Skip to main content
x
ከውጭ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ተከታትሎ ለውጤት የማድረስ ችግሮች እንዳሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
በኖርዌይ ልዑል አልጋወራሽ የተመራው የንግድ ልዑክ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ተነጋግሯል

ከውጭ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ተከታትሎ ለውጤት የማድረስ ችግሮች እንዳሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረሞች ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የንግድ ልዑካንን ተከታትሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉ ላይ ክፍተት እንደሚታይ ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ የሚካሄዱ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ምክክር መድረኮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ቢመጣም፣ ፍሬያማነታቸውን እስከ መጨረሻው በመከታተል ለውጤት ማብቃቱ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ 34 የቢዝነስ ፎረሞች ተካሒደዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ጀነራል የቢዝነስ ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሔር እንደገለጹት፣ ፎረሞችን ማካሄድ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ‹‹ምን ጥቅም ተገኝቶባቸዋል የሚለው ነገር በትክክል መታየትና በፎረሙ የተገኙ ልዑካንን ተከታትሎ  [ያመጡትን የፕሮጀክት ሐሳብ] ወደ ትግበራ እንዲያስገቡ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ከሚታየው የክትትል ችግር ባሻገር፣ አመቺ የኢንቨስትመንትና የንግድ አማራጮችን ከማስተዋወቅ አኳያም ትልቅ ችግር መኖሩ ተገልጿል፡፡ ፕሮግራሞችን በማስተባበር በኩልም ክፍተት እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ልዑካን እዚህ ድረስ መጥተው ከተገቢው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሳይገናኙ የሚመለሱበት አጋጣሚ አለ፡፡ ከዚህ ባሻገር ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ የውጭ ኩባንያዎች ድንገት ጉዟቸውን ሰርዘው ሲቀሩ ይታያሉ፤›› በማለት በማስተባበር ሥራ በኩል ያሉትን ችግሮች አቶ አርዓያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በእንዲህ ያለው ሥራ ውስጥ ደላሎች ጣልቃ ሲገቡ እንደሚታዩ፣ ይህም በአገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ሐሳባቸውን ሰርዘው እንዲመለሱ እያስገደዳቸው እንደሚገኝም አቶ አርዓያ ጠቀሰዋል፡፡

አቶ አርዓያ ይኼንን ያብራሩት፣ የኖርዌይ አልጋ ወራሽ ልዑል ሀኮን ማግኑሥ ከልዕልት ሜቲ ሜሪት ጋር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሰሞኑን አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ነው፡፡ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ ተዘጋጅቶ በነበረው የቢዝነስ ፎረም ወቅት ከልዑላውያኑ ጋር የመጡ 60 የንግድ ልዑካንም ታድመው ነበር፡፡ በተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩት ልዑካኑ፣ በአግሪ ቢዝነስ፣ በማዕድንና በኃይል ዘርፍ በኢትዮጵያ የመሥራት ፍላጎት እንዳሳዩም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያና ኖርዌይ የረዥም ጊዜ ግንኙነት ቢኖራቸውም በንግድና በኢንቨስትመንት ረገድ ያላቸው መስተጋብር አመርቂ አልነበረም፡፡ ከዴንማርክና ከስዊድን ጋር ነበር ብዙ ስንሠራ የቆየነው፡፡ አሁን ግን ኖርዌጂያኑ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት ያላቸው ይመስላል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህም የልዑላውያኑ መምጣት ትልቅ ተምሳሌት ነው ብለዋል፡፡

ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮችም ይበልጥ እንዲጠናከር የማድረግ ዓላማ ያለው የሰሞኑ ጉብኝት በሦስት ቀናት ቆይታ ተጠናቋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2017 በነበረው ጊዜ ውስጥ 67.7 ሚሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ኖርዌይ የላከቻቸው የቡና፣ የአበባና የማር ምርቶች  32.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳስመዘገቡ ይገመታል፡፡ ተገጣጣሚ የሕንፃ ግድግዳዎች፣ የተለያዩ ማሽኖችና ማዳበሪያዎች ኢትዮጵያ ከኖርዌይ የምትገዛቸው የምርት ዓይነቶች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካል የታየው የንግድ ልውውጥ ባለፈው ዓመት በ22.3 በመቶ መጨመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡