Skip to main content
x
ሰንደቅ ዓላማን የጋራ የማድረግ ፈተና

ሰንደቅ ዓላማን የጋራ የማድረግ ፈተና

ሰንደቅ ዓላማ የአገራዊ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ትዕምርት (ምልክት) ነው፡፡ ሁለት አገሮች ወደ ጦርነት ወይም ወደ ጠብ ሲገቡና ዜጎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት በሚያደርጓቸው የተቃውሞ ሠልፎች ላይ ባንዲራ ማቃጠል በፊት በፊት እንደ ፋሽን ይታይ ነበር፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ክስተት ከቅርብ ከዓመታት ወዲህ ባይዘወተርም፣ አሁንም ድረስ ባንዲራ በማቃጠል ተቃውሞ የመግለጽ ስሜት አለ፡፡

የባንዲራ ትዕምርታዊነት ሰፊ በመሆኑና የሚዳስሳቸው፣ የሚገልጻቸውና የሚያንፀባርቃቸው ቁም ነገሮች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ የባንዲራንና የአገርን፣ እንዲሁም ባንዲራው የሚገልጸውን ማንነትና ምንነት ለመግለጽ ‹ቬክሲሎሎጂ› የተሰኘ የጥናት ዘርፍ ተቋቁሞ በስፋት ይጠናል፡፡

ለዚህም ይመስላል ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጀምሮ በብሔራዊ ደረጃ በኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እየተከበረ የሚገኘው፡፡ ምንም እንኳን የባንዲራ ቀን በብሔራዊ ደረጃ ከመከበር ቀደም ባሉት ዓመታት ባንዲራው ተዋርዷልና የሚገባውን ክብር አልተሰጠውም የሚሉ ትችቶች በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይ ሲሰነዘሩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ይኼን ታቃውሞ የሚያሰሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ባንዲራው ተገቢው ክብር አልተሰጠውም በማለት ተቃውሟቸውን ያሰማሉ፡፡

በተለይ ገዥው መንግሥት ኢትዮጵያን ማስተዳደር በጀመረባቸው የመጀመርያዎቹ አሥር  ዓመታት ከአንድነት ይልቅ፣ በአገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ልዩነት ያለልክ በመለጠጥ ከፍተኛ ሥራ በማከናወን የባንዲራ ትዕምርታዊ ትርጉም ቦታ አልተሰጠውም በማለት የሚተቹ በርካታ ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በሰጡት አስተያየት ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ማለታቸው፣ ባንዲራን በተመለከቱ ውይይቶችና ንግግሮች መሀል የበርካታ ውዝግቦችና ንትርኮች መነሾ ነበር፡፡

ለዚህም ይመስላል በተለይ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ አንድነትን የበለጠ ሊያጠናክሩ ይችላሉ የተባሉ በርካታ ዕርምጃዎች በገዥው መንግሥት እየተወሰዱ ያሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል የባንዲራ ቀንና የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሆኖም ከእነዚህ ዕርምጃዎች መወሰድ በኋላም ቢሆን የአገሪቱ አንድነት በእነዚህ ክብረ በዓሎች ወይም ዝግጅቶች በሚፈለገው ደረጃ መመለስ እንዳልተቻለ፣ እንዲያውም የአገሪቱ አንድነት ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ ነው በማለት የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም በተለያ አጋጣሚዎች ሲገለጽ እንደነበረው ለኢትዮጵያ ባንዲራ የአንድነት መግለጫ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፖለቲካ ልዩነት ማንፀባረቂያ እንደሆነ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡

ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ሆነ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውለበለቡ ባንዲራዎች ብዛትና ልዩነት፣ የፖለቲካ አመለካከቶችን የሚወክል ይመስላል፡፡

ባለ ኮከቡ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ፣ ልሙጡ፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ ደግሞ የሞ አንበሳ ዓርማ ያለበትን የኢትዮጵያ ባንዲራ ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ ሆነ ለድጋፍ በሚያደርጓቸው ሠልፎችና ሕዝባዊ ስብሰባዎች መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ይኼን ከመሰለ ወጥነት የሌለው የባንዲራ አጠቃቀም በተጨማሪ በአገር ውስጥም ቢሆን የባንዲራ አዋጅን ተከትሎ ወጥነት ያለው ባንዲራ መጠቀም አስገዳጅ ቢሆንም፣ በበርካታ የመንግሥት ተቋማትም ሆነ በተለያዩ ግዙፍ የግል ተቋማት ውስጥ ተሰቅለው የሚውለበለቡት ባንዲራዎች ቀለማቸው የወየበ፣ ያረጁና የተቀደዱ እንደሆኑ መመልከት ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር መንግሥት ጉዳዩን ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታነት በዘለለ የምር ጉዳዩን እንደማይከታተለው የሚተቹ ወገኖች፣ እነዚህን ሁኔታዎች በመንቀስ ለመከራከሪያቸው ማስረጃነት ይጠቀሙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የባንዲራ ቀን በሚከበርበት ሰሞን በየአደባባዮችና በተለያዩ ሥፍራዎች የሚውለበለቡት ባንዲራዎች የመጠን ልዩነት የሚስተዋልባቸው እንደሆኑ በመግለጽ፣ ጉዳዩ የግብር ይውጣ እንጂ በሥነ ሥርዓት የታሰበበት እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡

ከመጠን ባለፈም ባንዲራውን ስቀሉ በመባላቸው ብቻ እንደሰቀሉት የሚያሳብቁ ክስተቶች ይስተዋላሉ፡፡ ለምሳሌም ባንዲራውን ገልብጦ መስቀል፣ ከሚሰቀልበት ቦታ ማጠር የተነሳ መሬት ላይ የሚያርፉ ባንዲራዎችም እንዲሁ የባንዲራ ዕለት ክስተቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር መንግሥት የባንዲራ ቀንን ከማክበር ባለፈ ስለአከባበሩ፣ እንዲሁም ስለባንዲራዎቹ መጠንና ስብጥር ወጥ የሆነ የአሠራር መመርያ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የባንዲራ አዋጅን በመጥቀስ፣ ባንዲራ እንዴት ማክበር እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ተመድ ባንዲራን በተመለከተ ባለው ሕግ መሠረት የባንዲራውን መጠን፣ የቀለም ዓይነት፣ ዓርማው ከባንዲራው ጋር ያለውን ስብጥር፣ እንዲሁም ባንዲራው ሲሰቀልና ሲወርድ ምን ዓይነት ሥርዓቶች እንደሚኖሩት በዝርዝር ይገልጻል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ባንዲራም መጠኑ፣ ቀለሙና የአሰቃቀል ሥርዓቱ ምን መምሰል እንደሚኖርበት የወጣውን አሠራር በተግባር የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል መኖር እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚሁ አንፃር መጠኑ ሲባል ሁሉም አንድ ዓይነት ይሁን ወይ አይሁን የሚል ሳይሆን፣ ባንዲራዎች የሚውለበለቡበትን ሥፍራ ከግምት ያስገባ ወጥ የሆነ ደረጃ እንዲኖረው ለማሳሰብ ነው፡፡

ከቀለም ጋር በተያያዘም ምንም እንኳን ባንዲራው መሀል ላይ ኮከቡ ወደ ውጭ የሚፈነጥቅ ሰማያዊ ኮከብ ያለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንዳሉት የተገለጸ ቢሆንም፣ ምን ዓይነት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ሥራ ላይ ይዋሉ የሚለው በግልጽና በዝርዝር አልተቀመጠም ተብሎም ቅሬታ ይቀርባል፡፡ ምክንያቱም በጣም የፈዘዙ ወይም በጣም የደመቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ከዚህ አንፃር ይኼን ወጥ በሆነ ደረጃ መደንገግ እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

እንዲህ ዓይነት ወጥ አሠራር መዘርጋት ከተቻለ ደግሞ ከባንዲራ ቀለም መወየብና ከማርጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በቀላሉ መፍታትና ማስተካከል፣ እንዲሁም ለባንዲራው የሚገባውን ክብር ለመስጠት ዕድል ይፈጥራል የሚል አመለካከት ያላቸው አሉ፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደሚስተዋለው ባንዲራ የአንድነት ምንጭ በመሆን ዜጎችን በማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ መሣሪያ መሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በባንዲራው እንኳን አንድ መሆን እንደተሳነን የሚገልጹ በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ግለሰቦች ይስተዋላሉ፡፡

‹‹እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት ሲቀነቀን የነበረውና ሰፊ ሥራ የተከናወነበት ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን ነው፡፡ ሰዎች ልዩነት አይኑራቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድነትን ማስጠበቅ እስካልተቻለ ድረስ ልዩነት ላይ ትኩረት ካደረግን ትንንሽ አገር ሆነን ነው የምንቀረው፤›› በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡት፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የጥናትና ምርምር ኃላፊ የሆኑት አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ናቸው፡፡

ይህ ያልተመጣጠነ ክፍተት ቀስ በቀስ ጉዳት እንዳመጣም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ቀደም ሲል ከአንድነት ይልቅ ልዩነቱን ያራገቡት ሥራዎች ከፍተኛ ችግር አስከትለዋል፡፡ የችግሩን ገፈትም አሁን እየቀመስነው ነው፤›› በማለት አንድነት ላይ ሥራ አለመሠራቱን ያወሳሉ፡፡

በአንድነት ስሜት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁሙት አቶ ዋስይሁን፣ ለዚህም አንዱ መንገድ የባንዲራ ቀን ማክበር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ምንም እንኳን የባንዲራ ቀን ማክበር ለአገሪቱ አንድነት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንዳለ ቢያመለክቱም፣ ‹‹በሚያሳዘን ሁኔታ እኛ ብቻ ነን በባንዲራ ላይ እንኳን የጋራ መግባባት የሌለን አገር፤›› በማለት የባንዲራ ቀንን ከማክበር ባለፈ፣ በጋራ ሊያግባባ የሚችል ባንዲራ መፈጠር ላይ በአትኩሮት ሊሠራ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፉት ዓመታት የተጠናከሩ ሥራዎች ማከናወን እንዳልተቻለ ገልጸው፣ የባንዲራ ቀን ማክበር ዘግይቶ ቢመጣም ከዚህ በተሻለ ሁኔታ መጠናከር እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡

‹‹የባንዲራ ቀን ከማክበር ባለፈ ግን ባንዲራው የትኛው ነው የሚለው ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ባንዲራውን የሁላችንም የማድረግ ላይ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መከናወን ይኖርበታል፤›› ይላሉ፡፡

ችግሩ የባንዲራ ቀንን ማክበር አልያም አለማክበር ላይ እንዳልሆነ የሚገልጹት አቶ ዋስይሁን፣ ‹‹ችግሩ የባንዲራ ቀንን ከማክበር ላይ አይደለም፡፡ ባንዲራውን የጋራ ማድረግ ላይ ነው ችግሩ፡፡ ባንዲራውን የጋራ ማድረግ ላይ ደግሞ የተሠራው ሥራ በቂ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ይኼን ለማድረግ ከሕፃናትና ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ የተጠናከረ ሥራ መከናወን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

የባንዲራ ቀን መከበር ላይ ችግር እንደሌለባቸው የገለጹት የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ የባንዲራ ቀን ማክበር ቀደም ብሎ መጀመር እንደነበረበት ያወሳሉ፡፡

‹‹ባንዲራውና የሚገባውን ክብር ነፍገኸው ቆይተህ መጀመርያ ላይ ስታፈርስ የነበረውን ነገር አሁን ለመገንባት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ሰው አስተሳሰብ ጠብ የሚል ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡

‹‹አንድነትን የሚሰብኩ ተግባራት ከመጀመርያው ተሠርተው ቢሆን ኖሮ ጥሩ የአገር ፍቅር ስሜት መፍጠር ይቻል ነበር፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ከረፈደ መጀመር የሚኖረው ፋይዳ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ይገልጻሉ፡፡

በእነዚህ ሁሉ ንትርኮች ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ባንዲራ ለበርካታ አፍሪካዊ አገሮች ግን እንደ ነፃነት ምልክት የሚቆጠር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከ55 የአፍሪካ አገሮች መካከል 17 ያህሉ ኢትዮጵያን እንደ ነፃነትና ለውጭ ወራሪ እምቢኝ ማለቷን ተምሳሌት አድርገው፣ ሦስቱን የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት ለየአገሮቻቸው ባንዲራ ተጠቅመውባቸዋል፡፡

ምንም እንኳን በርካታ የአፍሪካ አገሮችና የመላው ዓለም ጥቁሮች ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካዊ ወንድማማችነት የኢትዮጵያ ባንዲራን ቀለማት መነሻ አድርገው እየተጠቀሙ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ግን በባንዲራው ላይ እንኳን የጋራ መግባባት መፍጠር እንደከበዳቸው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ግለሰቦች ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ቀጣዩን የባንዲራ ቀን ለማክበር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ባንዲራውን የጋራ ንብረትና ማንነት መገለጫ እንዲሆን መሥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡