Skip to main content
x
የኢትዮጵያ ቡና ያነገሣቸው ተወዳዳሪዎች

የኢትዮጵያ ቡና ያነገሣቸው ተወዳዳሪዎች

በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ መገኛውን ያደረገው ጉድ ፉድ ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም፣ በየዓመቱ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች መስክ ውድድር ያዘጋጃል፡፡ ከሚያዘጋጃቸው ልዩ ልዩ ውድድሮች መካከል፣ ‹‹ጉድ ፉድ አዋርድስ›› የተባለውና በምግብና መጠጦች ዙሪያ የሚሰናዳው ይገኝበታል፡፡

በዚህ ረገድ በምርጥ ጣዕማቸው የታወቁ፣ በዓይነትና በዝግጅታቸው የተመሠረከረላቸው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች ለውድድር ይቀርባሉ፡፡ በታወቁ ዳኞች ይፎካከራሉ፡፡ አሸናፊዎችም ለሜዳልያ ይበቃሉ፡፡ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡና በዚህ ውድድር በኩል ትልቅ ስምና ሞገስ እያገኘ መምጣቱን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ለውድድሩ የሚቀርቡ ቡና ቆዪዎች በብዛት በኢትዮጵያ ቡና አማካይት በጅምላ ለአሸናፊነት ሲበቁ መታየቻውን ድረ ገጾች አስነብበዋል፡፡ ሮስት ሜጋዚን የተሰኘው የድረ ገጽ አውታር፣ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያን ቡናዎች ለመወዳደሪያነት ይዘው ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል አብዛኞቹ ለመጨረሻው ዙር ማለፋቸውን አስነብቧል፡፡ በጥር ወር በሚካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚሳተፉ ከሚጠበቁት የተለያዩ ተወዳዳሪዎች መካከል 27 የአሜሪካ ቡና አዘጋጆች በኢትዮጵያ ቡናዎች እንደሚወዳደሩ ታውቋል፡፡

ስምንተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ይህ የሽልማት ሥነ ሥርዓት፣ ከምግብ ጥራት ባሻገር በዘላቂ አቅርቦት፣ እንዲሁም በማኅበራዊ መስክ መልካም ተግባራትን በመወጣት ረገድም አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ኩባንያዎች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ለውድድር የሚቀርቡት የምግብና የመጠጥ ምርቶች ከዚያው ከአሜሪካ የሚቀርቡ ቢሆኑም፣ ቡና ግን ከሌሎች በተለየ ከተለያዩ አገሮች ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርብ ብሎም ለውድድር የሚያበቃው ደረጃ ላይ የሚገኝ ምርት ነው፡፡ ምንም እንኳ ከመላው ዓለም የሚቀርቡ ቡናዎች የሚቀርቡበት ይህ ውድድር ዘንድሮ ግን በተለየ መልኩ በርካታ ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ቡና ለመወከል ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን መረጃው አስፍሯል፡፡

ኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን የተወከለችበት ውድድር መነሻው ምን ሊሆን እንደሚችል መላምታቸውን ያስቀመጡት የድረ ገጹ ጸሐፊ ካስቀመጧቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይጎላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ቡና አምራች አካባቢ የተለየ ከፍተኛ ጣዕምና ቃና ያለው ቡና አምራች መሆኗ አንደኛው መነሻ ነው፡፡ ከተቆላ በኋላ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚችል የተመሰከረለት የኢትዮጵያ ቡና፣ ለውድድሩ ብቁ ካደረጉት መሥፈርቶች መካከል ተመራጭ እንደሚያደርገውም ይታመናል፡፡

በሽልማት ድርጅቱ መሥፈርት መሠረት ኢትዮጵያ የቡና ደረጃዎችን በመመደብና የጥራት ማረጋገጫ በመስጠት ረገድም ቀዳሚነቷ መረጋገጡን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ደግሞ ለዘለቄታው አስተማማኝ የቡና ምንጭ ስለመሆኗ መተማመኛ የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱን አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች የአገሪቱን ቡና ለውድድር መጠቀማቸው ሌላኛው ማሳያ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

አሜሪካውያኑ ተወዳዳሪዎች ያቀረቧቸው ቡናዎች በተፈጥሮ ሒደት የሚዘጋጁ ምንም ዓይነት የኬሚካልም ሆነ የፋብሪካ ንክኪ የማይታይባቸው ሆነው መገኛታቸውም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡናዎች ለአሸናፊነት ያገኙት ቅድመ ግምት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በተፎካካሪነት የቀረቡ የሌሎች ተፈጥሯዊ ያልሆኑ የቡና ዓይነት እምብዛም አለመሆናቸው፣ የተፈጥሮ ቡናዎችም ሆነው ከሌሎች አገሮች ለውድድር የቀረቡ አለመኖራቸው ግርምትን አጭሯል፡፡

ባለፈው ዓመት በተካሄደ ውድድር የኢትዮጵያን ቡና የተጠቀሙ ቡና ቆዪዎች አብዛኞቹ ማሸነፋቸው፣ በዚህ ዓመት ለቀረቡት 27 የአሜሪካ ተወዳዳሪዎች መነሻ እንደሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም በመጪው ጥር ለሚደረገው የፍፃሜ ውድድር ከቀረቡት 27 ኩባንያዎች መካከል የኢዶዶ፣ የይርጋጨፌ፣ የገደብ፣ የሐምቤላ፣ የሐምቤላ አለቃ፣ የሐምቤላ ቅርጤ፣ የአማሮ ጋዮ፣ የሊሙ፣ የጉጂ፣ የሻኪሶና የሌሎችም አካባቢዎች ቡናዎች በኩባንያዎቹ ለውድድር የቀረቡ ቡናዎች ሆነዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተደረገው ውድድር ወቅትም ለውድድር ከቀረቡ 25 የመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ውስጥ 19ኙ የተወከሉት በኢትዮጵያ ቡናዎች እንደበነበር ሲታወቅ፣ አብዛኞቹም ለአሸናፊነት እንደበቁ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ካቻምናም በተመሳሳዩ አብዛኛውን የቡና ቆይዎች ቀልብ ከኢትዮጵያ የሚላኩ ቡናዎች ለመግዛት ቢችሉም፣ ኬንያ ዋና ተፎካካሪ እንደነበረች ተጠቅሷል፡፡

ከዓለም አቀፍ ዕውቅናው በተጓዳኝ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ቡና ጠጪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለውጭ ከሚቀርበው ያልተናነሰ መጠን ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና በ2009 ዓ.ም. ቡና ከ890 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱም አይዘነጋም፡፡ ሰሞኑን በተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ሳቢያም የቡና የወጪ ንግድ መጠን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጭማሪ እንዳሳየ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አኃዞች እንደሚያሳዩትም በዚህ ዓመት መስከረምና ጥቅምት ወራት ከተገበያዩት የግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና ትልቁን ድርሻ በመያዝ በዋጋም በመጠንም ቀዳሚነቱን በማስጠበቅ እየተጓዘ እንደሚገኝ ነው፡፡