Skip to main content
x

ኧረ ምን ይሻለናል?

በገነት ዓለሙ

ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ዴሞክራሲና ልማት የማይደራረሱ ነገሮች አይደሉም፡፡ ፖለቲካ ወደ ኢኮኖሚነት ይተረጎማል፡፡ ኢኮኖሚም ይቦተለካል፡፡ ልማቱን እንቅ ገተር የሚያደርገው፣ ሲመቸውም መላወስና መንቀሳቀስ የሚያስችለው፣ አደገ ተመነደገ የሚያስብለው ከዚህ በላይ መስፋፋትና መገስገሱን የሚጠናወተው ፖለቲካው ነው፡፡ ከኢሕአዴግ በፊት የደርግ ወታደራዊ የፍለጠው ቁረጠው ፖለቲካና የተቃዋሚዎች እርስ በርስ መበላላት፣ በኋላም የገነባው የወታደራዊ አምባገነንነትና ሁለንተናዊ አዛዥነት ምን ያህል መቀመቅ እንደከተተን ይታወሳል፡፡

ለልማት፣ ለነፃነትና ለፍትሕ የታገለው ኢሕአዴግ በተተካ ጊዜ (በትግሉ ወቅትም ጭምር) የችግሮች ሁሉ የበላይና የዴሞክራሲ ሁለመና መፍቻው፣ መውጫው፣ መወጣጫው፣ ማምለጫው የብሔሮች ጥያቄ ሆኖ አረፈ፡፡ ዛሬ ለቀቅ ባለው ፖለቲካ ልክና ውስጥ መላወስ የጀመረውን ልማትና ዕድገት ማስደንገጥ፣ ከሩቁ ማባረር፣ ድራሹን ለማጥፋት መሞከር የቻለውም ይኼው የበላይነት የያዘው ብሔርተኝነትና የብሔር ፖለቲካ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሽሙንሙን ስሙ ኪራይ ሰብሳቢነት ብለው የጠሩት ሙስና፣ ምዝበራ፣ ስርቆት፣ መግደል፣ ሁሉ የተካተተበት የአገር ምድር ወንጀል ሽፋን ያገኘውም እዚሁ ብሔረሰባዊ ነፃነትና ንቃት ውስጥ ነው፡፡

አገሪቷን የሚንጣትን፣ ማለቂያና ትርጉም የለሽ የወሰን ግጭትንና በግለሰባዊ ጠብ ላይ ሳይቀር የሚበቅል የብሔር ለብሔር ጠብን ግን ከፌዴራሊዝምና ከቡድን መብቶች መጠበቅ ጋር ማምታታት ሲበዛ ያሳስታል፡፡ አደገኛም ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብሔር/ብሔረሰቦችን ልብና ክንድ የከፋፈለውን፣ ለውስጥ ‹‹የዳር ድንበር›› ፖለቲካና ውጊያ ያጋለጣቸውንና የዳረጋቸውን የየራስ ‹‹የርስት ምድር›› ፖለቲካ ለመረዳትና ለመራቅ፣ እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ ለማጣላት የሚደረጉ መከራዎችን ለማክሸፍና ሰበቦችን ለማጥፋትም ይህንኑ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ችግራችን ፌዴራሊዝምና ሕገ መንግሥቱ አይደለም፡፡

የዚህ የሥር መሠረቱ በ1960ዎቹ መጨረሻ ኅብረ ብሔራዊ ትግል ተንኮታኩቶ የየብሔር ትግል ቦታውን መውሰዱ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ ዋናው ጥያቄ ወይም ቅራኔ የብሔር ነው ከሚል ስህተትና ጥፋት ወጥቶ የሁሉም ብሔረሰቦች የትግል አስኳል ዴሞክራሲያዊ ነፃነት፣ ፍትሕና ከድህነት መውጣት መሆኑን ለማየትና በእነዚህ የጋራ ጥቅምች ላይ ትኩረቱን ለማደላደል የበቃ ትግል አለመኖሩ ነበር፡፡ የትግሉ ጩኸት የአንድ ብሔር የበላይነት፣ የብሔሮች እስረኝነትና ሙሉ መብት እስከ መገንጠል ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ባለብዙ ብሔረሰቦች መሆኗን ተቀብሎ ይህንን እውነት ከአገራዊ ትስስር ጋር የሚያግባባ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይዞ ወደ ሕዝብ መቅረብ ፈተና ሆኖ ዘለቀ፡፡ የትግሉ ጩኸትም በዋናው የዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ ጥላ አጥልቶ በፀረ ዴሞክራሲያዊ ውዥንብር የሕዝቡን ፀረ ደርግ ትግል እስከ ማስጠቃትና ኢሕአዴግም በገዛ ራሱ ላይ ‹አገር የማፍረስ›› ክስና ውንጀላ ሲጠራ ኖረ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ከላዩ ላይ ማውረድ ያልቻለው ኢሕአዴግ በትግሉ ወቅት ክሱ እየበረታ ሲወጥረው ደግሞ ለክሱ ማፍረሻ መሆን ያልቻለ፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ መጎዝጎዝ ያላበቃው አሁን እየባሰበት የመጣውን አደጋ መከላከል ያላገዘው ባዶ ትንተና ውስጥ ገባ፡፡ ይህ የተሳሳተ አቅጣጫ ባለመታረሙ ይልቁንም ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አገኘ መባሉ ለዛሬው እየጠና እየከፋ ለመጣው ቀውስ ጠንቅና ችግር ዳርጎናል፡፡

የችግሮች ሁሉ የበላይና የዴሞክራሲ ሁለመና የብሔር ጥያቄ ሆኖ በመደምደሙ ዴሞክራሲያችንና ፌዴራሊዝማችንን፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታችንን የሚያሰናክሉ ተከታታይ ጣጣዎች ግትልትል ችግሮች ተናነቁን፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ትንንሽ ፓርቲዎች ረቡ፡፡ የየአካባቢው ትናንሽ ገዥነትንና ‹‹ሉዓላዊነትን›› አቋቁመን በክልሎች መካከል የባቢሎን ግንብ አጥር ገነባን፡፡ የመኖሪያ ሥፍራን የመምረጥ ነፃነት በ‹‹ማንነት›› እና በመገኛ ምድር ውስጥ የታጠረና የተገደገደ የብሔረሰቡ ተወላጅ መብት ብቻ ሆነ፡፡ በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ውስጥ የተደነገገው በመራጭነትም ሆነ በዕጩ ተመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስፈልገው፣ በምርጫ ክልል ውስጥ በሕጉ ለተቆረጠው ጊዜ ያህል በመደበኛነት የመኖር ቅድመ ሁኔታ የፓርቲ የፖለቲካ ጥቅምን እያሸተተ እንዳሻው ሲሻሻል፣ ሲፈርስ፣ ሲሠራ ባየንበት አገር (የ85፣ የ87፣ የ92 የምርጫ ሕጎችን ታሪክ ይመለከቷል) የአገር ትርጉም በክልልና በወንዝ ጠበበ፡፡ ከ‹‹ወንዙ›› ውጪ የመጣው ባዳ፣ እንግዳ፣ መጤ ሆኖ አረፈው፡፡

የብሔር/ብሔረሰብ ውክልና ገና ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሕዝብ ድጋፍ የማይመዘን የራስ በራስ ሹመት ሆነ፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥቅም ውክልና የኢሕዲን/ብአዴን የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት፣ የኦሮሞ ሕዝብ የኦሕኦዴድ፣ የደቡብ ሕዝቦች የደኢሕዴግ/ደኢሕዴን፣ ወዘተ እያለ ቀጠለ፡፡ ኢሕአዴጋዊ ያልሆነ ሌላ አለሁ ባይ ሕዝብን የማይወክል የጥቂቶች ጥርቅም ተባለ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ትክክል የሚባለው አተያይና አቦዳደን (ከፖለቲካ እስከ ትዳር) ብሔረሰባዊ ሆነ፡፡ ከተወራረሰ ገጽታ ይልቅ ልዩ ወይም የብቻ የሆኑ መለያዎችን መፈለግና ማጉላት ሚዛን ደፋ፡፡ የብሔር/ብሔረሰብ ማንነት በሆነ ማኅበረሰብ ባህልና ቋንቋ በመቀረፅ የሚገለጽ ከመሆን አልፎ የትውልድ ጀርባን መርምሮ፣ የጠራና ያልጠራ እስከ መለየት ድረስ ፈር ለቀቀ፡፡ በተለያየ ደረጃ የሚታይ የማኅበራዊ ቅልቅሎሽ ገጽታን እንደ በጎና ተፈጥሮአዊ እውነት መቀበልና ማክበር ችግር ሆነ፡፡ በተዋሳኝ ብሔረሰቦች ዘንድ ያለ ጉራማይሌ ማኅበራዊ ጥንቅር፣ በተለይ በከተሞች ዘንድ ያለ ከአማርኛ ተናጋሪነት ጋር የተሳሰረ ውጥንቅጥ ስብስብ በብሔርተኞች ዘንድ ያልተፈለገ ዕድገትና ችግር ሆኖ ተቆጠረ፡፡ ብሔረሰባዊ መካለስ ወይም መሰባጠር የሚታይባቸውና በዚያኔው አዲሱ አከላለል የተቆረጡ ማኅበረሰቦች፣ በብሔርተኞች ጥንቅር የማጥራት ወይም እውነተኛ ብሔራዊ ባህልንና ቋንቋን የማስፋፋት እንቅስቃሴ መረበሽ ግድ ሆነባቸው፡፡

ጉራማይሌ ባህልና አነጋገር፣ ከሌላ ብሔር መጋባትና መዋለድ የሚያስንቅ ሲሆን ታየ፡፡ እንዲህ ያለውን ‹‹የማይፈለግ›› ገጽታ የሚያደክም ዘመቻ ተከፈተ፡፡ ብሔርተኛ ንቃቱ ተዛመተ፡፡ በመኖርያም፣ በሥራ ቦታም፣ በመታወቂያም፣ በትውውቅም፣ ብሔራዊ ማንነትን መለየትና መምረጥ ግድ ሆነ፡፡ የራስንና የልጆችን መጠርያ እስከ መቀየርና የሌላ ብሔር የትዳር ጓደኛን እስከ መፍታት የዘለቀ ጉድ ተከሰተ፡፡  

ከተለያየ ብሔር በመወለድ ምክንያት የተቸገረው፣ የብሔር ፖለቲካን መቃወም የፈለገውና የብዙ ብሔሮችን እውትነት በ‹‹አንድ ሕዝብ›› ምኞት የተካው ሁሉ ተደምሮ ‹‹ብሔር የለኝም/ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ያለ፣ ‹‹የብሔር መብት የሚፃረር ትምክህተኛ›› ተደርጎ ተመደበ፡፡ በአንዱ ወይም በሌላው ብሔር ውስጥ ራስን አለመመደብም ሆነ ብሔርተኛ አለመሆን መብት መሆኑም ተዘነጋ፡፡ በብሔር ቡድን ውስጥ መግባት ያልፈቀደና የብሔር ጉዳይን እንደ ሃይማኖት ያላጠበቀ በብሔር ማንነቱ የሚያፍር ተደርጎ ተበየነ፡፡

በዚህ ሁሉ ላይ ከውሱን ታሪካዊ መረጃ ጋር አፈ ታሪኩን እያዛመዱና እያስፋፉ አኩሪ የየብሔር ታሪክ የማሰናዳት ጥድፊያም ተያዘ፡፡ የከዚህ ቀደሙ ያለ የሌለ ግፍ ተቆፈረ፡፡ ተራ ፌዝና ብሽሽቁም እየተለቃቀመ የበደል ማስረጃና የሕዝብ ስሜት ማደፍረሻ ሆነ፡፡ ሁሉንም ብሔርተኛ ማድረግ አጠቃላይ ሥልት ሆነ፡፡ የብሔር ጭቆና ያልነበረበት አማራው ሳይቀር በግድ ብሔርተኛ ካልሆንክ፣ ‹‹ብሔር . . ብሔር›› ካላልክ፣ ኢትዮጵያዊነትን እስካጠበቅህ ድረስ ለሌላው አደጋ ነህ ተብሎ ተወጠረ፡፡ ብሔርተኛ አለመሆን ከ‹‹ምርጥ ኢትዮጵያዊነት›› ጋር ተምታታ፡፡

የኢትዮጵያን ብሔሮች የሚያያይዛቸው መፈቃቀድ መሆኑ ሲሰበክ የዚህ የመፈቃቀድ አንድ ትልቅ ጉዳይ ከእርስ በርስ ትርምስ አምልጦ የማደግ ጥቅም መሆኑ ተፈልቅቆ ሳይወጣ ቀረ፡፡ መፈቃቀዱ የዘፈቀደ ምርጫ እስኪመስል ድረስ አንዱ ለአንድነት ተንበርክኮ ለማኝ፣ ሌላው ተለማኝና በሩ ከተዘጋ እወጣለሁ እያለ አስፈራሪ ወይም ለሌላው ሲል የሚቆይ እስኪመስል ድረስ አመለካከታችን ተበለሻሸ፡፡ በመነጠልም ሆነ በአንድነት ጥቅምና ጉዳት ላይ ሕዝብ ያለው የመወያየት መብት ነውር ይመስል ታፍኖ ታለፈ፡፡

በቋንቋ መናገር፣ መተዳደር፣ መዳኘት፣ መማርና መጻፍ ይብዛም ይነስ ቢቻልም ኢሕአዴግ አለኝ የሚለው አኩሪ ለውጥ ይኼው ብቻ ሆነ፡፡ የዚህ ምክንያት ለተግባባ ትድድር የተሸነሸነውና የተከፋፈለው የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት፣ የገዥው ፓርቲ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የርስት ምድርና ትንንሽ ‹‹አገር›› ሆኖ የተመረቀላቸው መሆኑ ነው፡፡ የፀብ እሳት የሚፈጥረው አደገኛነት አልመክን ያለው፣ ይልቁንም እየተባባሰ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አስተዳደር አባላት የሆኑት ክልሎች፣ ለቁጥራቸውና ለማንነታቸው ምክንያት የሆነው አከፋፈል መነሻ እስከተቻለ ድረስ ተንጣልሎ የሚገኝ የሕዝብ ተመሳሳይነትን ለመከተል ነው፡፡ ለተግባባ ትድድርና ዕድገት ነው፡፡ ይህ አሸናሸንና አከፋፈል ግን የአስተዳደር ይዞታንና በዚያ ይዞታ ሥር ያለን መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የብቻ የድርሻ ካርታ አድርጎ አላቃረጠም፡፡ የብቻ ምድሬ ባይነትን አልመረቀም፡፡ ብሔረሰቡን ወይም ማኅበረሰቡን በየ‹‹መገኛ›› ሥፍራው የሚገድብና የሚያጥር፣ በዚያ በተከለለ የርስት ምድሩ አስሮ የሚያቆይ አይደለም፡፡ ክልል ማለት ለብሔረሰቡ ብቻ የተከለለ፣ ለሌላው የተከለከለ የይዞታ ቅርጫ አይደለም፡፡ ይህ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ያለ የተሳሳተ ዕይታ ግን ኢትዮጵያዊነትን የሚያምስ፣ ኢትዮጵያን የሚያተራምስ፣ ብሔራዊ ድርጅቶችን ደግሞ በሚገዙት የርስት ምድራቸው ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ አድርጓቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በጋራ የሚያብከነክን፣ አንድ ልብ የሚያደርግ የሚጋፈጡትና የሚታገሏቸው ሕመሞች ብሶቶችና ፍላጎቶች ቢኖሩም፣ ከእነሱ የወጡት የፖለቲካ ቡድኖች የያዙት ቅዳጅና ጥብቆ ዓላማ ግን የሕዝቦችን የጎሪጥ የመተያየት አደጋ አስከትሏል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ለማከፋፈልና ለማደላደል መነሻ የሆነው መልክዓ ምድራዊ ክፍለ አገራዊ ሽንሸና የብቻና የቅርጫ የድርሻ ካርታ ተደርጎ በመወሰዱ፣ ግዛት ቆጠራ ውስጥ የተገባው ድንገት መገንጠል ቢመጣ ተብሎ ገና ሲጀመር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የአንድ ወረዳ ወይም ቀበሌ በሌላ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ መግባት መሬትን በመንጠቅ ተተርጉሟል፡፡

ውስጥ ውስጡን ሲብላሉ (ሲያባብሏቸው) የኖሩትና ሪፈረንደም እንኳን ያልፈታቸው መሬቴ፣ ወንዜ የሚሉ ውዝግቦች የጎተቱትና አምጠው የወለዱት ቀውስ መስከረም 2010 ዓ.ም. ላይ ያሳየን ምልክቱንና ማስጠንቀቂያውን ብቻ ነው፡፡ ከመስከረም 2010 ዓ.ም በፊትም በየጊዜው እየተደጋገመና እየተጠናከረ የመጣውን የብሔራዊ ክልልነት፣ የዞንነትና የልዩ ወረዳ መብት ጥያቄዎችንና ግጭቶችንም በሚገባ ዓይተናል፡፡ ይህን የመሰለ ሽፋን የያዘ የሥልጣንና የዝርፊያ ሽኩቻ ሲበዛ ተበራክቷል፡፡ ባሉበት አካባቢ ውስጥ ሥልጣንን በጎሳና በጎጥ እስከ መተሳሰብ መውረድ እንደ አዋቂነትና እንደ ንቃት እየተቆጠረ የመጣው ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ቅድሚያ ለአካባቢው ብሔር ተወላጅ፣ ብሔራዊ ተዋጽኦን ማመጣጠን ማለት ይፋ ፖሊሲ ሲሆን ጎሰኝነትም ቀናው፡፡ ተዛነፉ የአካባቢው ብሔር አባላት ልዩ መብት ባለማግኘታቸው የመጣ ይመስላል፡፡ ይህም ተዛነፍ  በ‹‹በጎ አድልኦ›› ይወገድ ይመስል አሁንም ድረስ በገዛ አገሩ ‹‹መጤ›› ወይም ‹‹አናሳ›› የሚባለው የማኀበረሰቡ አባላት በውስጥና በውጭ ትምህርትና የሥልጠና ውድድር፣ በሥራ ቅጥር፣ በዕድገትና በሹመት ላይ የሚንገዋለሉበት አሠራር መጣ፡፡ ውጤትና ብቃት ዋና መመዘኛ ከመሆን ወጣ፡፡ ይህ ጥቃት ተዛነፍን በማስተካከል ዓላማ ይጀመር እንጂ፣ አድልኦው ያለፈ በዳይነትንና አድሎአዊነትን በዛሬ ተራ የማወራረድ ውስጣዊ ግፊት ሁሉ ነበረው፡፡

ግፊቱ እየተሠራጨ እየገፋና እየከፋ አድልኦው በኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ በመሬት አሰጣጥና በግብር አተማመን ውስጥ ሁሉ መግባት ችሏል፡፡ የዕለታዊ ግጭቶች፣ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ክሶች አፈታት ሁሉ ከብሔር ተወላጅነት ጋር ይገናኝ ዘንድ ተደርጓል፡፡ በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ሳይቀር በጎሳ ደረጃ መፈላለግና መወጋገን አዋቂነት ሆኗል፡፡ ከአንድ ብሔረሰብ በላይ ባቀፉ የአስተዳደር አካበቢዎች በብሔራዊ መብት/ድርሻ ሽፋን የሥልጣን፣ የበጀት፣ የዕርዳታ እህል፣ የግዛት ድርሻ ሥሌቱና የጥቅም ማስፊያ ዱለታውና ፍትጊያው ከክልል እስከ ወረዳ አገር ያደረሰ አሠራር ነው፡፡ በሒደቱ ጥቂት ብልጣ ብልጦች የመክበሪያ መንገዳቸውን ያመቻቹበታል፡፡ ይከብራሉ፡፡ የብዙኃኑ ‹‹ጥቅም›› ግን በመጠቀሚያነት መታመስ መሸካከርና በፀብ መደራረስ ነው፡፡ ከከብት አርቢው ተነቃናቂነት ጋር ያልተጣጣመው የውኃና የግጦሽ የክልል ይዞታነት የብሔርተኞች ቅስቀሳ ተጨምሮበት ተጎራባች ማኀበረሰቦችን ማጋጨቱ ጨምሮ ተባብሷል፡፡ እያንዳንዱን ነገር በጎሰኛ ዓይን ማየትና መመዘን ተስፋፋቷል፡፡ የአገሪቱ ማኅበራዊ ንቃትና ግንዛቤም ሆኗል፡፡   

ከእኔ ብሔር ከእኔ ጎሳ ምን ያህል ተሾመ? የተሾመው፣ የተመደበው፣ የተመረጠው ወይም የወረደው ብሔሩ ከየት ነው? በሬዲዮና በቴሌቪዥን መግለጫ የሚሰጠው ከየት ብሔር ይመስላል? በፀቡ የተመታው ማነው? መቺውስ? ገዳዩስ? ወዘተ እያሉ የግል ግጭቶችን ጭምር በብሔረሰባዊ ጥቃት እስከ መጠርጠርና መመንዘር ድረስ አዕምሮ ተጠምዷል፡፡ የሌላ ብሔር አባል ወይም ለአካባቢው አዲስ የሆነ ሰው ግንባታ ሲያካሂድ ሲያዩ ሌላው ቀርቶ ካርታ አንሺና የአፈር፣ የዕፀዋት ተመራማሪ ሲያዩ መሬቴ፣ ማዕድኔ እያሉ በስስት ማለቅ ‹‹ብሔራዊ›› ስሜት ሆኖ ተቋቁሟል፡፡

የዚህ ሁሉ መነሻና ምክንያት የአደጋውን ኤግዚቢሽን ደጋግሞ ያሳየውና ያስመረቀው ብሔርተኛ አተያይና አደረጃጀት እንጂ ፌዴራሊዝም አይደለም፡፡ ወይም ለብሔር/ብሔረሰብ የቡድን መብት ዕውቅና መስጠት አይደለም፡፡ አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለው ብሔራዊ ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር መታየትና መመዘን ያለበት በመሬት ድርሻ ማረጋገጫነት ለአንዱ ብቻ በተከለለ፣ ለሌሎች ግን በተከለከለ ምድርነት ሳይሆን ተስማምቶ ለመተዳደርና ዕድገትን ለማምጣት በሚኖረው ብቃት ነው፡፡ ለማሻሻልም ሆነ እንዳለ ለማቆየት መሠረት መሆኑ የሚገባው ይኼው ጉዳይ ነው፡፡

ብሔርተኛ አተያይና አደረጃጀት ግን አደገኛ ሥራቸውን ቀጥለውና አስፋፍተው ዛሬ እዚህ ደርሰናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገውና በታሰበው በብሔር መብትና በሌላ በኩል ደግሞ በጎሰኝነት መካከል የልዩነት ድንበሩ ጠፍቷል፡፡ ይልቁንም ጎሰኝነት፣ ጎሰኛ አድልአዊነት (የብሔር ወገንን በሥልጣንም በሌሎች ጥቅሞች ዙሪያ የማስበለጥ ሩጫ) ወረራ ይዟል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ታሪክ እንዲመች እየተለመጠ የጥላቻና የበቀል ስሜት ለመቀስቀስ መሣሪያ ሆኗል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ እየኖሩ ካሉበት ውስን አካባቢ ውጪ መምጣትን የባዕድነት መለያ አደረግን፡፡ ይህንን በማድረጋችን በሌላ በኩል ራስንም ለቀሪዎቹ ወገኖች ወይም ብሔሮች ባዕድ ማድረጋችንን ባሰፈንነው ብሔራዊ ንቃትና ግንዛቤ አረጋገጥን፡፡ ዛሬ በመላው አገሪቱ የሚታየው፣ ከዚህ በፊትም ታይቶ ግን ትምህርት ትቶ ያላለፈው ግጭት አንዱ መነሻ ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ በተለያዩ ሥፍራ የሚገኙ ውህዳን የሚባሉ ወገኖች (ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ የሚኖሩ አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ አሮሚያ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ፣ የአማራ፣ ወዘተ ተወላጆች) ባልታወቀ አንድ ጎደሎ ቀን ያልተጠበቀ ግጭት ተከስቶ መዘረፍ፣ መባረርና መገደል ይደርስብን ይሆን? ወይስ ባዕድነት ሳይሰማን መኖራችን ይቀጥል ይሆን? የሚል ጥያቄ አብሯቸው ይኖር ነበር፡፡ ዛሬ ‹‹ባዕድነት ሳይሰማን መኖራችን ይቀጥል ይሆን?›› የሚለው አማራጭ (እሱም አማራጭ ሆኖ) የተዘጋ ይመስላል፡፡ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሶማሌ ክልሎች የሚሰማው ወሬ የሚያረዳው ይህንኑ ነው፡፡

በግለሰቦች መሀል የተፈጠረ አምባጓሮና ብሔር ጠቀስ መተራረብ ሳይቀር፣ ፖለቲካዊ ሙሌት እየተሰጠው የሚራገብ በመሆኑ አደጋው ዛሬ ከምን ጊዜውም በላይ ሰፍቶና ከፍቶ፣ የገዥውን ፓርቲ ግንባርም በብሔር ለይቶ ማላጋትና ማጠዛጠዝ የጀመረ ይመስላል፡፡ ከአፍ ዕላፊ ጨዋታ ተነስተው በብሔር ወደ ተቧደነ ጥል የሚቀየሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ውዝግቦች የ‹‹ድንጋይ ዳቦ›› ዘመን ወጎች ሆነው፣ ዛሬ ይበልጥ በመሰይጠን በሌላ ‹‹ከአገሬ ውጡልኝ›› ጭፍጨፋ አከል ግፎች ተተክተዋል፡፡ ዛሬም በአንድ ግለሰብ ላይ የተሰነዘረ ዘለፋ ወይም ጥቃት በሌሎች የብሔር ባልንጀሮቹ ወይም በጠቅላላ ብሔሩ ላይ የተሰነዘረ ያህል ይቆጠራል፡፡ የአንድ ግለሰብ የአፍ ዕላፊ ጥፋትም ሆነ የወንጀል ድርጊት በአጥፊው ሰው ብሔር ወገኖችም የተፈጸመ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ እስከ ግለሰብ ፀብ የወረደ ብሔረሰባዊ ወገንተኛነት በተለያየ ሥፍራ እየደጋገመ መታየቱ፣ አሁን ደግሞ ከሌሎች ችግሮቻችን ጋር የአገር ተስቦ ሆኖ መፈንዳቱ፣ በጥበትም ሆነ በትምክህት የሚመጣ አለመግባባትን ለማሳፈር የሚችል አገራዊ ፖለቲካ አለማቋቋማችን ማስረጃ ነው፡፡

ይህ እየሰፋ፣ እየገፋና እየከፋ የመጣው የብሔሩ አባል ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ባዕድ ወይም የጨቋኝ ብሔር አባል እያሉ በልዩ ልዩ ሥልት ማጥቃት፣ በስመ መዋጮ ማለብ፣ ንብረቱን ጥሎ እንዲጠፋ ሥውር ሽብር መልቀቅ፣ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ ብሎ ማስጠንቀቅ፣ መተናኮልና መዝረፍ፣ ሀብታችን አይወጣም እያሉ የንግድ እንቅስቃሴን በኬላ ፍተሻ በዕገዳና በልዩ ቀረጥ በመልቀም ማወክ ሁሉ ትናንት ‹‹ሕጋዊ›› የነበሩ፣ የዛሬውን የለየላቸውን ነውጦች ቀፍቅፈው የወለዱ አብራኮች ናቸው፡፡ የአንድ አገር ዜጎችን ጉርብትናንና አብሮ አደግነትን የበጣጠሰው፣ መጀመርያ ወደ መኮራረፍ፣ ኋላም ወደ ዛሬው የጠላትነት አዝማሚያዎች የለወጠው የጥንት የጠዋቱ ‹‹ኃጢያት›› ዋናው ጥያቄና የአገር ችግር የዴሞክራሲ አይደለም፣ የብሔሮች ጥያቄ ነው የተባለው ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ትርምሶችና አደጋዎች ትንሽ ሙቀትና አየር ብቻ የሚፈልግ ተቀጣጣይ ነገር እንዳለ አመላክተዋል፡፡ መንግሥት ነክ ቅዋሜዎች ጭምር መንገድ ስተው መግደልና መጋደል ወይም መጨፋጨፍ ውስጥ ሊከት ከሚችል አደጋ ጋር እየኖርን መሆናችንን ይናገራሉ፡፡ እንደነ ሩዋንዳ ተከፋፍሎ የመጨፋጨፍ አደጋ እየታከከን ስለመሆኑ ታሪክ ደጋግሞ አስጠንቅቆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ የማስጠንቀቂያ ዕድል ላናገኝ እንችል ይሆናል፡፡ ተለያይቶ መጨፋጨፍ አንዴ ከተጀመረ በኋላ ‹‹የምታደርጉት ልክ አይደለም! እኔ ዴሞክራት ነኝ አልገባበትም!›› ባይነት ወይም የገላጋይነት ዕድል አይኖርም፡፡ የሁቱ ጨፍጫፊዎች ቱትሲዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ለዘብተኛ›› ሁቱዎችንም ነበር የጨፈጨፉት፡፡ ይህን መሰል አስቀያሚ አደጋ የማስቀረቱ ተግባር ይደር የማይባል፣ ሥልጣን የያዘና ያልያዘን፣ በፓርቲ የተደራጀና ያልተደራጀን የማይለይ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ አንድ አገር ነች፡፡ ሉዓላዊ አገርም ነች፡፡ ሉዓላዊነትም የአገሪቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚያቋቁመው ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ብሔራዊ የየብቻ ምድር ገዥነትን እንደ ሥርዓት አቆምን፡፡ በዚህ ምክንያት የካፒታልና የሠራተኛን ነፃ እንቅስቃሴ አወክን፡፡ የዜጎች በመረጡት የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና መኖርያ ቦታ የመመሥረት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለአደጋ እንዲጋለጥ አደረግን፡፡ ለክልላዊ አድሎአዊነት፣ ለጎጇዊ ብሔርተኝነትና ለብሔረሰባዊ ወገንተኝነት መስፋፋት የሚመች አመለካከትና አደረጃጀት አራብተንና አሠልጥነን፣ ሕገ መንግሥታዊውን የማንኛውንም ሰው የሕይወት የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት በሰውየው መገኛ ሥፍራ ብቻ እንዲወሰን ፈቀድን፡፡ በየብሔር ጎሬዎች ተሰባስቦ ለወንዝ ልጅ ማድላት የሌለበት መልካም አስተዳደር መፍጠር ተቸገርን፡፡ የመፍትሔው መነሻ ይህንን መሠረታዊ ችግር አውቆና አውግዞ አገራዊ ውይይት መጀመር ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡