Skip to main content
x
ያልተቋጨው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባዔ
ከግራ ወደ ቀኝ አቶ አበበ ገላጋይ፣ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ አቶ ጁነዲን ባሻ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬና አቶ አሊሚራህ መሐመድ

ያልተቋጨው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባዔ

  • ምርጫው ከ45 ቀን በኋላ በአፋር ይከናወናል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሥረኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ጥላውን ያጠላው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኀበር (ፊፋ) ማስጠንቀቂያ፣ ለወትሮውም ግራ የተጋባውን ጉባዔተኛ ይብሱኑ ሲያዘበራርቀው ታይቷል፡፡ ጉባዔውን ለመታዘብ የመጡት የፊፋው ተወካይ ራሳቸው ግራ ተጋብተው የአስመራጭ ኮሚቴውን ማንነት ለማወቅ ሲጠይቁ ታይተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት (ጥቅምት 30 - ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም.) በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል የተካሄደው ይኼው ጉባዔ፣ ከመነሻው አዲስ ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማካሄድ ላይ ያነጣጠረ የነበረ ቢሆንም፣ ፊፋ የምርጫውን ሒደትና ሥርዓት ከመነሻው በመኮነኑ የተነሳ በጉባዔው አብላጫ ድምፅ እንዲራዘም ሆኗል፡፡ ይህም ሆኖ ጉባዔው የተካሄደበት ሥነ ሥርዓት ቅጥ ያጣ ከመሆኑም በላይ፣ አንዱ ሌላውን በሰከነና በሠለጠነ አግባብ የማያዳምጥበት የክልል ፖለቲካ የተንጸባረቀበት፣ በምክንያትና በአቋም ሳይሆን በሰሞነኛ ፖለቲካ ጎራ የሚዘናጠሉ ሰዎች በስፖርቱ መድረክም ሲካካቡና ሲጓሸሙ ተስተውለዋል፡፡

በመጀመርያው ቀን የጉባዔው ውሎ ምርጫው ይራዘም የሚለውን ሐሳብ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ፌዴሬሽኖች ሲደግፉ፣ የአዲስ አበባና የደቡብ ክልሎች ምርጫው ይካሄድ ሲሉ ክርክር ገጥመው እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ቆይተው ነበር፡፡ በመጨረሻም በድምፅ ብልጫ እንዲራዘም ተወስኗል፡፡ የአፋር ክልል ግን የጉባዔ አዘጋጅነቱን  በመቀማቱ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

የተሳታፊዎቹ ወገንተኝነት ለስፖርቱና ሊወክሉት ክልል ከመሆን ይልቅ አንዱ ጉባዔተኛ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹እከክልኝ፣ ልከክልህ ዓይነት አሰላለፍ›› የታየበት ይህ ጉባዔ፣ መጨረሻው ሳያምር ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ዋና ከተማ፣ ሰመራ የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ለማካሄድ በመወሰን መጠናቀቁ ሳይነገር ተጠናቋል፡፡

በጉባዔው ለሥራ አስፈጻሚነት 11 ክልሎች 11 ተወካዮች መጥተው አንዱ ብቻ ወድቆ ሌሎቹ የሚያልፉበት አሠራር ‹‹ውክልና›› እንጂ ምርጫ ስላልሆነ፣ ውድድር ያለበት እንዲሆን ተወካዮቹ በዛ ይበሉና በፉክክር ይመረጡ በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ቢደረግም የተቋጨ ነገር የለም፡፡

ለዘንድሮው ምርጫ እዚህ ደረጃ መድረስ በምክንያትነት ሲጠቀስ የቆየውና ፊፋም ፌዴሬሽኑን አበክሮ የጠየቀው የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫና ማንነት በዚህ ጉባዔ መመረጥና መታወቅ ሲገባው ምንም ሳይባል ጉባዔው ተበትኗል፡፡

በጉባዔው አካሄድ ግራ የተጋቡ ብዙዎቹ የጉባዔ አባላት ለምርጫው መራዘም አንዱና ዋነኛው ምክንያት የአስመራጭ ኮሚቴ ወይም አካላትን መሰየም እንደነበር ያምናሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉባዔውን የሚመራው በማን እንደሆነ ለማወቅ በሚያዳግት ሥነ ሥርዓት፣ በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑን ሲያስተዳደሩ የቆዩት አመራሮች ጉዳይ የጉባዔው መቋጫ ሳይታወጅና አቅጣጫ ሳያስቀምጥ በእንዲህ መልኩ መጠናቀቁ አስገርሟቸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በተለይ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ያሳሰባቸው እነዚሁ ጉባዔተኞች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ‹‹ወደደም ጠላ›› ምርጫው ከሚደረግበት የአፋሩ ጉባዔ በፊት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሊጠራ የሚገደድበት ሁኔታ መኖሩን ጭምር ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ድምዳሜ ግራ ተጋብተው የታዩት የፊፋ ተወካይ በተቀመጡበት የስብሰባ አዳራሽ ለ20 ደቂቃ ላላነሰ ጊዜ በመቀመጥ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና ከሌሎችም ጥቂት አመራሮች ጋር ሲወያዩ ቆይተው በመጨረሻም ተሰውረዋል፡፡ ጉባዔው በምን አግባብ እንደተጠናቀቀ፣ የአስመራጭ ኮሚቴው ምርጫና በአፋር ሰመራ ስለሚካሄደው የምርጫ ሒደት አስመልክቶ፣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ጀምሮ ይመለከተኛል ያለ አካል አሰተያየት ለመሰጠት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ሁሉም ‹‹በቃ›› ከማለት ያለፈ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡