Skip to main content
x
‹‹የማናውቃቸውና በነፍሳት የሚተላለፉ አዳዲስ  በሽታዎች እየመጡብን ነው››

‹‹የማናውቃቸውና በነፍሳት የሚተላለፉ አዳዲስ በሽታዎች እየመጡብን ነው››

ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትሮፒካልና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ኃላፊ

ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከቤልጅየም መንግሥት ጋር በትብብር ሲተገብረው የቆየው የቭሊር አይዩሲ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሁለተኛው የፕሮጀክቱ ክፍል መተግበር ከጀመረ ጥቂት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ለ12 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን ፕሮጀክት የቤልጅየሙ ገንት ዩኒቨርሲቲ ሲያስተባብረው ቆይቷል፡፡ 118 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተይዞለት ሲተገበር የቆየው ይህ ፕሮጀክት በሥሩ ሰባት ፕሮግራሞችን ነድፎ አስተግብሯል፡፡ የሕፃናት ጤናና ሥርዓተ ምግብ፣ በቡና ምርምር ላይ የሚሠራው የኢኮሎጂ ፕሮግራም፣ የአፈር ለምነት፣ የተለያዩ ማኅበራዊና ፆታዊ ጉዳዮች፣ አይሲቲ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችና ወባ ላይ የተሠሩት ሥራዎች በፕሮጀክቱ ሲተገበሩ ከቆዩት ፕሮግራሞች ይጠቀሳሉ፡፡ ውጤታማ ከሆኑ ፕሮግራሞቹ መካከል በኢንፌክሺየስ ዲዚዝ ሥር የተቋቋመው የትሮፒካልና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ነው፡፡ ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው የትሮፒካልና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ኃላፊ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ምርምር ለማድረግ እ.ኤ.አ. በ2010 ነበር የተቋቋመው፡፡ በማዕከሉ በሚሠሩ ምርምሮች፣ ወባ በሽታ አሁን ላይ ምን ዓይነት ገጽታ እንዳለውና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን የማዕከሉን ኃላፊ ፕሮፌሰር ድልነሳውን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስለማዕከሉ ቢያብራሩልን፣

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- ማዕከሉ የተቋቋመው የበሽታዎችን የመተላለፊያ መንገዶች፣ ሰዎችን ለሞት እንዴት እንደሚዳርጉ፣ እነኚህን በሽታዎች የሚያስተላልፉ ነፍሳትን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጥናት ነው፡፡ እንዲሁም በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልባቸውን መንገዶች ያጠናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለተላላፊ በሽታዎች የሚሆኑ የተሻሉና አማራጭ መመርመሪያ መሣያዎችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችና መንገዶችን በተመለከተም ምርምር ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ከተቋቋመ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተጨባጭ የሠራውን ቢገልጹልን?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- ትልቁ የምርመር ውጤት በወባ ዙሪያ የተሠራው ነው፡፡ በወባ ዙሪያ የተደረገው ምርመር በፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ ነበር፡፡ ወባን በምንከላከልበት ብሔራዊ የወባ ቁጥጥር ፕሮግራም፣ በሽታውን ለመከላከል አጎበር ተሠራጭቷል፣ የኬሚካል ርጭት ተካሄዷል፡፡ እነዚህ ከመድኃኒቱ ውጪ ዋነኞቹ የመቆጣጠሪያ መንገዶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የወባ ሥርጭት ያለመቀነስ ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ እንዲሁም ቤቶች ላይ ኬሚካል ተረጭቶም ወባን የሚያስተላልፉ ትንኞች ቁጥር የመቀነስ ነገር አይታይም ነበር፡፡ ጥናቱን ያደረግነው ከፍተኛ የወባ ሥርጭት በሚኖርበት በግልገል ጊቤ የኤሌክትሪክ ግድብ ዙሪያ ነበር፡፡ በግድቡ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ለሚኖሩ ዜጎች ወባን ለመከላከል በአንድ በኩል አጎበር፣ በአንድ በኩል ደግሞ ኬሚካል ርጭት ይካሄድ ነበር፡፡ እንደዚህም ሆኖ እኛ ጥናት ስናደርግ የወባ ትንኞቹም ሆነ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የመቀነስ ሁኔታ እያሳዩም ነበር፡፡ ይህም ለምርመራችን እንደ መነሻ ሆነን፡፡ የሚረጨውን ኬሚካል ተቋቁመውት እንደሆነ ብለን ምርመር ማድረግ ጀመርን፡፡ በምርምራችን ስናየው ሙሉ ለሙሉ ተቋቁመውታል፡፡ ትንኞቹን ለማጥፋት ለአራት አሠርታት ያህል ዲዲቲና ማላታይን ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ተደጋጋሚ ጥናቶች ሠርተን ትንኞቹ ኬሚካሎቹን እንደተቋቋሙ አረጋገጥን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚያስ ምን ተደረገ?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- የተቋቋሙበት መንገድ ምንድነው የሚለውንም ወርድን አጥንተን ነበር፡፡ በጥናታችንም በጅን ወይም በሞለኪውላር መጠን ደረጃ እንደተቋቋሙት አወቅን፡፡ ከዚያም ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውጤቱን ሰጠን፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም የራሱን ጥናት አካሄዶ የእኛ ጥናት ትክክል መሆኑን አረጋገጠ፡፡ እኛም የምርምራችንን ውጤት በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳተምን፡፡ ከዚያም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማላሪያ ኮንትሮል ፖሊሲውን ቀየረ፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናቶቻችሁን ውጤት ተከትላችሁ መፍትሔ የሚሆን ነገር ብላችሁ ያቀረባችሁት የምርምር ውጤት አለ?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- አንዳንዶቹ ትንኞች ከሰው ይልቅ ከብቶችን ያጠቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ሁለቱንም ያጠቃሉ፡፡ በዚህ ላይ እንዴት ከወባ ትንኝ ንክሻ መከላከል ይቻላል የሚል ምርምር አካሄደናል፡፡ ከብቶችን የሚያጠቁ ጥገኞች አሉ፡፡ እነሱ ከብቶችን እንዳያጠቁ የምንጠቀምበት መድኃኒት አለ፡፡ መድኃኒቱ በከብቶች ውስጥ የሚገኙትን ጥገኞች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ተህዋሲያን ይገድላል፡፡ ይህንን መድኃኒት የወሰዱ ከብቶችን የሚነክሱ የወባ ትንኞች ይህንን መድኃኒት አብረው ስለሚወስዱ ይሞታሉ፡፡ ይህንን እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ እንደሚቻል አሳይተናል፡፡  የተለያዩ ዕፀዋቶችን ለይቶ ማውጣትና ትንኞቹን የመግደል አቅማቸውን የመለየት ሥራ እያካሄድን እንገኛለን፡፡ በዚህ ረገድ ብርብራና እንዶድ ላይም ጥሩ ውጤት አግኝተናል፡፡ ሁለቱንም የምርምር ውጤቶች አሳትመናቸዋል፡፡ ብርብራ ላይ ያካሄድነው ምርምር ትንኞቹን በምን ያህል መጠን መግደል ይቻላል? በሚለው ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ብርብራ ውኃ ላይ ሲጨመር ሌሎችንም ጠቃሚ ነፍሳት ይገድላል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ዓሳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናልም፡፡ ስለዚህ ሌላ አማራጭ መፈለግ ነበረብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኘው ወደ 45 ከሚሆኑት የትንኝ ዝርያዎች መካከል አራቱ ብቻ ናቸው ወባን የሚያስተላልፉት፡፡ አኖፊለስ አራቢያንስ የሚባለው ዋና አስተላላፊ ነው፡፡ አብዛኛው የወባ በሽታ የሚከሰተውም በዚሁ የወባ ትንኝ ዝርያ ነው፡፡ 75 በመቶ በሚሆነው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም ይገኛል፡፡ የተቀሩት ሦስቱ ግን የሚያስተላልፉት አልፎ አልፎ ነው፡፡ ዋናው አስተላላፊ ግን ትናንሽ ውኃ በሚይዙ ቦታዎች ላይ  የሚራባ ነው፡፡ በከብቶች ዱካ ላይ ከሚቋጠር ውኃ ጀምሮ በሚገኙ ጥቃቅን ውኃ ባቆሩ ቦታዎች ላይ መራባትን ይመርጣል፡፡ በትልልቅ ኩሬዎችና ሐይቆች ላይ አይራባም፡፡ እነዚህ ቦታዎች ጊዜያዊ የመራቢያ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ዓሳም ሆነ ሌላ እንስሳት አይኖርባቸውም፡፡ ስለዚህ ብርብራውን በእነዚህ ትንንሽ ቦታዎች ላይ መጨመርና ትንኙ እንዲሞት ማድረግ እንችላለን፡፡ በእንዶድ ላይ ባደረግነው ምርምርም በጣም ጥሩ ውጤት አግኝተናል፡፡ እንዶድ ወባ ትንኞችን ከዕጭነት ደረጃ ጀምሮ ያሉትን መግደል እንደሚችል ዓይተናል፡፡ ሌላ የሠራነው ደግሞ የትንኞቹን ሥርጭት፣ ምን ዓይነት የትንኝ ዝርያዎች እንዳሉ፣ ክምችቱን ማጥናት የሚችል ሞስኪቶ ትራፕ የሚባል መሣሪያ ነው፡፡ ይህንንም በጆርናል አሳትመናል፡፡   

ሪፖርተር፡- አጋር ድርጅቶች አሏችሁ ወይ? ካላችሁስ በጋራ ምን ምን ዓይነት ሥራዎችን ትሠራላችሁ?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜድስን፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አቴንስ፣ ስዊዝ ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜድስንና ሌሎችም በአጠቃላይ ከሰባት አጋሮች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ከዚህ ሌላም መሣሪዎችን ከሚያመርቱ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እንሠራን፡፡ ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ2030 ወባን ጨርሶ ለማጥፋት ዕቅድ ይዛ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከመቆጣጠር ወደ ማጥፋት ለሚደረገው ጉዞ ግን ትልልቅ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ችግር ትንኞቹ ያሉትን መድኃኒቶች ሁሉ መቋቋም መቻላቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ፓራሳይቱ በራሱ መድኃኒቱን መቋቋሙ ነው፡፡ ሦስተኛው የትንኞቹ ባህሪ ተለዋዋጭ መሆኑ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የትንኞቹ ባህሪ ተለዋዋጭ መሆኑ ምን ያህል ችግር ነው?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- ትንኞቹን ለመከላከል የሚደረጉት ጥረቶች ሁሉ ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ርጭት የሚካሄደው ቤት ውስጥ ነው፡፡ አጎበርም የሚዘረጋው ቤት ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ ትንኞች ቤት ውስጥ ገብተው ይነክሱና ውጪ ወተው ያርፋሉ፡፡ ስለዚህ እቤት የመረጨቱ ነገር ዋጋ የለውም፡፡ ነክሶ ሳያርፍ ነው የሚወጣው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ውጪ የሚናከሱ (ኧርሊ ባይተሮች) ናቸው፡፡ አጎበር ውስጥ ሳንገባ ከቀን ጀምሮ ነው የሚነክሱን፡፡ ዋናው የወባ አስተላላፊ የሚባለው አኖፍለስ አረቢያንስ በፊት እኩለ ሌሊት አሊያም ጎህ ሲቀድ አካባቢ ይናከስ ነበር፡፡ አሁን ግን ባህሪውን ቀይሯል፡፡ የተረጨ ቤት ካለ የተረጨበት ግድግዳ ላይ ሳያርፉ ነው የሚወጡት፡፡ ከዚህ ቀደም ግን ሰውን እንደነከሱ ግድግዳ ላይ ሄደው ያርፉ ስለነበር ኬሚካሉ ይገድላቸዋል፡፡ ይህ የባህሪ ለውጥ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ትንኞቹ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ፣ መድኃኒቱን እንዲላመዱ ያደረጋቸው ነገር ምንድነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የእኛ ተቋምም የትኛው ወባ ትንኝ እንደሆነ፣ መድኃኒቶቹን መቋቋም አለመቋቋሙን፣ ትንኙ በውስጡ ጥገኛ (የወባ በሽታ) መያዝ አለመያዙን መለየት የሚችል ቀላል መሣሪያ በመሥራት ላይ ነው፡፡ ይህ በጣም ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ ትንኙ መድኃኒት መቋቋም አለመቋቋሙን ካወቅን ምን ያህል መቋቋም መቻሉን፣ የተቋቋሙ የወባ ትንኞች ሥርጭት ምን ያህል መሆኑንና ሌሎችም ተያያዥ ሁኔታዎች በአካባቢው ብሎም በአገሪቱ ምን ያህል እንደሆኑ እንድናውቅ ያደርገናል፡፡ ከዚህ ሌላም ምን ያህሉ ትንኝ ቫይረሱን እንደያዘ ለማወቅ ይረዳል፡፡ ለምሳሌ እኛ አገር ለግብርና የምንጠቀምበት ፀረ ተባይ ኬሚካልና ለወባ የምንረጨው ኬሚካል ከአንድ ቤተሰብ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ማሳ ላይ ሲረጭ ዝናብ አጥቦት ወደ ወንዝና ሌሎች ውኃማ አካላት ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ የወባ ትንኞቹ ፀረ ተባይ ኬሚካሉን እንዲያገኙና መቋቋም እንዲችሉ ዕድል ይፈጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ከወባ ባሻገር ለአገሪቱ የሚያሠጉ በነፍሳት የሚተላለፉ በሽታዎች አሉ?

ፕሮፌሰር ድልነሳው፡- የማናውቃቸውና በነፍሳት የሚተላለፉ አዳዲስ በሽታዎች እየመጡብን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ መከሰቱ ሪፖርት ተደርጎ የማያውቅ የደንጊ በሽታ እ.ኤ.አ. በ2013 በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ነበር፡፡ ሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን፣ ድሬዳዋና ሌላ አንድ አካባቢ ወረርሽኙ ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ የነፍሳቱን ኢኮሎጂ፣ ባዮሎጂና የበሽታውን ኢፒዲሞሎጂ ስለማናውቅ ለእኛም ለአገሪቱም ትልቅ ችግር ነው፡፡ እንዴት መቆጣጠር መቻል እንዳለብንም አናውቅም፡፡ ይህንን ቫይረስ የሚያስተላልፈው ከወባ ትንኝ የተለየ ሌላ ትንኝ ነው፡፡ አሁን እሱንም በተመለከተ እየሠራን ነው፡፡ ሌላው ሌሽማኒያሊስ ወይም ቁንጭር የሚባለው በሽታ ነው፡፡ በዚህም ላይ እንሠራለን፡፡