Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ከአንድ የውጭ አገር የዕርዳታ ድርጅት ኃላፊ ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል፡፡
 • እኔም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
 • ዛሬ የመጣነው ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ በምናደርግበት ፕሮጀክት ላይ ለመነጋገር ነው፡፡
 • ሁሌም ስለምታደርጉልን ድጋፍ እናመሰግናለን፡፡
 • የዛሬው አመጣጤ ስለዛ ፕሮጀክት ለማውራት ነው፡፡
 • ስለየትኛው ፕሮጀክት?
 • ለሚኒስትር መሥሪያ ቤትዎት ውስጥ አስገነባዋለሁ ስላሉት ፕሮጀክት ነዋ፡፡
 • የቱ ፕሮጀክት ነበር?
 • የላይብረሪው ፕሮጀክት፡፡
 • በእውነት በመጀመርያ ለዚህ ፕሮጀክት የምታደርጉትን ድጋፍ በመንግሥትና በሕዝብ ስም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
 • ሁሌም ከጎናችሁ ነን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በእናንተ ድጋፍ ፕሮጀክቱን በአፋጣኝ ነው ዕውን የምናደርገው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ትንሽ ስለፕሮጀክቱ ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል፡፡
 • የመንግሥታችን ዋና ዓላማ ሕዝቡን ከሁለት ነገር ማላቀቅ ነው፡፡
 • ከምንና ከምን?
 • ከድህነትና ከኋላ ቀርነት፡፡
 • ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እነዚህን ሁለት ጠላቶቻችንን የምናጠፋው ደግሞ የሕዝቡን ዕውቀት በማጎልበት ነው፡፡
 • እስማማለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በመሆኑም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት ይኼን ወሳኝ ፕሮጀክት ከመሥሪያ ቤታችን ለመጀመር ወስነናል፡፡
 • የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው የሚለውን አባባል አስታወሱኝ፡፡
 • እኛ እንኳን ይኼንን ፕሮጀክት ለመሥራት ያሰብነው በራሳችን ነበር፡፡ ሆኖም አንዳንድ እንቅፋቶች እያጋጠሙን ነው፡፡
 • ምን ዓይነት እንቅፋት?
 • የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እሱ ችግር በጣም አንገብጋቢ ይመስለኛል፡፡
 • እኛም አንገብጋቢነቱን ተረድተን የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡
 • ሰሞኑን የተደረገው የብር የመግዛት አቅም መቀነስም ለዛው ይመስለኛል፡፡
 • ለዚህ ነው እኛም የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ያለነው፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ይኼን ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ እኛ ለመሸፈን ወስነናል፡፡
 • በእውነት በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡
 • ለፕሮጀክቱ ግን ድጋፍ የምናደርገው በቁስ ነው፡፡
 • በቁስ ስትል?
 • ማለቴ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ግንባታ እንፈጽማለን፡፡
 • እሺ፡፡
 • ለላይብረሪው የሚያስፈልጉትን መጻሕፍት እናመጣለን፡፡
 • እሺ፡፡
 • በተመሳሳይም ኮምፒዩተሮች እናስመጣለን፣ ለላይብረሪው የሚያስፈልገውን የኢንተርኔት ወጪ እንሸፍናለን፡፡
 • በቃ?
 • ክቡር ሚኒስትር ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን በሙሉ እናሟላለን ስልዎት?
 • እየቀለድክ ነው?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር? አጠፋሁ እንዴ?
 • ቁም ነገር መስሎኝ የያዝነው፡፡
 • እኔም እኮ ቁምነገር ነው የማወራዎት፡፡
 • እኔ በጥሬው የምትሰጡን መስሎኝ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ጥሬ ሥጋ መልመድ እኮ አቅቶኛል፡፡
 • እኔ የማወራው ስለሌላኛው ጥሬ ነው?
 • ስለየትኛው ጥሬ?
 • ስለ ዶላር!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር ሰሙ አይደል?
 • ምኑን?
 • ፌስቡክ ላይ የሚወራውን አልሰሙም እንዴ?
 • እኔ እኮ ፌስቡክን ስም አውጥቼለታለሁ፡፡
 • ምን ብለው?
 • ፌክቡክ፡፡
 • ለምን?
 • እንዴ ፌስቡክ እኮ የአደገኛ ቦዘኔዎች መፈንጫ ሠፈር ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ እዛ የሚወራው ወሬ ፌክ ነው፣ ሰዎቹም ፌክ ናቸው፡፡
 • መረጃ ታዲያ ከየት ነው የሚያገኙት ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱን ለእኛ ተወው፡፡
 • ከየት ነው የሚያገኙት?
 • ከተለያዩ የመረጃና ደኅንነት ምንጮቻችን አሊያም ከታወቁ ሚዲያዎች መረጃ እናገኛለን፡፡
 • ስለዚህ ፌስቡክ አይሆንም እያሉ ነው?
 • ነገርኩህ እኮ እሱ ፌክቡክ ነው፡፡
 • ለማንኛውም ከፌስቡክ ውጪ ከተማ ውስጥ እየተወራ ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • በጣም በጣም አስደንጋጭ ዜና ተከስቷል፡፡
 • የምን አስደንጋጭ ዜና?
 • ወዳጃችን እኮ ተይዘዋል እየተባለ ነው፡፡
 • ማን?
 • እኛ ትልቁ ባለሀብት፡፡
 • እኔ ሳላውቅ ማን አባቱ ነው የሚነካቸው?
 • ቢሰሙስ ምን ያመጣሉ?
 • እዚህች አገር ላይ ምን እየተሠራ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የታሰሩት እዚህ አገር ሳይሆን ሌላ አገር ነው፡፡
 • እስቲ ማን ነሽ ውኃ ስጪኝ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ልቤ በጣም በኃይል መታ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ቀረብኝ ማለት ነው እኮ፡፡
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ጡረታዬ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ኢንቨስተር ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጉድ ሠራችሁኝ አይደል?
 • ሰሙ አይደል ወሬውን?
 • ይኼ እኮ ለእኔ መርዶ ነው፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሜዳ ላይ ነው እኮ ያስቀራችሁኝ፡፡
 • እንዴት ሆኖ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ ቼክአፔ እንደደረሰ ታውቃለህ?
 • አውቃለሁ፡፡
 • ውጭ የሚማሩት ልጆች ክፍያም ደርሷል፡፡
 • ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የውጭ ምንዛሪ እንኳን ለእኔ ለመንግሥት ራሱ የራስ ምታት ሆኗል፡፡
 • እውነት ነው፡፡
 • ታዲያ ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው?
 • የደወልኩት እኮ አንድ መላ ልነግርዎት ነው፡፡
 • የምን መላ ነው? አንተ ነህ ለዚህ ሁሉ ያበቃኸኝ፡፡
 • ለምን አይሰሙኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድነው የምሰማው?
 • ይኼ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
 • የምን አጋጣሚ?
 • ከሰማይ መና እንደወረደልን ቁጠሩት፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ሁላችንም የድርሻችንን እንከፋፈላለና፡፡
 • እንደዛ ይቻላል እንዴ?
 • ማን ይጠይቀናል?
 • እ…
 • ስለዚህ አሁን ጊዜው ነው፡፡
 • የምኑ?
 • የምንጠራበት ነዋ፡፡
 • ምን ተብለን?
 • እውነተኛ ሚሊየነር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአማካሪያቸው ደወሉለት]

 • አንተ ቅድም አይደለም እንዴ ና ያልኩህ?
 • ሥራ ይዤ ነው፡፡
 • ከእኔ በላይ ሥራ አለ እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ብዙ ሥራ ያለብኝ ሰው ነኝ፡፡
 • በጣም ቀልደኛ ሆነሃል በል ቶሎ ና!

[አማካሪያቸው ቢሯቸው ገባ]

 • ለምንድን ነው የፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቷ ላይ ያሉትን ነገሮች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
 • ለዚህ ነው የጠሩኝ?
 • አዎ፣ ችግር አለ?
 • ለዚህ ፍሬከርስኪ ወሬ እንዴት ይጠሩኛል?
 • ምንድነው ያልከው?
 • ያልኩትንማ ሰምተውኛል፡፡
 • በጣም ተናንቀናል መሰለኝ፡፡
 • ሥራ ባያስፈቱኝ ጥሩ ነው፡፡
 • ሥራ የምሰጥህ እኔ መስሎኝ? ከመቼ ጀምሮ ነው እንደዚህ የልብ ልብ የተሰማህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ላይ ከመደንፋት ሥራዎን ቢሠሩ አይሻልም?
 • የምን ሥራ?
 • ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነዋ፡፡
 • እሱን ማን ንገረኝ አለህ?
 • ለነገሩ ሥራውን የት ያውቁታል?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ትክክለኛ ሥራውን የምንሠራው እኛ፣ እርስዎ እኮ የእኛን ሪፖርት ነው በየቦታው የሚያቀርቡት፡፡
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
 • የፖለቲካ ሹመኛ ነዎት እያልኩዎት ነው፡፡
 • በጣም ተናንቀናል፡፡
 • እኛ ባንኖር እኮ መሥሪያ ቤቱ ቀጥ ነው የሚለው፡፡
 • እንዴት ነው ልብህ ያበጠው?
 • በፊት የነበሩበት መሥሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ ውድቀት ውስጥ ገብቶ አይደል እንዴ ወደዚህ የመጡት?
 • ሥነ ሥርዓት ብትይዝ ይሻላል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ እውነቱን ነው የነገርኩዎት፡፡
 • የናቅከኝ አይመስልህም?
 • የናቅኩዎት እኔ አይደለሁም፡፡
 • ታዲያ ማን ነው?
 • ሕዝቡ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደወለላቸው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ደህና ነኝ፡፡
 • ምንድነው የምሰማው?
 • ምን ሰማችሁ ደግሞ?
 • በጣም ግራ እየተጋባን እኮ ነው፡፡
 • በምኑ ነው ግራ የተጋባችሁት?
 • ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ማስፈን አልተቻለም ማለት ነው?
 • ይኼ የፀረ ልማት ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
 • ኧረ ይኼን የድሮ ሙዚቃ አይተውትም እንዴ?
 • ለምንድነው መንግሥት የሚናገረውን እንደ ውሸት የምትወስዱት?
 • እውነት አውርቶ ስለማያውቅ ነዋ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም በዓለማችን ያሉ ባለሥልጣናት ይዋሻሉ፡፡
 • እንደዚህ አትሳሳት፣ እንደውም መንግሥታችን ብቸኛው እውነት ተናጋሪ መንግሥት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ግን ተስፋ አለን?
 • የምን ተስፋ?
 • ይኸው አንዱ ክልል ከሌላው ጋር እየተጋጨ በርካቶች እየሞቱ አይደል እንዴ?
 • ችግሮቻችንን ለመፍታት እየሠራን ነው፡፡
 • አገሪቷ የምትበታተን እኮ ነው የምትመስለው?
 • ይኼ የጠላቶቻችን ምኞት ነው፡፡
 • እኔ ለአገሬ ያለኝ ፍቅር ጥልቅ ነው፡፡
 • የአገር ፍቅር ስትል?
 • የተባለውን አልሰሙም እንዴ?
 • ምን ተባለ?
 • ኢትዮጵያዊነት እንደ ሃሺሽ ሱስ ያስይዛል የተባለውን ነዋ፡፡
 • እንደ ሃሺሽ?
 • ለነገሩ እርስዎን ሱስ ያስያዝዎትን አውቀዋለሁ፡፡
 • ምንድነው?
 • ሙስና!