Skip to main content
x

ኢኮኖሚስቱ ኬንስ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ይል ነበር?

በጌታቸው አስፋው

አዳም ስሚዝ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በገበያ ውስጥ በምርት ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር በሚፈጠር የምርት ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ትርፋማነት ድርጅቶች ሠራተኛ ለመቅጠርና ላለመቅጠር በሚወስዱት ውሳኔ ሥራ አጥነት ይጨምራል፣ ይቀንሳል የሚል የግል ኢኮኖሚ ትንታኔ (Microeconomic Analysis) ሰጥቶ የሊበራል ገበያ ኢኮኖሚን በመተንተን የኢኮኖሚክስ አባት ሆነ፡፡

ኬንስ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሥራ አጥነት ምክንያት ጥቅል አገራዊ የምርት ፍላጎት መጠን ከጥቅል አገራዊ የማምርት አቅም በታች መሆን ነው በማለት፣ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥም ገብቶ መሠረተ ልማትንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት፣ ለሸማቹ ተጨማሪ ገቢ ፈጥሮ ጥቅል አገራዊ የምርት ፍላጎትን በማነቃቃት ኢኮኖሚውን ማሳደግ አለበት ብሎ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተነተነ፡፡

ስለዚህም ኬንስ የዋጋ ትንታኔን በገቢ መጠን ትንታኔ፣ የግል ኢኮኖሚ ትንታኔን በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ (Macroeconomic Analysis) ተክቶ፣ የአዳም ስሚዝን ሊበራል የግል ገበያ ኢኮኖሚ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀልብሶና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በፖሊሲ የገበያ ኢኮኖሚ ቀይሮ የብሔራዊ ኢኮኖሚ አባት የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡

የሁለቱም ዓለም አቀፍ ታዋቂና ዝነኛ ኢኮኖሚስቶች ትንታኔ ያነጣጠረው ዛሬ እኛን በሚያስጨንቀን ሥራ አጥነት ላይ ነው፡፡ የኬንስ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔም ጥቅል አገራዊ ምርትን እስከ የማምረት ሙሉ አቅም ማሳደግ ሥራ አጥነትን እንደሚቀንስ እንጂ እንደማይጨምር ያረጋግጣል፡፡

በኬንስ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ ብዙ የዓለም መሪዎች አገራቸውን በፖሊሲ መርተዋል፡፡ ለምሳሌም የአሜሪካው ሪቻርድ ኒክሰንና የኢኮኖሚ አማካሪያቸው ታዋቂው የጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚስት (Monetary Economist) ሚልተን ፍሬድማን አሁን ሁላችንም የኬንስ ኢኮኖሚክስ ተከታዮች ነን ብለው ነበር፡፡ ኬንስ ራሱም ስለኢኮኖሚ አመለካከትና የልሂቃን ሚና የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡

 “ከልሂቃን አመለካከት ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ የሚመስላቸው የተግባር ሰዎች ብዙ ጊዜ የአንድ ሙት ኢኮኖሚስት ሐሳብ ባሪያዎች ናቸው፡፡ ከአየር ላይ ድምፅ የሚሰሙ ዕብድ ባለሥልጣናት ከስሜታዊነታቸው የሚነፁት ከጥቂት ዓመታት በፊት ሲሞነጫጭር ከነበረ ምሁር ነው፡፡”

ጆን ሜናርድ ኬንስ

የአዳም ስሚዝና የኬንስ ሁለቱ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች የካፒታሊስት ዓለም ሕዝብ የሚከተላቸው ብቸኛ ፈር ቀዳጅ የነፃ ገበኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፡፡ እዚህችም እዚያችም አንዳንድ ማበልፀጊያዎችና ማሻሻያዎች ለማድረግ የደፈሩ ኢኮኖሚስቶች ቢኖሩም፣ እንደ ሁለቱ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣ ግን የለም፡፡

ታዳጊ አገሮች የሚመሩበት የኢኮኖሚ ልማት ወይም የልማት ኢኮኖሚም በኬንስ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ መንግሥት ከመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ባሻገር፣ የገበያውን ጉድለት ለመሙላት የገበያ ሸቀጥንም ማምረት ይችላል ከሚለውና መንግሥት ጠቅላላውን ኢኮኖሚም በዕቅድ ይመራል ከሚለው ሁለት ተጨማሪ ነገሮች ባለፈ አዲስ ነገር የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ1980ዎቹ ከነበረበት ከ20 ቢሊዮን ብር በታች ዛሬ መቶ ዕጥፍ አድጎ ሁለት ትሪሊዮን ብር እየተቃረበ ነው፡፡ የሕዝቡ ገቢና ኢኮኖሚው ይህን ያህል አድጎም ለተፈጠሩት ተቃውሞዎችና አለመረጋጋቶች ዋናው ምክንያት የወጣቶች ሥራ አጥነት መሆኑን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ በቅርቡ ለቢቢሲ ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ 

ይህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትና ሥራ አጥነት ተቃርኖ ሁኔታ አገራዊ ገቢና አገራዊ ምርት ሲያድግ፣ ሥራ አጥነት ይቀንሳል ለሚለው የኬንስ ኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ራሱ ኬንስ የዛሬ ሰባ ዓመት የፈጠራቸው ከእኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ማስቲካ ገዝተው ሳያውቁ ዕድሜ ልካችንን ስለኖርንበት ኢኮኖሚ ለእኛ የሚነግሩን ደቀ መዝሙሮቹ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክም እንቆቅልሹን አልፈቱልንም፡፡

ከላይ የቀረበው ኬንስ ስለተግባር ሰዎች የተናገረው መልዕክት ግን የእንቆቅልሹ መልስ ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሊቆቹም እኛው መሪዎቹም እኛው የተባለበት ዘመን ነበር፡፡

ገበያው ሳይጠራቸው በልሂቃን መሪዎቻችን ትዕዛዝ ከተፈጠሩት ሥራ ፈጠራዎች ውስጥ ከግማሽ በላዩ ፈርሰው፣ ዛሬ ከፈረሱት ለተበተኑትም ለአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎችም ሥራ መፍጠር አስፈልጓል፡፡ የልሂቃን መሪነት ዳግመኛ ስህተት ውስጥ አሁንም እየተገባ ስለሆነ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ድርጅቶች ፈርሰው ለሚበተኑትም ሆነ ለአዳዲስ ሥራ ፈላጊዎችም ሥራ መፍጠር ጣጣ ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህም ዓይነት ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ የሥራ አጡ ቁጥር ዕጥፍና የዕጥፍ ዕጥፍ እየሆነ ይቀጥላል፡፡

በልማት ኢኮኖሚ ስትራቴጂው ዳክሮ አልሳካ ያለው መንግሥት አክራሪ የገበያ ኃያሎች ሲላቸው የነበሩትን ኒኦ ሊበራሎች በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ስም ማባበሉን ተያይዞታል፡፡ አገራችን ልሂቃን መሪዎቻችን በነደፉት ሁለት ዓይነት የኢኮኖሚ ፍልስፍና እየተመራች ነው፡፡

በአንድ በኩል የአገሬው ሕዝብ በልማታዊ መንግሥት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ነጭ ላብ እስከሚያልበው ግብር እንዲገብር እየተገደደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኒኦ ሊበራሎች እስከ ደጃፋቸው መሠረተ ልማት እየተነጠፈላቸው በዓለም አቀፍ የነፃ ገበያ ሥርዓት እየሠሩ ነው፡፡ ልማታዊ ኒኦ ሊበራሊዝም የሚል ጥምር ስያሜ እንስጠው?

የሠራተኞች ደመወዝ ከዓለም የመጨረሻው ርካሽ እንደሆነ ቃል ተገብቶላቸው ይመጣሉ፡፡ በዲክሺነሪ ትርጉም ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ድህነት ጎን ለጎን ርካሽ ጉልበትም ቢጨመርበት የሚገርም አይሆንም፡፡ ሰሞኑን መንግሥት አዲስ የሠራተኛ አዋጅ አርቅቆ ከኢሠማኮ ጋር የገጠመው አታካራም፣ የሠራተኛውን መደራጀት እንደ ጦር የሚፈሩትን የውጭ ኢንቨስተሮች ለማስደሰት የተደረገ ሙከራ ሊሆን ይችላል፡፡

ፈረንጆች የዋዛ ሰዎች አይደሉም፡፡ ለሰላሳና ለአርባ ዓመታት ነው የሚያቅዱት፡፡ በ1980ዎቹ አጋማሽ የዋሽንግተን መግቢያ ስምምነት የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ይዘው መጥተው ሳይቀናቸው ተሰናበቱ፡፡ በርካታ ዓመታትን ጠብቀው የውጭ ምንዛሪ አሳጥተው፣ አዳክመውና እጅ ጠምዝዘው፣ አንዳንዴም ቆርኪ እየሸለሙ ይኸው ሥር እየሰደዱ ነው፡፡

አንድ ጋዜጣ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ ‹‹የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞች ደመወዝ ጉዳይ›› በሚል ርዕስ በአልባሳት ምርት የተሰማሩ ወጣቶች የሚያገኙት ደመወዝ ከአንድ ሺሕ ብር እንደማይበልጥ፣ ተቆራርጦ እጃቸው ውስጥ የሚገባውም ከስድስት መቶ ብር እንደማይበልጥ ጠቁሞ ይህም ለዕለት ኑሯቸው በቂ ባለመሆኑ አራትና አምስት ሆነው አንድ ቤት ለመከራየት የተገደዱ መሆናቸውን ገልጾ ነበር፡፡

ይህ ስድስት መቶ ብር የተጣራ የወር ገቢ ወደ ቀን ሲሰላ በቀን 20 ብር ወይም ከአንድ ዶላር በታች በመሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከድህነት ወለል 1.90 ዶላር ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በታች ነው፡፡

ኢሕአዴጎች ከሊቅነቱና ከመሪነቱ አንዱን ካልለቀቁ የሥራ አጥነት ችግር የሚፈታው ዴቪድ ሪካርዶ ለ18ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚ በተነተነው የሠራተኛና የደመወዝ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የሪካርዶ ጽንሰ ሐሳብ የሚለው የሠራተኛ ፍላጎትና የሠራተኛ አቅርቦት እኩልነት የሚፈጠረው የሠራተኞች ገቢ (ደመወዝ) ትዳር ለመያዝ በማያስችል መጠን፣ እንደ ሐዋሳው ፓርክ ሠራተኞች ተዳብለው እየኖሩ ራሳቸውን (ትውልድ) ለመተካት በማይፈልጉበት ዝቅተኛ ደረጃ ወርዶ የሕዝብ ቁጥር ሲቀንስ ነው፡፡

እባካችሁ መሪዎቻችን አንደኛውን ምረጡ፡፡ ወይ ሊቃውንቶቻችን ሁኑ ወይ መሪዎቻችን ሁኑ፡፡ ከሦስት ሺሕና ከአራት ሺሕ ዓመታት በፊት በሶቅራጥስና በአሪስቶትል ዘመን ፍልስፍና እውነትን ፍለጋ ስለነበረ ፈላስፎች የአገር መሪዎች ቢሆኑ ይመረጥ የነበረበት ዘመን አልፏል፡፡ በዛሬው ውስብስብ ዓለም አንዱንም መያዝ አልተቻለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡