካ በሴንት ሉዊዝ ዩኒቨርሲቲ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ቀይ ቀለም ያላቸው ወንድ ወፎች በቀላሉ ተጓዳኝ (አጋር) ያገኛሉ፡፡ አጋር የማግኘት ዕድላቸውም ሌላ ቀለም ካላቸው ወፎች ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ነው፡፡

ጥናቱ እንደሚያመለክተው ቀይነት በብዙ የወፍ ዝርያ ጥንዶች እንደ ጥራት የሚታይ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል የተወሰኑ ወፎች እንደ ካናሪስና ዜብራ ፊንችስ ያሉ ቢጫ ቀለም የሚሰጣቸውን እንደ ጥሬ፣ ፍራፍሬና ነፍሳት ይመገባሉ፡፡ በተጨማሪም ቀይ ቀለምን በመለየትና ቀይ ቀለም በመያዝ ረገድም የተለየ ነገር ያላቸው የወፍ ዝርያዎች እንዳሉ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

*******

ዋሻ ውስጥ ድብብቆሽ

አንድ ስኮትላንዳዊና አንድ እንግሊዛዊ በባቡር ወደ ታስማንያ እየተጓዙ ነበር፡፡ መሃላቸው አንዲት ቆንጆ ሴት ተቀምጣለች፡፡ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ማለፍ ስለነበረበት ወደዚያ ሲገባ ድቅድቅ ጨለማ ወረሰው፡፡ የጥንት ባቡር ስለሆነም መብራት አልነበረውም፡፡ ወዲያውኑ የመሳም ድምፅ ተሰማና ጥፊ ተከተለ፡፡

ባቡሩ ከዋሻው ሲወጣ ሴቲቱና ስኮትላንዳዊው ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ተረጋግተው ተቀምጠው ሳለ እንግሊዛዊው ግን በጥፊ የተቃጠለ ፊቱን እያሻሸ ነበር፡፡ ለርሱ የመሰለውም ስኮትላንዳዊው ሴቲቱን ስለሳማት ተቆጥታ የሰነዘረችበት ጥፊ እርሱ ላይ በስህተት ያረፈ ነው፡፡ ሴቲቱ በበኩሏ ‘እንግሊዛዊው ሊስመኝ ሲሞክር ተሳስቶ ስኮትላንዳዊውን ስለሳመው በጥፊ አቃጥሎታል’ ስትል ገምታለች፡፡ ስኮትላንዳዊው ደግሞ ‘ግሩም አጋጣሚ ነው የተፈጠረልኝ፤ ባቡሩ ከፊታችን ያለው ዋሻ ሲገባ የተለመደውን የመሳም ድምፅ አሰማና ያን ሞልፋጣ እንግሊዛዊ አጠናፍረዋለሁ’ እያለ በማሰብ ላይ ነበር፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

****

‹‹የርሶም መረጃ በቂ አይደለም››

ሙላህ ለምስክርነት ቀርቦ ነው፡፡ ዳኛው ሙላህን

“ሰውዬው ሲገድል ተኩሱን በትክክል አይተሀል?” አሉት፡፡

ነስሩ “ድምፁን ሰምቻለሁ” አለ፡፡

“በቃ መረጃህ በቂ አይደለም” አሉ ዳኛው ቀና ብለው፡፡

ነስሩ ከዳኛው ጀርባ አሻግሮ ሲያይ ምን እንደሚያይ ግራ ገብቷቸው ወደ ኋላቸው ሲዞሩ፣ ነስሩ ከት ብሎ ይስቃል፡፡

ዳኛው ተናደው “ችሎት ስለተዳፈርክ ቅጣት ይጠብቅሀል” አሉት፡፡

“ምን አድርጌ?” አለ ነስሩ

“ችሎት ፊት ካለአግባብ ስቀሀል”

“እርሶ እኔ ስስቅ አይተውኛል?”

“ድምፅህን ሰምቻለሁ” አሉት

“የርሶም መረጃ በቂ አይደለም” ብሎ እርፍ፡፡

  • መሃመድ ጣፋ ‹‹ነስሩዲን እና ቀልዶቹ›› (1998)