Skip to main content
x

ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ባንሰጣጥስ?

እነሆ መንገድ! ታክሲያችን በወሬና በጫጫታ ደምቃለች። ወያላችን ደጋግሞ ፀጥታ እያለ ተንሸራታቹን በር ይደልቀዋል። ‹‹ምንድነው ነገሩ? ቤተ መጻሕፍት የገባን መሰለው እንዴ ሰውዬው?›› ይነጫነጫሉ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ ወጣቶች። ‹‹ምናለበት አንዴ ወሬ ብንሰማ? ድምፅ ስጠው አቦ፤›› ወያላው ቀንድ ሊያበቅል ምንም አልቀረውም። ሾፌራችን የሬዲዮኑን ድምፅ ይጨምራል። ‹‹አሁን እኮ ጥያቄው ምርጫው ይራዘም? ወይስ አይራዘም ነው? አድማጫችን በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?›› ጋዜጠኛው ይጮሃል። ‹‹እንዴ ሳንሰማ ሳናይ ምርጫ ደግሞ መጣ? የምርጫ ካርድ ሳናወጣ?›› ትላለች ሁለተኛው ረድፍ ላይ ከአንድ ጎልማሳ ጋር የተሰየመች ሎጋ። ‹‹ስለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምርጫ ነው የሚወያዩት። ያማ ገና ነው።  ደርሶማ ቢሆን እንዲህ ፈዘን ታይን ነበር?›› አላት ጎልማሳው። ‹‹ምን ታመጣ ኖሯል?›› ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ወይዘሮ ዘወር ብለው ጠየቁት።

‹‹ምን እኔን ብቻ ይጠይቁኛል? ምን እናመጣ ኖሯል አይሉም አንድያውን? በዝምታ ጦርነት አድፍጠን የምንጠብቀው እኮ ድምፃችን የሚቆጠርበት ቀን እስኪመጣ ነው፤›› አላቸው። ወይዘሮዋ ፈገግ ብለው፣ ‹‹ሆሆ... የሕዝብ ድምፅ ይቆጠራል እንጂ ይተነበያል እንዴ?›› ሲሉት፣ ‹‹እንጃ እስኪ ጠይቁልን፤›› ትላለች ሎጋ ሸጋዋ እያሳሳቀች። ‹‹ኧረ አመለጠን እንስማበት። ይኼ እኮ የወደፊት ብሔራዊ ቡድናችንን ዕጣ ፈንታ የሚመለከት ሁነኛ ክስተት ነው፤›› ወያላው  አሁንም ይነጫነጫል። ‹‹ኤድያ። አይታክታችሁም ግን እናንተ ልጆች? ብለን ብለን እኮ የቀረን በኤሊ መሸነፍ ነው። በቀደም በሜዳችን በሩዋንዳ ተሸነፍን። እኔ የምለው ግን ሁልጊዜ ተመሳሳይ ፊት ነው የማየው። በቃ ኳስ ተጫዋች ካልሞተ በስተቀር አይሞገስም ያለው ማን ነው?›› ሲሉ ተሳፋሪው በሳቅ አወካ። እንኳንም የሳቅ ምርጫ አልኖረ የሚያስብል ነው እኮ!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። ምርጫና ትንታኔውን ተከትሎ ወይዘሮዋ ጥያቄ ይጎርፍላቸዋል። ‹‹ኳስ ያያሉ ማለት ነው?›› ጠየቃቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት። ‹‹ወድጄ ነው? ዘመኑ እንደሆነ የመንከባለል ነው። እኛም የሚያስቆጥረን አጥቂ አተን እንጂ ኳስ ሆነናል፤›› ይመልሳሉ። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ሰውን በአምሳላችን እንፍጠር ብሎ ፈጣሪ ፈጥሮን ሲያበቃ በኳስ ስንመሰል አይደብርም?›› መጨረሻ ወንበር የተሰየመች ተሳፋሪ ጠየቀች። ‹‹ቢደብር ባይደብር ምን እናመጣለን? ለገዛ ጥቅሙና ዓላማቸው ሲሉ አገርን እንደ ኳስ በሚጠልዙ ጥቂት ግለሰቦች አልተዋጥንም እንዴ?›› ጎልመሳው የወይዘሮዋን ሐሳብ ደግፎ መለሰ። ‹‹ለዚያ አይደል ታዲያ ልዩነታችን በነጥብ የሚሰላው?›› ከጎኔ የተሰየመች ዝምተኛ መሳይ ጨዋታውን ተቀላቀለች። ‹‹ያውም በስድስት ዲጂት ነዋ። ዕድሜ ለፈጣኑ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን፤›› ይላል አንድ አላጋጭ ወጣት ከመጨረሻ ወንበር።

‹‹እግዚኦ እንዲያው አንተ ፈጣሪ በምታወጣ አውጣን ብቻ ዘንድሮ፤›› ይላሉ ወይዘሮዋ። ‹‹አይዞን እማማ። ግፋ ቢል በወራጅ ቀጣናው አማካይነት ሁለተኛ ዲቪዚዮን ብንወርድ ነው። መውረድ ደግሞ ብርቃችን አይደለም፤›› ይላል ከጎናቸው። ይኼኔ ሾፌራችን ወሬያችን ሰልችቶት ጣቢያ ይቀይራል። አየሩን በሞኖፖል የተቆጣጠሩት የጉግል ጎልጓዮች ስለትዳር ትተው ስለግብረ ሥጋ ግንኙነት ዓይነትና አኳኋን እየተመፃደቁ ይተነትናሉ። ወይዘሮዋ ደጋግመው ‹‹እግዚኦ!›› ይላሉ። ‹‹ኧረ እባክህ እነዚህን ሰዎች ቀይርልን። ምን ጉድ ነው የመጣብን ዘንድሮ?›› ይላል ተሳፋሪው። ወያላው ያሽሟጥጠናል። ደግሞ ጣቢያው ሲቀየር ስለምሽትና አመሻሹ በቢራና በኮንዶም ማስታወቂያ ታጅቦ ይደመጣል። ደግሞ እሱ ሲቀየር ስለኳስ። ይኼኔ ወይዘሮዋ፣ ‹‹አላልኳችሁም? የእኛ ነገር ዘንድሮ በኳስ ካልተመሰለ ታዲያ በምን ሊመሰል ኗሯል? ስንት የሚያሳክክ ነገር በሞላባት አገር ያልበላንን ማከክ ሆኗል እኮ ሥራችን፤›› ሲሉ ጎልማሳው ተቀብሎ፣ ‹‹ከአየር ንብረት ለውጥ የባሰን የአየር ሰዓታችንን የቀሙን ሰዎች እንቶ ፈንቶ አይመስልዎትም?›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ። ሩቅ እያሰበ  ቅርብ ለሚያድር ሰው አስረዝሞ መተንፈሱም ተስፋ ነው!

ታክሲያችን  እየተጓዘች ነው። ጨዋታችንም ቀስ በቀስ ስር ሰደደ። ‹‹ወይ አዲስ አበባ! ታመሰች እኮ እናንተዬ?!›› ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ የተቀመጠች ወጣት። ‹‹በምን?›› ይላታል ከአጠገቧ። ‹‹በልማት ነዋ። የሕንፃውን ግንባታ አታየውም እንዴ?›› ትለዋለች በየዋህነት ምን ይጠይቀኛል ዓይነት። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ግን አዲስ አበባ በተጣደፈች ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በፈጣን የረብሻና የፀብ ሥራ ተወጥሯል መባሉ ነው። ከሰው የቀደመ ልማት መጨረሻው ይኼው ነው!›› ሲል ከመጨረሻ ወንበር አንዱ፣ ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች የምታወሩትን ልብ በሉ። ደግሞ ብለን ብለን በገዛ እጃችን ሌላ መዋጮ እናስጀምር እንዴ? ለስንቱ አዋጥተን ልንችለው ነው?›› ይላል ጎልማሳው።

‹‹ስለመዋጮ ተወራ እንዴ?›› ሲል የቀደመው ተናጋሪ፣ ‹‹ያው ነው ከዓባይ ሌላ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የልማት ሥራ የለውም ካልን ፀሐዩ በጥልቅ ታዳሹ መንግሥታችን በምን እንደሚመጣብን ምን እናውቃለን? ወረቀት በተወደደበት ያሰቡትን በተግባር የሚያሳዩት ከስንት አንድ በሆኑበት ዘመን ራዕይ አላልቅበት ያለ መንግሥት እኮ ነው ያለን፤›› የምትለው ከሾፌሩ ጀርባ ያለች የቀይ ዳማ ናት። ‹‹ራዕይ ሲበዛማ ጥሩ ነው። ራዕይ አስፈጻሚ ሲሰበሰብ ግን ችግር ነው፤›› ብሎ ሳይጨርሰው ጎልማሳው፣ ‹‹ለማንኛውም ለመዋጮ መጨነቅ ድሮ ቀርቷል። መጀመርያም ስንናገር የሚሰማን አጥተን እንጂ ገንዘቡ ያለው ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ ኪስ እንደሆነ ታይቷል። ምን ዋጋ አለው ጉልቤ የሚበረታው ደካማ ላይ ነው፤›› ይላል አጠገቧ የተቀመጠ ተሳፋሪ። በዘመነ ዴሞክራሲ አገር ምድሩ በሽሙጥ የተጠመደው እውነት ልማት ነው ልመና አስጨንቆት አያሰኝም?

ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ ነው። ነገረ ሥራችን ሁሉ ‘ሲሪየስ’ የሆነበት አንድ ልጅ እግር ተሳፋሪ፣ ‹‹‘ፌስቡክ’ ላይ ‘ቫት’ ሊጀመር ነው አሉ፤›› ብሎ ጨዋታ ጀምሯል። ታክሲዋ በድንጋጤ ጎርፍ ተጥለቅልቃለች። ‹‹አይደረግም ይህ የሙሰኞች ወሬ ነው፤›› ትላለች የቀይ ዳማ ወጣት ከወደ ፊት መስመር ጆሮዋን ደፍናበት የነበረውን ‘ኢርፎን’ እየነቀለች። ተሳፋሪው ታዝቧት፣ ‘እንዴ ‘ኢርፎኑ ማስክ’ ነበር እንዴ?’ እየተባባለ ያማታል። የዛሬ ሰው እንዲያው ‘ማስከኛ’ ነው ዓይነት ወሬ ደርቶባታል። ‹‹እውነትህን ነው? እንዴት ሆኖ?›› አብዛኛው ተሳሪፋሪ የሚጠይቀው በጭንቀት ነበር። ልጁ ‘ፌስቡክ’ ማለት ከሦስቱ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ሊመደብ ምንም እንዳልቀረው ታዝቦ ሲያበቃ፣ ‹‹ኧረ እኔስ ለጨዋታ ነው፤›› ብሎ ተሳፋሪውን አረጋጋው። የእፎይታው ንፋስ ብርድ እንዳያሳምመን እስክንሰጋ ድረስ።

‹‹እኔ ደግሞ ሰሞኑን የዓለም ባንክ የደጎመው ገንዘብ አልበቃ ብሎ ደግሞ በዚህም ‘ሊፈልጡን’ ነው ብዬ አስቤ ክው አልኩ፤›› ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ሥጋቱ ከምን መንጭቶ እንደደነገጠ ሲያብራራ፣ ‹‹አይደለም ዓለም ባንክ ለዓባይ የምናዋጣው ገንዘብ አመርቂ አይደለም ተብሎ በሚተችበት አገር ይኼ ሊገርምህ አይገባም። አስቡት እስኪ። በስንት ፀሎት ወር ሲመጣ ከምናገኛት መናኛ ደመወዝ አዋጥተን አዋጥተን በሙስና የሚጠፋው ገንዘብ ሁለት ዓባይ ይገድባል ሲባል አያሳፍርም? እንዴት ነው ግን የእዚህ አገር ነገር ትንሽ አልበዛም?›› እያለች መነጫነጭ የጀመረችው ከሾፌሩ ጎን ያለች ወጣት ናት። ‹‹እኔስ የምፈራው ‘ሙሰኛ ማለቂያ የለው ሕዝብ ሲልጥ ይኖራል’ እንዳይሆን ነው መጨረሻችን፤›› የሚለው ከኋላዬ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። ነገር በፖለቲካ አዋዜ እየተጠቀሰ ይሰለቅ ጀመር። ‹‹ጀምሮ ማፈግፈግማ አይታሰብም ጎበዝ! ባይሆን የነጣቂና የቀማኛውን ነገር አንድ እየተባለልን ከሄደ ሌላው ቀላል ይሆናል፤›› ሲሉ ወይዘሮዋ ነገሩን አለዘቡት። ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ ጨርሷል። የእኛ ነገር ‘የነብር ጭራ አይዙ ከያዙም አይለቁ’ ከሆነ ቆያይቷል!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ግራ ቀኝ ወሬው ሁሉ ማጣትና ማጣት ሆኗል። ይኼን አይቶ ጎልማሳው፣ ‹‹ኧረ ለአፍታ እንኳን ብላችሁ በዶላር ማሰብ አቁሙ?›› ይላል። ‹‹ታዲያ በምን እናስብ? አሁን ይህቺን መኪና ሞተሯን አውጥተህ ጥለህ ሂጂ ትላታለህ? ንገረኛ!›› ብሎ አንዱ አፈጠጠበት። ‹‹ይገርማል እናንተ። በአንድ መሬት ላይ የሁለት ዓለም ሰው ሙግት መስማት ሲሰለች፤›› ትላለች መጨረሻ ላይ። ጎልማሳው ትንፋሹን ሰበሰበና ‹‹አባባሌ እንዲያው አንዳንዴ ምን አለበት ያልተከፈለ ያልተመነዘረበትን ነገር ብናስብ ማለቴ ነው። ስንት ነገር የለም የተደገፍንበት? ግን የማንከፍልበት? የዶላር መናር! የኑሮ መወደድ! የቤት ኪራይ ጣሪያ መንካት፣ የትራንስፖርት ዕጦት፣ የፖለቲካ ገጭጓ የማያናጋው የማይነካካው ስንት ነገር የለም ዛሬ ላይ ያቆመን? ምናለበት አንዳንዴ ተመሥገን ቢቀናነን?›› እያለ ሲቀጥል ገሚሱ ባልሰማ ደጅ ደጅ ያያል። ሌላው ደግሞ የባጃጅና የሲኖትራክ ባለዕድል ይሁኑ የሚል ቴክስት እያቆራረጠው ፌስቡክ ይጎረጉራል። ጎልማሳው ፊት መነሳቱን አስተውሎ ባሰበት። ‹‹ለስሙ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ሃይማኖት፣ ጂኒ ቁልቋል ሲባል እኛን ያላየ እኛን ያልሰማ ዓይኑ ድንጋይ ጆሮው ብሳና እንላለን። ወዲህ ጊዜ ያገዘው ጦር ተምዘግዝጎ ሲመጣብን ጊዜ እንዳመጣው ጊዜ እስኪመልሰው ዝግ ብለን ማሳለፍን ከአባቶቻችን ለመማር ሲያልፍም አይነካን። ምን ዓይነት ግብዝነት ነው? ያላችሁን እስኪ ቁጠሩት። ከዚያ እንነጋገር፤›› ብሎ ወራጅ አለ ግዳዩን እንዳየ አዳኝ። እሱም ወረደ እኛም እልፍ ብለን ተከተልነው። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም እየተሰጣጠን። መልካም ጉዞ!