Skip to main content
x

እንዲያው በጨረፍታ ልባችን አይምታ!

እነሆ መንገድ ከመገናኛ ወደ አያት። ‹‹የቆጡን እናወርዳለን ብለው የብብታችንን አስጣሉን እኮ እናንተ!›› ይላል አንዱ። ደንዳና ሰውነቱ መተማመኛ ዛኒጋባ እንዳጣ ያስታውቅ ነበር። ‘እንዴት? እነማን ናቸው እነሱ?’ መሰል ተመሳሳይ ጥያቄዎች የሚጠይቀው ሰው አጠገቡ የለም። መንገዱ ተወጥሮ ከአሁን አሁን ተነፈሰ እያስባለ ያራምደናል። ታሪክ ቆጣሪ ያለፈውና የሚመጣውን አቀናጅቶ በሚያሰናኝበት የብራና ቅኝቱ የሚከተብና የማይከተብ ሀቅ እዚህ ጎዳና ላይ ይቀመራል። ውለውም ሆነ አድረው ተጠያቂዎቹና ተተቺዎቹ ተመሳሳይ ናቸው። በምንመላለስበት ጎዳና ሁሉም የሰው ጉድፍ ጠቋሚ ነው። ራሱን የሚታዘበውና የሚተቸው ማን ነው? ወደ ውስጥ ከመተንፈስ ወደ ውጭ እየቀለለን አንዳንዱ አተነፋፈሳችንን ግብዝነት እያጠቃው የመጣ ይመስላል። ከትናንት እስከ ዛሬ ምናልባት ነገም ይኼ ክፉ አመል ከመንገዱ ላይ የማይኖር አይመስልም።

ከጥግ እስከ ጥግ በዘርፍ በዘርፉ ወግ ይሰለቃል። ሐሜቱ፣ ብስጭቱ፣ ምሬቱ፣ እንጉርጉሮው... ልክ አልነበረውም። ልክ ያለው ነገር ጠፍቷል። እንቅስቃሴውና ሒደቱ ግን ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በትናንቱ ጎዳና ላይ ዛሬም የሰለቹ ኮቴዎች ከእነ እንጉርጉሯቸው አቧራ ማቡነኑን ገፍተውበታል። ትዝታ አዘሉ ሒደት በማድያት የተወረረ ነው። ትውልድ ሊያጠራው ያልቻለ ችኮነት አለበት። እንኳን ነዋሪው እንኳን ተወላጁ መንገዱም ይኼን ችኮነት ሳይሰለቸው አልቀረም። ከግዑዝ እስከ ነፍስ አዋቂው የዚህች ምድር ቋጠሮ ያላማረረው የለም። ግን ለመኖር ነገን መናፈቅ ግድ ነውና፣ ያልታየን መመኘት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነውና፣ ከመሞት መሰንበት ዛሬም የኃይል ሚዛኑን እንደተቆጣጠረ ነው። ‹‹ይህ ባይሆን ምን እንሆን ነበር?›› ይላል ከጎኔ የተቀመጠ ወጣት። አባባሉ ብቻ ከሐሳቤ ገጠመ እንጂ በምን ሰበብ እንዲያ እንዳለ አልተረዳሁትም። ይሄም አንድ ገጽታችን ነው። አለመደማመጥ!

ጉዟችን እየተጀመረ ነው። የታክሲያችን ወያላ የሚጠግብ አይመስልም።  ‹‹እህ ትሄጃለሽ እሙዬ? እ? አጎቴ? አክስቴ? አባቴ? እናቴ?›› እያለ ያልተዛመደውን እያዛመደ አፉ ሰው ያጠምዳል። ‹‹ኧረ እንሂድ? ሞልቷል እኮ...›› ይሉታል መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ። ‹‹የት ለመድረስ ነው ይህን ያህል ችኮላ? ግፋ ቢል አንድ እንቁጣጣሽ፣ አንድ ገና፣ አንድ አረፋ፣ አንድ ረመዳንና አንድ ፋሲካ ናቸው የሚቀሩን። ስንገፋው የማይገፋ ስናልፈው የማያሳልፍ የመፈጠር ዕዳ...›› ብሎ ወያላው ወደ ሾፌሩ እየተገላመጠ ምልክት ሰጠው። ሾፌሩ ማንቀሳቀስ ጀመረ። ‹‹አንድ አንድ ስትላቸው ቀላል ይመስላሉ። ሲመጡ ጭንቁን የምናውቀው የወለድነውና የከበድነው ነን። እናንተማ ምን አለባችሁ?›› ብለው መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጡት ወይዘሮና ጎልማሳ አጉተመተሙ።

‹‹እኛ እነማን ነን?›› አላቸው ወያላው። ‹‹ወጣቶች! በየሄዳችሁበት ለምዳችሁ ያገኛችሁትን ተካፍላችሁ፣ በጎደለባችሁ ተፅናንታችሁ ታልፉታላችሁ። የወለደ ግን ስንት ጭንቅ አለበት መሰለህ? ልጅ የለመደውን ነገር በቀላሉ አይረሳልህም። የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ የገንዘብ የመግዛት ዋጋ ማሽቆልቆል የዶላር አራት ብር መጨመር ለእነሱ ምንም ናቸው፤›› ሲሉት፣ ‹‹እዚህ ሠፈርም ኑሮ ይወደዳል እንዴ? አይመስለኝም ነበር። ለማንኛውም ለሚመጣው እሱ ያውቃል አይዞን፤›› ብሎ እጁ ላይ ያለውን ገንዘብ መቁጠር ጀመረ። ‹‹ምን አልፎ ነው ለሚመጣው እሱ የሚያውቀው? ሌላ ጎርፍ መጣ እንዴ?›› ብላ መጨረሻ ወንበር የተሰየመች ወጣት ስትጠይቅ፣ ‹‹ኧረ ዝም በይው። በሰላም አገር በሰላም ያለፍነውን ዓውደ ዓመት እኮ ነው እንዲህ ምፅዓት ያስመስለው፤›› ይላታል ከጎኗ። ደስታና እርካታ ዱሮስ ለጎደለበትና ላልጎደለበት እኩል ነው እንዴ?!

ጉርድ ሾላን አልፈናል። በተቀደደው ስፒከር በኩል ‘ወገኔ ያገር ልጅ ወገኔ’ የሚል ዜማ አትኮሮታችንን ሰርቆ ይሰማል። ‘እንሟገትላት እናንሳት እያሏት፣ መቼም ያፈራችው አይጠላት አይጠላት’ የሚለው ስንኝ ተሳፋሪዎችን ከንፈር ያስመጥጠዋል። ‹‹ይገርማል እኮ እናንተ አላችሁ በሚሉን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅመን ከምንጮኸው ይልቅ፣ በአምባሰልና በትዝታ ቅኝት የምንተነፍሰው ተሻለን እኮ?›› ይላል ከመሀል። ሌላው ደግሞ ይቀበልና፣ ‹‹በባዶ ሆድና በባዶ ጭንቅላት መብት ብሎ ነገር ነው የማይገባኝ!›› ይላል። ሰው የሚናገረው በገባውና በሚያውቀው ልክ መሆኑን አስምረንበት እንደማመጣለን። ‹‹ታዲያ መብታችንን ለሆድና ለጥቅም አሳልፈን እየሰጠን ሙሰኛውና አምባገነኑ ቢፈነጭብን ምን ይገርማል?›› ትላለች ወጣቷ። ‹‹ንሺማ ጠይቂው?›› ይላል በወዲህኛው መደዳ ጋቢ የለበሰ የአገር ቤት ሰው።

‹‹ይኼ እኮ ነው የአገሬው ችግር። ሦስተኛው ዓለም ውስጥ እንደምንኖር እንረሳዋለን። የዕውቀትና የምግብ ዋስትናችንን ሳናረጋግጥ የመብት ዋስትና ለማረጋገጥ የኋሊት እንራመዳለን። በዴሞክራሲ ስም ዲክታተር እንኮለኩላለን። በአብዮት ስም ትህትናን ጥለን ትዕቢት እንሸላለማለን፤›› እያለ ወጣቱ አባባሉን ለማስረዳት ተጣጣረ። ‹‹አቦ አትፈላሰፍ! ፍልስፍና እንኳን ለአንተ ለእነ ማርክስ ለእነ ሌኒንም አልጠቀመ፤›› ሲል ከወዲያ ማዶ አንዱ ቀጠን ባለ ድምፅ  ወዲህ ደግሞ፣ ‹‹አንዳንዱ ሰው እኮ ይገርማል! በቋሚነት ለማይኖር ሐውልትና ስም ኖሮ ለማለፍ ይፍጨረጨራል። ዘመኑ የዚህ (ብር እንደሚቆጥር አውራ ጣቱንና ጠቋሚ ጣቱን እያፋተገ) መሆኑ እየታወቀ ላም ባልዋለበት ኩበት ይለቅማል፤›› ይላል። ከጎኑ የተቀመጠ ጎልማሳ። ልጁ ገንዘብ በገነነበት ዘመን ሐሳብ ለማንጠር በመፍጨርጨሩ በራሱ ሲበሳጭ ይታያል። የጭውውቱና የሚነሱት ሐሳቦች ጉራማይሌነት ሰው በትክክል የሚያስበውንና የሚፈልገውን ማወቅ እንደተሳነው ያሳብቁበታል። መንገድ ሀቅን ሁሉ ዘርግፎ ታዘቡት ይለናል። እንሄዳለን እኛ!

ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ወይዘሮዎች የያዙት ጨዋታ በአካባቢያቸው ያለነውን ተሳፋሪዎች ቀልብ ስቧል። ሁለቱ ወይዘሮዎች እርስ በርሳቸው አንቱ እየተባባሉ ነው የሚጨዋወቱት። ዘመናቸው ያስጠናቸው እንዲህ ያለውን መቀባበልና መከባበር ብቻ ይመስላል። ‹‹ልጅዎ እንዴት ነው? እየተማረ ነው?›› ይላሉ በመስኮቱ በኩል ጥግ የተቀመጡት። ‹‹ኤድያ ምኑን ይማረዋል? ያንዛርጠዋል እንጂ!›› ይላሉ መልስ የሚሰጡት ወይዘሮ። ‹‹የለም መምከር መቆጣት ነው። ልጅ አይደል...›› ሲሉ በምናብ የሳልነውን ታዳጊ ልጅ ጉዳይ ያነሱት ወይዘሮ፣ ‹‹የዘንድሮ ልጅ ነው የሚመከረው? ጫትና ‘ቻት’ ያለዕድሜያቸው ይለምዳሉ፣ አንድ ሲሏቸው አንድ ይላሉ። መቼ ያዳምጣሉ?›› አሉ የወዲህኛዋ። ‹‹ይኼን ጫት ያላመረረና ያላማረረው የለም እ? ታዲያ ምን እንብላ? አንድ ሺሕ ብር በማትሞላ ደመወዛችን እንኳን ጤፍ ልንሸምት ከሱቅ እንጀራ ገዝቶ መብላት የሚቻል አልሆነም፤›› ይላል ሌላው።

ነገሩ እየተጋጋለ ሄደ። ‹‹መንግሥትስ እሱን ብሎ አይደል ወጣቱ ሲደነዝዝ በርቱ የሚል በሚያስመስል ዝምታ የተጀቦነው?›› ብላ አንዲት ወጣት ዘው አለች። ‹‹ምን ብንለው ምን ስቅ ላይለው በከንቱ እኮ ነው ስሙን የምናነሳው?›› አላት ከጎኗ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹እሱስ እውነትህን ነው፤›› ብላ ዝም ከማለቷ ሁለቱ እናቶች ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ‹‹እሱ ፈጣሪ ይርዳቸው ማለት እንጂ ይኼን ዘመን ምን ዓይነት ምክር ያሳልፋቸዋል ብለው ነው?›› ይባባላሉ። ‹‹እውነት ነው! እውነት ነው!›› ሥጋትና ቅሬታ ልሳናቸው ውስጥ ለውስጥ ይሹለከለካሉ። ‘እህትማ ነበራት ያውም የእናት ልጅ፣ ተሟግቶ የሚረታ ወንድም አጣች እንጂ’ ሆኖባቸው ነገሩ ግራ ተጋብተዋል። ግጥሙን ሳይቀር ‘ኢትዮጵያ አገሬ ታጠቂ በገመድ ልጅሽን ሱስ ነው እንጂ አይቀብረውም ዘመድ’ ብለው ሳይቀይሩት አልቀሩም። ኅብረት ጉልበት አጥቶ ትውልድ ምግባር ላይ ሲያለምጥ እያዩ የሚያደርጉት ቢያጡም በሐሳብ መብሰልሰላቸው አልቀረም። ምንስ ቢሆን የወለደ መቼ ይችላል?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መልስ ያልተቀበሉ ተሳፋሪዎች ወያላው ላይ ይጮሃሉ። ያለ የሌለውን ሳንቲም አሰባስቦ ላልደረሳቸው ማዳረስ ሲጀምር፣ ‹‹ለመሆኑ እጅህን በሳሙና ታጥበሃል? ቀኑ እኮ እጅ የመታጠብ ቀን ነው፤›› አሉት ወይዘሮዋ። ወያላው ፈገግ ብሎ ነገር ሲያስብ ጋቢና የተሰየመው ወጣት፣ ‹‹እጃችን ቢታጠብ ብሩ ካልታጠበ ምን ዋጋ አለው ብለው ነው? እኛን እስኪ አሁን ጀርም ሊገለን?›› አለ። ‹‹ጀርም ያለው ጀርመን ነው ሲባል አልሰማህም?›› አለው። ‹‹ጀርመንን ለቀቅ ዶላርን ጠበቅ ወንድሜ። ዩሮ ምን አደረገን? እሮሮአችንን የሚያባብሰው ዶላር ነው። ይኼው በቀደም አከራዬ ዶላር ጨመረ ሲባል ሰምተው ገና ከእንቅልፌ ሳልነቃ፣ እንኳን የዶላርን መጨመር የዶሮ ጩኸት ሳልሰማ በሬን በተጠባባቂ ቁልፋቸው ከፍተው ገብተው ከእንቅልፌ ቀስቅሰው የቤት ኪራይ እንደጨመሩብኝ ነገሩኝ። ይኼን ይዘህ ቤት የሌለውን ቤተኛ አሳሩን ቁጠር፤›› አለ ከመጨረሻ ወንበር አንዱ። ‹‹እግዚኦ ማለትም አላዋጣን አለ እኮ ዘንድሮ፤›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹አየር ንብረቱንና ንፍቀ ክበቡን ትራምፒዝም ተቆጣጥሮት ፀሎታችንስ በየት አድርጎ አርያም ይድረስ?›› ብለው ወይዘሮዋ ጥያቄን በጥያቄ አጣጡ።

‹‹ፀሎትም በዶላር መመንዘር ጀመረ እያሉን እንዳይሆን?›› ሲል ደግሞ ጎልማሳው፣ ‹‹ይቀራል እንዴ?›› አለ የወጣቱ ድምፅ በጋራ። ‹‹ይብላኝ ለሚወለደው እንጂ እኛስ ሞትን በቁም ተለማምደን ጨርሰናል፤›› ብሎ ጎልማሳው አጉረመረመ። ‹‹አይዞህ ድምፅን ከፍ አድርገህ ተናገር። የአገራችን ችግር የድምፅ አይደለም። የትርጉምና የምንዛሪ ነው አለው፤›› ከጎኑ ተደርቦ በከፊል አየር ላይ የሚንሳፈፈው ተሳፋሪ። ‹‹ታዲያ ይኼ ሁሉ ብሶት እያለ ነው እጅን በሳሙ የመታጠብ ቀን በመላው ዓለም በአንድ ቀን የሚከበረው?›› ስትል ደግሞ ከጎኔ፣ ‹‹እሱንስ ማን አየብን? ባልታጠበ እጅና ሐሳብ እያቦካነው መሰለኝ ችግርና ጠኔ ያሻቀበብን፤›› አላት የጋቢናው። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሏል። መጣያ ያጣውን ቆሻሻና ማረፊያ ያጣውን ምስኪን መንገደኛ ብሶት ሰብስቦ አሳዳሪ ጨለማ አገሩ የት ይሆን ነው ጥያቄው። ገፋ ሲል ደግሞ ከዶላሩም በላይ ከዩሮውም በላይ የሚያሳስበን የውሎና የአዳራችን ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዲያው በደምሳሳው እንዲያው በጨረፍታ ልባችን አይምታ ማለትስ አይገባንም? መልካም ጉዞ!