Skip to main content
x
ረቂቅ የሊዝ አዋጁ አዳዲስ ለውጦች ይዟል

ረቂቅ የሊዝ አዋጁ አዳዲስ ለውጦች ይዟል

  • አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በምደባ የማቅረብ ጉዳይ አልለየለትም

የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው ወረፋ የተያዘለት የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 በድጋሚ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ፣ ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስ ለውጦች ተደርገውበታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ ከኅዳር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲተገበር በቆየው የሊዝ አዋጅ ያልተካተቱና ተካተውም ቢሆን፣ የአሠራር ክፍተት የፈጠሩ አንቀጾች መሻሻላቸው ተመልክቷል፡፡ 

በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ ከተደረጉት መካከል ተነፃፃሪ ካርታ ያላቸው ባለይዞታዎች ማልማት ያለመቻላቸው፣ የማስፋፊያ መሬት የሚፈልጉ ፕሮጀክቶች መስተናገድ ያለመቻላቸው፣ አከራካሪ ቢሆንም አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ቦታ በምደባ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ ለውጥ ተደርጓል፡፡

በንፅፅር ካርታ በአንድ ግቢ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ይዞታዎች በያዙት መሬት ስፋት ሲመዘኑ፣ አብላጫ ወደያዘው አካል እንዲጠቃለል በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክቷል፡፡

የመሬት ስፋት ብልጫ የያዘው አካል አነስተኛውን የሚጠቀልል በመሆኑም ለተነሽ ባለይዞታዎች አስፈላጊው የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ፣ ለሕጋዊ የመንግሥት ቤት ተከራዮች ምትክ ቦታ እንደሚመቻችና ዝርዝሩ በደንብ እንደሚወሰን በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክቷል፡፡

ይህ አሠራር ከዚህ ቀደም ሲል በወጣው አዋጅ ላይ ባለመደንገጉ በርካታ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ሲቀርብ የቆየ ሲሆን፣ በተለይ የንፅፅር ካርታ ያላቸው የግል ባለይዞታዎች ንብረታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብና አሮጌ ቤቶቻቸውን ለማደስ ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የማስፋፊያ ቦታ ነው፡፡ ከኅዳር 2004 ዓ.ም. በፊት ቦታ ተሰጥቷቸው ግንባታ ያካሄዱ ባለሀብቶች፣ ፕሮጀክታቸውን ለማስፋፋት ቦታ በሚጠይቁበት ወቅት በሊዝ አዋጁ ባለመፍቀዱ አይስተናገዱም ነበር፡፡ አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ግን ከነባሩ ፕሮጀክት አጠገብ በቂ ቦታ ካለ፣ በምደባ ቦታ ሊፈቀድ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡ በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ፕሮጀክቶቻቸውን ለማስፋት ላለፉት አምስት ዓመታት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ መስተናገድ ያልቻሉ በርካታ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በከተማው ይገኛሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በምደባ ቦታ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ የሊዝ ሥሪት በይፋ የተጀመረ ቢሆንም፣ በኅዳር 2004 ዓ.ም. በድጋሚ የወጣው የሊዝ አዋጅ ለመሻሻሉ መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የሙስና መንሰራፋት ነው፡፡

በረቂቅ አዋጁ ለማብራራት በተዘጋጀው ሰነድ ላይ እንደተቀመጠው ኪራይ ሰብሳቢነትን (ሙስና) ለመቀነስና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በግልጽ የተቀመጠው ድንጋጌ መሬት በጨረታ ማስተላለፍ ነው፡፡ በተለይ ለመኖርያ ቤትና ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት በመደበኛ ጨረታና በልዩ ጨረታ መሬት የማስተላለፍ ጉዳይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

‹‹የመሬት ምደባ፣ አቅርቦትና አሰጣጥ በምን አግባብ እንደሆነ፣ እንዲሁም የማስተላለፊያ ዋጋ በየትኛው የሊዝ መነሻ መሆን እንዳበት ባለመመላከቱና ግልጽ ድንጋጌ ባለመቀመጡ፣ መሬት በምደባ የማስተላለፍ አሠራር በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መካከል የተለያዩ አሠራሮች በመተግበር ላይ ይገኛሉ፤›› በማለት ረቂቅ አዋጁን በሚያብራራው ሰነድ ላይ ተመልክቷል፡፡

‹‹ይህ አሠራር ለሙስናና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር በመክፈቱ ሕዝብና መንግሥት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በማስቀረት ላይ ይገኛል፤›› በማለት ሰነዱ ያብራራል፡፡

ነገር ግን ረቂቅ አዋጁም ቢሆን በምደባ ቦታ ስለሚቀርብላቸው ፕሮጀክቶች ሲያብራራ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ለበርካታ ዓመታት ሲጉላሉ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ሳይጠቅስ አልፏል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በምደባ ቦታ የሚቀርብላቸውን ፕሮጀክቶች ሲዘረዝር ለፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች፣ ለኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ሕንፃዎች ግንባታ፣ ለልማት ተነሽዎች፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በንፅፅር ካርታ ምክንያት ወደ አንድ ለሚጠቃለሉ ባለይዞታዎች፣ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮችና አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚል ነው፡፡

በጥቅሉ በረቂቅ አዋጅ ላይ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በምደባ ይቀርባል ተብሎ መታለፉ፣ አሁንም ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ እንዲቀጥል ሊያደርገው እንደሚችል ይታሰባል፡፡

ሐሙስ ኅዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተወካይ እንዳሉት፣ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ጉዳይ አመራሩንና ሠራተኛውን ሲያወዛግብ የቆየ ነው፡፡

‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በጥልቀት ዓይቶ እንደተረዳውም አዋጁ የአሠራር ክፍተት ያለበት ነው፡፡ አሁንም በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር አለመቀመጡ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉ ተወካዩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ለስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለከፍተኛ ንግድ ማዕከልና ለዩኒቨርሲቲ ግንባታዎች የቦታ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ለእነዚህ ግንባታዎች መሬት በምን አግባብ እንደሚተላለፍ በግልጽ ባለመደንገጉ፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ባለሙያዎችም ሆኑ ካቢኔው መግባባት ላይ ባለመድረሳቸው አልሚዎች መስተንግዶውን ሳያገኙ እስካሁን ቆይተዋል፡፡ ረቂቁ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በሚል ብቻ በድፍኑ በመታለፉ፣ የቀድሞውን አለመግባባት ሊደግመው እንደሚችል ከወዲሁ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

በወቅቱ ረቂቅ አዋጁን አስመልክተው የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም አድማሴ፣ ‹‹በአዋጅ ቁጥር 721/2004 ዓ.ም. አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በምደባ ይፈቀዳል፡፡ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅም አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በምደባ ይፈቀዳል፡፡ ነገር ግን ድንጋጌው ያላግባብ እየተተረጎመ በመሆኑ አሁን ለያይተን አስቀምጠናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዝርዝሩን ክልሎች በሚያወጡት ደንብ ላይ ይቀመጣል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አምባቸው መኰንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በወቅቱ የተነሳው አለመግባባት መንስዔ ሁለት አንቀጾች በመቀላቀላቸው ነው፡፡ ማኅበራዊ ተቋማትን የመሳሰሉ የአገልግሎት መስጫዎች በልዩ ጨረታ ይስተናገዳሉ በማለት፣ አሁንም በምደባ ሳይሆን በልዩ ጨረታ እንደሚስተናገዱ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ ከአምራች ኢንዱስትሪ በስተቀር የሊዝ ባለይዞታዎች ግንባታ ሳይጀምሩ ወይም ከግማሽ በላይ ሳያጠናቅቁ በዋስትና ማስያዝና በካፒታል አስተዋጽኦ ለመጠቀም የሚፈቀድላቸው፣ በከፈሉት የሊዝ ክፍያ ልክና በቦታው ላይ በፈሰሰው ንብረት መጠን ብቻ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡

ከዚሁ ጋርም ማንኛውም ሰው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ ግንባታ ሳያጠናቅቅ የሊዝ መብቱን ማስተላለፍ እንደማይችል፣ የሊዝ መብቱን ለሦስተኛ ወገን አስተላልፎ ቢገኝ ለተከታታይ አምስት ዓመታት በማንኛውም የሊዝ ጨረታ መሳተፍ እንደማይችል በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩልም ረቂቅ አዋጁ በከተሞች በሕግ ከተፈቀደው ይዞታ ጎን፣ በግለሰቦች ተይዘውና ታጥረው የሚገኙ በርካታ ራሳቸውን ችለው የማይለሙ ቁራሽ ቦታዎች በስፋት እንደሚገኙ በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ የከተማ አስተዳደሮች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ በማድረጉ፣ ቁራሽ ቦታዎች ወደ ግለሰቦች የሚካተቱበት ዕድል በረቂቅ አዋጁ ላይ ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ አዋጁ የጨረታ ማስከበሪያ ከአምስት በመቶ ወደ 25 በመቶ ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን መሞከሩ ተገልጿል፡፡  

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ በወቅቱ እንደገለጹት መሬት የሕዝብና የመንግሥት እንደመሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱ የተፈጥሮ ሀብትና መሬትን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ሕግ እንደሚያወጣ፣ ክልሎች ደግሞ እንደሚያስተዳድሩ መደንገጉን አመልክተዋል፡፡

‹‹ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ያልተካተቱና ቢካተቱም ክፍተት የታየባቸውን ጉዳዮች ለማስተካከል በጥንቃቄ ተዘጋጅቷል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በኅዳር 2004 ዓ.ም. የወጣው የሊዝ አዋጁ በአገሪቱ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ የተቀረፀ ነው፡፡ ረዥም ርቀትም ይዞን መጥቷል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ካለችበት የዕድገት ደረጃ ግስጋሴና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም ስላለበት ተሻሽሏል፤›› ብለዋል፡፡