Skip to main content
x
ያገለገሉ ንብረቶች አስወጋጅ የግል ኩባንያ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ
የእንደራስ ሀብት አስተዳደር ኩባንያ ኃላፊዎች ስለ ድርጅቱ የአሠራር ሥርዓት ሲያብራሩ

ያገለገሉ ንብረቶች አስወጋጅ የግል ኩባንያ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ

በተለያዩ የግልና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶችን የማስወገድ አገልግሎት የሚሰጥ እንደራስ ናሽናል አሴት ማኔጅመንት የተባለ አገር በቀል የግል ድርጅት ላለፉት ሁለት ዓመታት በንብረት ማስወገድ ተግባር ውስጥ ድርጅቶች የሚገጥማቸውን ውጣውረድ ሲያቃልል እንደቆየ አስታውቋል፡፡

ተቋሙ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች በማስተዳደርና ጨረታ በማውጣት  ለገዢዎች የማስረከብ ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡ እንደራስ ኩባንያ፣ በሦስት ዓበይት የአገልግሎት መስኮች ሲንቀሳቀስ ጥቂት ቆይቷል፡፡ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ዋጋ መገመትና ለተገቢው አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ፣ በማንኛውም መልኩ የተወረሱ፣ የተበላሹና አገልግሎት የማይሰጡ ነገር ግን ከሚገባው በላይ የተከማቹ ንብረቶችን በተለያዩ ዘዴዎች የማስወገድ ተግባር ላይ የሚያተኩር እንዲሁም ከመድን ድርጅቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እንደ ቅድመ ግምት፣ ድኅረ ግምት ከአደጋም ጊዜ በኋላ የሚደርስ ጉዳት መጠን ገምቶ ካሳ የተከፈለባቸውን ንብረቶች ማስወገድ ቀዳሚ ከሚሆኑ የሥራ ዘርፎች ውስጥ እንደሚካተቱ ተጠቅሷል፡፡

ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የኩባንያው ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ተቋሙ  ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የንብረት ግመታ አገልግሎት በመስጠት የመኖሪያ፣ የንግድና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሕንፃዎች፣ መጋዘኖችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችን፣ ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ማሽነሪዎች እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን በሽያጭና በተለያዩ የንብረት ማስወገድ ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን የኩባንያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ፈለቀ አብራርተዋል፡፡ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን በመካኒካል መሃንዲሶች አማካይነት የማይንቀሳቀሱትን ደግሞ በሲቪል መሃንዲሶች በኩል አስፈላጊውን ሙያዊ ጥናት በማካሄድ ለማስወገድ ወይም በጨረታ እንዲሸጡ እንደሚደረግ አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡

ንብረት ማስወገድ ሌሎች እንዲጠቀሙበት በሽያጭ ማስረከብንም ያካትታል ያሉት አቶ አንተነህ፣ በባንክና በኢንሹራንስ አማካይነት በአደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ንብረቶችን ኃላፊነት ወስዶ ኩባንያቸው እንደሚያስወግድም ጠቅሰዋል፡፡

ንብረቱ እንዲወገድለት ከሚፈልገው አካል ጋር በሚደረግ ውለታ አማካይነት ተቋሙ የኮሚሽን ክፍያ እየተቀበለ እንደሚሠራ ሲገለጽ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለፍርድ ቤቶችና ለኢንሹራንስ ድርጅቶች አገልግሎቱን ሲያቀርብ  መሰንበቱን አብራርተዋል፡፡

ንብረቶችን ባሉበት ሁኔታ በጨረታ ለማቅረብ አሊያም ለማስወገድ በሚል ስምምነት የሚደረግ ሲሆን፣ የንብረቱን የጨረታ ዋጋ ግምት የማውጣት ሥራና ስለንብረቱና ስለአወጋገዱ ያለውን ሒደት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በማሳወቅና በማስነገር የማስረከብ ተግባር እንደራስ ኩባንያ የሚወጣቸው ኃላፊነቶች መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

ንብረቶቹ ከመወገዳቸው በፊት ባሉበት ሁኔታ ላይ ያገለገሉበት ጊዜን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዋጋ ተመን እንደሚወጣባቸው ያብራሩት አቶ አንተነህ፣ ለአብነት ለአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት የተወገዱና 34 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ንብረቶች በዚሁ አግባብ እንደተስተናዱ አስታውሰዋል፡፡

ንብረቶች በተገቢው መንገድ ባለመወገዳቸው ወይም ባለመሸጣቸው ምክንያት በአካባቢ፣ በሰዎች ጤናና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለማቃለል እንዲህ ያለው ሥራ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

በ500 ሺሕ ብር ካፒታል ወደ ሥራ የገባው እንደራስ እሴት ማኔጅመንት፣ ከንብረት ማስወገድ በተጨማሪም በዕዳ የተከለሉና የተገኙ ንብረቶችን ማስተዳደር፣ የተወረሱ ንብረቶችን፣ የፋብሪካ መዘጋት፣ ያልተሳኩ የቢዝነስ ዕቅዶችና የተለያዩ ሰፊ የሆኑ የገበያ ጥናት አገልግሎት ይሰጣል፡፡