Skip to main content
x
በሰፋፊ እርሻዎች የተንሰራፋውን ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ተጠየቀ

በሰፋፊ እርሻዎች የተንሰራፋውን ችግር ለመፍታት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ተጠየቀ

በተለያዩ ክልሎች በሰፋፊ እርሻ ሥራ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያወጣው የብድር ፖሊሲ ሊያሠሯቸው እንዳልቻለ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ልማት ባንክ ጉዳዩ የፋይናንስ አቅርቦት ብቻ ስላልሆነ ችግሩን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት መሳተፍ ይኖርባቸዋል አለ፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ፣ በሶማሌና በጋምቤላ ክልሎች በሰፋፊ እርሻ ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ባቋቋሟቸው ማኅበራት አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባቀረቧቸው ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ‹‹ልማት ባንክ ያወጣው የብድር ፖሊሲ ፍጹም ከግብርና ዘርፍ ጋር የማይጣጣምና የማያሠራ በመሆኑ መንግሥት ሊያስተካክላቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበራቱ ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባስገቡት ደብዳቤ፣ የብድር ወለድ ምጣኔ ከ8.5 በመቶ ወደ 12.5 በመቶ ከፍ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም መሬት በሔክታር ለማልማት የሚፈቀደው 45,000 ብር በመሆኑና ይህ ገንዘብም ቢሆን በቂ አይደለም ተብሎ ቅሬታ እየቀረበ እያለ፣ ልማት ባንክ ግን ለአንድ ሔክታር የሚፈቅደውን ብድር በሔክታር ከ11,000 እስከ 25 ሺሕ ብር ዝቅ ማድረጉ አግባብ ባለመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ሲሉ ማኅበራቱ ጠይቀዋል፡፡

ተበዳሪው አካል የሚበደረውን ብድር ባወጣው ቢዝነስ ፕላን መሠረት ሊመራ ሲገባ፣ ልማት ባንክ ግን ከአቅራቢዎች ጋር በቀጥታ በመደራደር ለሦስተኛ ወገን ወይም ለኮንትራክተር የመክፈል አሠራር መዘርጋቱ አግባብ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡

በእርሻ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የግል ካፒታል መጠናቸው ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወይም የፕሮጀክቱ ወጪ መጠን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን መወሰኑ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብድር እንዳያገኙ እንቅፋት በመሆኑ ሊሻሻል እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር በአገሪቱ ካለው የአክሲዮን አሠራር ደንብ ውጪ ተበዳሪዎች የአክሲዮን ድርሻቸው ከአሥር በመቶ በላይ ሲሆን፣ ከግል ንብረታቸው በተጨማሪ ለብድር ዋስትና እንዲያሲዙ የሚያደርግ አሠራር መውጣቱ አግባብ አለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ ጎፋና ሰገን ዞኖች የግብርና ኢንቨስትመንት ኅብረት አስተባባሪ አቶ ደመወዝ ካሳሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእርሻ ሥራ በባህሪው አስቸጋሪና በቀላሉ ለትርፍ ተብሎ የሚገባበት ባለመሆኑ፣ እንዲሁም ዘርፉ ከሚያበረክተው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ታይቶ ሰፊ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ነገር ግን ልማት ባንክ ዘርፉን በዚህ ረገድ ተመልክቶ እየደገፈ አይደለም ሲሉ አቶ ደመወዝ ይወቅሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተለይ በዝቅተኛ ቦታዎች የሚገኙ የእርሻ ሥራዎች በተለያዩ ችግሮች ተተብትበው የሚገኙ በመሆናቸው፣ ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ በተለያዩ መድረኮች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብድር አንድ ነጠላ ጉዳይ ነው፡፡ የሰፋፊ እርሻ ዘርፍ ከዚያ በላይ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡

‹‹የተዘረዘሩት ችግሮች የፖሊሲ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ በጥናት እየታዩ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ፣ የዘርፉን ችግሮች ወጥ በሆነ መንገድ መፍታት ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ተሾመ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ ያለውን ዋና ዋና ችግር ሲጠቅሱም፣ በተለይ የምርታማነት ችግር በኤክስቴንሽን ፕሮግራም አለመደገፍ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶች አቅርቦት ችግር፣ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ የአፈሩ ባህርይ አለመታየቱና ሜካናይዝድ ለመሆን አለመቻልን ችግር ጠቁመዋል፡፡

‹‹በአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ ብድር ሰጥተናል፡፡ ነገር ግን አዋጭ ሆኖ ባለመገኘቱ ተበዳሪዎች ብድራቸውን ለመክፈል ተቸግረዋል፤›› ሲሉ አቶ ተሾመ ገልጸው፣ ‹‹ጋምቤላ አካባቢም የተገኘ ምርት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሳይገባ በደላላ ሲሸጥ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በሰፋፊ እርሻ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም የሚመለከተው አካል መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትም ሥራዎች ተጀምረዋል፤›› ሲሉ አቶ ተሾመ ገልጸዋል፡፡