Skip to main content
x

የኢሕአዴግ ከራስ ጋር ኩርፊያና ፖለቲካዊ አንድምታው

በይናገር ጌታቸው

ኤድዋርድ ጊቢን የመካከለኛዋን ዘመን ኢትዮጵያ ሲገልጽ ‹‹ዓለምን ረስታ፣ በዓለምም ተረስታ፣ በጠላት ተከባ በሮቻን ዘግታ ለሺሕ ዘመናት ያንቀላፋች አገር፤›› ይላታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አገላለጽ ከዛሬው ዘመን የፖለቲካ ጉዞችን ጋር ኩታ ገጠም ነው፡፡ ኢሕአዴግ በውስጥና በውጭ ጠላቶቹን ተከቦ፣ ስለ እሱ ማወቅ የሚፈልጉ ዜጎቹንም ረስቶ በሮቹን ዘግቶ አንቀላፍቷል፡፡ በዚህ ሰዓት ደኢሕዴን 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ከመሆኑ ውጪ ስለኢሕአዴግ ወቅታዊ ሁኔታ ማንም በእርግጠኝነት መናገር የሚችል አይመስለኝም፡፡ ባለፉት ሳምንታት ሁለቱ የኢሕአዴግ ታላላቅ አመራሮች ከነበሩበት ኃላፊነት ለመልቀቅ መወሰንና የአንደኛው አጭር ገለጻ ማድረግም የመረጃ ፆሙን ለመፍታት በቂ አይደለም፡፡ የእኛ አገር ፖለቲካ አሁንም ፕሉቶና አርስቶትል ያደንቁት ከነበረው የቀላልነት መንግሥታዊ ሥርዓት (Simple Form of Government) አልወጣም፡፡

በዚህ ፖለቲካ እጅግ በተወሳሰበበትና የተጠያቂነት አሠራር በጎላበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ግን በአስፈጻሚው ይሁንታ ላይ የተንጠለጠለ ፖለቲካን እየተከተለች ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ያለፈው ዓመት ጥናት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ውስብስብ የፖለቲካ ሥርዓትና የመንግሥት አካላት የእርስ በርስ ተጠያቂነት ባልሰፈነባቸው አገሮች ቀጣዩ መንገድ አስፈሪ ነው በሚባልበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ አሁንም የአስፈጻሚው አካልን ኃያልነት ታውጃለች፡፡ ፓርላማው ሥልጣኑን ተጠቅሞ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጠርቶ በወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ የሚጠይቅባትን አገር እስክናገኝ ድረስ የመረጃ አምሮታችን በአሉባልታ እንደተገራ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ አሉባልታ አገር የሚገነባ ሳይሆን አገር የሚንድ ነው፡፡

ሁለቱን ጎምቱ ባለሥልጣናትና ባለውለታዎቹን ያሰናበተው ኢሕአዴግ ሰሞነኛ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ፓርቲው ጥርት ያለ መረጃ ባለመስጠቱ፣ ተቃዋሚው ወገን ኢሕአዴግ እየተፈረካከሰ ነው የሚል የድል ነጋሪት መጎሰም ጀምሯል፡፡ አፍቃሪ ኢሕአዴግ የሆነው ወገን ደግሞ ሰሞነኛው የባለሥልጣናት መልቀቅ የድራማው መጨረሻ እንጂ መጀመሪያ ስላልሆነ ኢሕአዴግ በሰላም ተገላግሏል ይላል፡፡ ጥያቄው ግን አሁንም አለ፡፡ ኢሕአዴግ ቤት ምን እየተደረገ ነው?

በተለይም የአቶ በረከት ስምኦን ከኃላፊነት የመነሳት ጥያቄ በአንዳንድ ለኢሕአዴግ ቅርበት አለን በሚሉ ጦማሪያንና በአገር ውስጥ ኅትመት ውጤቶች ከመስመር ልዩነት የመነጨ ነው መባል፣ ወቅታዊውን ሁኔታ በድጋሚ እንድናጤነው ያስገድደናል፡፡ በዚህ ገፊ ምክንያትም ፓርቲያዊ ማፈንገጥ (Faction) በቀጣዩ የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያለውን ሚና ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የማፈንገጥ ፖለቲካዊ አንድምታ

ፓትሪክ ኮልነርና ማትያስ በሴዱኡ ‹‹Factionalism in Political Parties›› በተሰኘ ጥናታቸው በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለን አካሄድ በመቃወም በዚያው በፓርቲው ውስጥ የሚደረግ ተቃውሞና ትግል የፓርቲ ፍንገጣ (Faction) እንደሚባል ይገልጻሉ፡፡ ዛራሲክ ግን በፓርቲ ውስጥ ያለን አሠራርና አካሄድ በመቃወም የሚካሄድ ትግል በሙሉ ፓርቲያዊ ፍንገጣ ሊባል አይገባውም ይላል:: ይልቁኑም ፓርቲያው ማፈንገጥ የሚባለው ልዩነቶቹን ተከትሎ የሚወጣው ውጤት ነው የሚል ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ የፓርቲው አባላት ያላቸው አቋም እየሰፉ ሲሄድና ሊታረቅ የሚችልበት ዕድል ሲጠብ አንደኛው አንጃ ወደ ማፈንገጡ ያመራል፡፡ እንዲህ ያለው ልዩነት ታዲያ ለሌላኛው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ማኦር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የግጭት መናኸሪያ የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

‹‹Rethnking Factionalism›› የተባለ ጥናት እ.ኤ.አ. በ2009 ያቀረበው ፋራንሽይዝ ቡክ ከእስካሁኖቹ የፖርቲ ማፈንገጥ ብያኔዎች ሁሉ በዛራሲክ የቀረበው ትንተና ውኃ የሚያነሳ ነው ይላል፡፡ ለዛራሲክን ፖለቲካዊ ማፈንገጥ ተመሳሳይ ግብን ባነገቡ ኃይሎች የተመሠረተ ፓርቲ ውስጥ የሚከሰትና ሊደርሱበት ካሰቡት መንገድ የሚያሰቀር የግንብ ግንባታ ነው፡፡ ዛራሲክን እንዲህ ያለው ግንብ በመሀል እስካለ ድረስ ፓርቲው ሕመም ላይ ነው ይላል፡፡ በመሆኑም ፓርቲው ፈጣን የትግል መስመርን የመለየት ተግባር ውስጥ መግባት አለበት፡፡

ከላይ የጠቀስናቸውን ሐሳቦች ጠቅለል ስናደርጋቸው ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ፍንገጣ በፓርቲ ውስጥ መከፋፈል መኖሩን ተከትሎ የሚመጣ ውጤት መሆኑን መረዳት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፓርቲ ፍንገጣ በፓርቲው ውስጥ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ተግባር መሆኑ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የፓርቲ ንቅዘትን ይወልዳልና ነገሮችን ለማስተካከል አዳጋች ይሆናል፡፡

በየትኛውም አገር ያሉ ፓርቲዎች የፖለቲካ ማፈንገጥ የሚገጥማቸው በውጫዊና በውስጣዊ ምክንያቶች ነው፡፡ ውጫዊ ምክንያቶች ከማኅበረሰባዊ ጫናና ከሚታገሉለት ሕዝብ አቋም አንፃር የሚፈጠር ሲሆን፣ አንዳንዴም ሕዝበኛ (Populist) አቋምን በመያዝ ሊታጀብ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው የፖለቲካ ማፈንገጥ ወደ ሕዝብ የሚደርስ ከሆነ፣ ሕዝቡ ካፈነገጠው አንጃ ጎን በመቆም ለገዥው ፓርቲ ጥላቻ ሊያሳይ ይችላል፡፡

በአገራችን በቅርቡ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ጉዳይ በዚህ መነጽር የሚታይ ይመስላል፡፡  አፈ ጉባዔው በብሔራዊ ድርጅታቸው ለመቀጠል የወሰኑ ሲሆን፣ ከመረጣቸው ሕዝብ ጎን በመቆምም እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው መሠረታዊ ጥያቄ ታዲያ የእሳቸው የማፈንገጥ አዝማሚያ ከማን ጋር ለመታገል ነው የሚል ሐሳብን ያስከትላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ደግሞ የፖለቲካ ማፈንገጥን ከመዋቅር አንፃር እንድንመለከተው ያስገድዳል፡፡

የኢሕአዴግ ፓርቲያዊ ማፈንገጥ ከመዋቅር አንፃር?

ሮሲና ቴን እንደሚሉት ማፈንገጥ ሥር የሰደደ የፓርቲ ችግር ውጤት እንጂ፣ የድንገቴ ፖለቲካ ጨዋታ መዳረሻ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያትም ማፈንገጥን ከመዋቅር አንፃር ስንመለከተው ሦስት መልኮችን የሚይዝ ይመስላል፡፡ የመጀመሪያው የአጠቃላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅሩ ፈጣን ተለዋዋጭነት ሲሆን ሁለተኛው መደበኛ የሆነ ተቋማዊ መነሻ ነው፡፡ ሦስተኛው የፖለቲካዊ ማፈንገጥ ምንጩ የፓርቲው ውስጠ ዴሞክራሲ አካሄድ የሚፈጥረው ነው፡፡ ከእነዚህ ሦስት ጉዳዮች አንፃር የገዥው ፓርቲን ወቅታዊ ሁኔታን ለመመዘን ከሞከርን ቢያንስ በአንዱ በፓርቲው ውስጥ የፖለቲካ ፍንገጣዎች እንዳሉ ፍንጭ እናገኛለን፡፡

በአገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በበርካታ አካባቢዎች በመንግሥት ላይ ያነጣጠሩ ተቃውሞዎች ሲስተጋቡ ከርመዋል፡፡ እንዲህ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴም ፓርቲው ወደ ተሃድሶ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡ ይህ ዓይነቱ በውሉ ያልታሰበበት የተሃድሶ ዘመቻም በፓርቲው ውስጥ መዋቅራዊ አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ በዚህ መነሾም በኢሕአዴግ ቤት አንድ ዓመት ባልዘለለ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥልጣን መጥተው የወረዱ ከፍተኛ አመራሮቹን መመልከት የተለመደ ሁኗል፡፡ ከእንዲህ ያለው የፓርቲው አለመረጋጋት ማሳያነት በተጨማሪም፣ በኢሕአዴግ ልሂቃን ውስጥ መታደስ ያለበት መንግሥት ነው? ወይስ ገዥው ፓርቲ? ብቻ ነው የሚል ንትርክ እንደነበር በአንድ መድረክ በአጋጣሚም ቢሆን ለመስማት ተችሏል፡፡ ፈጣን የሆነ የማኅበራዊ ኢኮኖሚ ለውጥ የወለደው ያለፉት ዓመታት የተቃውሞ እንቅስቃሴ በየትኛውም መመዘኛ ኢሕአዴግን በተረጋጋ መንገድ እንዲሄድ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ አለመረጋጋት ደግሞ ፖለቲካዊ ፍንገጣን ያስከትላል፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው የአቶ አባዱላ ገመዳ በኃላፊነቴ ለመቀጠል ፍላጎቱ ስሌለኝና ከሕዝቤ ጋር ለመታገል ስለፈለግኩ ፖለቲካዊ አንድምታም ከዚህ የሚርቅ አይመስልም፡፡ እንዲህ ያለውን የአፈ ጉባዔውን አነጋገር ከፓትሪክ ኮልነርና ከማትያስ ባሴዱት የመዋቅር ትንተና አንፃር ካየነው ግን ምላሹ አዳጋች ይሆናል፡፡ የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪው ባሴዱና ለፖለቲካ ቅቡልነት አጥኝው ኮልነር የፓርቲ ፍንገጣ በሁለት መስመሮች ላያ ያርፋል፡፡ ግለሰባዊና ተጨባጭ (Real) የሚለው የሁለቱ ምሁራን መዋቅራዊ ምደባ የቀድሞውን የጦር መሪና አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ የተቃርኖ መነሻ በውሉ እንዳንለየው ያደርገናል፡፡

ሳሪቶ ‹‹Political Parties and Party System›› በተባለ ሥራው የፓርቲ ፍንገጣ ከመዋቅር አንፃር በአራት መደቦች የሚወድቅ ነው ይላል፡፡ እነሱም ድርጅታዊ መከፋፈል፣ ርዕዮተ ዓለማዊ፣ በቀኝና በግራ ፖለቲካ ውስጥ ያለ እሰጥ አገባና ሌላ አጀንዳን ይዞ መገኘት ናቸው፡፡ በእነዚህ የመዋቅር የፖርቲ ፍንገጣዎች ውስጥ አሁንም ኢሕአዴግ ቢያንስ በሁለቱ እየተፈተነ ይመስላል፡፡

የመጀመሪያው ድርጅቱ ራሱ ያመነውና በተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት ለይቼዋለሁ የሚለው ከፓርቲው ዓላማ ጋር የሚጋጨው ሌላ አጀንዳን ይዞ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በፓርቲው ውስጥ ስለመኖሩ ያምናል፡፡ ከሕዝብ ይልቅ የራስን ጥቅም የሚያስበልጡ አባላት በየደረጃው እንደነበሩበትም ይገልጻል፡፡ ይህ ዓይነቱ የእምነት ክህደት ቃልም ኢሕአዴግ ቢያንስ የጠራ ድርጅታዊ መስመርን ለመያዝ እንዳነሳሳው መገመት አያዳግትም፡፡

ሁለተኛው ከሳሪቶ የመዋቅር ገለጻ የምንረዳው ነገር ኢሕአዴግ ውስጥ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት አለ ወይ የሚል ጥያቄን እንድናነሳ ያስገድዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመሠረታዊነት በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መነሻ ይሆነናል፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት ዓመታት በስፋት ከገባባቸው የኢኮኖሚ ትግበራዎች ውስጥ አንዱ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራትን ማስፋፋትና በጊዜ ሒደት እነዚህን ማኅበራት ወደ መካከለኛ ከዚያም ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ ማድረግ የሚለው ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡

ይህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ አተያይ በተለይም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በስፋት የተሳሰረና በተለያዩ ቦታዎችም ሳይቀር ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ አማራጭ ተብሎ ያስወደሳቸው ጉዳይ ነበር፡፡ በልማታዊ መንግሥታት እሳቤ ውስጥ ጉልህ ቦታን ይዞ ብቅ የሚለው የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት እንቅስቃሴ  በኢትዮጵያ አሁን አሁን እየደበዘዘ የመጣ ይመስላል፡፡ የደቡብ ኮሪያውን ሳምሰንግ ተሞክሮ እያጣቀሰ የተጓዘው የኢሕአዴግ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ጉዞ ዛሬ ላይ የተባለውን ተስፋ በውል አልሰጠም፡፡

የድኅረ መለስ ዜናዊን ኢትዮጵያ የሚቃኙ ምሁራንም አሁን አገሪቱ የምትጓዝበት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ከቀደመው የተለየ ስለመሆኑ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ራስን ለውጭ ባለሀብቶች በስፋት ማጋለጡ ለአፍሪካ የማይሆን መንገድ ነው ብለው ሲሞገቱ የኖሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገር አሁን ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብታ የውጭ ባለሀብቶችን መማፀን ጀምራለች፡፡ ይህ ዓይነቱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መንገድም ‹‹Dead Ends New Beginnings››  የተባለው የአቶ መለስ የኢኮኖሚ ሀልዮት ከእሳቸው ጋር አብሮ ያንቀላፋ አስመስሎታል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት ወደ መገንባት ፊቷን ማዞሯ የሳምሰንግ አምሳያ የተባለውን ከጥቃቅንና አነስተኛ ተነስቶ ወደ መካከለኛ፣ ከዚያም ከፍተኛ ኢንዱስትሪ የመሆን ተስፋ እንደ ጉም መበተን ያመላክታል፡፡ በዚህ መሠረትም እንዲህ ብሎ መጠየቅ ነውርነት የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከውጭ በመጡ ባለሀብቶች ሳይሆን በራሷ ልጆች ታትራ ኢንዱስትሪዎች ይኖሯታል የሚለውን የኢሕአዴግ ተስፋ ምን ባለው?

ይህን ጥያቄ መነሻ አድርጎ ከላይ ያነሳነውን በኢሕአዴግ ውስጥ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ተፈጥሯል ወይ ብሎ አሰሳ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዝምተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ እያደረገ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ መነሻ ከላይ ያነሳሁት በአዳዲስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተስፋ ያመጣል የሚል አዝማሚያ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም አንዳንድ የፓርቲው ልሂቃን ደስተኛ እንዳልነበሩ ይነገራል፡፡

በተለይም በፓርቲው ውስጥ ለረጅም ዓመታት ርዕዮተ ዓለማዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሲያድረጉ ለምናውቃቸው አቶ በረከት እንዲህ ያለው አዲስ የኢሕአዴግ የኢኮኖሚ መስመር ሊዋጥላቸው የሚችል አይመስልም፡፡ በመሆኑም የአቶ በረከት ሰሞነኛ በመስመር ተለዩ ገለጻ አንዱ ምንጭ ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ እዚህ ግምት ላይ መስማማት ባይቻልም፣ የአቶ በረከት ከፓርቲ ፖለቲካ የመራቅ አዝማሚያ ከርዕዮታዊ የፓርቲ ፍንገጣ መደብ የሚወጣ አይደለም፡፡  ለእንዲህ ያለው መከራከሪያ ማስረጃነትም ይኼንን ፓርቲያዊ ፍንገጣ መነጽር ከማንም የሚረዳን ነው፡፡ ይኼን ፖለቲካዊ ፍንገጣን ከመዋቅር አንፃር በሁለት ይከፈላል፡፡ ድርጅታዊና ፖሊሲያዊ/ርዕዮተ ዓለማዊ በሚል፡፡ በዚህ መሥፈርት የአቶ በረከት ድንገት ከኢሕአዴግ የመነጠል አዝማሚያ ፖሊሲያዊ/ርዕዮተ ዓለማዊ እንደሚሆን አያከራክርም፡፡

የፓርቲ ፍንገጣ መልኮችና ኢሕአዴግ

አምባገነናዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ የመነሳት ዕድሉ ጠባብ ነው የሚባለው ፓርቲያዊ ፈንገጣ ከሞላ ጎደል ዴሞክራሲን መለያቸው ባደረጉ አገሮች የሚስተዋል ነው፡፡ ፍራንሲስ ፋኩያማ ዴሞክራሲ በራሱ ለፓርቲዎች ፍንገጣ መነሻ ነው የሚለውም ለዚህ ነው፡፡ ግን ፍንገጣዎች ሁሉ በአንድ ፈርጅ ውስጥ የሚታዩና ለፓርቲው አሠራር አደጋ ተደርገው የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ መነሻው የፓርቲ ፍንገጣዎች የየራሳቸው መልክ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡

ፍራንሻይዝ ቡክ የፓርቲ ፍንገጣዎችን ድጋሚ ማጤን በሚለው ጽሑፉ ሁሉም ፍንገጣዎች አደጋ አለመሆናቸው ለመተንተን ይሞክራል፡፡ በእሱ መከራከሪያ ቢያንስ ሁለቱ የፍንገጣ መልኮች ፓርቲውን የሚጎዱበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ የመጀመሪያው የፍንገጣ መልክ ተደጋጋፊ የሆነ ፍንገጣ (Cooperative Faction) የሚባለው ሲሆን፣ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ ለዓላማ መሥራትን ያስቀድማል፡፡ ከልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በማስቀደም የሚካሄደው ይህ ዓይነቱ ፍንገጣ፣ ፓርቲው ውስጥ ያሉ ልዩነቶች ፓርቲውን የሚያበለፅጉና የተሻለ ተግባርን እንዲወጡ የሚያደርጉ በመሆናቸው የሚጠላ አይደለም፡፡

ሁለተኛው የፖለቲካ ፍንገጣ ዓይነትም ለቡክ ብዙ አሥጊ የሚባል አይደለም፡፡ ተፎካካሪያዊ ፍንገጣ (Competitive Faction) የሚባለው ይህ መንገድ በፓርቲው ውስጡ አንጃዎች በሐሳብ አሸንፎ ለመገኘት ብዙ ማስረጃዎችን የሚያቀርቡበትና ለተግባራዊነቱ የጋራ ርብርብ የሚደረግበት በመሆኑ ለሕዝቡ ጥሩ አጋጣሚን ያመጣል፡፡ ይሁን እንጂ የፓርቲው ፍንገጣ የአመራርነትን ቦታን ለመያዝ የሚደረግ ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

አደገኛ የሚባለው የፍንገጣ ዓይነት የመፈረካከስ አዝማሚያን የያዘው ፍንገጣ (Degenerate Faction) ነው፡፡ ይህ ፍንገጣ በፓርቲው ውስጥ ያሉት ኃይሎች ከመደማመጥ ይልቅ መገፋፋት ላይ የሚያተኩሩበት ስለሆነ፣ ፓርቲውን የማፍረስ ኃይል አለው፡፡ የጣሊያኑን ዲሲ ፓርቲን ለብተና የዳረገው እንዲህ ያለው መንገድ ነው፡፡ በሩሲያና በደቡብ አፍሪካም በዚህ መንገድ የመጣው የፓርቲ ፍንገጣ የውስጥ ኃይሎች የራሳቸውን ፓርቲ ለመመሥረት መገንጠልን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል፡፡

ሀልሜል እንደሚለው የፓርቲ ፍንገጣ የፓርቲዎች ሕይወት አንድ አካል እንጂ እንግዳ ነገር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ውስጥ የፓርቲ ፍንገጣ ይኖራል ማለት ፓርቲው አበቃለት የሚል ሟርትን አያስከትልም፡፡ ይልቁንም በፓርቲው ውስጥ ያለው ፍንገጣ ከላይ ከጠቀስናቸው መልኮች በየትኛው ሊሠፍር ይችላል ብሎ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ ጤናማ የሆኑ ፍንገጣዎች ቢኖሩ ለአገሪቷ የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም፡፡ አሳሳቢው ነገር ግን ሦስቱም የፍንገጣ መልኮች ተወራራሽ ሊሆኑበት የሚችለው ዕድል ተደጋጋፊ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጣሊያኑ ዲሲ ፓርቲ በመጀመሪያ ተደጋጋፊ ፍንገጣ ታየበት፡፡ ከዚያም ከ1960 እስከ 1970 ወደ ተፎካካሪ  ፍንገጣ አመራ፡፡ በመጨረሻም ከ1970ዎቹ ጀምሮ በሄደበት የመፈረካከስ መንገድ ለመበተን ተዳረገ፡፡ ኢሕአዴግ ከእነዚህ ፍንገጣዎች የትኛው ውስጥ ይመደባል ካልን ከግለሰቦቹ ማንነት በመነሳት ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ፍንገጣዎች የሚርቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ሁለቱ ጎምቱ ባለሥልጣናት ኢሕአዴግን ለማፈራረስ ይጥራሉ ተብሎ ስለማይገመት ነው፡፡

ይህ ማለት የአቶ በረከት ሰሞነኛ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ የማፈግፈግ አዝማሚያ ቀላል ነው ተብሎ እንዲታለፍ አያደርገውም፡፡ ለ44 ዓመታት በፖለቲካው ዘርፍ የተጓዙት፣ ባለፉት 25 ዓመታት ተተኪ የኢሕአዴግ አባላትን የመለመሉት፣ አዕላፍ አመራሮችን ስለፓርቲያቸው ርዕዮት ዓለም ያስተማሩት ሰው ከፖለቲካ የማፈግፈግ አዝማሚያ የአንድ ግለሰብ የመገንጠልን ሐሳብ ብቻ አያመለከትም፡፡ ይልቁንም ፓርቲው ውስጥ ያለውን የማፈንገጥ አዝማሚያ በውሉ እንድናጤነው ያስገድዳል፡፡ አልያም የዛራሲክን የፓርቲ ፍንገጣ ብያኔ ተውሰን ኢሕአዴግ ውስጥ የመለያየት ግንብ እየተገነባ  ስለመሆኑ መናገር ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግ ውስጥ ካለ ማፈንገጥ ማን ያተርፋል?

ፍራንሲስ ፋክያማ ‹‹Political Order and Political Decay›› በተሰኘ መጽሐፍ የፖለቲካ ንቅዘት (መበስበስ የሚለው ቃል ስለሚጎረብጠኝ ነው) ከሁለት መሠረታዊ ነገሮች ይመነጫል ይላል፡፡ የመጀመሪያው ማኅበረሰቡ ከሚፈልገው ደረጃ ፖለቲካው አለመድረሱ ሲሆን፣ ሁለተኛው አዳዲስ ሐሳቦችን የያዘው ቡድን ነባሩን ቡድን መፈተን ሲጀምር ነው ይላል፡፡ ለፋኩያማ ሁለቱም መንገዶች ፖለቲካን የማዘመኛ ፈለግ በመሆናቸው ለማኀበረሰቡ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የማይፈቱ ከሆነ ጊዜያዊ ችግሩ በአገር ላይ ትልቅ ጥፋት ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አዲስ ሐሳብን ያልያዘው ቡድን የማሸነፍ ዕድሉ ከሰፋ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ያለው ልዩነት እስካልተፈታ ድረስ የፖለቲካ ንቅዘቱ ይቀጥላል፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አሁን የሚስተዋለው ፍንገጣ በምን ዓይነት የፖለቲካዊ አቋም መነሻ የመጣ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል የወደፊቱን ለመተንበይ ያዳግታል፡፡

ነገር ግን ፖለቲካዊ ፍንገጣዎች እስካሉ ድረስ ሁሌም ለውጥ ይኖራል፡፡ ይህ ለውጥ ግን የተሻለ ወይም ወደ ባሰ ሁኔታ አገሪቷን ሊያደርሳት እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ በዘ ኢኮኖሚስት የአገሮች የዴሞክራሲ ውጤት እ.ኤ.አ. በ2006 ከአሥር 4.7 የነበረችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ 3.6 አሽቆልቁላለች፡፡ ይህም በፓርቲ ፍንገጣ ውስጥ የነበሩትና አሁን ለመልቀቅ የተንደረደሩት አመራሮች ከኃላፊነት መነሳት፣ በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ይቀንሰዋል፡፡ ግን ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከማንም በላይ የሚረዱት ሰዎች መልቀቅ ለኢሕአዴግ የለውጥ ምጥ ጅማሮው እንጂ ድሉ አይደለም፡፡

      ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡