Skip to main content
x
የብር ምንዛሪ ለውጥ የነዳጅ ዋጋ ያንራል የሚል ሥጋት ፈጥሯል

የብር ምንዛሪ ለውጥ የነዳጅ ዋጋ ያንራል የሚል ሥጋት ፈጥሯል

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በብር ምንዛሪ ላይ ያደረገው የ15 በመቶ ለውጥ የነዳጅ ዋጋ ያንራል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የተዳከመውን ኤክስፖርት ዘርፍ እንዲያንሠራራ ለማድረግ የብር ምንዛሪ በ15 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ዕርምጃው የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎችን አስደንግጧል፡፡ የምንዛሪ ለውጡ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንደሚፈጥር፣ በገቢና በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ዋጋ ጭማሪ በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን ያባብሳል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተማራማሪ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የምንዛሪ ለውጡ አገሪቱ ከውጭ ገዝታ በምታስገባቸው የነዳጅ ምርቶች ላይ በቀጥታ ቢያንስ የ15 በመቶ ጭማሪ ያስከትላል፡፡ ‹‹መንግሥት ወዲያውኑ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ላያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የምንዛሪ ለውጡ በነዳጅ ግዥ ላይ የ15 በመቶ ጭማሪ ያሳድራል፤›› ያሉት ተመራማሪዎች የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ በሁሉም ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስከትል ገልጸዋል፡፡

የብር የመግዛት አቅም በአንድ በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ በዕቃዎቹ ዋጋ ላይ የሁለት በመቶ ጭማሪ እንደሚያስከትል ገልጸው፣ የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ በመደረጉ በዕቃዎች ዋጋ ላይ የ30 በመቶ ጭማሪ እንደሚያስከትል ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ድምር ውጤቱ ሲሰላ 30 በመቶ የዋጋ ግሽበት ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ነው በዚህ መጠን የምንዛሪ ለውጥ መደረግ የለበትም የምንለው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ በየዓመቱ በአሥር በመቶ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት 3.8 ሚሊዮን ቶን የደረሰ ሲሆን፣ ለዚህም መንግሥት ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምንዛሪ ለውጡ በነዳጅ ግዥ ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ‹‹የምንዛሪ ማስተካከያው በነዳጅ ግዥ ላይ የተወሰነ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ስትራቴጂካዊ ምርት በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርግበታል፡፡ እንደ ማንኛውም ምርት የሚታይ አይደለም፡፡ በግዥ፣ በተመን አወጣጥና በማከፋፈል ሥራ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት የተለየ ምርት ነው፡፡ ዛሬ የምንዛሪ ለውጥ በመደረጉ ነገ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይደረጋል ማለት አይደለም፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ መንግሥት የነዳጅ ተመን ማስተካከያ በሚያደርግበት ወቅት በርካታ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት እንደሚያስገባ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የነዳጅ ውጤቶችን ራሱ ገዝቶ የሚያመጣቸው በመሆኑ ያለውን ወቅታዊ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ዋጋ ተንተርሶ የዋጋ ተመን እንደሚያደርግ ገልጸው፣ የምንዛሪ ለውጥ በሌለበትም ጊዜ የዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የነዳጅ ተመን ሲያወጣ ያለውን የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታና የኑሮ ውድነት ከግንዛቤ እንደሚከትና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከብሔራዊ የፕላን ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

‹‹ሁልጊዜም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዳ በተቻለ መጠን መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ በቅርቡ የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ በነዳጅ ግዥ ላይ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይደረግ ወይስ አቻችሎ ባለው ይቀጥል የሚለው የፖሊሲ ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የየዕለቱን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በመመልከት የወሩን አማካይ ዋጋ በማውጣት ለንግድ ሚኒስቴር የሚያቀርብ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ የቀረበለትን ዋጋ ተመልክቶ የራሱን ቀመር በመሥራት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ካፀደቀ በኋላ በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

የየወሩን የአገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ ተመን የሚያወጣው ንግድ ሚኒስቴር የምንዛሪ ለውጡ በነዳጅ ተመን ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የሚኒስቴሩ አንድ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ የመጨረሻውን የነዳጅ ተመን ማስተካከያ ያደረገው መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ቀጣይ የተመን ማስተካከያ የሚደረገው ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. መሆኑን ገልጸው፣ የነዳጅ ተመን ሥሌት የሚሠራው በከፍተኛ ሚስጥራዊ አሠራር በመሆኑ ከወዲሁ ይጨምራል ወይም ይቀንሳል ብሎ መናገር እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሊጨምር ይችላል ወይም ባለበት ይቀጥል ሊባል ይችላል፡፡ ይህን የሚወስነው የበላይ አካል ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡