Skip to main content
x
ለንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ለመጀመርያ ጊዜ ከሁለት በላይ ዕጩዎች ቀረቡ

ለንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ለመጀመርያ ጊዜ ከሁለት በላይ ዕጩዎች ቀረቡ

አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውና በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ለመጀመርያ ጊዜ ከሁለት በላይ ዕጩዎች ቀረቡ፡፡ ሪፖርተር ሕትመት እስከገባት ዓርብ ምሽት ድረስ አራት ዕጩዎች መጠቆማቸው ታውቋል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መካሄድ ከነበረበት በአንድ ዓመት ዘግይቶ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለፕሬዚዳንትነት ቦታው እንዲወዳደሩ አባል ምክር ቤቶች ዕጩ አድርገው ካቀረቧቸው መካከል ከኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አቶ ፈይሳ አራርሳ፣ ከአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ አቶ መላኩ አዘዘው (ኢንጂነር) እንደሚገኙበት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ በአሁኑ ወቅት በንግድ ምክር ቤቱ ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ጉድ ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ  ውብሸት ኃይሉ (ኢንጂነር) ተወዳዳሪ አድርጎ ሲያቀርብ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ደግሞ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ሌላው ዕጩ ተወዳዳሪ አድርጓቸዋል፡፡ ዕጩዎቹ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ዕጩዎችን ምርጫው ከመደረጉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለ18 አባል ምክር ቤቶች እንዲያሳውቁ በተደረገው ጥሪ መሠረት ነው፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በተሰጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ 18ቱም አባል ምክር ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ድርሻዎች ላይ ሊሠሩልን ይችላሉ ያሏቸውን ሁለት ሁለት ዕጩዎች በማቅረብ ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ18ቱ አባል ምክር ቤቶች ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ አድርገው ከላኩት አራት አባል ምክር ቤቶች ሌላ፣ የኢትዮጵያ ዘርፍና ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ አንድ አባሉን ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል፡፡

የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በዕጩነት ያቀረባቸው አቶ መላኩ በቅርቡ የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት  ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዕጩ ያደረጋቸው አቶ ፈይሳ አራርሳ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ሌላው በዕጩነት የቀረቡት አቶ ፋሲል ደግሞ ለበርካታ ዓመታት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ በ176 ወንበሮች የሚወከል ሲሆን፣ እያንዳንዱ አባል ምክር ቤት ባሉት አባላት ቁጥር ልክ የወንበር ውክልና ተደልድሏል፡፡ በዚህ ድልድል መሠረት የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 49፣ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 31፣ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት 27፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ 21 ወንበሮችን በመያዝ ከፍተኛ ድርሻ ይዘዋል፡፡ አሁን በተደረገ ውክልና መሠረት ከሁለት በላይ ተፎካካሪዎች የሚወዳደሩበት የሚደረግበት ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እስከ ዓርብ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ዕጩዎቻቸውን ያላሳወቁ ንግድ ምክር ቤቶች ለፕሬዚዳንትነትም ሆነ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታው ተወዳዳሪዎችን ሊልኩ እንደሚችሉ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡