Skip to main content
x

ቀደም ብለን ስለምርጫ ብንነጋገርስ?

በዳግም አሳምነው ገብረ ወልድ

ሰሞኑን የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልውናን ያቀፈ ‹‹ቅይጥ ትይዩ›› እንዲሆን ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡ ለጊዜው ዝርዝሩ ላይ ለመነጋገር ባይቻልም ምርጫን በተመለከተ አንዳንድ ሐሳቦችን ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡

መቼም ገና  ታዳጊ  የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ  ለቆመች አገር መቼውንም  ቢሆን ስለምርጫና ሁለንተናዊ ገጽታ ብናወራ ነውር  የለውም፡፡ በተለይ አሁን ደግሞ ሰለሰላምና ዴሞክራሲ መጎልበት በወሳኝነት መነጋገር እንደማስፈለጉ ‹‹ምርጫ መቼ ደርሶ ነው ወጉ የቀደመው?›› አያስብልም፡፡ ለነገሩ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻና የመንግሥት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ ላይም ጉዳዩ መነሳቱን እናስታውሳለን፡፡ 

ስለዚህም ለዛሬ ከወራት በኋላ ስለሚካሄደው የአዲስ አበባ ምርጫም ሆነ የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ለመሰናዳትም ሆነ፣ በ2012 ዓ.ም. የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የተሻለ ዴሞክራሲያዊነትን ተላብሶ ከጭቅጭቅና ብጥብጥ የፀዳ ብሎም ለትውልዱ አንዳች በጎ አርዓያነት አስተምሮ እንዲያልፍ፣ ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቀውን ለመቆም ርዕሰ ጉዳዩን መርጨዋለሁ፡፡  

በቅድሚያ ግን ሕዝባዊ ምርጫን ዋነኛ የመገለጫው ማሳያ ስለሚያደርገው  ዴሞክራሲ  አንዳንድ ነጠቦችን ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ዴሞክራሲ ማለት የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ  የቆመ ሥርዓት ነው፡፡ በዛሬዋ ዓለም ደግሞ ዴሞክራሲ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሕዝባዊ ምርጫ በመሆኑ ደግሞ፣  ምርጫ  የህልውና ጉዳይ ሆኖ መምጣቱ አይቀርም፡፡

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል ምርጫ የሚካሄደው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥና ተቃዋሚ ሳይባል) ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሊያስገኝ  አይችልም፡፡ ለዚህም ነው በምርጫ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር ከተፈለገ  የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስፈላጊነት ማመንና መቀበል ግዴታ  ነው የሚባለው፡፡

ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና የጎላ ነው በሚለው ከተስማማን ደግሞ፣ በዚያው ልክ ሁሉንም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ወገኖች ሊያንቀሳቅስ የሚችል የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር የግድ ያስፈልጋል፡፡ በዚሁ ልክም ፓርቲዎቹ ‹‹ቆመንለታል›› የሚሉትን ሕዝብ (ቡድን) መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል አማራጭ ሐሳቦችን  ማመንጨት እንዳለባቸውም  መረዳት  ያስፈልጋል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን  በአገራችን እስካሁን ብልጭ ድርግም እንጂ፣ በዚህ በኩል ብዙም የተሳካ ጅምር አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡

     የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ገና ለጋ መሆኑ ቢታወቅም በሒደት ይጠናከርና ይጎለብት ዘንድ፣ ፓርቲዎች ሐሳቦቻቸውን ለቆሙለት ኅብረተሰብ (ቡድን) እና በጠቅላላው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በትኩረት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሐሳቦች በዴሞክራሲያዊ አኳኃን ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቃት ያለው አመራር አግኝተው መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚችሉበትን ሁኔታ በተግባር እንዲታይ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የተቃዋሚ ኃይሎችን ሚና ስንመለከተው በ1997 ዓ.ም. ሦስተኛው ዙር ምርጫ የተሻለ ወደ ሕዝብ የቀረበ ሚና እንደነበራቸው መጥቀስ እንችላለን፡፡

      ከዚያ  በፊትም ሆነ በኋላ በተካሄዱ ምርጫዎች ግን ከገዥው ፓርቲ ውጪ ያሉት     ፓርቲዎች በዝርዝር የተተነተኑ ሐሳቦችን ይዘው ሕዝቡን ለመሳብ የቻሉበት ዕድል ፈጥረው ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ እውነት ለመናገር የአገራችን አብዛኛዎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በተፅዕኖና በስሜት ‹‹ከመምረጥ›› ወጥተው መብትና ጥቅማቸውን የሚያስከብርላቸውን ፓርቲ፣ ካሉት ፓርቲዎች መካከል ለመምረጥ የሚችሉበት ዕድል አግኝተው ነበር ማለት ያስቸግራል፡፡ እስካሁን በፓርቲዎቹ ድክመትም ይባል በዴሞክራሲ ምኅዳሩ መጥበብ፣ የግራ ቀኙን ሰምተውና መዝነው ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ በራሳቸው ፈቃድ በነፃ ምርጫ ድምፃቸውን ሰጥተው  የሚመርጡበት ታሪካዊ ሁነት ላይ  ደርሰዋል የሚል ደፋርም አይገኝም፡፡

በየትኛውም አገር የሠለጠነ የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ማንኛውም ፓርቲ የሕዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ሲል የፈለገውን ቢሠራ፣ መራጩን ሕዝብ ‹‹በግድ እኔን ምረጥ›› ብሎ እጁን ይዞ በምርጫ ወረቀቱ ላይ ምልክት እንዲያደርግለት ማስገደድ አይችልም፡፡ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ግን በተለይ ገዥ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣናቸውን ጭምር በመጠቀም ይህን አንደሚያደርጉ በገሃድ የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ ሐሜት የፀዳ ነው ሊባል አይችልም፡፡

በእርግጥ ለዚህ ዓይነቱ ችግር መባባስ የሕዝቡ ግንዛቤ ወደ ኋላ መቅረትና በተደራጀና በሰላማዊ  መንገድ መብቱን ለማስከበር ያለመትጋት የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ ዕሙን ነው፡፡  በመሠረቱ  የምርጫ ሳጥን ውስጥ የሚገባው የምርጫ ወረቀት የመራጩን ስምና አድራሻ የያዘ አይደለም፡፡ ማን ማንን እንደ መረጠና እንዳልመረጠ ተለይቶ የሚታወቅበት ዘዴም  የለም፡፡ እንዲኖርም አይፈለግም፡፡ የተሰጠው ድምፅ በታዛቢዎች ፊት ተቆጥሮ አሸናፊው ከሚለይ በስተቀር ሌላ የመቆጣጠሪያና የማስገደጃ አሠራር የለም፡፡ አይኖርምም፡፡ ይህ በሚሆንበት አሠራር የመራጩ ፍርኃት፣ ይሉኝታም ሆነ ስሜት መወገድ ያለበት የዴሞክራሲ እንቅፋት ነው፡፡ ይህንን ብዥታ ሕዝቡ እንዲያስወግድ ፓርቲዎች፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሚዲያዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ግድ ይላቸዋል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ‹‹እነ እገሌ አልመረጡኝም›› ለማለት የሚያስችልና ለበቀል የሚዳርግ አሠራር የለውም ቢባልም፣ አንዳንድ ሕገወጥ አስፈጻሚዎችና ፀረ ዴሞክራሲ አስተዳዳሪዎች ችግር አይፈጥሩም ለማለት አይቻልም፡፡ ግን ሕዝቡ ከነቃ፣ ከተደራጀና የምርጫን አስፈላጊነት በአግባቡ ከተገነዘበ ሊያስቆማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የፓርቲዎች ሚና የቆሙለትን ማኅበረሰብና አጠቃላዩን ሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ሐሳባቸውንና ዓላማቸውን  ለመራጩ ሕዝብ ማሳወቅና ማሳመን ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ ይልቁንም በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ  የምርጫ ሒደት ውስጥ ሕዝቡ ከፍርኃት ቆፈን ወጥቶ ያመነበትን በነፃነት እንዲመርጥ ማነሳሳትም ሊሆን ይገባል፡፡

በመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምንላቸው አንድን የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ በዚያ ዓላማ ዙሪያ መሰባሰብና መታገል የሚፈልጉትን ዜጎች ለማደራጀት የሚሠሩ፣ መነሻና መድረሻቸውን በያዙት የፖለቲካ ዓላማ ላይ ብቻ ያደረጉትን ነው፡፡ ዓላማቸውን በሚገባ የተረዱና ያወቁ፣ የተነሱለትን ግብ  ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመተንተን፣ ለማቀናበርና ለሕዝብ ለማቅረብ ፍላጎትና አቅም ያላቸውን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በእኛ አገር ከምንም ተሰባስቦ ምንዱባን ለመለቃቀም የተሠለፈውን ዓይነትና በገዥው ፓርቲ ድክመቶች ዙሪያ የተኮለኮለውን ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ›› ሁሉ ሊያካትት እንደማይችል ግልጽ ነው (እዚህ ላይ ሰሞኑን ኢኤንኤን የተባለው የተሌቪዥን ጣቢያ በጉዳዩ ላይ ቀረበውን ሂስ አዘል ዘገባ ለማወደስ እወዳለሁ)፡፡

ፓርቲዎች የምንላቸው የራሳቸው ርዕዮተ ዓለም ያላቸው፣ ከሌላው የሚለያቸውን  አቋም  በግልጽ ያስቀመጡና ዓላማቸውን ማራመድ የሚችሉ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲገነባ መሆኑን በመገንዘብ የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ ለማድረግ የሚሠሩትን ነው፡፡ ከሌሎች የሚለያቸው አንድም መሠረታዊ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይኖር፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለአገሪቱ ዕድገት እንዲሁም ለሕዝቡ ተጠቃሚነት የተለየ አማራጭ ማቅረብ ሳይቻልና የብሔር ባርኔጣ እያጠለቁ በፓርቲ ስም የተሰባሰቡትን ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው›› ለማለት ይቸግራል፡፡ ደግሞም አይደሉም፡፡

ፓርቲዎች የምንላቸው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረውና የሕግ ማዕቀፉን ጠብቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱትን ነው፡፡ ስለሆነም የአገራችን ፓርቲዎች ለመጪው ጊዜ በተለይም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም፣ ዓላማና ግብ ያላቸው ምርጫውን በብቃት ለመወዳደር በመካከላቸው ያሉትን አነስተኛና መለስተኛ ልዩነቶች በውይይት በማጥበብና በመቻቻል ወደ አንድ ወይም ወደ ሁለትና ሦስት ፓርቲ ተሰባስበው ድምፃቸው ሰሚ እንዲያገኝ መሥራት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ መሰባሰብ ወይም መቀናጀት ለተወዳደሪነትና ለፍትሐዊ ምርጫ የሚበጅ እንጂ፣ ሌላውን ፓርቲ ለማጥፋት በጥላቻ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋቸዋል፡፡

መሰባሰባቸው በዓላማቸው ውስጣዊ አንድነት ላይ እንጂ አንድን ወገን ለመጣል ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ መሰባሰብ ሕዝባዊ አመኔታን ካለማስገኘቱም በላይ፣ በድቡሽት ላይ እንደተሠራ ቤት የሚፈራርስ አንድነት ይሆንና ለሥልጣን ሊያበቃቸው አይችልም፡፡ በሌላ በኩል መሰባሰብና መቀናጀት ካልተቻለ ማለትም የተወዳዳሪ ፓርቲዎች መብዛት ካለ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ ዓላማውን ለማስረዳትና መራጩን ለማዘጋጀት በሚዲያ የመጠቀም ዕድል (የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ) መጠን በቂ አይሆንም፡፡ በሌሎች ዘዴዎች ለመቀስቀስም ቢሆን በግል ሲንቀሳቀሱ ለኅትመትና ለስብሰባ የሚወጣው ወጪ ከአቅም በላይ ይሆናል፡፡

      ሕዝቡም የሁሉንም ፓርቲዎች መግለጫ ለማዳመጥና ለመመዘን ሳይቻለው ይቀርና የተደራጀውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድና ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በተቻለ መጠን መሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ የምንረዳው የፓርቲዎች ቁጥር (አናሳዎችን ጨምሮ) የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን፣ ለምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎች ግን ከሁለት ወይም ከሦስት አለመብለጡን ነው፡፡ መሰባሰብ ኃይል ነውና ፖለቲከኞች ሊያተኩሩበት ይገባል (በእርግጥ አሁን ያለው የአገራችን ፌዴራላዊ የፓርላማ ምርጫ፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫን በሚመስል መንገድ የተወዳዳሪ ዕጩዎችንና ፓርቲዎችን ለመቀነስ የሚያስችል እንዳልሆነም ማጤን ተገቢ ነው)፡፡

     በአገራችን ብቻ ሳይሆን ኬንያን በመሳሰሉ ታዳጊ አገሮች ምርጫ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር፣ ፓርቲዎች ሽንፈታቸውን ከወዲሁ እየተነበዩ የሚያቀርቧቸው ሰበቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በእኛም አገር አንዳንድ ፓርቲዎች የሚያነሱትን ሰበብ ለመረመረው ሰው ክፉኛ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ አንዳንዶቹ መንግሥት አገር በመምራቱ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት እንደተለየ ጥቅም በመቁጠር እኩል ምኅዳር ላይ አይደለንም ይላሉ፡፡ በምርጫው እንሳተፍ? አንሳተፍ? ወይም በሒደቱ ከገቡ በኋላ እንውጣ? አንውጣ?  የሚል ውዝግብን በመፍጠር የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ማለትን ማብዛቱ የትም ሊያደርስ አይችልም፡፡ መታረም ያለበትም ያልተገባ ዝንባሌ ነው፡፡ ስለሆነም መቼም ቢሆን ሕጋዊና ዴሞክራሲውን መንገድ ይዞ ሕዝቡንም እማኝ እያደረጉ በትግሉ በፅናት መጓዝ ብቻ ነው አማራጩ፡፡

በእርግጥ መንግሥትና አስፈጻሚዎች ከሕግና ሥርዓት በመውጣት ወይም የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት ለማሟላት የሚሠሩትን ሸፍጥ ማጋለጥና መታገል የፓርቲዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና የሕዝቡም መሆን አለበት፡፡ ሕዝቡ መንግሥት በሠራቸውና ባስመዘገባቸው ውጤቶች ተደልሎ ገዥውን ፓርቲ ይመርጣል ብሎ ማሰብና መሥጋት ሕዝቡን ከመናቅ የመነጨ እንዳይሆን፣ ሕዝቡን ለመርህና ለሕግ ዘብ እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በመሠረቱ ሕዝቡ ምንም ተደረገለት ምን ድምፅ የመስጠት መብቱ በእጁ ነው፡፡ ድምፅ አሰጣጡ በሚስጥር ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ይታለላል (አርሶ አደሩም ቢሆን) ብሎ በመሥጋት መሠረተ ቢስና አሳማኝነት የሌለው ሥጋት ውስጥ ከመግባት፣ ከምርጫ ቅስቀሳው ባልተናነሰ ለምርጫው ሕግጋት ጥብቅና እንዲቆም፣ ብሎም ለዴሞክራሲ ዘብ እንዲቆም ማድረግ ለነገ የሚባል ሥራ ሊሆን አይገባም፡፡

ምርጫ በመጣ ቁጥር በፓርቲዎች በኩል ከሚደጋገሙ ጩኸቶች አንዱ ‹‹የምርጫ ቦርድ ነፃ አይደለም. . . በመንግሥት ቁጥጥርና ተፅዕኖ ሥር ነው. . . በዚህ ቦርድ አመራር ፍትሐዊ የምርጫ ውጤት አናገኝም. . .›› ወዘተ. የሚል ነው፡፡  ይህንንም  ቢሆን በጥሞና ካጤነው ሕዝቡ በንቃት ፍርድ መስጠት ከቻለ የምርጫ ቦርድ ድምፅ አይሰጥም፡፡ ሕዝቡ ድምፁን በኮረጆ ውስጥ ያስገባል፡፡ ዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ታዛቢዎች (እዚህ ላይ ፓርቲዎች የራሳቸውን ታዛቢዎች ያለሥጋት ማሳታፋቸው መረጋጋጥ አለበት) እንዲሁም የተለያዩ የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ኮሮጀው ተከፍቶ በግልጽ ይቆጠራል፡፡ ይህ ውጤት ከየምርጫው ጣቢያዎች ወደ ቦርዱ ይተላለፋል፡፡ ቦርዱ ይህንኑ አጣርቶ አሸናፊውን ያውጃል፡፡ አለቀ በቃ! ይኼው ነው፡፡ ስለዚህ ቦርዱ እንደ ሥጋት የሚታይበት ሁኔታ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ካልሆነ ደግሞ በቂ መረጃ ይዞ ፍትሕ ደጃፍ ለመቆም ማሰብ ክብደት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ፓርቲዎች መሠረት በሌለው የ‹‹እንሸነፋለን›› ፍርኃት ወይም ሥጋት ራሳቸውን ለመደበቅ በማሰብ፣ በምርጫው ላለመሳተፍ መወሰን ወይም የምርጫ ጊዜው እንዲራዘም መጠየቅ ሊወገድ የሚገባው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ መጀመርያ እንደ ፓርቲ ሁሉም ቢሆኑ ተግባራቸው አድርገው መውሰድ ያለባቸው ማንኛውንም  ምርጫ በተነሳሽነት ለመሳተፍ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡

ሁለተኛ ማንም ሆነ ማን  በምርጫው መሸነፉን ቢገምት  እንኳን፣ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የእኔ መወዳዳር ያስፈልጋል የሚል እምነት መሰነቅ አለበት፡፡ ከሽንፈት ብዙ ትምህርት ይገኛል፡፡ የመራጩን ሕዝብ አቋምም ለመለካት ያስችላል፡፡ ለቀጣዩ ምርጫ በተሻለ ብቃት ለመዘጋጀት አመቺ ጎዳናን ያመላክታል፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ቀሪ ሥራዎችን አከናውኖ በምርጫ መሳተፍ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ የሆነው የምርጫ ወቅት እየመጣ እያለ ‹‹ምረጡኝ›› እንደ ማለት ፋንታ አመፅ ለማነሳሳት ወይም ሁከት ለመፍጠር ማሰብ፣ በአደባባይ ተሰብስቦ መቀመጥ፣ አካባቢዎችን በጩኸት መቀወጥ፣ የዩኒቨርሲቲና የከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለሁከት ማነሳሳት፣ በመንግሥትና በግለሰብ ሀብቶች ላይ ጉዳት ማድረስ. . . የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ፡፡ ምንም ተባለ ምን አገር ከመበደልና ሕዝብን ከማማረር ምንም አይፈይዱም፡፡  

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚነሱ ግርግሮች ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ባለመሆናቸው፣ ንቅናቄዎቹ ከቀስቃሾቹ ፓርቲዎች የመቆጣጠር አቅም በላይ ስለሚሆኑ ሰላምና ፀጥታን ያደፈርሳሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ ብቻ ሳይሆኑ ፓርቲዎችም ያለባቸውን ኃላፊነት  መወጣት  ይኖርባቸዋል፡፡

በእርግጥ በየትኛውም ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ አካሄድን እስከተከተሉ ድረስ በምርጫው ወቅት አንዳችም ዓይነት ወከባ፣ ወይም አፈና ወይም ወደ ገጠር አካባቢዎች ለቅስቀሳ እንዳይወጡ የሚያደርግ ማዕቀብ በመንግሥት ወይም በሌሎች ፓርቲዎች ወይም በማንኛውም ወገን ሊደረግባቸው አይገባም፡፡ ይህም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ በፓርቲዎች የሚቀርብ ስሞታ እንዳይሆን፣ የምርጫ ቦርድና የዴሞክራሲ ተቋማት ኃላፊነት በትጋት ላይ መመሥረት አለበት፡ መንግሥትም በአገር መሪነቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊከታተለው ይገባል፡፡

ከዚህ በኋላ በአገሪቱ የሚካሄዱ ማናቸውም ምርጫዎች ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ሁሉን አሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ሁሉም ወገን በዴሞክራሲያዊ አኳኋን መወያየትና በሠለጠነ መንገድ ተግባብቶ ወይም ተቻችሎ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝቡ ተሳትፎ የነቃና የሠለጠነ መሆን ይኖርበታል፡፡

የመወያየት ነገር ከተነሳ በምርጫ ወቅት ለሕዝብ በቀጥታም ሆነ ተቀርፀው  በሚዲያ የሚተላለፉ የፓርቲዎች የፖለቲካ አቋም ክርክሮች መኖራቸው ግድና አስፈላጊ ነው፡፡ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ጠቀሜታ ሲባል የክርክር ነጥቦችን በማስረጃ በተደገፈና አሳማኝ በሆነ ትንታኔ የተብራራ አቋምን ማሳወቅ ደግሞ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ ይጠበቃል፡፡ መረጃና ማስረጃዎችን በመደበቅ ወይም በመሸፋፈን ወይም በማዛባት የማቅረብ አካሄድ ሕጉ ስለማይፈቅድ ብቻ ሳይሆን፣ ከሞራልና ከሥነ ምግባር አኳያም ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት፡፡

ተወዳዳሪዎች በክርክሩ ውስጥ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ጨዋነት የተሞሉባቸው፣ አቀራረባቸውም በመከባበርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ማድረግም ለትውልዱም ከማሰብ ሊመነጭ ይገባል፡፡ ፓርቲዎች ለሠሩትና ላስመዘገቡት መልካም ውጤት ዕውቅና መስጠትን በማስቀደም የነበሩባቸውን ችግሮች በግልጽ በማሳየት እነሱ ቢሆኑ የነበራቸው አማራጭና አፈጻጸም ምን እንደሆነ በማስረዳት፣ ራስን የመፍትሔው አካል አድርጎ የምርጫ ድምፅን ለማግኘት በቀና መንፈስ የሚደረግ ክርክር ማንሳትም ያስፈልጋል፡፡

የአገራችን ሚዲያዎችም በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች የፓርቲዎችን የክርክር ነጥብና አቋም ሚዛናዊ በሆነ ሙያዊ አሠራር በመዘገብ መረጃዎችን ለሕዝቡ ማድረስ አለባቸው፡፡ የአንዱን ፓርቲ ቃል ሙሉውን አስተላልፎ የሌላውን ፓርቲ መልዕክት ቆራርጦ ማቅረብ ሙያዊም ፍትሐዊም አለመሆኑን ከወዲሁ ከግምት ማስገባት አለባቸው፡፡

      የፓርቲዎቹ ሐሳብና መልዕክት በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያስከብር፣ በፌዴራል መርሆዎች ላይ የተመሠረተ፣ በነፃ ምርጫና በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ በእምነትና በፆታ እኩልነት የሚሠራ የሕግ የበላይነት. . . ወዘተ. ለመሳሰሉት እሴቶች ዕውቅና እየሰጠ ‹‹አሉኝ›› የሚላቸውን የተሻሉ አማራጮች የሚያቀርብ እስከሆነ ድረስ፣ መቆራረጥም ሆነ በኤዲቲንግ ማሸት እንደማያስፈልግ መረዳትና ልበ ሙሉ መሆን የሙያው ግዴታ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሚዲያዎቻችን ከወዲሁ ፖለቲከኛውም ሆነ ሕዝቡ ከምርጫው ምኅዳር በመራቅና የማያግባቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሰበብነት በመደርደር የተጀመረው ጉዞ እንዳይደናቀፍ ግልጽነት መፈጠር አለባቸው፡፡ የሌላውን ዓለም ተሞክሮ ከአገራችን እውነታ ጋር አዛምዶ ማሳወቅም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም አካላት መሬት ላይ  ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የአቅምን ያህል ለመታገል ፊት ለፊት ተገናኝቶ መከራከር፣ ሕዝቡም የእርስ በርስ ጥላቻን ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት የመነጋገርና የመቻቻል አካሄድን ባህሉ እንዲያደርግ ለማስተማርና የራሱን ግንዛቤ ወስዶ ውሳኔውን እንዲሰጥ ለማስቻል መሥራትም  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ከሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው  ሳይኮሰምን ረዥም ርቀት ለመሄድ ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡