Skip to main content
x

የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

  • አንድ ሦስተኛ ያህሉ ጎልማሶች ለደባል አጫሽነት ተጋልጠዋል

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 3.2 ሚሊዮን ትምባሆ አጫሾች እንዳሉ፣ በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ከሚገኘው አንድ ሦስተኛ ያህሉ ደግሞ ለደባል (ለእጅ አዙር) አጫሽነት እንደተጋለጠና ኅብረተሰቡን ከዚህ ዓይነት አደጋ ለመታደግ የሚያስችል አስቸኳይ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ሲጋራ ማጨስን አስመልክቶ የተሠራውና ሰሞኑን ይፋ የሆነው የዳሰሳ ጥናት አመለከተ፡፡ 

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በጋራ የሠሩት የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ለደባል አጫሽነት ከተጋለጠው ኅብረተሰብ መካከል 60.4 በመቶ ያህሉ በቡና ቤቶችና በምሽት ክበቦች ውስጥ የተጋለጡ ናቸው፡፡ 31.1 በመቶ በሬስቶራንቶች፣ 29.4 በመቶ በዩኒቨርሲቲዎች መጋለጣቸውም ታውቋል፡፡

አገሪቱ ውስጥ የትምባሆ ዋጋ ዝቅተኛ መሆን፣ ለአጫሾችና ለደባል አጫሾች ቁጥር መብዛት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነና ለዚህም እንደ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው በትምባሆ ላይ ዋጋ መጨመርና ከፍተኛ ታክስ በመጣል የትምባሆ ሱስ የያዛቸው ወገኖች እንዳያጨሱ፣ ወጣቶችም ሆነ ሌሎች ትምባሆ የማያጨሱ ሰዎች ትምባሆን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ማድረግ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በትምባሆ ሾኬዎች ላይ ትምባሆ ማጨስ አደገኛ መሆኑን የሚያመላክቱ ጽሑፎችና ሥዕላዊ ምልክቶች እንዲያሳትሙ እንዲሁም በማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ በስፖንሰርሺፕነት እንዳይሳተፉ ግፊት እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡