Skip to main content
x

ወደ ኋላ ሳያዩ ወደ ፊት መሄድ ይቻላል ወይ?

በይነገር ጌታቸው

ይህች አገር ምናባዊ ሆናለች፡፡ በደራሲው ላይ እንደሸፈተ ገጸ ባህሪ መነሻውን እንጂ መድረሻውን ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ አበቃላት ተብሎ ደረት ሲደቃ ድንገት ትባንናለች፡፡ ደግሞም ደህና ሆነች ሲባል ተመልሳ ታስጨንቃለች፡፡ በተቃዋሚው ጎራ ለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ተጠያቂ የሚደረገው በብሔር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም፣ በእነዚህ ወገኖች በሚወደስ ሌላ መድረክ ላይ ሲሞገስ እንሰማለን፡፡ በዚህ ተቃርኖ መሀል ዥዋዥዌ ተጫውተን ስንወርድ ሌላ ‹‹ፔንዱለም›› ይጠብቀናል፡፡ በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ለምትመሠረተው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ቻርተር እያዘጋጀን ነው የሚሉ የወጭ ኃይሎች፣ አዲስ አበባን የከበባትን የሕዝብ ተቃውሞ እኛ አናውቀውም ይሉናል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ዥዋዥዌ ውስጥ ሆነን ከሌላ አስደንጋጭ እውነት ጋር እንፋጠጣለን፡፡ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ስለመፈጸሙ እንሰማለን፡፡ ሰው በድንጋይ ሲወገር እናያለን፡፡ ከዚህ የሐዘን ድባብ እነዚያው ሐዘን ቁጭ እንበል ያሉን ሰዎች ጮቤ መርገጥ ያስበረግገናል፡፡ ‹አገሬ ስቃይሽ ስንት ነው?› እያሉ ሙሾ እያወረዱ የሚያስለቅሱን ሰዎች በቅፅበት ‹እልል በይ አገሬ› ይሉናል፡፡

ሰሞነኛው የኦሕዴድና የብአዴን ፓርቲዎች የባህር ዳር ውይይትም ከደስታና ከሐዘን መሀል የበቀለ ግብታዊ ነገር ይመስላል፡፡ በአንዳንዶች አገላለጽ ለአንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መሠረት ለመጣል ጉዞ የተጀመረበትን የኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዘንግቶ የታወጀ ሌላ የአንድነት ቀን ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በከፊል አመክኗዊ ነው፡፡ ነገር ግን የባህር ዳሩን ድግስ ስህተት ብለን ለመደምደም የሚያስችለን አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ስለአንድነትና ፍቅር ለመስበክና ለመወያየት፣ ስለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ለመምከር የትኛውም ቀን ክፍት ሊሆን ይገባል፡፡ በእኔ ግምት ሰሞነኛው የሁለቱ ፓርቲዎች ወግ ሊዳኝ የሚገባው በፖለቲካ ሚዛን ነው፡፡ በዚህ መነሻም የባህር ዳሩን ውይይት ለአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታና መፃኢ ዕድል የሚኖረውን አንድምታ ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡

የዶክተሩ ትንቢት

መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በ2008 ዓ.ም. ለንባብ ባበቁት ‹‹የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ህልሞች›› በተሰኘ መጽሐፋቸው ለዛሬው ዘመን የፖለቲካ መቆርቆዝ የሦስቱ ኃይሎች ግብግብ ተጠያቂ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ስለሦስቱ ኃይሎች አሠላለፍ ሲተርኩም  የአማራ ፖለቲካ ልሂቃን አኃዳዊ ሥርዓት ላይ ሙጭጭ ማለታቸው፣ የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃን ሥልጣን በሞኖፖል ይዘው ለመቀጠል መሻታቸውና የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን የማፈንገጥ ፍላጎት ማሳየትን ያብራራሉ፡፡ ለፖለቲከኛውና ለተመራማሪው መረራ የእነዚህ ኃይሎች መንገድ ለየቅል መሆን አገሪቷን የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ከቷታል፡፡ የወደፊት መንገዷንም አሥጊ አድርጎታል፡፡ እንዲህ ያለው የአንጋፋው ፖለቲከኛ ትንታኔ ግን በጨለምተኝነት አይደመደምም፡፡ ይልቁንም አጭር መፍትሔ ይጠቁማል፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፖለቲካ ቁልቁለት ጉዞ ለማስተካከል ሦስቱ ኃይሎች ህልማቸውን መግራት አለባቸው፡፡ ህልማቸው ሲገራ የአማራ ፖለቲከኞች ከአኃዳዊና የመጠቅለል አስተሳሰባቸው ይላቀቃሉ፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከኦሮሞ ይቅደምና የመገንጠል አስተሳሰባቸው ይፋታሉ፡፡ የትግራይ ልሂቃንም ፍታሐዊና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመተግባር ቁርጠኛ ይሆናሉ፡፡

የመረራ ተምኔታዊት ኢትዮጵያ በእሱ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ የምትገኝ እውነት አይደለችም፡፡ ስለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚያውቁት ዶናልድ ሌቪን (ፕ/ር) ‹‹Greater Ethiopia Reconsidered›› በተባለ አጭር ጽሑፋቸው ከላይ የተጠቀሱት የፖለቲካ ኃይሎች ፉክክር ሁሌም አገሪቷን ዕረፍት እንደነሳት ነው ይላሉ፡፡ ሀብታሙ አለባቸውም ጆን ማርካኪስን ጠቅሶ የድኅረ ምኒሊኳ ኢትዮጵያ ቁልፍ የፖለቲካ ችግር አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሰሜኑ የፖለቲካ ኃይሎች፣ በቁጥር በሚበልጧቸው የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ላይ የወሰዱት ብልጫ የፈጠረው ነው ይላል፡፡ የሌቪንም ሆነ የማርካኪስ መፍትሔም ከመረራ የራቀ አይደለም፡፡ የህልም መገራት ለፖለቲካዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ላይ ከሞላ ጎደል ይስማማሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በባህር ዳር የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስም በቁሙ ሲመለከቱት ቢያንስ የሁለቱ ህልሞችን መገራት የማብሰር አቅም አለው፡፡ የአማራ ፖለቲካ ልሂቃን ለዘመናት የግላቸው አድርገው የኖሩት የአንድነት ቅስቀሳ ላይ፣ አሁን አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በጉልህ አለሁበት ማለት ጀምሯል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ለዘመናት አኃዳዊ ሥርዓትንና አንድነት ሲሰበክ የኖረው የአማራ ፖለቲካ ልሂቅ፣ ስለአማራ ብሔርተኝነት አስፈላጊነት ሙግት ይዟል፡፡ እዚህ ላይ ሦስተኛውም ህልም እየተገራ ስለመሆኑ ቢያንስ በቁም ተመልክቶ መናገር ይቻላል፡፡ የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃን ሥልጣንን በሞኖፖሊ ይዞ አለቅም ማለት፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የበፊቱን ያህል ጉልበት ያለው አይደለም፡፡ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሠላላፍ ለሚመለከት ገለልተኛ ሰውም የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃን ሠፈራ በኢሕአዴግ ውስጥ እየደበዘዘ መሄዱን መታዘብ ይችላል፡፡ ይህን መሰሉም ፈለግ  የሦስቱ የፖለቲካ ኃይሎች ህልም በግርድፉም ቢሆን አየተገራ ስለመሆኑ የሚያውጅ ነው ፡፡

ከሰሞኑን በበርካታ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ተከታዮች ሙገሳ የተቸረው የኦሕዴድና የብአዴን የሰላም ኮንፈረንስም በቁሙ ከተመለከትነው ለተምኔታዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ ወሳኝ ሚናን የሚጫወት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ገራገራዊ ድምዳሜ ግን የባህር ዳሩን የሰላም ኮንፈረንስ በቁሙ ለተመለከተው እንጂ፣ በፖለቲካ ሚዛን ላስቀመጠው ሰው በርካታ ጥያቄ የሚያስነሳበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥያቄም ፖለቲካዊ የአንድነት መንፈሱን ሥር ለማስያዝ እስከሆነ ድረስ ከየትኛውም ወገን ቢመጣ የሚያስቆጣም ሊሆን አይገባውም፡፡ በዚህ መነሻም ልዩነትን ወደ ጎን ብለን አንድነትን እንዘምር ላሉንና የተቀደሰ ሐሳቡን ላመጡት የፖለቲካ ልሂቃን፣ ቢያንስ እነዚህን ጥቂት ጥያቄዎች ልናነሳላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመርያው የውል ታሪክ ላይ መግባባት ሳንችል የውል የፖለቲካ ሥነ ልቦና ልናመጣ እንችላለን ወይ? ሁለተኛ ለብሔር ግንባታው ወሳኝ የሆነውንና በየአካባቢው ያለውን ወቅታዊ ችግር የፈጠረውን የፈጣን ልማት ጥያቄ በተጨባጭ የፖሊሲ ለውጥ ለማስተካከል ሳይሹ አንድነትን ማምጣት ይችላል ወይ? ሦስተኛ ማኅበራዊ እሴት መኮትኮቻ ተቋማት (Socialization Agents) ስለአንድነት ምን ያህል የሚሰብኩ ናቸው? አራተኛ እንደኛ ባለች አገር ለብሔር ግንባታ የመንግሥት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁለቱ ፓርቲዎች ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ ናቸው? አባላቶቻቸውስ ምን ያህል ለዚህ የአንድነት ፕሮጀክት ዝግጁ ሆነዋል? (በቅርቡ በተከሰቱ የኦሮሚያ ክልል ግጭቶች ውስጥ ይህን መሰል አዝማሚያ መስተዋሉን መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ አረገግጠዋል) የመጨረሻው ጉዳይ የሚሆነው ይህ የሁለቱ ፓርቲዎች ሰሞነኛ የአንድ ነን ዝማሬ ከሚወክሉት ሕዝብ የተቀዳ መሠረታዊ ጉዳይ? ወይስ የፓርቲዎች የፖለቲካ ቁማር መንገድ ነው? 

አንድነት እንዴት?

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በባህር ዳር የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ‹ወደ ኋላ እያየን ወደፊት ልንራመድ አንችልም› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተመሳሳይ አንድምታ ያለውን ሐሳብ  ሰንዝረዋል፡፡ የእነዚህ ሁለት ሐሳቦች መመሳሰልም ድርጅታቸው ኦሕዴድ ከብአዴን ጋር ሊያቀራርበው የሚችለውን መንገድ የቀየሰባቸው ተደርገው የሚወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የሁለቱ የወቅቱ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን ሐሳብ አንድነት ለመዘመር እስከተነሳ ድረስ ሁላችንንም እንዲያግባባን  በሌላ ሐሳብ ልንሞግተው እንችላለን፡፡ ይህ ዓይነቱ ሙግትም ወደ ኋላ ሳያዩና ባለፈው ነገር ላይ ሳይሰማሙ ስለነገው አብሮነት ማውራት ይችላል ወይ?  በሚል የታጀበ ነው፡፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራንን ባነጋገሩበት ወቅት የሚከተለውን ሐሳብ ሰንዝረው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክና በአገሪቱ ታሪክ መካከል መራራቅ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ መሰሉ መለያየትም በሐውልት ሳይቀር የታጀበ በመሆኑ የወደፊቱ አንድነታችንን አደጋ ውስጥ ይጥለዋል (ሐሳቡ ቃል በቃል የተወሰደ አይደለም)፡፡ የዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር አባት የሚባሉት ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) አስተያየት ከትናንት ታሪክ ሙጥኝ የማለት ፍላጎት የወለደው ሳይሆን፣ በተጨበጭ ለነገው የአገሪቱ አንድነት በኋላ ታሪካችን ላይ ከሞላ ጎደል መስማት መቻል እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህን መሰሉን ታሪክ የማዕዘን ድንጋይ ያደረገ የነገ አንድነት ተስፋም ከየትኛውም ነገር በላይ ለአገራችን የብሔርተኝነት ሐሳብ ወሳኝ ቦታን የሚይዝ መሆኑን ማስረገጥ ይገባል፡፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚካሄድ የአገራዊ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ የወል ታሪክን በማጉላት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡፡ እንዲህ ያለው የወል ታሪክ ፈጠራም ዜጎች ስለአገራቸው ያላቸውን አስተሳሰብ ለማቀራረብ የጎላ አሻራ ያኖራል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዓለማችን ላይ ላለ የአገራዊ አንድነት ሒደት ፈረንሣይ ከየትኛውም አገር በላቀ በተመራማሪዎች አብነት ሆና ትቀርባች፡፡ ፈረንሣይ የፈረንሣይ ብሔርተኝነትን ለማስፈን የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅማለች፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን የታሪክን ያህል ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ጉዳይ የለም፡፡ ፈረንሣዮች በዜጎቻቸው ውስጥ ያለውን የጎጠኝነት ስሜት ለማጥፋት የወል ታሪክን መፈለግ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህን መሰሉ ታሪክ ደግሞ ሁሉንም የሚያግባባ ሆኖ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት የወቅቱ የአንድነት አቀንቃኞች የኋላውን ትቶ ወደፊት መራመድን ምርጫቸው አላደረጉም፡፡ የወቅቱ መንገዳቸው በዚህ ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ በተለያዩ አገሮች ስደተኞች የተመሠረተችው ፈረንሣይ ዛሬ ታሪክ የመሆን ዕድል ይኖራት ነበር፡፡

የፈረንሣዮች የወል ታሪክ መነሻ ናፖሊዮን ነው፡፡ ናፖሊዮን በአገሩ ፈረንሣይ  ጥሩም መጥፎም ትውስታዎች ያሉት መሪ በመሆኑ በጠቅላላው ዜጋ ሊወደስ አይችልም፡፡ ነገር ግን ለነገ የሚሆን ስንቅ ጥሎ ያለፈ መሪ በመሆኑ የናፖሊዮን አባባሎች ለፈረንሣይ አንድነት የቃል ኪዳን ሰነድ ሆነው አገለገሉ፡፡ ማንኛውም ፈረንሣዊ ገና በልጅነቱ ስለሪፐብሊኩ እየሰማ ስለአገሩ ታላቅነት እየዘመረ ነገውን ይሠራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ከመጥፎ ትውስታ ይልቅ በጥሩ ትዝታ የተነደፈ የፈረንሣይ ብሔርተኝነት በማኅበራዊ መስተጋብርም እንዲዳብር ተደረገ፡፡ ፈረንሣይ የፈረንሣዊነት አስተሳሰብ እንዲጎላ ለማድረግ የኋላ ታሪኳን በውሉ በመመርመር የናፖሊያዊ ዘመን አባባሎች ተጠቅማለች፡፡ በሁሉም ፈረንሣዊ ልብ ውስጥ አገር ምን ማት እንደሆነ የሚገልጹ ሐሳቦችን በስፋት ለመቀስቀሻነት አውላለች፡፡

ይህ ዓይነቱ ታሪክን መርምሮ የወል አስተሳሰብን ለመቅረፅ መሞከር ግን ብቻውን ለፈረንሣይ አንድነት የሚያበቃ አልነበረም፡፡ በዚህ መነሻም በየአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች ወጥነት ያለውን ሥርዓተ ትምህርት እንዲተገበሩና የአንዱን ለአንዱ አስፈላጊ መሆን እንዲያምኑ ፈጣን የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች አካሂዳለች፡፡ በዚህ ሁኔታም አንዲት ፈረንሣይ ተፈጠረች፡፡

የኢትጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) እንደሚሉት የብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር የተኳረፈ ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል ዕድል ያለው የፖለቲካ ልሂቅም ጎራ ይዞ ከመወነጃጀል ያለፈ ተግባር አልተወጣም፡፡ እንዲህ ባለው ድክመት ደግሞ የወል ታሪክ በአግባቡ ሳንፈጥር ስለአንድነት ብናወራስ ምን እንሆናለን? ከሚል ገረገራዊ ሐሳብ ደጃፍ አደረሰን፡፡

የወል ታሪካችን መነሻ ተብሎ የሚነገርለት የዓደዋ ድል ላይ እንኳ ሦስቱ የፖለቲካ ኃይሎች አሠላለፋቸው ለየቅል የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ የዓደዋ ድል በዓል የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል ነው ከሚል ጥልቅ ሐሳብ ወጥቶ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ነው በሚል የዘውጌ ብሔርተኛ ገለጻ ተተክቷል፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገርም የዘውጌ ፖለቲከኞችን በዓደዋ ድል የእነሱ ብሔር የነበረውን አስተዋኦ በመመዘንና በድሉ ውስጥ የነበራቸውን አሠላለፍ በማጉላት ላይ እንዲጠመዱ አድርጓል፡፡ ዓደዋ በአሁኑ ወቅት ለትግራይ ልሂቃን የባሻ አዋሎም የስለላ ጥበብ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ለኦሮሞ ፖለቲከኞች የፈረሰኞቹ አባቶቻቸው የጦር ድል አድራጊነት ስጦታ ነው፡፡ ለአማራ ልሂቃን በአንፃሩ ዓደዋ የታላቁ ንጉሥ አፄ ምንሊክ ገፀ በረከት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

የሦስቱ የፖለቲካ ኃይሎች የታሪክ ሺሚያ ወፍ ዘራሽ ሳይሆን አዕላፍ ተከታዮችን ያፈራ እንቅሰቃሴ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የነገዋን አንዲት ኢትዮጵያ የመፍጠር ሙከራ አዳጋች ሆኗል፡፡  

ለብሔርተኝነት ኃልዮት ተመራማሪው አርነሰት ጌርነር ታሪክ የአገራዊ ብሔርተኝነት አንዱ ወሳኝ አላባ እንጂ ብቸኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ መሠረትም ስለአገራዊ አንድነት ሲወራ ተቀራራቢ አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠር ማድረግ ተገቢ ነው ይላል፡፡ ለጌርነር ይህ ዓይነቱ ተቀራራቢ አስተሳሰብ የመፍጠር ሒደት ከትውፊታዊ ሥርተ ማኅበር ወደ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር የሚመጣ ነው፡፡ ሽግግሩ ከዘውጌ ብሔርተኝነት ወደ አገራዊ ብሔርተኝነት የመለወጥ አቅምን ይፍጥራል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ለአገራዊ አንድነት የአገሮችን ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥና የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘዴ መቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መገንዘብ ይቻላል፡፡

የጌርነርን ሐሳብ በአጭር ምሳሌ ጠቅሼ ልለፍ፡፡ ቅድመ ካፒታሊስት ማኅበረሰብ ቡድናዊነት የሚስተዋልበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ቡድናዊነት የባህል የበታችነት የተሰማው ማኅበረሰብ (የፖለቲካ ባህልን ይጨምራል) የባህል የበላይነት ባለው ላይ እንዲነሳ የመንቀሳቀስ ኃይል ይኖረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አንድነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህን መሰሉ የአንድነት ሥጋት በፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር የሚመታ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ መገልበጥም መፍትሔውን ይጠቁማል፡፡ ኢንዱስትሪያል በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ከቡድንተኝነት ይልቅ ግለኝነት ይሰፍናል፡፡ ግለኝነቱም እንደ ቀደመው ዓይነቱን የብሔር ሽኩቻ ይቀንሰዋል፡፡ ሠራተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከመንግሥት ጥገኝነት የተላቀቀ በመሆኑ፣ እንደ ቀደመው ሥርዓተ ማኅበር በቀጥታ የብሔር ፖለቲካው ተፅዕኖ የሚመለከተው አይሆንም፡፡ እንዲህ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ መፈንቅለ ባህል እንዳይኖር በመከላከል ለአንድነት መሠረት ይሆናል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ከላይ ከጠቀስኩት ቅደመ ካፒታሊስት ማኅበረሰብ ፍላጎት ጋር የመቀራረብ ነገሩ የጎላ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፈጣንና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ የባህር ዳሩ ጉባዔ ከሌላ ፈታኝ ሐሳብ ጋር የሚጋፈጠውም እዚህ ላይ ይመስለኛል፡፡ የሁለቱ ሕዝቦችን አንድነት ለማረጋገጥ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማትን ማስፈን የፓርቲዎቹ ሥራ ነው፡፡ ይህን ግን ባለማድረጋቸው ማኅበረሰቡ የመንፈቅለ ባህል (ብሔርተኝነት) ሙከራ እያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሙከራም የሥልጣን ባለቤት ሆኗል በተባለው ነዋሪ ላይ ሲያነጣጥር ይስተዋላል፡፡ የመጀመርያው ቀድሞ ሥልጣኑን ይዞታል ተብሎ በሚነገረው የአማራ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ ሁለተኛው በአሁኑ ወቅት የሥልጣን ባለቤት ሆኗል በሚባለው የትግራይ ሕዝብ ላይ የተጀመረ ነው፡፡ ለእነዚህ ሁለት ወቅታዊ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔም የወል ታሪክ መፍጠርና ከቅድመ ካፒታሊስት ወደ ኢንዱስትሪያል ማኅበረሰብ ሽግግር ማድረግ ናቸው፡፡

የሁለቱ ፓርቲዎች ሰሞነኛ የተቀደሰ ሐሳብም የሰፌድ ላይ ሩጫ ሆኖ ብቅ የሚለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የውል ታሪክ ማበጀት ላይ ባለፉት ዓመታት ስኬታማ ሥራ አልሠሩም፡፡ እንዲያውም ከዚህ ይልቅ የሕዝቡ የሆነውን ታሪክም ሲያጠፉ ኖረዋል፡፡  አሁን ባለው ሁኔታም የወል ታሪክን ይፈጥራሉ ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡ እዚህ ላይ ሰሞነኛውን የአኖሌና የጨለንቆ ሐውልት አፍርሱልን ጥያቄ ከአማራ ፖለቲካ ልሂቃን መደመጥን ልናነሳ እንችላለን፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም በአማራ ልሂቃን በኩል አፄ ምኒሊክን የወል የማድረግ አስተሳሰብ ለድርድር የሚቀርብ አይመስልም፡፡ የሁለቱ ፖለቲካ ልሂቃን አክራሪዎች ከመሆናቸው የተነሳ በዚህ ሐሳብ ላይ የሚኖራቸው መቀራረብ አሁንም በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡ የባህር ዳሩ የሰላምና አንድነት ኮንፍረንስ በሌላ ጥያቄ የሚፈተነው ደግሞ፣ ፈጣን የሆነ የክልሎችን የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ፓርቲዎች ተፋጠረዋል ወይ? በሚል ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁለቱ ፓርቲዎች ባለፉት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ነውጥ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ለግጭቱ መነሻ የተለያየ ሰበብ ቢሰጡትም ሕዝቡ ግን በነቂስ በመውጣት ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ እንዲህ ያለው የፖለቲካ ቅቡልነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ድርጊት ሌሎች ምክንያቶች ቢጨመሩበትም ፓርቲዎቹ የሚጠበቀውን ያህል አለመሥራታቸውን ያሳያል፡፡ ብአዴን አምራች ማኅበረሰብ ይዞ በአገሪቱ በምግብ ድህነት ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ክልል አፍርቷል፡፡ ኦሕዴድም ሰፊ ሀብት ያለውን ክልል ይዞ በኢኮኖሚው በኩል ለክልሉ ወጣት በቂ የሥራ ዕድል እንኳን መፍጠር አልቻለም፡፡  ከዚህ በመነሳትም የነገው የፓርቲዎቹ መንገድ ከፖለቲካ ቅቡልነት አንፃር ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ በጥያቄነት ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን የነገውን የአገሪቱን አንድነት ለመመሥረት ዋስትና ይሆናል ያልነውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ጥቂቶች ግን አሁንም በአንድ ነገር ያምናሉ፡፡ ኢሕአዴግን እየጠሉ  ኢሕአዴግን መውደድ በአገሪቱ እየተንሰራፋ ስለሆነ ፓርቲዎቹን የሚታገስ ሕዝብ አሁንም አይጠፋም ይላሉ፡፡ ለእንዲህ ያለው ሐሳብ መነሻው ደግሞ ብአዴንና ኦሕዴድ የኢሕአዴግ አካል ሆነው እያለ ለኢሕአዴግ ጥላቻ የሚያሳየው ተቀዋሚ ለሁለቱ ፓርቲዎች ድጋፍ ሲሰጥ መስተዋሉ ነው፡፡

ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ ይታደራል ወይ?

አርሚን ቮን፣ ስቴፈን ሀቨርለር፣ ፍሌክስ ሀንስቸማንና ራፌል ኡዝ በጋራ ባቀረቡት ምርምር የአገረ መንግሥት መዳከም (State Failure) ለአገራዊ ብሔርተኝነት መዳከም (Nation Failure) የራሱ ሚና አለው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ይህ ዓይነቱ አመክንዮ ሚዛን የሚደፋ ይመስላል፡፡ በመሆኑም ውጤታማ አገረ መንግሥትን የመመሥረት ሥራ (State Building) የአገሪቱ ህልውና ቁልፍ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የሁለቱ ፓርቲዎች ሚና ውጤታማ አገረ መንግሥትን በመመሥረት ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ ይህ መሰሉ ጥገና ታዲያ ከላይ ያነሳናቸውን የአንድነት መሠረታዊ ነጥቦች የወል ታሪክ ግንባታና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይልቁንም እነሱን በፓርቲዎቹ ለማስረፅ የሚረዳ መንገድ ተደርጎ የሚቆጠር ነው፡፡ በዚህ በኩል የአንድ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መሠረት ይሆናል የተባለውን ሕገ መንግሥት በአግባቡ ለመተግበር መሞከር ትልቅ ቦታ ይይዛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ዕድገት ዘገምተኛነት፣ በተለይም ከነበረበትም በቅርቡ እየተንሸራተተ መምጣት ማስተካከል ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ለአንድነት ምሥረታው ጉዞ የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡ የኢሕአዴግ ጥምር ፓርቲ መሆን አሁንም ለነገሮች መባባስ የራሱን አስተዋጽኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የኢሕዴግ ውህደት መፍጠር በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ለአንድነት የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡ በመጨረሻም የሰሞኑን የሁለቱን ፓርቲዎች መቀራረብ ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ጋር ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን  የሰሞኑን ውይይት ከአንድነት መሠረትነቱ ይልቅ አየርላንድና ስኮትላንድ በእንግሊዝ ላይ የተከተሉትን የመገንጠል መንገድ በአገራችን እንዲደገም በር ከፋች ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡