Skip to main content
x
የናይል ኢንሹራንስ ካፒታል ከእጥፍ በላይ እንዲያድግ ባለአክሲዮኖች ወሰኑ
የናይል ኢንሹራንሽ ጉባዔ በተካሔደበት ወቅት የቦርድ አመራር አባላት ስለኩባንያው ዓመታዊ እንቅስቃሴ አብራርተዋል

የናይል ኢንሹራንስ ካፒታል ከእጥፍ በላይ እንዲያድግ ባለአክሲዮኖች ወሰኑ

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ 23ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ ባለአክሲዮኖች የኩባንያውን ካፒታል ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰኑ፡፡

ኩባንያው ሐሙስ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት በአሁኑ ወቅት የተፈቀደ ካፒታሉ 200 ሚሊዮን ብር የሆነው ናይል ኢንሹራንስ፣ ካፒታሉን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ወደ 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ስምምነት ተደርጓል፡፡ እስካለፈው ሒሳብ ዓመት መጨረሻ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል መጠን 188.13 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ናይል ኢንሹራንስ በ2009 ዓ.ም. ክንውኑ፣ የ419.5 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከ2008 ዓ.ም. አኳያ የ3.5 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ የኩባንያው ቦርድ ዳይሬክተር አቶ መቅደስ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡ ከተጣራ የአረቦን ገቢ አኳያም በ14 በመቶ ጭማሪ የታየበት የ371 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ያዋለው የተጣራ የካሳ ክፍያ መጠን 224 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የካሳ ክፍያው መጠን ከካቻምናው አኳያ በሁለት በመቶ እንደሚያንስ ተጠቁሟል፡፡ ለካሳ ክፍያ የዋለው ወጪ በኢንዱስትሪው ከሚታየው የካሳ ጥያቄ አኳያ ቀንሶ መገኘቱ እምብዛም ያልተለመደ አሰኝቶታል፡፡

የካሳ ክፍያው ከካቻምናው ያነሰበት ምክንያት በዋናነት በአካል ጉዳትና በገንዘብ ነክ ሥራዎች ላይ የቀረበ የካሳ ክፍያ በመቀነሱ እንደሆነ የኩባንያው ቦርድ ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ በ2009 ዓ.ም. የቀረበው የተጣራ የካሳ ክፍያ ላይ የ6.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ለቀረበው የካሳ ጥያቄ መጨመር ምክንያት ከሆኑ መካከል ለገንዘብ ነክ ዋስትና፣ ለምሕንድስና እንዲሁም ለተሽከርካሪ ጠቅላላ ውድመት የተያዘው መጠባበቂያ መጠን ከፍ በማለቱ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ላልተከፈለ ካሳ የተያዘው መጠባበቂያ በ2008 ዓ.ም. ከነበረው የ133.5 ሚሊዮን ብር መጠን ጋር ሲነፃፀር በ2009 ዓ.ም. የ32.4 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 176.7 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡

በሪፖርት ዓመቱ ላልተሰበሰበ አረቦን፣ ላልተከፈለ ካሳና ለሌሎች ቴክኒካል መጠባበቂያዎች በድምሩ 388 ሚሊዮን ብር የተያዘ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው 348.7 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ11.3 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡ ለቴክኒካል መጠባበቂያዎች የተያዘው በጀት ከፍ ለማለቱም ከቀረቡ ምክንያቶች መካከል ላልተከፈለ ካሳ የተያዘው መጠባበቂያ መጠን ከካቻምናው አንፃር የ32.4 በመቶ ወይም የ43.27 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱ ይጠቀሳል፡፡

የኩባንያው የውል አፈጻጸም ውጤት በ2008 ዓ.ም. ከነበረው 56.50 ሚሊዮን ብር አኳያ ሲነፃፀር የ61 በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 90.8 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል፡፡ ይህም የተጣራ አረቦን ገቢ ዕድገት የተሻለ በማሳየቱና በካሳ ክፍያ ላይ መሻሻል መታየቱ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ አቶ መቅደስ ጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው በ2009 ዓ.ም. ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ያገኛቸው ገቢዎች ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሱት ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ የተገኘው የወለድ ገቢና በአቢሲኒያ ባንክ ውስጥ ካለው ኢንቨስትመንት የተገኘው የትርፍ ድርሻ ነው፡፡ በሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ በጊዜ ገደብ ከሚቀመጥ ገንዘብ ወለድና ከአቢሲኒያ ባንክ የአክሲዮን ድርሻ የተገኘው የትርፍ ድርሻ በድምሩ ከ48.4 ሚሊዮን ብር በላይ ለኩባንያው አስገኝተዋል፡፡

ከእነዚህ የገቢ ምንጮች ባሻገር ከሌሎች ምንጮችም ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን የገለጸው ኩባንያው፣ በ2009 ዓ.ም. ከሌሎች ምንጮች የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እንዳሳየና 16.9 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ገልጿል፡፡ ለዚህም በፍርድ ቤት ክርክር የወለድ ቅጣትን ጨምሮ በ11.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ከተከሰሱ የኩባንያው ደንበኛ ማግኘት መቻሉ ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያው በባህር ዳር ከተማ ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ከሚያስተዳድረው ሕንፃ ኪራይ ገቢና አሮጌ መኪኖች ሽያጭ የተገኘው ገቢ ለጭማሪው አስተዋጽኦ በማበርከት ለዓመታዊ ትርፉ ማደግ አጋዥ እንደነበር ጠቅሷል፡፡

የኩባንያው አስተዳደራዊና ጠቅላላ ወጪዎች ካቻምና ከነበረው የ78.3 ሚሊዮን ብር መጠን ጋር ሲነፃፀሩ የሁለት በመቶ ቅናሽ በማሳየት 76.8 ሚሊዮን ብር እንደደረሱ ተገልጿል፡፡ በዋና ዋና ወጪዎች ላይ ቁጥጥር በማድረጉ የተመዘገበ ለውጥ ስለመሆኑም የቦርድ ሰብሳቢው ያቀረቡት ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ ከሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዙ ወጪዎች ዕድገት ማሳየታቸው፣ ኩባንያው ብቁ ሠራተኞችን ለመሳብና ያሉትንም ለማቆየት ጥናት ላይ የተመሠረተ የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ በማድረጉ ነው ተብሏል፡፡ የኩባንያው የ2009 ዓ.ም. ትርፍ 100.7 ሚሊዮን ብር ማስመዝገቡም ተጠቅሷል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት በ41 ቅርንጫፎች በመላ አገሪቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡