Skip to main content
x
አበበ ቢቂላ እና ጥቅምት 11 በቶኪዮ ኦሊምፒክ

አበበ ቢቂላ እና ጥቅምት 11 በቶኪዮ ኦሊምፒክ

‹‹በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ
አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ፤
በጥቅምት 11 በሩጫው ገበያ
አቤ ይዞት መጣ የወርቁን ሜዳሊያ››

የሚለው ዘፈን ከተዘፈነ ጥቅምት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. 53 ዓመት ሞላው፡፡
ኢትዮጵያ በየአራት ዓመቱ በሚከናወነው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለመጀመርያ ጊዜ በማራቶን በሮም ኦሊምፒክ (ጳጉሜን በ1952 ዓ.ም.) ያስገኘው አበበ ቢቂላ (1925-1966) በቀጣዩ የቶኪዮ ኦሊምፒክ (በጥቅምት 1957 ዓ.ም.) ሁለተኛውን ወርቅ በድል አድራጊነት ሲያጠልቅ ነበር፤ የመሥሪያ ቤቱ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሙዚቀኞች እነ ጥላሁን ገሠሠ የዘፈኑለት፡፡

 ቶኪዮ 18ኛውን ኦሊምፒያድ ስታስተናግድ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ድሉ ሲያመራ ሁኔታው አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ ከውድድሩ 42 ቀናት በፊት የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና አድርጎ ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም ነበር ወደ ሥፍራው ያመራው፡፡

አበበ ቢቂላ ከኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ቡድን ጋር አብሮ ወደ ቶኪዮ ሲጓዝ በርትቶ ይወዳደራል ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም። አበበ እንደሮም በባዶ እግሩ ሳይሆን ጫማ አድርጎ ለማራቶን ውድድር ከአርባ አንድ አገሮች ከተውጣጡ ሰባ ዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ጋር የተሰለፈው ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ነበር፡፡ 
በውድድሩ ሒደት በ15ኛው ኪሎ ሜትር ላይ አብረውት የነበሩት የአውስትራሊያው ሮን ክላርክና የአየርላንድ ጄምስ ሆጋን ብቻ ነበሩ። አበበ ቢቂላ በቀዶ ሕክምናውም ሆነ በሞቃታማው የአየር ሁኔታ ምንም ዓይነት እንከን አልታየበትም።

 አበበ ቢቂላ ኦሊምፒክ ስታዲዮሙ ውስጥ የገባው ብቻውን ነበር። በዚያም ይጠባበቅ የነበረው 70 ሺሕ ተመልካች በከፍተኛ ሁኔታ አድናቆቱን ገልጾለታል። በዚህ ውድድር ላይ የራሱን ክብረ ወሰን በድጋሚ በመስበር አሻሽሎታል። አዲሱ ክብረ ወሰንም 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ ነበር። ውድድሩንም እንደጨረስ ምንም ዓይነት ድካም አልታየበትም። እንዲያውም ገና ሊሮጥ የሚሰናዳ ነበር የሚመስለው። ተመልካቹን በጣም ያስገረመው በውድድሩ ምክንያት ጡንቻውና መገጣጠሚያዎቹ እንዳይተሳሰሩ የተለያዩ የሰውነት ማሟሟቂያ እንቅስቃሴዎች ሲሠራ መመልከታቸው፣ እንዲሁም እርጋታውና ቅልጥፍናው ነበር። አበበ ከውድድሩ በኋላ ተጠይቆ ሲመልስ ሌላ 10 ኪሎ ሜትር ጨምሮ መሮጥ ይችል እንደነበር ተናግሯል። ደምሴ ወልዴ በአሥረኛ ደረጃ ሲጨርስ በ10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ማሞ ወልዴ ግን ሕመሙ አገርሽቶበት 15ኛው ኪሎ ሜትር ላይ አቋርጦ ከውድድሩ ወጣ።

አበበ ከሮሙ ድሉ አራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ ድሉን ሲደግም የኦሊምፒክን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ክብረ ወሰን መስበር ችሏል። ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድልንም ፈጸመ። ይኸም ብቻ አይደለም ባሸናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰከንድ)፣ 8 ሣልሲት (ማይክሮ ሰከንድ) የሰበረበት ነው:: በውድድሩ አበበን ተከትለው የገቡት እንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይና ጃፓናዊው ኮቺ ሱባራያ ናቸው፡፡ 

‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፤ 
ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደ ቆሎ፤›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊና የልዑካኑ መሪ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914 - 1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል። 

ፎቶዎቹ በቅደም ተከተል አበበ የኦሊምፒክ ልዑካንን እየመራ (ከኋላው በግራ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ)፣ በልምምድ ከደምሴ ወልዴ ጋርና የውድድሩ ሒደትና ፍጻሜ እስከ ሽልማት ሥነ ሥርዓቱ፣ እንዲሁም ከታዋቂ የጫማ አምራች ኩባንያ ባለቤት ጋር ሆኖ ያሳያሉ፡፡

- ሔኖክ መደብር 

*****
‹‹አበበ እንጂ መቼ ሞተ!››
የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለት፤ የምድር አጥናፍና አድማሱ
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል
የምድር ዓለሙ ገሞራ
አገሩን በክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ።
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ
ያረጋት የኦሊምፒክ ዓርማ
በወገኖቹ ልቦና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ፤ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍሥሐዋን አዋጅ ለዓለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የዓለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ፤ ‹‹አበበ እንጂ መቼ ሞተ!››

ጸጋዬ ገብረመድኅን