Skip to main content
x
ከውጤት ባሻገር ለመሪም ያልታደለው እግር ኳስ

ከውጤት ባሻገር ለመሪም ያልታደለው እግር ኳስ

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሚያደርገው የፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የሚደመጡ አስተያየቶች እግር ኳሱን የበለጠ ማጥ ውስጥ እንዳይከቱት ሥጋት አሳድሯል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሊያካሂደው የነበረው የፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ትክክለኛውን አካሄድ አልጠበቀም፣ ሆን ተብሎ ተወዳዳሪዎችን ለማገልገል የተደረገ ሩጫ አስመስሎታል ያለው ፊፋ ምርጫው በተቀመጠለት ቀነ ገደብ እንዳይካሄድ ማስጠንቀቁ ይታወቃል፡፡

ፊፋ ይህንን ቢልም የፌዴሬሽኑ አንዳንድ አመራሮች ግን የፊፋ ማስጠንቀቂያ አያሳስብም እያሉ ነው፡፡ ኃላፊነቱንም እንወስዳለን፣ ምርጫው በተቀመጠለት ፕሮግራም መሠረት መካሄድ አለበት ብለው ሲናገሩም እየተደመጡ ይገኛል፡፡

ለፊፋ ማስጠንቀቂያ መነሻ የሆኑት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው፣ የዓለም አቀፉን ተቋም ማስጠንቀቂያ ‹‹ቸል ልንለው አይገባም፡ ማስጠንቀቂያው ከፊፋ የመጣ አይደለም፡፡ ስለሆነም ምርጫውን ብናካሂድ ምንም የሚመጣ ነገር የለም፤›› በማለት ከፌዴሬሽኑ አንዳንድ አመራሮች ጀምሮ ሌሎችም ሰዎች ሲናገሩ እንዳደመጡ ተናግረው፣ ጉዳዩ የአገርና የሕዝብ እስከሆነ ድረስ ሰከን ብሎ መመልከቱ የተሻለ እንደሚሆን ነው የሚያስረዱት፡፡

ምርጫው መደረግ ‹‹አለበት? የለበትም?›› በሚል በሁለት ጽንፍ ከተከፈለው የፌዴሬሽን አመራር አስተያየት በመነሳት የሚነገሩ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፣ ምርጫውን ተከትሎ እየተደመጠ ያለው ነገር ከማስገረምም አልፎ እንደሚያሳዝናቸው ይናገራሉ፡፡

ምክንያቱን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በአንድም ሆነ በሌላ እግር ኳሱ በተለይ በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት ደረጃ ለዚህ ግርግር መነሻ ሊሆን አይገባም፡፡ እንደ አለመታደል ካልሆነ በስተቀር፣ ለዚህ እግር ኳስ ውድቀት መፍትሔ እንሆናለን ብለው የሚያምኑ አካላት ከተገኙ በውዝግብ ሳይሆን ሥርዓቱን በተከተለ አግባብ ኃላፊነቱ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በአሁኑ ወቅት እየተደመጠ ያለው ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የሚደመጥ እንዳልሆነ፣ ችግሩንም በሰከነ አግባብ ለመመልከት ዝግጅት የማይስተዋልበት በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ  ሥጋታቸውን ይጠቁማሉ፡፡