Skip to main content
x
አወዛጋቢው የምንዛሪ ለውጥ የፈጠራቸው ውጥረቶች

አወዛጋቢው የምንዛሪ ለውጥ የፈጠራቸው ውጥረቶች

አቶ እንግዳ በላይ (ስሙ የተቀየረ) በአነስተኛ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረት ሥራ ላይ የተሰማራ ግለሰብ ነው፡፡ በዚህ ሥራ መስክ ላይም ከ15 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ሦስት ሥራዎችን ተረክቧል፡፡ የብር ምንዛሪ ለውጡ ይፋ ከተደረገበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሚሠራበት አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ደንበኛው ቁምሳጥን እንዲሠራላቸው ባዘዙት መሠረት ቀብድ ተቀብሏል፡፡ እንደ አቶ እንግዳ ገለጻ፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ለተረከባቸው ሥራዎች ዋጋ ያወጣውና ከደንበኞቹ ጋር የተስማማው ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በነበረው የገበያ ዋጋ መሠረት ነው፡፡

ነገር ግን ለተረከባቸው ዕቃዎች የሚውሉ ግብዓቶችን ለመግዛት የምንዛሪ ለውጡ ይፋ በተደረገበት ዕለት ማለትም፣ ረቡዕ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ገበያ ሲወጣ ያጋጠመው የተለየ ነገር ነበር፡፡ ዕቃዎቹ ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው ዋጋቸው ላይ ጭማሪ እንደተረገባቸው ይገነዘባል፡፡ በተለምዶ የጣሊያን ኮምፔርሳቶ ወይም ቺፕውድ የሚባለው ምርት ቀድሞ በ120 ብር ይሸጥ የነበረበት ዋጋ በአሁኑ ወቅት ወደ 150 ብር አሻቅቧል፡፡ የተለበጠ የጠረጴዛ፣ የበር ወይም ሌላ እንጨት ሠራሽ የቢሮና የቤት መገልገያ (ላሚኔትድ ኤምዲኤፍ) ከነባሩ የ700 ብር ዋጋ ወደ 950 ብር አድጓል፡፡  ይህንኑ ምርት እስከ 1,100 ብር የሚሸጡ መደብሮችም ምርቱን አንቀው እንደያዙ ባለሙያው ይናገራል፡፡ ለተለያዩ የፈርኒቸር ምርቶች ግብዓት የሚውለው የለበሰ  ወይም የተለበጠ ኤምዲኤፍ ከሌሎች በተለየ ዋጋው መጨመሩን የጠቆመው አቶ እንግዳ፣ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በ1,150 ብር ሲገዛ ቢቆይም አሁን ላይ 1,350 ብር ደርሷል ይላል፡፡ በተመሳሳይ ሥራ መስክ የተሰማራው ሌላኛው ወጣትም በተለያዩ የኤምዲኤፍ ምርቶች ላይ ከ300 እስከ 500 መቶ ብር ድረስ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል ብሏል፡፡ የተለበጠ ኮምፔርሳቶ ከ220 ብር ወደ 260 ብር ሲጨምር፣ እንደማስትሽ ያሉ የማጣበቂያ ምርቶችም የምንዛሪ ለውጡ በተደረገ ማግስት ከ150 ብር ወደ 170 ብር ዋጋቸው መጨመሩን ታዝቧል፡፡ እንደ ሁለቱ ባለሙያዎች ገለጻ፣ ለተረከቡት ትዕዛዝ ማጠናቀቂያ የሚውሉ የብረትና የእንጨት ውጤቶች ዋጋቸው በመጨመሩ ምክንያት ቀድመው በተነጋገሩበት ሒሳብ ሠርቶ ማስረከብ ኪሳራ ላይ እንደሚጥላቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ እንግዳ የምንዛሪ ለውጡ ባመጣው ያልታሰበ የዋጋ ለውጥ ሳቢያ ከኪሳራ ለመዳን ደንበኞቹን ለማነጋገርና የዋጋ አስተያየት እንዲያደርጉለት ለማድረግ አስቧል፡፡ የገበያው ጭማሪ ተገንዝበው ማስተካከያ ካላደረጉለት ግን ውሉን በማፍረስ የተቀበለውን ቅድመ ክፍያ እንደሚመለስ፣ የጀመራቸውን ሥራዎች ግን ኪሳራውን እንደምንም አቻችሎም ቢሆን በማጠናቀቅ ከደንበኞቹ ጋር በመደራደር ከተስማሙበት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲያደርጉለት እንደሚጠይቅ ገልጿል፡፡

እንዲህ ያሉ ገጠመኞች የሰሞኑ የገበያ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ በ15 በመቶ ያዘቀዘቀው የብር የመግዛት አቅም ከተገመተው በላይ የዕቃዎች ዋጋ ላይ ጭማሪ አስከትሏል፡፡ የዋጋው ግለት ወሰን አልባ ነው፡፡ የተሽከርካሪ ጎማዎች፣ የለስላሳና የቢራ መጠጦች፣ የእህልና የቅመማ ቅመም ምርቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥና የመሳሰሉት፣ ያለምንም ልዩነት ዋጋቸው ጨምሯል፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት የገቡት ዕቃዎች ከለውጡ በኋላ ከገቡት ጋር የሚለዩበት አሠራር ሳይዘረጋ በጅምላ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ እየታየ ነው፡፡

የጎማ ዋጋ ላይ ከአስመጪዎቹ ጀምሮ እስከ ቸርቻሪዎች ድረስ በቅብብሎሽ ያደረጉት ጭማሪ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ለአብነት ፒሬሊ 1፡00 R20 የሚባለው የከባድ ተሽከርካሪዎች ጎማ የማከፋፈያ ዋጋው ከ13,050 ብር ወደ 14,000 ብር አድጓል፡፡ 7፡50-16 የሚባለው የፒሬሊ ጎማ የማከፋፈያ ዋጋው ከ4050 ወደ 4400 ብር ጨምሯል፡፡ ከአነስተኛ ጎማዎች 20SR16 የተባለው የጎማ ዓይነት ከ3,600 ብር ወደ 4,000 ብር ጨምሮ እንደሚከፋፈል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በዚህ ዋጋ የተረከቡ ቸርቻሪዎች በየራሳቸው መንገድ ዋጋ ጨምረው እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ 12፡00R20 የተባለውን የጎማ ዓይነት ከ14,800 ብር በላይ በሆነ ዋጋ ይሸጣሉ፡፡ ጭማሪው ይለያይ እንጂ ሁሉም የጎማ ምርቶች እንደጨመሩ ታይቷል፡፡ የጎማ የማከፋፈያ ዋጋም እንደሌሎቹ ምርቶች የጨመረው የብር ምንዛሪ ለውጡ በተሰማ በቀናት ልዩነት ውስጥ ነው፡፡ አንድ የከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረት አሥር ጎማዎችን መቀየር ቢፈልግ፣ አሁን ባለው የችርቻሮ ዋጋ መሠረት ከ12 ሺሕ ብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ  ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ትንታኔ ሲሰጡ፣ የምንዛሪ ለውጡ ጭማሪ ሊያስከትል ቢችልም በለውጡ ሰበብ የሚከሰተው ጭማሪ ከ15 በመቶው አኳያ ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል ብለው ነበር፡፡ ይህ ጭማሪ የሚደረገውም በአዲሱ የምንዛሪ ተመን አማካይነት ተገዝው ወደ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ አወት ተክሌም ከምንዛሪ ለውጡ በፊት የነበሩ ምርቶች ላይ የታየው ጭማሪ ትክክል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የገበያው ተዋናዮች ግን በራሳቸው መንገድ ገበያውን ለመምራት አጋጣሚው አመችቷቸዋል፡፡ ያልተገባ የገበያ ውድድርን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው እንደ ንግድ ሚኒስቴር ያሉ ተቋማትም የዋጋ ጭማሪውን በመቃወም ዕርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምርት ተሸሽጎባቸዋል የተባሉ መደብሮችና መጋዘኖችን ማሸጉም ተሰምቷል፡፡

በምንዛሪ ለውጡ ሰበብ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከታየባቸው ምርቶች ውስጥ ብረት አንዱ ነው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የሚታመንበት ጭማሪ የታየው የግንባታ ግብዓቶች ላይ ሲሆን፣ ያነጋገርናቸው ተቋራጮችም ይህንኑ ገልጸዋል፡፡

በግንባታ ግብዓቶች ላይ በተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ተቋራጮች ማኅበር አባላቱን በአስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ለማነጋገር ወስኗል፡፡ በገበያው ውስጥ የታየው የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ በማስጠናት ለመንግሥት ለማቅረብ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህንን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ኮሚቴውን እንዲመሩ የተመረጡት አቶ መላኩ አርጋሞ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምንዛሪ ለውጡ ከተደረገ በኋላ የቧንቧ፣ የፓምፕ፣ የጄኔሬተር፣ የአርማታ ብረትና የመሳሰሉት ከ30 እና በ40 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ አስደንጋጭ ሁኔታ መፈጠሩ እየተነገረ ነው፡፡

በ80 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ቀረጢት ጄሶ፣ ወደ 120 ብር ያሻቀበባቸው ተጠቃሚዎች ለምን? ሲሉ የሚሰጣቸው ምላሽ ዶላር ስለጨመረ የሚል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የቤት ማስዋቢያ፣ የቀለምና የሌሎች ምርቶችም ዋጋ ጨምሯል፡፡ ከጥቂት ቀለም ማምረቻዎች ለማወቅ እንደተቻለው የ15 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ነው፡፡

የዋጋው ትኩሳት በሸማቾች ዘንድ ምሬት አስከትሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ጭራሹኑ የማይመለከታቸው ምርቶችም ዋጋ ጨምረዋል፡፡ ቡና፣ ሽሮ፣ በርበሬና ዘይት በምንዛሪ ለውጥ ሰበብ ዋጋ እየተጨመረባቸው ነው፡፡ እንደ ጤፍ ያሉ የእህል ምርቶች በአንድ ኪሎ ከሁለት እስከ አምስት ብር ጭማሪ ተደርጎባቸው ሲሸጡ ታይተዋል፡፡ የለስላሳና የቢራ ፋብሪካዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የማከፋፈያ ዋጋቸውን ጨምረዋል፡፡

በሐይኒከን የተጀመረው የዋጋ ጭማሪ ሁሉንም የቢራ ፋብሪካዎችን አዳርሶ ከ10 እስከ 15 በመቶ የዋጋ ለውጥ እንዲያደርጉ አብቅቷቸዋል፡፡ ይህንኑ ጭማሪ ተከትሎም ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ቡና ቤቶች የቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪው ካስከተለው በላይ ዋጋ እንዲጨምሩ መንገዱን ከፍቶላቸዋል፡፡ ከቢራ ፋብሪካዎች የተገኘው መረጃ ጭማሪው የተደረገው በርካታ የቢራ ግብዓቶች በውጭ ምንዛሪ ስለሚገቡ ነው፡፡

በምንዛሪ ለውጡ ሰበብ የታየው የዋጋ ጭማሪ ብቻ አይደለም፡፡ ምርት የመሸሸግ ተግባር ተከስቷል ነው፡፡ እርግጥ ነው የምንዛሪ ለውጡ እንደሚደረግ ከተገለጸበት ምሽት ጀምሮ በማግስቱ ይፋ እስከተደረገበት ቀንና ከዚያም ወዲህ ምርቶች ሲደበቁ ታዝበናል፡፡ ወደፊት ከአሁኑም በላይ ዋጋ ይጨምራል በሚል ግምት ነጋዴዎች ምርት መሸሸጋቸው እየተሰማ ነው፡፡ ከንግድ ውድድርና የሸማቾች ባለሥልጣን በዚህ ሳምንት ብቻ የዋጋ ጭማሪውን በተመለከተ በርካታ ጥቆማዎች ደርሰውታል፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ግብረ ኃይል አቋቁሞ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርት በሸሸጉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እየወሰድኩ ነው ብሏል፡፡  

ተቋማቱ የተደረገው ጭማሪ አግባብ አይደለም በማለት መግለጫ ቢያወጡም፣ ከማሸግ ይልቅ ኢኮኖሚዊ ትርጉም ያለው ዕርምጃ አለመውሰዳቸው ክስተቱን እንዳባባሰው ይታመናል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመርካቶ አካባቢ የተወሰኑ ሱቆችንና መጋዘኖች ቢያሽግም፣ ችግሩ ግን በሁሉም የንግድ ዘርፍ ውስጥ እየተንፀባረቀ ከመሆኑ አንፃር አስቸጋሪ አዝማሚያ እንደተፈጠረ ታይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በላይነት ወልደ ሰንበት  ምርት አከማችተዋል የተባሉ ስድስት መጋዘኖች እንደታሸጉ ገልጸዋል፡፡፡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የብረታ ብረት መሸጫዎችም ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው፣ ወደፊትም ዕርምጃው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

አቶ መላኩ እንደሚገልጹት ነጋዴዎች  ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ የተደረጉ ጭማሪዎች አግባብ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ በፊት በነበሯቸው ምርቶች ላይ ዋጋ የጨመሩ አስመጪዎች አድራጎት እንደሚያሳዝን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ መንግሥት የወጪ ንግድን ለመደገፍ የምንዛሪ ለውጥ የማድረጉ በጎነት እንዳለ ሆኖ ያልተገባ የዋጋ ንረት በመፍጠር በየአጋጣሚው የሚደረገውን ኮንነዋል፡፡ መንግሥት በቶሎ ካላስተካከለው ችግሩ ይባባሳል የሚል ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በተለይ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር ቀላል እንደማይሆን ተገልጿል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረ የውጭ ምንዛሪ ስሌት መሠረት የተፈጸሙ የግንባታ ውለታዎችና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውም ከወዲሁ ካልታሰበባቸው አስቸጋሪ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በተቋራጮች የተያዙ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ የመንግሥት ከመሆናቸው አኳያ መንግሥት ለታየው የገበያ መናጋት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሏል፡፡ አብዛኞቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከለውጡ በፊት በነበረ የምንዛሪ ተመን ተሰልተው የተጀመሩ ናቸው፡፡ የ15 በመቶ ለውጥ ሲመጣ ግን ለግንባታ የሚያውሏቸው ግብዓቶች የለውጡን ያህል ዋጋ ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የፕሮጀክት ወጪዎች በትንሹ የ15 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ሊያሳዩ እንደሚችሉ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡

እንደ አቶ አወት ትንታኔ ከሆነ፣ የገንዘብ ለውጥ ቢከሰት ምን ይደረጋል የሚለው በኮንትራት ውላቸው ውስጥ በሰፈረው ስምምነት መሠረት ይስተናገዳሉ፡፡ የዋጋ ወይም የምንዛሪ ለውጥን የሚመለከት የውል ስምምነት ከሌለ ግን የግንባታ ሥራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ አቶ መላኩ በበኩላቸው፣ መንግሥት የምንዛሪ ለውጡን ሲወስን በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ሊኖር የሚችለውን አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ አጥንቶ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይሁንና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ዋነኛ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ ጫና መፈጠሩ አይቀርም፡፡ እሳቸው ባሉበት ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ለመጠጥ ውኃ ግንባታ የሚውሉ አብዛኞቹ ዕቃዎች አገር ውስጥ የሚመረቱ ቢሆኑም፣ ግብዓቶቻቸው የሚመጡት ከውጭ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት መፍትሔ ካላዘጋጀ፣ አብዛኛው ተቋራጭ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ፍንጮች ስለመታየታቸውም ጠቅሰዋል፡፡

 እንዲህ ባለው ወቅት ተቋራጮች አስተያየት ሊደረግላቸው እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ አወት፣ የመንገድም ይሁን ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከታቀደላቸው   ወጪ በላይ መጠየቃቸው አይቀርም ይላሉ፡፡ ከምንዛሪ ለውጡ አንፃር ታይቶ የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ እንደ ሲሚንቶ ያሉ ግብዓቶች ላይ የምንዛሪ ለውጡ ብዙ ልዩነት ስለሚያመጣ ጭማሪ ሊኖር እንደማይገባ የሚጠቅሱ ቢኖሩም፣ እንደ ከሰል ድንጋይ ያሉት የኃይል ምንጮች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ በሲሚንቶ ምርቶች ላይም የዋጋ ጭማሪ እንደማይቀር እየተነገረ ነው፡፡ በመሆኑም በአቶ መላኩ ሥጋት መሠረት የዋጋ ጭማሪው በአገር ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች ጭምር ላይ በመሆኑ፣ ችግሩን በጥናት ላይ በተመሠረተ መረጃ አስደግፎ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ የተቋራጮች ማኅበርም ይህንኑ ነው ማድረግ የፈለገው ብለዋል፡፡

የምንዛሪ ለውጡ ባስከተለው የዋጋ ጭማሪ ሰበብ የተቋራጮች ሥራ ስለመስተጓጎሉ ቢነገርም፣ አቶ መላኩ ግን እስካሁን የቆመ የግንባታ ሥራ የለም ብለዋል፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ተቋራጭ ግንባታውን ሲረከብ ዕቃ ለመግዛት ካሰበውና በጨረታ ሰነዱ ካሰፈረው ዋጋ በላይ ሲሆንበት፣ ግንባታውን ለጊዜውም ቢሆን ሊገታ ይችላል እንጂ የቆመ ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉና መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ካላስተካከለ፣ ሥራዎች ሊስተጓጎሉ የሚችሉበት አዝማሚያ ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ በተለይ የግንባታ ዘርፍ ከያዘው የሰው ኃይል አንፃር ችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

የዋጋ ለውጥ ቢደረግም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለመኖሩ ግን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቀውስ እንዳይፈጠር አስግቷል፡፡ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርበው ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ብቻ ነው፡፡

ለንግዱ ማኅበረሰብ የውጭ ምንዛሪ በተገቢ መጠን ቀርቦ የነበረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የዶላርም ሆነ የምርት ክምችት ገበያው ውስጥ እንደሚፈለገው መጠን የለም፡፡ ለንግዱ ማኅበረሰብ የውጭ ምንዛሪ እየቀረበ ባለመሆኑ፣ በለውጡ ሰበብ የከፋ የገበያ አለመረጋጋት ሊከተል እንደሚችል በየአቅጣጫው ሥጋቱ ተንሰራፍቷል፡፡

ይህ ይባል እንጂ መንግሥት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ የሚወስደው ዕርምጃ በነጋዴዎች ዘንድ ግርምትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ መመዘኛው ምንድነው፣ ነባሩ ዕቃ ከለውጡ በኋላ ስለመግባት አለመግባቱ ማወቂያው ስልቱ ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችም እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች በብር የመግዛት አቅም ላይ የ15 በመቶ ለውጥ ሲደረግ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት ጥቁር ገበያው የ16 በመቶ ለውጥ አድርጓል፡፡

ይህ የሆነው በቂ የውጭ ምንዛሪ ባለመቅረቡ ነው ያሉ ነጋዴዎች፣ በቂ አቅርቦት ቢኖር ኖሮ ነጋዴው ያለውን ዕቃ ለገበያ በሰፊው ከሸጠ በኋላ ተጨማሪ ለማስመጣት ይሄድ ነበር በማለት የመንግሥትን አካሄድ እየተቹ ነው፡፡

የምንዛሪ ለውጡን ተንተርሰው መንግሥታዊ ተቋማት ጭምር የዋጋ ለውጥ አድርግዋል፡፡ ለአብነት ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማስከፈል የጀመረው ቀረጥ በአዲሱ ተመን ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ዕቃ ከውጭ እያስገቡ የነበሩ አስመጪዎች፣ ከባንኮች ሰነዳቸው የተሠራላቸው ግን በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት ነው ሲሉ ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ዕቃዎች በአሁኑ ወቅት ገበያ ውስጥ እየገቡ በመሆኑ በንግድ ሚኒስቴር የተቋቋመው ግብረ ኃይል፣ በምን ዓይነት መረጃ ላይ ተመሥርቶ ዕርምጃ እንደሚወስድ ግራ እንደገባቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡  

‹‹ይልቅስ መንግሥት ገበያውን ባይነካካው መልካም ነው፡፡ ገበያውን ለማረጋጋት የዶላር አቅርቦቱ ላይ መሥራት ይኖርበታል፡፡ በግብታዊነት የሚወሰድ ዕርምጃ ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም፤›› ሲሉ እኚህ ነጋዴ ያስታውቃል፡፡