Skip to main content
x
በአዲስ አበባ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ

በአዲስ አበባ የተንሰራፋውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት በ13 መሥሪያ ቤቶች ላይ ባካሄደው ጥናት፣ 211 ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳቦችን አቀረበ፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥናት ከተካሄደባቸው ተቋማት መካከል የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ቢሮ፣ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ይገኙበታል፡፡

በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና በሥሩ በሚገኝ መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 16 የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በ1997 ዓ.ም. በተነሳው መስመር ካርታ ቤታቸው ወይም ይዞታቸው የማይታይ ነባር አርሶ አደሮችን ያለማስተናገድ፣ የአያት ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች የሊዝ ውልና የካርታ ጥያቄ አለመፈታት፣ በሊዝ ሕጉ መሠረት ለመጨረሻ ጊዜ የግንባታ ማጠናቀቂያና ማሻሻያ የወሰዱ አልሚዎች ግንባታ አለማጠናቀቃቸው፣ ግንባታቸው ከ30 በመቶ በታች በመሆኑ የሊዝ ውል ለተቋረጠባቸው የመኖርያ ይዞታዎች መፍትሔ አለመስጠት፣ ለረዥም ዓመታት ታጥረው ሳይለሙ የተቀመጡ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ አለመውሰድ፣ ለኤምባሲዎችና ለአፍሪካ ባህል ማዕከል ግንባታ ቦታ የተሰጣቸው ግንባታ ሳያካሂዱ ለዓመታት አጥረው ማስቀመጣቸው፣ በተመሳሳይ የመንግሥት ተቋማት ቦታ ወስደው ሳያለሙ አጥረው መያዛቸው ከተነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ከውሳኔ ሐሳቦቹ መካከልም ከ1997 ዓ.ም. በፊት ቦታው ላይ ስለመኖራቸው የሚያስረዳ ሰነድ ካቀረቡና ወረዳውም ካረጋገጠ አርሶ አደሮቹ መብት እንዲኖራቸው ጠይቋል፡፡

የአያት ሪል ስቴት ጉዳይን በተመለከተ ለካቢኔው የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ፣ ከ30 በመቶ በታች የገነቡት ደግሞ የሊዝ ደንቡ ሲፀድቅ በሚዘጋጀው መመርያ ውስጥ ጉዳዩን ለመፍታት ማሻሻያ ማድረግ፣ በውሉ መሠረት ግንባታ ያላካሄዱ ተቋማትን ቦታ ወደ መሬት ባንክ ማስገባት፣ ከኤምባሲዎች ጋር በመነጋገር በተቀመጠው ጊዜ ማልማት የማይችሉ ከሆነ መሬቱን መንግሥት ተረክቦ ኤምባሲዎቹ ለማልማት ዝግጁ ሲሆኑ ሌላ ቦታ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣ የመጨረሻ ዕድል የተሰጣቸው አልሚዎች ዕድላቸውን ካልተጠቀሙ ካርታቸውን ማምከን ከቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በኢንዱስትሪ ቢሮ ላይ በተካሄደው ጥናት ሦስት ችግሮች ነጥረው ወጥተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ዞኖች የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ ወደ መካከለኛ ለተሸጋገሩ ባለሀብቶች የኤክስቴንሽን አገልግሎት ያለመጠትና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የተሰጣቸውን መሬት ለሦስተኛ ወገን የማስተላለፍ፣ አጥሮ ማስቀመጥና ማከራየት ናቸው፡፡

ቢሮው ለእነዚህ ችግሮች ያቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ በተለይ 264 የሚሆኑ መካከለኛ ኢንቨስተሮች የሚገኙበት የአቃቂ ቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን መንገድ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ መስመር እንዲዘረጋ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ቢሮው ከዚህ በተጨማሪም በኢንዱስትሪ መንደሮች ለሚገኙ 800 የሚሆኑ ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት ለተሸጋገሩ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርና ብድር እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡

በቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በ40/60 እና በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም በድምሩ 16 ችግሮች ተለይተው ወጥተዋል፡፡ በቤቶች ልማት ቢሮ ከተነሱ ችግሮች መካከል ለአንድ ቤት ሁለት ምዝገባ ያደረጉ፣ ለተለያዩ ቤቶች ሁለት ምዝገባ ያደረጉ መኖራቸው፣ ከመልሶ ማልማት ለሚነሱ የቀበሌ ቤቶች በአፋጣኝ ያለማቅረብ፣ መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች መኖራቸውና ለማስተላለፍ አስቸጋሪ መሆኑ፣ ውል በተገባውና በተላለፈ ቤት የካሬ ሜትር ልዩነት መኖሩ፣ የልማት ተነሺ ሆነው ለሁለት ዓመት ያልተስተናገዱ መኖራቸው ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡

የ40/60 ቤቶችን በተመለከተ በተላለፉ ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራ አለማለቅ፣ የውኃ አቅርባት አለመኖር፣ ያልተከፈለ የአማካሪና የተቋራጭ የቆየ ክፍያ መኖር፣ በግንባታ ሳይቶች ያልተነሱ ዕቃዎች መኖር፣ ለግንባታ እንቅፋት መሆናቸውና ከዲዛይን ውጭ የተመረቱና የጥራት ችግር ያሉባቸው ምርቶች መኖር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም እንዲሁም የማጠናቀቂያ ሥራ መጓተት፣ ከመኖሪያ ቤቶች እኩል የማኅበራዊ መገልገያ ግንባታዎችን ያለማካሄድ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ያለመሟላት፣ የክፍያ መዘግየት፣ ለተጠቃሚዎች በተላለፉ ባለስምንት ወለል ሕንፃዎች አሳንሰር አለመገጠሙ ተጠቃሽ ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

ከቀረቡ መፍትሔዎች መካከል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በክላስተር ተደራጅተው እንዲሠሩ ማድረግ፣ ወጥነት ያለው የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት፣ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ፣ ከመሠረተ ልማት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ በጋራ መሥራት፣ ተረፈ ምርቶችን በወቅቱ ማንሳት፣ አሳንሰርና የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር በማዕከል ግዥ እንዲፈጸም ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ ሐሙስ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ይህንን ጥናት ለከተማው ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፣ በከተማ አስተዳደሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስፋትና ጥልቀት ያለበት ደረጃ ሲታይ አሁንም በተሟላ ደረጃ ችግሩን መፍታት አለመቻል የሥርዓቱ በሽታ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በከተማው ውስጥ ከፍተኛ ምሬትና እንግልት እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ አቶ ይስሃቅ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ሲሉም የችግሩን ፅኑነት ጠቁመዋል፡፡