Skip to main content
x

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ከፕሮፓጋንዳ ተላቆ ለአገር ግንባታ ይዋል

አገራችን ኢትዮጵያ ቋሚና ብዙ ታሪክ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ካላቸው አገሮች ግንባር ቀደም ናት፡፡ ይሁንና ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ አወዛጋቢ የሆኑ ቃላት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ክርክር ላይ በተለያዩ ግለሰቦች ስለተነሱ፣ ኅብረተሰቡ ስለሰንደቅ ዓላማ የነበረውን አመለካከትና እምነት እንዲሸረሸር፣ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለው እምነት በጥርጣሬ ዓይን እንዲታይ የበኩሉን ድርሻ ነበረው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የክልሎች እንዲሁም የኢሕአዴግና ብሔራዊ ድርጅቶቹ ጨምሮ በአገራችን ብዙ ባንዲራዎች አሉ፡፡ ክልሎችም ይሁን ገዥ ብሔራዊ ድርጅቶች ከዋናው የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ይልቅ፣ ለራሳቸው ባንዲራና ዓርማ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በመሆናቸው የፌዴራል ሰንደቅ ዓላማ የሚጠበቅበትን ያህል በአገራዊ ግንባታ ስንጠቀምበት አልነበረም፡፡

በዚህም የተነሳ በሕዝባዊ በዓላትም ሆነሃይማኖታዊ በዓላት የተለያዩ ዓርማ ያላቸው ሰንደቅ ዓላማዎች እየተጠቀምን እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና የነበረውን ውዥንበርና ጥርጣሬ ማስተካከል እንዲቻልና አገራዊ መግባባት እንዲኖር ለማገዝ በአገር ደረጃ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንዲከበር በአቶ ተፈሪ የማነ (ጉዳዩ አወዛጋቢ ነው) ሐሳብ ቀርቦ፣ በመንግሥትም ታምኖበት ከሚሊንየም ጀምሮ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ በእኔ እምነት ይህንን በዓል ለአገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው መከበሩ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ ይሁንና ከጊዜያዊ ፖለቲካ ጥቅም በፀዳ መንገድ ማክበር አስፈላጊና መተኪያ ያለው አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝም በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 863/2006 መሠረት በብሔራዊ ደረጃ ጥቅምት በገባ የመጀመርያ ሰኞ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንዲከበር በታወጀው መሠረት ዘንድሮ ጥቅምት 6 ቀን 2010 .ም. ተከብሯል፡፡ ይህ በዓል አዋጅ ወጥቶለት መከበር ከጀመረ እነሆ አሥር ዓመታት ሞልተውታል፡፡

ይሁንና በዓሉ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ሪፖርት ብቻ የሚቀርብበትና ለዚህ አገር ምሥረታና ግንባታ መስዋዕትነት የከፈሉት ጀግኖች የማይታወሱበት በዓል ስለነበር፣ በዓሉ እንደ ሁሉም የመንግሥት በዓላት በአገር ግንባታ ላይ ምንሳይፈይድ ለአሥር ዓመታት ቀይቷል፡፡ ሰለሆነም መንግሥትና ሕዝብ ይህንን ዕድል እንዴት መጠቀም እንደሚገባን ለማመላካትና ከእኔ የሚጠበቀውን ለማድረግ በማሰብ ነው ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡ እንደሚታወቀው ሰንደቅ ዓላማ የሚወክለው አገር ነው፤ በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማ በዓል ስናከብር የአገራችን ቀን እንደ ማክበር ነው የሚሆነው፡፡ አንደኛ በዚህ በዓል በዋናነት መነገር የሚገባቸው ጉዳዮች ስለመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ሳይሆን፣ ለዚች ባንዲራ ሲሉ ደማቸውንና አጥንታቸው ስለ ሰጡ ጀግኖች አባቶችና እናቶች ነው መሆን ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ነው ይህ በዓል የአገር ግንባታ አንድ አካል ነው የምለው፡፡

ሀብታሙ አለባቸው ‹‹ታላቁ ተቃርኖ›› በሚባለው መጽሐፉብሔር ግንባታ መንፈሳዊና ቁሳዊ (ገጽ 135) እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀውና እንደምንገነዘበው ቁሳዊ ግንባታ በጣም እየተፋጠነና በጥሩ መንገድ መሆኑ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ የፍትሐዊነት ጥያቄ ቢነሳበትም፡፡ ይህንን የመሠረተ ልማት ግንባታ የቁሳዊ አካል ግንባታ አንድ አካል ሆኖ ሕዝቦችን የሚያገናኝና የሚያቀራርብ በመሆኑ፣ ለአገር ግንባታ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም ቁሳዊ ግንባታ ከሞላ ጎደል መንግሥት ባለው ችሎታና አቅም እየገነባ በመሆኑ አበረታች ነው በሚል አልፈዋለሁ፡፡ በሌላ በኩል በዋናነት አገር የሚገነባው በመንፈሳዊ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይኽም ማለት ሕዝቦች የጋራ እሴትና ጥቅም እንዳላቸው ከልብ ተቀብለው በአብሮነት መንፈስ ሲጓዙና ሲኖሩ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአገራችን ያሉት ሕዝቦች በአገር ግንባታ ላይ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል እስካሁን ያሉ ገዥዎች ሲሠሩበት አልተገነዘብንም፡፡ ይሁንና አባቶችና እናቶች በጥሩም ይሁን በመጥፎ አገር መሥርተው አስረክበውናል፡፡ በመሆኑም እነሱን ስናከብርና የእነሱ መንፈስ ለአገር ግንባታ በመጠቀም የመሠረቷትን አገር የሁላችንም እንደሆነች በማመን እንደ መልካም ዕድል ካልተጠቀምንበት፣ በቁሳዊ ነገር ላይ የሚደረገውአገር ግንባታ ሙከራ ዞሮ ዞሮ ፈራሽ ነው፡፡ ስለሆነም የሰንደቅ ዓላማ ቀን የመንፈሳዊ አገር ግንባታ አካል አድርገን በሚገባ መጠቀም ይገባናል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት በሰንደቅ ዓላማ ቀን አገራችንን ለመመሥረት፣ ብሎም ለመጠበቅ ያለፉ አባቶችና እናቶች ልናስባቸውና ክብር ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህንን ክብር ስንሰጥ አንደኛ የጋራ እሴት እንድናዳብር ያደርገናል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ቀጣይ ትውልድ እኛ የሠራነውን ከማፍረስ ይልቅ ዕውቅና ሰጥቶ ለቀጣይ እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን ሁልጊዜ መሠረታዊ ለውጥ እናምጣ እየተባለ የነበረውን በማፍረስ ከዜሮ መጀመር የአገራችን ግንባታ ወደ ኋላ እየመለሰ ይሄዳል፡፡ ይህ ደግሞ አገር ለመገንባት ይቅርና በአባቶችናእናቶች ራዕይና መስዋዕትነት በረዥም ጊዜ ጥረት የተመሠረተችውን አገር ሊያፈርስ ይችላል፡፡ ስለሆነም ይህንን በዓል ተጠቅመን አገር ለመገንባት ከሁሉም አካላት የሚጠበቀው ምን መሆን እንዳለበት እንደሚከተለው በዝርዝር አቀርባለሁ፡፡

አንደኛ መንግሥት ባለ ትልቅ ሀብት ባለቤት ስለሆነና መዋቅርም ሆነ ሚድያ በቁጥጥሩ ሥር በመሆናቸው በዓሉ ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ለአገር ግንባታ ቢያወለው፣ ትልቅ ውጤት የማምጣት አቅም ይኖረዋል፡፡ ውጤቱ በመንግሥትና በሕዝብ፣ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ያለው የመጠራጠር መንፈስ ሊያስወግድ ይችላል፡፡ ይህ የሚሳካው ግን እንደ ተለመደው የኢሕአዴግ መንግሥት እንደ ቅዱስ፣ በፊት የነበሩ መንግሥታትና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ሰይጣን ከመቁጠር ስንቆጠብና ለሁሉም ድርጅቶችና መሪዎች ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ሰጥተን ስናከብረው ነው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ያልታገለ መሪም ሆነ ሕዝብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ በመሆኑም ቢያንስ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ያሉ መሪዎችና ሕዝቦች ለአገር ምሥረታና ግንባታ ያደረጉት መስዋዕትነትና አስተዋጽኦ በተደራጀ መንገድ የባለሙያ ጥናት ሊቀርብ ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን ይፈጥራል

ሁለተኛ ትውልዱ ከአባቶቹና ከእናቶቹ በመማር ለአገር ግንባታ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ስንቅ ይሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል የሚቀርበው ጽሑፍም ሆነ ጥናት በባለሙያዎች የተደገፈና ኢሕአዴግ ኢሕአዴግ የማይሸት መሆን ይገባዋል፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ማንኛውም ድርጅት በአገር ግንባታ የራሱ አስተዋጽኦ ካለው በባለሙያ ጥናት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን በዓሉ የካድሬዎች ሪፖርት ጋጋታ ከሆነ በአገር ግንባታ የሚፈይደው ምንም ነገር የለውም፡፡ ትርፉ የሀብት ብክነት ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው በዓሉን ስናከብር አገር የጋራ መሆንዋ ታወቆ መንግሥት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መድረክ መፍጠር አለበት፡፡ አገራዊ መግባባትም ብሎም አገር መገንባት የሚቻለው በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ሳይሆን እንደነዚህ ባሉ ትልልቅ አገራዊ በዓላት ላይ ነው፡፡

ይሁንና በዓሉ አገራዊ በዓል ስለሆነ ሁሉም ያገባናል የሚሉ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ያለምንም ጣልቃ ገብነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሳተፉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነ ግን በዓሉ የኢሕአዴግ በዓል ይሆናል፡፡ ከሆነ ደግሞ የሕዝብና የአገር ሀብት ማባከን አይገባም፡፡ ግንቦት 20ን ማክበር ስለሚቻል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ እንዲከበር ማድረግ አለበት፡፡ አዋጁ ከወጣ ዘጠኝ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን በአዋጁተደነገጉ ድንጋጌዎች ሲከበሩ አላየንም፡፡ ለምሳሌ በተመሳሳይ ዓመት የወጣውን የፀረ ሽብር አዋጅ ጥሰዋል የተባሉ በርካታ የሕዝብ መሪዎችና ግለሰቦች ታሰረዋል፣ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይሁንና የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ የጣሱ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እስካሁን ክስ ሲመሠረትባቸውና ሲቀጡ አላየንም፣ አልሰማንም፡፡ ይህንን ምናልባት መንግሥት ለሥልጣኑ የሚጎዳ ሆኖ ስላላገኘው ይሆናል፡፡ ነገር ግንአገር ግንባታ ከአንድ ድርጅት ሥልጣን በላይ በመሆኑ አዋጁ ሊከበር ይገባል እላለሁ፡፡

ለምሳሌ በአዋጁ አንቀጽ 19 የፌዴራል ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ባንዲራ ያለው አቀማመጥ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይሁንና አሁን እየታየ ያለው ግን ከአዋጁ በተቃራኒ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ለሥራ ጉዳይ ወደ አንድ ክልል ከተማ ጎራ ብዬ ነበር፡፡ በዚህ ከተማ የተሰቀሉ የፌዴራሉና የክልሉ ሰንደቅ ዓላማዎች በእኩል ቁመት ነው፡፡ በተጨማሪም በተሰበሰብንበት የነበሩ ሰንደቅ ዓላማዎች የክልሉ በቀኝ፣ የፌዴራሉ ደግሞ በግራ ነበሩ፡፡ ይኼ የሚያሳየው መንግሥት በሰንደቅ ዓላማ ጥቅምና አገር ግንባታ ብዙ እንደማይጨነቅ ነው፡፡ ባይሆንማ ኑሮ ራሱ ያወጣውን አዋጅ ራሱ ባልጣሰ ነበር፡፡

ለነገሩማ መንግሥት ከዚህ ርዕስ ጋር ባይገናኝም የተለያዩ ሕጎችና ሕገ መንግሥት በመጣስ ቁጥር አንድ መሆኑን ሁልጊዜ የምንታዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሕገ መንግሥት ውጪ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢትዮጵያ ሶማሌ ሲል ሰይሞታል፡፡ ይህንን ስም ማስተካከል የሚያስፈልግ ከሆነም መጀመርያ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን መንግሥት ሥልጣኑን እስካልነካው ድረስ ሕጎች ብሎም ሕገ መንግሥት ቢጣስ ባይጣስ ምናገባው፡፡ ከተነሳሁበት አጀንዳ ወጣሁ ይቅርታ፡፡ ይሁንና መንግሥት ያወጣውን አዋጅ ማክበርና ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ ለአገር ግንባታ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ አነሳሁት እንጂ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም በሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች የሚስተዋል ችግር መሆኑን እኔ በግሌ የምታዘበው ነው፡፡ ይባስ ብሎም በአዲስ አበባ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ሰንደቅ ዓላማው ከደርጅታቸው ዓርማና ሎጎ እኩል ይሰቅሉታል፡፡ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቁበትም እዚያው ይኖራል፡፡ የሚያየውና የሚያስተውለው የለም፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት በዓሉ እንደ መልካም ዕድል ተጠቅሞ ለአገር ግንባታ ሊያወለው ይገባል እላለሁ፡፡ 

ሦስተኛው እስካሁን እንዳስተዋልኩት አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ በዓሉ የኢሕአዴግ በዓል እንደሆነ በማሰብ ብዙም ሲጠቀምበት አላየሁም፡፡ ሕዝቡ ለዚህ ጥርጣሬ ያበቃው ከላይ እንደገለጽኩት በአቶ መለስ ዜናዊ ስለሰንደቅ ዓላማ የተነገረውን አወዛጋቢ ቃልና የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚያደርጉት ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ሰንደቅ ዓላማ ማለት አገር ነው፡፡ የሚወክለው አገርን ስለሆነ በዓሉን ስናከብር አገራችንን ነው እያከበርን ያለነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢሕአዴግ ትናንትና ነው የመጣው፡፡ ነገ ደግሞ አይኖርም፡፡ አገርና ሰንደቅ ዓላማ ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም በምንም መመዘኛ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የኢሕአዴግ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቀው በዓሉ የአገርና የሕዝብ መሆኑን አውቀን ከኢሕአዴግ ልንቀማው ይገባል፡፡

በዓሉ የኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ ማሠራጫ እንዳይሆን ሁሉም ዜጋ በበዓሉ በመሳተፍ ጀግኖች አርበኞችን ልናሰታውሰቸው ይገባል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶች ምርምሮች በማድረግ ለበዓሉ ድምቀትና ለአገር ግንባታ የራሳችን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ካልሆነማ በገዛ በዓላችን ትናንትና የመጣና ነገ ደግሞ ትቶን ለሚጠፋ ድርጅት እንዲወስድብን ልንፈቅድ አይገባም፡፡ በእውነት ነው በዓሉ እየተከበረ ያለው ኢሕአዴግ መንግሥት ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ማለት በዓሉ የኢሕአዴግ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የአገርና የሕዝብ ምልክት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የመንግሥት ምልክት አይደለም፡፡ ሌላው ሕዝቡ ማድረግ ያለበት በየአካባቢው ያለውን የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም እንዲስተካከልና አገር በአንድ ሰንደቅ ዓላማ እንድትወከል የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ አለበለዚያ የሚወክለን ሰንደቅ ዓላማ ይጠፋንና በብዙ መስዋዕትነትና ጥረት በአባቶቻችንናእናቶቻችን የተመሠረተች አገር በማፍረስ፣ ሳናውቀው ድርሻ ይኖረንና በኋላ የታሪክ ተወቃሽ መሆናችን አይቀርም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ሚና መሆን የሚገባው በሕዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር በመረዳት አገራዊ ግንባታ እንዲፋጠን የተለያዩ አማራጮች ማቅረብና በሕዝብ ማስወሰን ነው፡፡ በእኔ እምነት መንገዱና አካሄዱ ይለያያል እንጂ፣ በአገር ግንባታ ፍላጎት የሚለያይፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለሆነም ከዚህ በፊት የተከበሩ የሰንደቅ ዓላማ ቀናት በተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች በጥርጣሬ ዓይን ሲታዩ ነበር፡፡ፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይሁንና በእኔ እምነት ሰንደቅ ዓላማ የአገር አስከሆነ ድረስ ጀግኖች አባቶችና እናቶች አስታውሶ መዋል ለፖለቲካ ድርጅቶች ከሕዝብ ጋር ያላቸው መቀራረብ ይበልጥ ሊያጠናክርላቸው ይችል እንደሆነ እንጂ የሚጎዳቸው አይመስለኝም፡፡ አለበለዚያ እነሱም በዓሉ ለኢሕአዴግ ብቻ ሰጥተው ከተውት ከዜሮ ለመጀመር የተዘጋጁ መሆናቸው ስለሚያሳይ በሕዝብ ላይ ያላቸው አመኔታ ከጥርጣሬ ውስጥ ይገባል፡፡

በእኔ እምነት የፓርቲዎቹ ፍራቻ ሚዲያ ስለማያገኙ በዓሉን ካከበርን ገዥው ፓርቲ ድጋፍ እንደሰጠነው አድርጎ በተቆጣጠራቸው፣ የሕዝብ ሚድያዎች ሊያቀርብ ይችላል የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ሥጋት ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ዘመን መልዕክት የምታሰተላልፍበት ሚድያ አማራጭ ብዙ ስለሆነ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሥጋታቸውን አስወግደው ሥልጣን እስከሚዙ ከመጠበቅ ይልቅ አሁኑኑ በዓሉበማክበር ለሰንደቅ ዓላማና ለአገር ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት መግለጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲሁም በአገር ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በውይይትና በመግባባት በማክበር ስለሆነ ይህ የአገር በዓል በፈቃዳችሁ ለአንድ ድርጅት አትስጡት፣ መድረኩ ተጠቀሙበት፡፡ የመንግሥትና የገዥው ግንባር ድክመት አሳዩበት ለአገር ግንባታ እንዲሠራ ገፋፉት፡፡ ለአገራችን ግንባታና ምሥረታ የደከሙና የለፉ አባቶችና እናቶች በማሰብና በማስታወስ፡፡ ግን በጥናትና ምርምር መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ፕሮፓጋንዳ ሆኖ ይቀራል፡፡

አራተኛ ለሚድያዎች ያለኝ አጭር ማሳሰቢያ ቀድማችሁ ሂዱ የሚለው ነው፡፡ አሁን እያየነው ያለነው የመንግሥት ጭራ ተከትላችሁ መዘገብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማንም ተራ ሰው ሊያደርገውሚችል ተግባር ነው፡፡ ጋዜጠኛ ግን ቀዳሚ መሆን አለበት፡፡ ቢያንስ ለአገር ምሥረታና ግንባታ ሕይወታቸውንና ጉልበታቸውየገበሩ ጀግኖች በጥናትና በምርምር ቀድማችሁ በማቅረብ ቀኑን ደማቅ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለው መንግሥት ለአገር ግንባታ የሚያደርገው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ በጥናት በተደገፉ ዘገባዎች በማቅረብ፣ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ በተጨማሪም የሰንደቅ ዓላማ አዋጅን ከማስከበር አንፃር መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ያለባቸውን ክፍተት በተጨባጭ ሕዝቡ ዘንድ በመውረድ ማሳየት ትችላላችሁ፡፡

በዓሉ ጀግኖቻችን የምናስታውስበትና ከፕሮፓጋንዳ የፀዳ እንዲሆን እየተመኘሁ፣ በዓሉ የሁሉም ዜጋ በመሆኑ ሁላችንም በድምቀት ሊናከብረው ይገባል፡፡ አገር ለመመሥረትና ለመገንባት ሕይወታቸውላጡና አካላቸውን ለከፈሉ ጀግኖች ክብር ይሁን!!

በተስፋዝጊ የዕብዮ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡