Skip to main content
x

ኢትዮጵያ ከልጅነት ልምሻ ነፃ ሆነች

  • ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል

ኢትዮጵያ ከልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በሽታ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ነፃ መሆኗን ለዚህም በአፍሪካ ደረጃ ከተቋቋመው የአፍሪካ አህጉር የፖሊዮ ነፃ ማወጅ ተቋም (አፍሪካ ሪጅናል ሰርቲፊኬሽን ኮሚሽን) ዕውቅናና ተቀባይነትን ማግኘቷን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ቀን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ውጤት ላይ ልትደርስ የቻለችው በሽታውን ለማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡትን ዋና ዋና ተግባራት ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ ስትተገብር በመቆየቷ ነው፡፡

ከተገበረቻቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከልም መደበኛ የክትባት አገልግሎትን ማጠናከርና በተከታታይ ሦስት ጊዜ የፖሊዮ ክትባት የወሰዱ ሕፃናትን ሽፋን 90 በመቶ ማድረስ ይገኝበታል፡፡

የሕፃናትን የፖሊዮ በሽታ የመከላከል አቅም ለማዳበር ተጨማሪ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን ማካሄድና የፖሊዮ በሽታ ቅኝትን ማጠናከር ካደረገቻቸው ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በመደበኛነት በተከታታይ ሦስት ጊዜ የተሰጠውን የልጅነት ልምሻ ክትባት የወሰዱ ሕፃናት ሽፋን በ1992 ዓ.ም. ከነበረበት 40 በመቶ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ወደ 97 በመቶ ለማድረስ እንደተቻለ፣ በተከናወኑት ተግባራትም በአገሪቱ ያለውን የፖሊዮ በሽታ ወረርሽኝ ክስተትና ሥርጭት ማስቆም እንደተቻለ መግለጫው አመላክቷል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በ2005 ዓ.ም. በተከሰተው ድንበር ተሻጋሪ የፖሊዮ ወረርሽኝ ምክንያት በሶማሌ ክልል በተለይም በዶሎ ዞን ወረርሽኝ ተከስቶ በሕፃናት ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ በመንግሥትና በአገር በቀል ድርጅቶች ድጋፍ ወረርሽኙን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሌሎች ክልሎች ከመዛመቱ በፊት ለማስቆም ተችሏል፡፡

በዚህም መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ጊዜ፣ እንዲሁም ከ16 ጊዜ በላይ ደግሞ ለበሽታው ሥርጭት ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የመከላከያ ክትባት በዘመቻ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም ደረጃ በ1980 ዓ.ም. በፖሊዮ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 350 ሺሕ እንደነበር፣ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር 37 ብቻ እንደሆኑ፣ ይኼም ሆኖ ግን ከፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ናይጀሪያ በስተቀር በሌሎች የዓለም አገሮች የበሽታውን ክስተትና ሥርጭት ማቆም ተችሏል፡፡

የልጅነት ልምሻ በሽታ ሕፃናትን ለሕመምና ለዘላቂ የአካል ጉዳት ከሚዳርጉ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ በሽታው የፖሊዮ ቫይረስ በሚባል ተዋህሲያን የሚመጣ ሲሆን፣ በአብዛኛው የማዕከላዊ ነርቭ ሥርዓትን የሚጎዳና የሚያጠቃ ነው፡፡ በሽታው በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝን ሰው የሚያጠቃ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመታት በታች የሆኑ ሕፃናትን ያጠቃል፡፡ መከላከል የሚቻለውም ሕፃናት ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ መደበኛና ተጨማሪ ክትባቶችን በዘመቻ መልክ በመስጠት ነው፡፡

‹‹የተገኘውን ውጤት በማስቀጠል ፖሊዮን ከኢትዮጵያ እናጥፋ›› በሚል መሪ ቃል በግዮን ሆቴል ለአምስተኛ ጊዜ በተከናወነው በዚሁ የዓለም አቀፍ ፖሊዮን የማጥፋት ቀን ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተገኝተዋል፡፡

የናሽናል ፖሊዮ ፕላስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ታደሰ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ ከስድስት ጎረቤት አገሮች ጋር የምትካለል በመሆኗ ድንበር ዘለል ፖሊዮ ሊመጣና ብዙ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመው፣ እንዲህ ዓይነቱ ችግር እንዳይከሰት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃንና ማኅበረሰቡ የየድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፖሊዮን ለማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተካሄደው እንቅስቃሴ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ለተከናወነው ተመሳሳይ ሥራ ደግሞ 450 ሚሊዮን ብር መለገሳቸውን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ወርቁ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች እምብርት እንደመሆኗ መጠን ድንበር አዋሳኝ ከሆኑ ጎረቤት አገሮች ጋር ፖሊዮን ለማጥፋት የሚያስችል የፕሮቶኮል ስምምነት መፈረሟን ገልጸዋል፡፡ 

የአምስት ዓመቱ የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕላን ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት 1,000 ሕፃናት መካከል በአሁኑ ጊዜ ያለውን 64 የሕፃናት ሞት በ2012 ዓ.ም. ወደ 30 ዝቅ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ማካተቱን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡ በዚህም ስትራቴጂ ቢያንስ ወደ 95 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ክትባቱን እንዲያገኙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል፡፡