Skip to main content
x
የአፍሪካ አገሮች ለወጣቶች ፍትሐዊ የመሬት ሥርጭትን የሚከተል ሥርዓት እንዲዘረጉ ተጠየቁ
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ የጀመረው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ላይ ያጠነጠነው ስብሰባ በተከፈተበት ወቅት አብደላ ሐምዶክ ከግራ ሦስተኛው እና ሌሎችም የኮሚሽኑ ኃላፊዎችና የስብሰባው አዘጋጆች የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በታደሙበት ወቅት

የአፍሪካ አገሮች ለወጣቶች ፍትሐዊ የመሬት ሥርጭትን የሚከተል ሥርዓት እንዲዘረጉ ተጠየቁ

የቀድሞው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኢኒሺዬቲቭ በአሁኑ አጠራሩ የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ማዕከል የተሰኘው ተቋም፣ ከኅዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየውና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ስብሰባ የታደሙ ባለሙያዎች ወጣቶችን አሳታፊ የሚያደርግ ፍትሐዊ የመሬት ፖሊሲ በአፍሪካ እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡

ስብሰባው በወጣቶች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ለውጥ ለማምጣት የመሬት ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል እንደሚገባ የሚያመላክት ይዘት ያለው ሲሆን፣ በስብሰባው እየተሳተፉ የሚገኙ ባለሙያዎችም የወጣቶችና የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡

ኒኮላስ ኪማኒ (ዶ/ር) የተባሉት ኬንያዊው የዘርፉ ምሁር እንደጠቀሱት፣ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ የተካሄዱ የመሬት ፖሊሲ ማሻሻዎች ወጣቶችን ያገለሉ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ኬንያ ያሉትን አገሮች ጨምሮ የዚምባብዌ ሰፋፊ የነጮች ይዞታ የነበሩ የእርሻ መሬቶች ለአገሬው ሲከፋፈሉ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የተቀሱት ኪማኒ፣ በደቡብ አፍሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች የተደረጉ ሪፎርሞች ወጣቶችን ረስተዋል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ በዓለም ከሚገኘው ያልታረሰ ሰፊ መሬት ውስጥ 60 በመቶው በአፍሪካ የሚገኝና እስከ 200 ሚሊዮን ሔክታር የሚገመት ስፋት ያለው ቢሆንም፣ ወጣቶችን ከዚህ መሬት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕድሎችን መንግሥታቱ መዘርጋት እንደሚገባቸው ምሁሩ ገልጸዋል፡፡

ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከሚወሰዱ ልዩ ልዩ የፖሊሲ መፍትሔዎች ውስጥ መሬት ሲካተት እንደማይታይ የገለጹት ኪማኒ፣ እንደ ብራዚልና ሜክሲኮ ባሉ አገሮች ውስጥ ወጣቶችን የመሬት ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የመሬት ፈንድ ፕሮግራሞች እየተተገበሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ይህ ሲደረግ ግን አይታይም፡፡

በብራዚልና ሜክሲኮ ወጣቶች የመሬት ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን የበቁት በአካቢያቸው የሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎችን በመውረር መውሰድ በመጀመራቸው የተነሳ እንደሆነ የጠቀሱት ኪማኒ፣ በአፍሪካም እንዲህ ያሉ ክስተቶች ከመምጣታቸው በፊት መንግሥታት ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ለወጣቶች የሚበጁ አሳታፊና አካታች የመሬት ተጠቃሚነት ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ፣ ያሉትም ከወጣቶች ተጠቃሚነት አኳያ በመቃኘት እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል፡፡

በአፍሪካ የእርስ በርስ ግጭት ከሚያስከትሉ መንስዔዎች መካከል የመሬት ይዞታና የከብት ግጦች እንዲሁም የውኃ ሀብት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከ90 በመቶ በላይ አብዛኛው የአፍሪካ መሬት በባህላዊ መንገድ፣ በጎሳ መሪዎች የሚተዳደርና በመንግሥት ባለመመዝገቡ ጭምር ወጣቶችን ከመሬት ባለቤትነት ውጭ ያደረገ ሥርዓት እንደሆነም ምሁራኑ ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ 65 በመቶው ከ25 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኘውን ወጣት ክፍል እንደሚወክል የጠቀሱት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ አብደላ ሐምዶክ (ዶ/ር)፣ አፍሪካ ይህንን አካል የሚያሳትፍ የመሬት ፖሊሲ የመቅረፅና የመተግበር ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰናዳው በዚህ ስብሰባ ወቅት በርካታ መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቅኝት ያላቸው ውይይቶች እንደሚደረጉ ሲጠበቅ፣ የአፍሪካ መንግሥታት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ካሳለፉት የአሳታፊ የመሬት ድንጋጌዎች አኳያም ትኩረት የሚደረግባቸው ሐሳቦች እንደሚንሸራሸሩ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታና ባለቤትነት ጉዳዮች ላይ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ያሳተመው የማኅበራዊ ጥናት መድረክም በአገሪቱ የገጠር አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች የመሬት አልባነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ይፋ ያደረገበት የቅርብ ጊዜ ጥናት ይታወሳል፡፡