Skip to main content
x
ለወል ትራንስፖርት የሚውሉ 1000 ታክሲዎች ሊገቡ ነው

ለወል ትራንስፖርት የሚውሉ 1,000 ታክሲዎች ሊገቡ ነው

  • በኪሎ ሜትር ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ያስከፍላሉ

ፒክ ፒክ ታክሲና ዮኪዳ ኮንሰልት የተባሉ ኩባንያዎች ከበላይ አብ ሞተርስ ጋር በመተባበር ለሰባት ተሳፋሪዎች የወል ትራንስፖርት አገልግሎት በስምሪት የሚሰጡ   አንድ ሺሕ ታክሲዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡

በቀን ለ16 ሰዓታት በመሥራት ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ይታይባቸዋል ተብለው በተመረጡ አካባቢዎች የሚሰማሩት ታክሲዎች፣ በ156 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያና በ520 ሺሕ ብር ጠቅላላ የሽያጭ ዋጋ ለገዥዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት አዳዲሶቹ ታክሲዎች ሰባት ሰው የመያዝ አቅም ሲኖራቸው፣ እያንዳንዱ ተሳፋሪ በኪሎ ሜትር ሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እንዲከፍል እየተደረገ፣ ሰባቱ ተሳፋሪዎች በድምሩ 17.50 ብር በመክፈል እንደሚሳፈሩ ከቀረበው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

የ2017 ሞዴል፣ የቻይና ሥሪት ታክሲዎቹ በቀንና በማታ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ያለባቸው ቦታዎችን መሠረት በማድረግ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥራዎችን ከሚሠራላቸውና ሪሴል ፒክ ፒክ አይሲቲ ቴክኖሎጂ በተባለው ኩባንያ አማካይነት ታክሲዎቹ ሁሉንም አቅጣጫ የሚያሳይ ካሜራ ይገጠምላቸዋል፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝም አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚቻል የፒክ ፒክ ታክሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ዓለሙ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ 112 የአውቶብስና 300 የሚኒባስ ትራንስፖርት መስመሮች ሲኖሩ፣ በብዛት የታክሲ እጥረት በሚታይባቸው ቦታዎች አዳዲሶቹ ታክሲዎች እንደሚሰማሩ ይጠበቃል፡፡

በላይ አብ ሞተርስ ተሽከርካሪዎቹን በፋብሪካው ገጣጥሞ ለባለሀብቶች የሚያስረክብ ሲሆን፣ ታክሲዎቹን ለመግዛት የ30 በመቶ ወይም የ156 ሺሕ ቅድመ ክፍያ መኪኖቹን በሚገዙ ግለሰቦች የሚሸፈን ሲሆን፣ ቀሪው 70 በመቶ ደግሞ ኅብረት ባንክ በሚያቀርበው ፋይናንስ እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡ ይሁንና የቀረበው የአንድ ታክሲ የመሸጫ ዋጋ ላይ አዲሱ 15 በመቶ የምንዛሪ ጭማሪ እንደሚካተትበትም ተጠቅሷል፡፡ በታክሲው ባለቤት የሚደረገው የ156 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ በዝግ የቁጠባ ሒሳብ ተቀማጭ ተደርጎ፣ ቀሪው ክፍያ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ የሚያስችል አሠራር ተካቷል፡፡

ታክሲዎቹ ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት፣ ፒክ ፒክ ታክሲ ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ለታክሲ ባለንብረቶች የመድን ዋስትና፣ የነዳጅ፣ የሾፌርና የባንክ ዕዳ ክፍያዎችን በመሸፈን በወር የ7,500 ብር ገቢ ለባለንብረቱ የሚከፍልበት መንገድ እንደተዘረጋ አቶ ዘነበ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያን ይዘት የሚያስተዋውቅ አዲስ አሠራር ይዞ ብቅ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

ታክሲዎቹ በሁለት ፈረቃ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ ከንጋት 12፡00 እስከ 8፡00 ሰዓትና ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የትራንስፖርት አቅርቦት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በቀን በሚኖረው ስምሪት ወቅት ሴት ሾፌሮች እንደሚያሰማሩም አቶ ዘነበ ጠቅሰዋል፡፡ ታክሲዎቹ በሊትር 14 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ ሲሆን፣ የጊዜውን ቴክኖሎጂ አካተዋል፡፡ 360 ዲግሪ የሚዞሩ ካሜራዎች የተገጠሙላቸው ናቸው፡፡ ተሳፋሪዎች ክፍያ ሲፈጽሙ ዲጂታል በሆነ መንገድ ወዲያውኑ ደረሰኝ መቀበል የሚችሉበት ቴክኖሎጂም እንደተካተተ የኪዮዳ ኮንሰልት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ነጂብ ሙሠማ አስረድተዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹን ለባለንብረቶች ለማስረከብ የሚፈጀው ጊዜ ከ150 እስከ 180 እንደሆነና በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ቅደመ ሁኔታ አጠናቀው ሥራ መጀመር እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡

በላይ አብ ሞተርስ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣትና በአገር ውስጥ በመገጣጠም ይታወቃል፡፡ በዘርፉም ስምንት ዓመታትን ከማስቆጠሩ በተጨማሪም ኩባንያው 11 ያህል እህት ኩባንያዎችም አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል በላይ አብ ኤሌክትሪክና ዳታ ኬብል፣ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል፣ ሊከን ኮንስትራክሽን ደረጃ አንድ ተቋራጭ፣ ሊዊስ ኮንስትራክሽንና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች አቅራቢ ድርጅት ተጠቃሾች ናቸው፡፡