Skip to main content
x

ኢትዮጵያዊነት በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል - ይዘምናልም

(ክፍል አንድ)

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

ብሔር ብሔረሰብ የሉም ማለት ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም እንደ ማለት ነው፡፡ የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ዕውቅና አለመስጠት አገራችን ዴሞክራሲ አያስፈልጋትም እንደ ማለት ነው፡፡ በእኔ አመለካከት የሥልጣኔ ማማ የነበረችው ኢትዮጵያችን በመሳፍንት ሥርዓት እየደቀቀች ብትሄድም፣ ሕዝቦች ባደረጉት ትግል በዓደዋ ላይ ነፃነታችንን ያረጋገጥን መሆናችን አሁንም በነፃነት አስበን የሚበጀንን ሕገ መንግሥት አፅድቀን የዓደዋን ድል እያደስን እንገኛለን፡፡ ነፃነታችን በሚመለከት አብዛኛው ስማችን አልዶ፣ ሉቺያ፣ ጀምስ፣ ወዘተ ወይም አብዛኛው አካባቢያችን ፒያሳ፣ ካዛንቺስ ወዘተ አለመሆኑ አይደለም፡፡ በነፃነት አስበን የሌሎች ሐሳብ ቀምረን የሚያስፈልገንን ብቻ ወስደን፣ ግን  ተመፅዋች ሳንሆን የመሰለንን ማድረግ ስንችል ነው፡፡ በዓደዋ የአፍሪካና የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት እንደሆነው ሁሉ በ21ኛው ክፍለ ዘመንም የህሊና ነፃነታችንን በመጠበቅ፣ ለመላው ዓለም ተምሳሌት የሚሆን ሕገ መንግሥት ሠርተን በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሽግግር ላይ እንገኛለን፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች በአስተሳሰባቸው ነፃነታቸውን ባለመረጋገጣቸው፣ የአውሮፓና የአሜሪካን ሕገ መንግሥት እንዳለ ቀድተው ስማቸውን ብቻ ቀይረው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ እኛ ፈር ቀዳጅ የተባለውን ብሔር ተኮር የፌዴራላዊ ሥርዓት ከነሙሉ መብቶች ተቀብለን አደጉ ተመነደጉ ለሚባሉትም ተምሳሌት ሆነናል፡፡

    ኩቤክና ካናዳን፣ ስኮትላንድና ታላቋ ብሪታንያን ያስተውሏል፡፡ ስፔን የካታሎናዊያን ጉዳይ በኃይልና በሕግ ለመፍታት እየተራወጠች ባለችበት ጊዜ እንደ ቢቢሲ በቅርብ ቀን ዘገባ፣ ‹‹The Spanish Government Will Consider Holding A Nationwide Referendum On Changing The Constitution To Allow For Legal Independence Referendums, The Foreign Minister Says›› እኛ ከ27 ዓመታት በፊት አንድነት በኃይል እንደማይሆንና የኢትዮጵያ አንድነት መሠረት ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በዋናነት ለዛሬም ለነገም የሁሉም ሕዝቦችዋ ዋስትና ለሁሉም ሕዝቦችዋ የሚጠቅም በመሆኑ፣ በመፈቃቀድ ብቻ የተመሠረተ አንድነት እንዲሆን የእነ ዋልልኝ መኰንን ተራማጅ ሐሳብ በሕገ መንግሥታችን አስፍረን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ይኼም ሆኖ ለዘመናት የሰፈነውና አሁንም እያስቸገረን ያለው መስፍናዊ ኋላ ቀር ፖለቲካዊ ባህል፣ የኢትዮጵያ አንድነትን ከሁለት አቅጣጫ የሚነሱ ከፍተኛ ተግዳሮች እያጋጠመው ነው፡፡ በአንድ በኩል ስለሕዝቦች ሳይሆን ስለመሬትና አየር አንድነት ማዕከል አድርጎ የአንድ ሕዝብ፣ ሃይማኖትና መንግሥት ጠቅላይ አግላይ አስተሳሰብና ተግባር፣ በሌላ በኩል በአግላይ ብሔራዊነት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያን እንወዳለን ማለት በዋናነት ሕዝቦችዋን መውደድ ማለት ስለሆነ፣ ጠቅላይና አግላይ ኢትዮጵያዊነትን በማውገዝና አግላይ ብሔራዊነት በመታገል፣ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አገሪቷ በሁለቱም ፅንፍ አስተሳሰቦች እንዳትናወጥ ሕዝቦችዋን በማስተማር መታገል ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ሲባል በመጀመርያ ስለማንነት፣ የማንነቶች ብዝኃነትና የማንነት ቅራኔዎች ከቀረቡ በኋላ ብሔርተኝነትና አገራዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመሳሰሉት ተግዳሮቶች መሠረት ካለውና ወሰን ከሌለው የሕዝቦች መብት የሚቀዳ ኢትዮጵያዊነት በሚል መፍትሔ ይደመድማል፡፡

ማንነት (Identity)

ሰብዓዊ ፍጡር ከሌሎች እንስሳትና ሌሎች ነገሮች ሲነፃፀር ተመሳሳይነት ቢኖረውም፣ በውስጡ ደግሞ በተለያዩ ማንነቶች ይገለጻል፡፡ ኅብረተሰብ ደግሞ በዘር ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ ወዘተ፡፡ አፍሪካ አውሮፓ፣ እስያ፣ አሜሪካ፣ ወዘተ፡፡ በክፍለ ዓለማት፣ በአፍሪካ ውስጥም ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ ወዘተ፡፡ በአንድ አገር ደግሞ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ፆታ፣ ሙያ፣ ወዘተ፡፡ በአንድ ብሔር ውስጥም የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ላብ አደር፣ ባለሀብት፣ ባል ሚስትና በትውልድ ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ወዘተ ያሉ ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ ላውለር (2008፣ 04) የተባለ ጸሐፊ፣ ‹‹The Concept Of Identity Is Centered On The Paradoxical Merger Of Sameness And Uniqueness›› ይለዋል፡፡ አንድነት የሚኖረው ልዩነት ሲኖር ነው፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሆኖ ልዩነትን ያለ አንድነት፣ አንድነትን ያለ ልዩነት ሊገልጸው አይችልም፡፡ አንድነት የሚለው ንድፈ ሐሳብ (Concept) የተለያዩ ማንነት ያላቸው ግን የጋራ ማንነት እንዳለቸው የሚገልጽም ነው፡፡ ሩሜንስና ጓደኞቹ (2003:02 “The Recognition Of Socially-Silent Similarities And Differences Forms The Very Corner-Story Of Social Interaction” ይላሉ፡፡ ሰብዓዊ ግንኙነት ማዕከሉ ተመሳሳይነትና ልዩነት መሆኑ ነው፡፡ ሰዎች፣ አገሮች፣ ብሔሮች ተመሳሳይ በመሆናቸው ተደጋግፈው በዓለም ላይ ያለውን ፀጋ አብረው ይጠቀማሉ፡፡ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አብረውም ይታገላሉ፡፡ ልዩነት ስላላቸው ደግሞ ከዚያ የሚመነጨውን በአስተሳሰብ ብዝኃነት ማስተናገድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የሠለጠነ ወይም ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ልዩነትን እንደ ፀጋ የሚወስደው ለዚህ ነው፡፡

የወል ማንነት (Collective Identity)

የሰው ልጅ እንደ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ነገድ፣ ብሔር፣ አገር፣ ወዘተ ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ የግለሰብ ማንነት ቢኖረውም እንደ ማኅበራዊ እንስሳ የቡድን የወል ማንነት አለው፡፡ የወል ማንነትን በተመለከተ የሀርቫርዱ ኢብዴላልና ጓደኞቹ (2009፡ 18-19) እንዲህ ይላሉ፡፡ የወል ማንነት በይዞታ (Content) እና በሚሟገቱና በሚወዳደሩ (Contestation) ሁለት አቅጣጫዎች የሚፈስ ማኅበራዊ ምድብ (Social Category) ብለው ይተረጉማሉ፡፡ ቀጥለውም ይዞታ የወል ማንነትን ትርጉም የሚገልጽ ሆኖ አራት የሚደጋግፉ ዓይነቶች ቅርፅ ሊይዝ ይችላል ይላሉ፡፡ 

  • መደበኛ (Formal) እና መደበኛ ያልሆኑና (Informal) ቡድኑን የሚገልጹ ሕጎች
  • የቡድኑ ማኅበራዊ ዓላማ የሚገልጹ የጋራ ግቦች
  • ራሳቸውን የሚገልጹበትና ከሌሎች የሚለዩበት ወሳኝ መግለጫዎች
  • ፖለቲካዊና ቁሳዊ (Material) ሁኔታና ጥቅሞች የሚገልጹበት የጋራ ራዕይ ናቸው፡፡

የሚሟገቱና የሚወዳደሩ (Contestation) በየትኛውም ማንነት የጋራ ይዞታ ትርጉም ላይ ያለ ስምምነት ወይም ልዩነት የሚገለጽ ነው፡፡ ማንነቶች በጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ስለሚለዋወጡና ስለሚያድጉ አባሎቹ ላይ በተገለጹት አራት የይዞታ ዓይነቶች የሚስማሙበትን ያህል የሚለያዩባቸው ይኖራሉ፡፡ በሕጎች፣ ግቦች፣ መግለጫዎችና ራዕይ ቀጣይ የሆነ ስምምነትና ልዩነት ይኖራቸዋል ይላሉ፡፡ ታላቋ ብሪታንያ የተለያዩ ብሔሮች አገር ናት፡፡ እንግሊዝ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስና ሰሜን አየርላንድ፡፡ የስኮትላንድ ብሔር ታላቋ ብሪታኒያ ከተቀላቀለ ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ሆነዋል፡፡ ሲቀላቀሉ የነበረው የስኮትላንድ ማንነት በየጊዜው እየተሠራ፣ እየፈረሰ እንደገና እየተሠራ (Constructed And Deconstructed) ብዙ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የስኮትላንድ ማንነት የሚባል አለ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014. በብሪታኒያ ውስጥ ለመቀጠል ወይም ተነጥለው በራሳቸው ነፃ አገር ለመመሥረት ሕዝበ ውሳኔ አካሂደዋል፡፡ ታይቶ በማይታወቀው የመራጭ ብዛት 44.7 በመቶ የሚሆኑት ነፃ አገር እንመሠርታለን ሲሉ፣ 55.3 በመቶ ደግሞ የለም ባለንበት እንቆያለን ብለዋል፡፡ 44.7 በመቶ የሚሆኑት ታላቋ ብሪታኒያ የምትባል አገር አንፈልግም፣ የራሳችን አገር እንፈልጋለን እያሉ ነው፡፡ የስኮትላንድ ማንነት ዓለማና ግብ እንዲሁም በውስጣቸውና ከታላቋ ብሪታኒያ ጋር ባለው ግነኙነት ከፍተኛ ልዩነት እየታየ ነው፡፡ የሰሜን አየርላንድ ክልል ሕዝቦችም በሃይማኖት ጭምር ተለያይተው ግማሹ ወደ አየርላንድ ለመቀላቀል ሲፈልጉ፣ የሚበዙት በታላቋ ብሪታንያ ሥር ለመቆየት ይፈልጋሉ፡፡ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የነጭ ዘረኝነት ማንሰራራት ተከትሎ በአሜሪካ ፉትቦል (NFL) ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች የማይነካ የሚመስለውን የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ቆመን አንዘምርም ማለታቸው፣ በተለይ አፍሪካ አሜሪካዊያን ተጫዋቾች አሜሪካ ከሚባለውና በሚታወቀው ማንነት ላይ ጥያቄ እያነሱ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በስፔን ካታሎኒያ የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ከሰጠው 92.01 በመቶ ነፃ አገር እንፈልጋለን እያለ ነው፡፡ የመጨረሻው ውጤት ምን ይሁን ምን ያን ያህል ሕዝብ እኛ ስፔናውያን አይደለንም የራሳችን አገር እንፈልጋለን እያለ ነው፡፡

 በየትኛው ሥፍራ የአገር ማንነት ጥያቄ የማይነሳበት አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት አገሮች በውስጣቸው በሚገኙ ሕዝቦች ፈቃድ ሳይሆን በኃይል የተመሠረቱ ስለሆኑ ነው፡፡ የአውሮፓ አገሮችን አመሠራረት ሚካኤል ሪር (2012፡37) እንዲህ ይላል፡፡ “Between The Fourteenth And The Twentieth Centuries, The Number Of Political Entities” In Europe Went From Approximately One Thousand To A Mere Twenty Five And That Process Of Consolidation Was Accomplished Largely By Force.” ማንኛውም አሁን ያለው አገር በውዴታ ብቻ የተመሠረተ የለም፡፡ በኃይልም ጭምር እንጂ፡፡ አገሮች በውዴታ ብቻ ቢመሠረቱ ኖሮ የማንነት ጉዳይ በተለይ የብሔር ማንነት ጉዳይ በላላ ነበር፡፡ የመደብና ሌሎች ማንነቶች ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ አገሮች በግዴታና በኃይል የተመሠረቱ በመሆናቸው የተለያዩ ብሔሮችን አጭቀው ይገኛሉ፡፡ ከአገር ግንባታ አንፃር ረጅም ርቀት ተጉዘዋል የሚባሉት የአውሮፓ አገሮች እንኳን፣ የብሔር ጥያቄ በበርካታ አገሮች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በስፔን፣ በጣሊያን፣ በቤልጂየም፣ በታላቋ ብሪታንያ፣ በስዊዘርላንድ፣ ወዘተ የታየ ነው፡፡ በሥርዓታቸው ልዩነት ካለ የብሔር ልዩነት ተቀብሎ አቃፊ ወይም አግላይ በመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ደግሞ የአቃፊነቱ ደረጃ ያለው ልዩነት ነው፡፡

የማንነቶች ብዝኃነት (Multiple identities)

አንድ ሰው ወይም አንድ የኅብረተሰብ አካል የብዙ ማንነቶች (Multiple Identities) ባለፀጋ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ የአንድ ቤተሰብ አካባቢ፣ ብሔር፣ አገር ወይም ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ሴት ወይም ወንድ፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወይም ደግሞ ላብ አደር፣ ቡርዧ፣ ገበሬ፣ ምሁር ወታደር፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ማንነቶች በተለያዩ ደረጃዎች ግለሰቡ አካሉ ውስጥ ህያውና ተደማሪ በሆነ መልኩ ተቀናጅተው ሰውዬውን ወይም አካሉን ይገልጹታል፡፡ ከሁሉም ማንነቶች አንድ ወይም ሁለቱ ግን በጊዜና በቦታ (Space) ጎልተው የማንነቱ ዋነኛ መገለጫ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንድ አካል ያሉ ማንነቶች እንደሚሰማሙ ሁሉ የተለያዩ ቅራኔዎችንም ያዘሉ ናቸው፡፡ ማንነት በጊዜና ዓውድ (Context) ሊለያይ ይችላል፡፡

የማንነት ቅራኔዎች (Identity Conflicts)

ቅራኔ (Conflict) የፖለቲካ ማዕከል (Cornerstone) ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ፖለቲካ ስንል የአንድ ማንነት (አገር፣ ብሔር፣ ፆታ፣ መደብ፣ ሃይማኖት፣ ሙያ፣ ወዘተ) ቁሳዊ ጥቅሞችንና እሴቶችን ለመጠበቅና ለማዳበር የሚደረግ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፖለቲካ በእነዚህ ጥቅመቶችና እሴቶች ዙሪያ ያለውን ቅራኔዎች በሰላማዊ ሆነ በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ለዚያ ነው ጦርነት የፖለቲካ የሰላ ጫፍ ነው የሚባለው፡፡ ሰዎች እንደ እንስሳ በንዋታዊ ቅራኔ ተዘፍቀው ይኖራሉ፡፡ እንደ ማኅበራዊ እንስሳ (Social Animal) ደግሞ የእሴት ልዩነት ወደ ቅራኔ ያመራል፡፡ አንዳንድ ምሁራን ሁሉም ቅራኔዎች የማንነት ቅራኔዎች (All Conflicts Are Identity Conflicts) ናቸው ይላሉ፡፡ በኔ ዕይታ ይኼ ዕይታ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ቁሳዊ ጥቅምና እሴት ተዋድደው የሚገለጹት በማንነት በመሆኑ፡፡ የመደብ ትግል በላብ አደርና በቡርዣ ንዋታዊና እሴታዊ ግጭት ማዕከል አድርጎ ይካሄዳል፡፡ በሃይማኖት ስም ሲካሄዱ የነበሩትና ያሉት ጦርነቶች የዕምነት ብቻ አልነበሩም አይደሉምም፡፡ ቁሳዊ ጥቅምን ማን የበለጠ ያረጋግጥ ጭምር ነው፡፡ የፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ትግልም የወንድ የበላይነት የሚባለውን መጥፎ እሴት አስወግዶ፣ ፖለቲካዊ እኩልነት የሚባል እሴት ለመተካት ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የማግኘትና የማጣት ጭምር እንጂ፡፡

 በአገሮች መካከል ጥቅሞችንና እሴቶችን ለማስጠበቅ ወደ ጦርነት መሄድ እየቀነሰ ቢሄድም አሁንም አልቀረም፡፡ ታዛቢዎች አሜሪካ ኢራቅን የወረረችበት ዋና ምክንያት የተፈጥሮ ሀብቷን (ነዳጅና ጋዝ) ለመዛቅና የሊበራል ዴሞክራሲ እሴቷን ለመጫን ነው ይላሉ፡፡ እንደነዚህ ምሁራን አባባል ለአካዴሚክ ጠቀሜታ ሲባል ቁሳዊ ቅራኔ (Resource Conflict) ወይም የእሴት ቅራኔ ብለን ለየብቻው መግለጽ ቢቻልም፣ እውነታው ግን አንዱ ከአንዱ ለመለየት በማያስችል ሁኔታ ተቆላልፈው ነው የሚኖሩት፡፡ በየትኛውም አገር የብሔር ደረጃ ሲታይ የተለያዩ ማንነቶች በተለያዩ ወቅቶች ኅብረተሰብን ለፖለቲካ ለማሳለፍ የተለያዩ አቅሞች ይኖሩዋቸዋል፡፡ የመደብ ትግል፣ በአገሮች መካከል የሚደረግ ትግል፣ የብሔር ትግል ወዘተ አንዴ አንዱ ጎልቶ ሌላ ጊዜ ሌላው ተደብቆ (Hibernate) የሚያደርጉበት ነው፡፡ ከስፔን መገንጠል አለብን ብለው የመረጡት ካታላውያን (Catalian) የመደብ፣ የፆታ፣ ምናልባትም የሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት በውስጣቸው መኖሩ የግድ ነው፡፡ ከስፔን ጋር ያለውን ቅራኔ ለመፍታት ቅድሚያ በመስጠት ግን ሌሎች ግጭቶችን በሁለተኛ ደረጃ ዓይተው ያቆያሉ፡፡

ብሔርነተኝነትና አገራዊነት

አማኑኤል ካስቴል (2004፡01) ‹‹Our World, And Our Lives, Are Being Shaped By The Conflicting Trends Of Globalization And Identity. The Information Technology Revolution, And The Restructuring Of Capitalism, Have A New Form Of Society.” ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ናት በተባለበት ሁኔታ የማንነት ፖለቲካ በዓለም ደረጃ እያገረሸ የመጣበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ልክ የግሎባላይዜሽን ለውጥ መቀበል የግድ እንደሚሆን ሁሉ፣ የማንነት ፖለቲካን የግድ ተቀብለን ለኅብረተሰብ አዎንታዊ ለውጥ እንዴት እንጠቀምበት ማለቱ ብቻ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ የማንነት ፖለቲካ የለም ወይም እንዲኖር አንፈቅድም ማለት ‹‹የሰጎን ፖለቲካ›› ነው የሚሆነው፡፡ ላለማየት ዓይንን አሸዋ ውስጥ እንደ መደበቅ ይታሰባል፡፡ በአውሮፓ እንደ እነ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ወዘተ የማንነት ፖለቲካ እያናወጣቸው ይገኛል፡፡ የካሊፎርኒያና የቴክሳስ ግዛቶችን በተለያዩ ምክንያቶች የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ቡድኖች በአሜሪካ መከሰታቸው ራሱ አቅጣጫ አመላካች ነው፡፡ ማርክሲስቶችና ሊብራል ዘመናውያን (Liberal Modernists) ብሔር ተኮር ማንነት መሸጋገሪያ እንደሆነና በግሎባላይዜሽን እየከሰመ እንደሚሄድ ይተነብዩ ነበር፡፡ ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው፡፡ ሩዶልፍ (2003) ብሔርተኝነት በዓለማችን ካሉ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች መካከል ቁልፍ ከመሆኑ ባሻገር ቀጣይነቱ እየሰመረ ይገኛል ይላል፡፡ ይኼ የሩዶልፍ ሐሳብ በሀችንሰንና ስሚዝ (1996) ድጋፍ ተችሮታል፡፡ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ብሔርተኝነት በማናቸውም አኅጉር በፖለቲካና በማኅበራዊ ሕይወት ቁልፍ ቦታ እየያዘ ሲሆን የመደብዘዝ ሁኔታ በጭራሽ እየታየ አይደለም ይላሉ፡፡ ምንም እንኳን አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግሥታት ይኼንን ሀቅ ቢክዱም፣ በብሔር ጉዳይ ለሁሉም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ማዕከል እየሆነ መሆኑም አላጌ (2004) የተባለው ምሁር ይገልጻል፡፡ ሳላህ (2001፡21) ‹‹ምንም እንኳን የአፍሪካ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች የራሳቸውን ብሔር መሠረት አድርገው የተፈጠሩ ቢሆንም፣ የአፍሪካ መሪዎችና ልሂቃን ሕዝቦቻቸው ብሔርን መሠረት አድርገው ፓርቲዎች እንዲያቋቁሙ ይከለክላሉ፤” ብሏል፡፡

የአፍሪካ ሕዝቦች በቅኝ ገዥዎች በተፈጠሩት አገሮች በጋራ ዕጣ ፈንታቸው ላይ ባላቸው ዕምነት ለአገረ መንግሥት ያላቸው ታማኝነት ዝቅተኛ ነው፡፡ ሲጀመር አፍሪካውያንን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ሲያስተዳድሯቸው ከነበሩት ቅኝ ገዥዎች በኋላ ሥልጣን ላይ የወጡት አፍሪካውያን ልሂቃን የተሻሉ አልነበሩም፡፡ አፍሪካውያን ከመንግሥታቸው ይልቅ አባል ከሆኑበት ብሔር ወይም የሃይማኖት ቡድን የጠነከረ ግንኙነትና ታማኝነት አላቸው፡፡ ድህነታቸውን፣ ዕድገታቸውን፣ ሁሉንም ነገራቸውን ከብሔር ከሃይማኖት ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ በዚህም ምክንያት በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ያለው ግጭት፣ በዋናነት በብሔርና በጎሳ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በቅርቡ በኬንያ የተደረገው ምርጫ እንደሚያመላክተው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአብዛኛው በብሔር ጎሳ ስም ባይጠሩም መራጩ በአብዛኛው በሚያምነው ግን በብሔር በጎሳ አባል ነው፡፡ ቢቢሲ እንደገለጸው፣ የፕሬዚዳንቱና የምክትል ፕሬዚዳንቱ ብሔር አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ምርጫ ሲጎርፉ፣ ተቃዋሚዎች በምርጫው አለመሳተፍ ጥሪ በተወዳዳሪዎቹ ኦዲንጋና ሽርካቸው ብሔር አባላት ተቀባይነት በማግኘቱ እዚያ አካባቢ ምርጫው ከሽፏል፡፡

 ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛችና ነፃነትዋን አሳልፋ ያልሰጠች ብትሆንምና የራስዋ የረዥም ጊዜ መንግሥት ቢኖራትም፣ ኢትዮጵያዊ አገራዊነት የተሻለ መሠረት ቢኖረውም፣ አንድ ጊዜ እየሰፋች ሌላ ጊዜ እየጠበበች እንዲሁም ማኅበረ ኢኮኖሚዋ የደቀቀ በመሆኑ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ የመገናኘት ዕድላቸው አነስተኛ ስለሆነ ከላይ ስለአፍሪካውያን የተገለጸው ይመለከታታል፡፡ የማንነት ፖለቲካ በዓለም ደረጃ እየተከሰተ ያለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ ሆኖ ብሔርተኝነትን ልንክደው የማንችል ቁልፍ ክስተት ሆኗል፡፡ በፀረ ደርግነት የተሠለፉት ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች (ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ወዘተ)፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ድርጅቶች (ሕወሓት፣ ኦነግ፣ ወዘተ) ነበሩ፡፡ ኢሕአፓ በነበረው የምሁራን ስብስብ፣ የአባላቱ ቆራጥነትና የተሻለ ዓለማዊ ዕውቅና ለምን አላሸነፈም የሚለው ጥያቄ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢችልም፣ ከኢሕአፓ ተገንጥሎ የወጣው ኢሕዴን ግን ከብሔራዊ ድርጅቶች ጋር ተሰልፎ ድል መጎናፀፉ አመልካች ነው፡፡ በእኔ ዕምነት ኢሕአፓ በመጀመርያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚል አቋም ቢኖረውም፣ በሒደት ግን ብሔራዊ ድርጅቶች ለአገራዊ የመደብ ትግል አደናቃፊዎች ናቸው የሚል አቋም ስለነበረውና ብሔራዊ ትግል ቢኖርም በኢሕአፓ ሥር መሆን አለባቸው የሚል ግትር አቋም በመያዙና ሕዝቦችን ማሳለፍ ባለመቻሉ ነው፡፡  ኢትዮጵያዊ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትና ብሔርተኝነት ጎን ለጎን ያሉ ማንነቶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ብሔርተኝነት ጎላ ብሎ የሚታይበት ሁኔታ እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያዊነትና ብሔርተኝነት ያላቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት መሠረት አድርገንና አዋህደን ፖለቲካው ካልተመራ፣ አንደኛውን መካድ ጥፋት እንጂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት አያመጣም፡፡

የኢትዮጵያዊነት እንቆቅልሽ

በ1899 ዓ.ም. (ከመቶ አሥራ አንድ ዓመት በፊት) በደብተራ ፍስሀ ጊዮርጊስ ግብይዝጊ ‹‹ታሪክ ኢትዮጵያ›› በሚለው የትግርኛ መጽሐፍ ኢትዮጵያ ስም አጠራር በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንዲህ ይላል፡፡ ከሰባቱ ከነዓናውያን አንዱ የሆነው ‹ኩሳ› የደረሰውን አገር በልጁ በኢትዮጵያ ሰየመው፡፡ አገርዋም ኢትዮጵያ ተባለች፡፡ በእሳቸው አጻጸፍ መሠረት አገራችን በሦስት ስሞች ትጠራለች፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሳባና ሀገረ አግዓዚ ወይም አግዓዚት፡፡ ባሕሩ ዘውዴ (2007፡01) ‹‹ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ መሠረቱ ግሪክ ሲሆን፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በውል ከታወቀችው ከግብፅ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የሚጠራበት አጠቃላይ ስም ነበር፤” ይላል፡፡ ‹አዲስ ጊዜ› ተብሎ የሚጠራው መጽሔት የመስከረም 2010 ዕትሙ እንደ ዘገበው ፓስተር በንቲ ኡጁሉ የተባሉ ፕሮቴስታንት መሪ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የሚለውን መጠሪያ ግሪኮች ያወጡልን ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹የተቃጠለ ፊት› በመሆኑና እኛን ዝቅ የሚያደርግ የዘረኝነት ስያሜ በመሆኑ በ‹ኩሽ› እንጠራ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ 45 ቦታ ኢትዮጵያ ተብሎ የተጠቀሰውን በኩሽ እንዲቀየር አድርገዋል፡፡›› አዲስ ጊዜ፡፡ ‹‹ዛሬ ያለችው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪቃም የኢትዮጵያ ግዛት ስለነበረ ኢትዮጵያ ይባል ነበር›› እና የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ምንጫቸው ቅድመ አባት ኢትዮጵያ የሚባል ሰው እንደሆነ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዳሉ አስነብቦናል፡፡ 100 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በተለያየ መልክዓ ምድር፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የተለያየ ውብ ተክለ ሰውነትና ዘር ያለው ያውም በአራት ሺሕ ዓመታት ከአንድ ሰው ነው የተገኙት የሚለውን ለማመን በጣም ቢያስቸግርም፣ መላው አፍሪካ የኢትዮጵያ ግዛት ነበር የሚለውን ግን ከዓለማዊ ሕግ (International Law) አኳያ የይገባኛል መብት ማንሳት አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ ይጭራል (ተረት ተረት ከፕሮፌሰር ዘንድ አንጠብቅም ከሚል እሳቤ)፡፡

ዶክተር ላጲሶ ጌ ዴሌቦ፣ ‹‹በኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሠረቶችና መሣሪያዎች (1999፡ 04) በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ታሪካዊ መነሻ ስያሜ በሚመለከት ከተጠቀሱት ጥንታዊ የአካባቢው ሕዝቦች፣ በተለይም ሁለቱ ግብፃውያንና አይሁዳውያን ‹ፑንት› ግሪኮች ‹ኢትዮጵያ› ዓረቦች ደግሞ ‹ሐበሻ› በተሰኙ የአገርና የሕዝብ ስሞች እንዲጠሩ ከታሪክ መረጃና ትምህርት ታውቋል፤›› ይላሉ፡፡ የአገራችንን አጠራር ታሪክ በዝርዝር ማየት ለዘርፉ ባለሙያዎች ትተን፣ አሁን ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ያለችን ሕዝቦች ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማስፈን በምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት በጋራና የግል በማንነታችን እጅጉን የተሳሰረ ስለሆነና የድሮ ማንነታችንና የአሁኑ እኛነታችን የወደፊቱ ኢትዮጵያዊነት ምን መምሰል እንዳለበት የጋራ መግባባት መኖር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት የኋላ ታሪክ (Background) ስሌለን ማለት መሐመድ፣ ድሌቦ፣ ገመቹ፣ ሐጎስ፣ ደስታ፣ ዓይሻ፣ ወዘተ ስለሆንን  በአንድ በኩል ከደቡብ፣ ምዕራብ፣ ምሥራቅ፣ ሰሜን፣ ከደጋ፣ ወይና ደጋ፣ ቆላ፣ ወዘተ በሌላ በኩል የተገኘን በመሆናችን፣ ለኢትዮጵያዊነት ያለን አረዳድ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል እያወቅን፣ ለሁላችን በሚያጋራ ኢትዮጵያዊነት ስቴት ላይ አትኩረን ለመሥራት መረባረብ ለሁላችንም ይጠቅመናል፡፡ አንድ ታሪክ ለሌላው ባዶ እንደሆነ የሚያመለክት ኋላቀር አስተሳሰብ ትተን፡፡ ነፃነታችን ጠብቀን የኖርንና በአንድ አካባቢ በመኖራችን ደግሞ በሕዝቦች ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መስተጋብር የተፈጠረች አገር ዋና እሴቶቿ እንደሆኑ በማመን ወደፊት መመረሽ ይጠበቅብናል፡፡

አሰፋ እንደሻው (1993፡ 13) የኢትዮጵያ ብርቅነትን ከገለጸ በኋላ፣ አሁን ያለነው ኢትዮጵያውያን የመልካም እሴቶቿ ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ዕዳ ተሸካሚዎቿ መሆናችንን በማመልከት የገለጸው አባባል ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ‹‹ከእነዚህ መሀል የመንግሥቷ አወቃቀር፣ የብሔረሰቦችና የቋንቋዎች ስብጥር የማያልቅ ትርምስና ግብግብ አስከትለዋል፡፡ ከውጭ ወራሪዎች መዳፍ ማምለጥ ቢቻላትም የተፈጥሮና ሰብዓዊ ሀብቶቿ በቅጡ አቀናጅቶ የሚመራት መንግሥት በማጣቷ ትርምሱና ግብግቡ እንደ ቀጠለ ነው፤›› ይላል፡፡

የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማንነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ማንነት፣ የብሔር ማንነት፣ የሃይማኖታዊ ማንነት፣ የመደባዊ ማንነት፣ የፆታዊ ማንነት፣ ወዘተ ለየብቻም ተሳስረውም ይገኛሉ፡፡ በአገራችን ጎልተው የሚታዩት የኢትዮጵያዊነትና የብሔራዊ ማንነት ቅራኔዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራን የኢትዮጵያዊነትና የብሔር ማንነት ቅራኔ የለም ይላሉ፡፡ የአማራው ልሂቃን የነበራቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ የኢትዮጵያዊነት ሽፋን ስለሚላበሱ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በእኔ ዕምነት ደረጃው ይለያይ እንጂ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ነን ስለሚሉ፣ በብሔራቸውና በኢትዮጵያዊነት መካከል ቅራኔ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ አንድ ግለሰብ በቤተሰቡ ውስጥ የተለያዩ ቅራኔዎች ይኖራሉ፡፡ ያ ቤተሰብ ደግሞ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ቅራኔ ይኖረዋል፡፡ ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሔር፣ አገር እያለም በተመሳሳይ መንገድ ስለሚሄድ ኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሔር ማንነት ቅራኔ መኖሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እነዚህን ቅራኔዎች እንዴት አድርገን በሰላማዊና ዘላቂነት ባለው መንገድ እንፍታው ነው መሆን ያለበት፡፡ ቅራኔዎችን ለመፍታት የኋላ ታሪካችን፣ መንፈሳችንና ስሜታችን ብቻ ሳይሆን የዛሬና የነገ ማንነታችን (ጥቅሞቻችንና እሴቶቻችን) ለማስጠበቅ አንድነት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባለን ዓለማዊ ሁኔታ እንኳን አንድ ብሔር አንድ አገር፣  በማደግ ላይ ያለን አገር ሆነን አደጉ ተመንደጉ የሚባሉት አገሮች እንኳን በእውነት ነፃነታቸውን፣ ደኅንነታቸውንና ልማታቸውን ለብቻ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ መሆኑን ተገንዝበው የተለያዩ ኅብረቶች ለመፍጠር የሚታገሉበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሳንበታተን የጋራ እሴቶቻችን መሠረት አድርገን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ንዋታዊ ጥቅሞችና እሴቶች በእኩልነት በመጠበቅ፣ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችን፣ ድኅነታችንንና ነፃነታችን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ በማያቋርጠው የኢትዮጵያዊነትና ብሔራዊነት ቅራኔዎች የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ በእነዚህ ላይ በሰከነ መንፈስ ተወያይተን የሚበጀንን የጋራ አስተሳሰብ መያዝ ይጠቅመናል ባይ ነኝ፡፡ እነዚህን በሦስት መሠረታዊ አመለካከቶች እከፍላቸዋለሁ፡፡

  1. አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ መንግሥታዊ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ ያለው መንግሥት

ይኼ ከአንድ ንጉሠ ነገሥት (ሞኣ አንበሳ ዘ እምነ ነገር ይሁዳ) አንድ መንግሥታዊ ሃይማኖት (ኦርቶዶክስ) አንድ ሕዝብ (ኢትዮጵያዊ) አንድ አገር (ኢትዮጵያዊ) ከሚል የሚመነጭ አስተሳሰብ በእኔ አመለካከት አግላይም ጠቅላይም ብቻ ሳይሆን፣ የሞተውን ሥርዓት ከመቃብር አውጥቶ ህያው ለማድረግ የሚሞክር ይመስለኛል፡፡ አግላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ44 ከመቶ የማይበልጡት የኦርቶዶክስ ተከታዮችን ማዕከል በማድረግ ከ56 በመቶ በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ያገላል፡፡ ዘ እምነ ነገደ ይሁዳ የሚባለው አስተሳሰብም የከፋው አግላይ ነው፡፡ ምናልባት ከ99 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የሚያገል ነው፡፡ ባሕሩ ዘውዴ (2008፡05) ‹‹… የሷ (ንግሥት ሳባ ማለቱ ነው) ጉዞና ጉዞው ያስከተለው የቀዳማዊ ምኒልክ መፀነስ ሥርወ መንግሥትን እንጂ የአገርን ታሪክ ልደት ስለሚያበስር ነው፡፡ አግላይ ነው ስንለው የሰሜኑን ታሪክ ብቻ የኢትዮጵያ ታሪክ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የሰሎሞናዊ ሐረግን በመጥቀስ፡፡ የዛጉዌ አገዛዝ ሕገወጥ እንደነበር ለማመልከት ጭምር ነው፡፡ ላሊበላን ማዕከል ያደረገውን የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለማግለል የሚቃጣ አባባል ነው፡፡ ይኼ አባባል የአገራችንን ሕዝቦች ልዩ ልዩ ታሪኮች እንዳልነበሩ ያደርጋል፡፡ የደቡብ፣ የደቡብ ምዕራብና የምሥራቅ ሥልጣኔዎች፣ ባህልና ቋንቋዎች በኢትዮጵያዊነት ያላቸውን ቦታ የሚያገል ነው፡፡ ላጲሶ (1999፡81) ዩኔስኮን (UNESCO) ጠቅሶ አገራችን በሁሉም አቅጣጫዎች የደረሰችበትን የሥልጣኔ ማማ ያበስረናል፡፡

የኢትዮጵያ የፖሌኦንቶሎጂና የአርኪዮሎጂ መረጃዎች ግኝት

 

መረጃ የተገኘበት ሥፍራ

 

የመረጃ ዕድሜ በዓመት

 

የግኝቱ ዘመን

1. የሀዳር ሰው አጽም

ከ4,000000 ዓመት በላይ

1973

2. የኦሞ ሰው አጽምና የድንጋይ መሣሪያ

ከ2,000000 ዓመት በላይ

1967-1968

3. የመልካ ቁንጥሬ ሰውና የድንጋይ መሣሪያ

ከ1.5 ሚሊዮን ዓመት በላይ

1965-1976

4. የሊጋኡዳ ዋሻ እንስሳት ሥዕል

4,000 ዓመት

1970-1978

5. የሻቤ ዋሻ እንስሳት ሥዕል

3,000 ዓመት

በ1920ዎቹ

6. የሸዋ፣የአሩሲ፣ የሐረር፣ የሲዳሞ ትክል ድንጋይ ሐውልቶች

የብዙ ሺሕ ዓመታት

በ1920ዎቹ

የደአማት-አክሱም የድንጋይ ላይ ጽሑፎች

2,500 ዓመታት

1959-1973

 

እነዚህና በተደጋጋሚ የሚገለጹትን ጨምሮ ከየትኛው የሥልጣኔ ማማ ወርደን ተመፅዋች የሆንንበት ታሪካችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አሁንም ከዚያ አሳፋሪ ውርደት ገና አልተላቀቅንም፡፡ መስፍናዊ ሥርዓት ይኼ ነው የሚባል ፖለቲካዊና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ማምጣት የተሳነው በመሆኑ፣ ይህችን ታላቅ አገር መቀመቅ አስገባት፡፡ አሰፋ እንደሻው (1999፡ 20) ያንን የበሰበሰ ሥርዓት በዚህ መልኩ ይገልጸዋል፡፡ ‹‹ስድስተኛ የሻገተው አስተሳሰብና ማኅበራዊ ሥርዓት እያዘገሙ ከሚያድጉት የከተማና የገጠር እንቅስቃሴዎች ይበልጥ የገጠጠና ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ረሃብ አገሪቱን በተደጋጋሚ ዓመታት የኖረ ቢሆንም የ1965/66 ድርቅ በሚሊዮኖች የሚገመት የትግራይ፣ የወሎና የሰሜን ሸዋ ሕዝብን በጠኔ መታው፣ በብዙ መቶ ሺሕ የሚሆነውንም ጨረሰ፡፡ ከብቱን፣ አጋሰሱንና ሌላውን የቤት እንስሳ ጨምሮ ሕዝቡን አራቆተው፡፡ የኩሩው ሕዝብ ቅስም በአውሮፓ ምፅዋት ተሰበረ፡፡ ለጥቁር ዘር የነፃነት ምልክት የነበረችው ኢትዮጵያዊ ስሟ አብሮ ጠፋ፡፡ … ዞሮ ዞሮ ያን በመሰለ መከራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲመታ ባንዲራዋ የጥቁሮች የነፃነት ምልክት ሆኖ ከመቅረቱ በስተቀር፣ የታሪኳ ገናናነትና አርዓያነቷ ሟሸሸ … ጥንታዊት ኢትዮጵያ የረሃብና የጠኔ ምልክት ተደርጋ በዓለም ሙሉ ተናቀች፤›› ይላል፡፡

አንድ ሕዝብ፣ አንድ ንጉሠ ነገሥት፣ ወዘተ የሚባል አስተሳሰብ ኢትዮጵያዊነትን እንዴት እንዳዋረደና እንዴት እንዳቆሸሸ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመው የንጉሠ ነገሥቱ 80ኛ ዓመት የልደት በዓል እንዳይበላሽ ሲባል ነው ድርቁ ያመጣው ረሃብ በመደበቁ ጥፋቱ ከፍተኛ የሆነው፡፡ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ያሉዋቸውን ሁሉ ዓይነት ፀጋዎች ከመጠበቅ ይልቅ፣ የመሳፍንቱን ጥቅም ማስጠበቅ ሆነ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባህርይ ያለውን ሥርዓት መከተሉ፣ የኮንሶ ሕዝቦች የውኃና የአፈር ጥበቃ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዴሞክራቲክ ሥርዓትን የማንገሥና ድርቁን መከላከል ወደ ጆሮአቸው የሚቀርብ አይደለም፡፡ ከግዛት ማስፋፋትና አንድነትን በሚመለከትም መሳፍንቶቹ ለአገር ጥቅም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ እነ አክሊሉ ሀብተ ወልድ የኤርትራ ፌዴሬሽን እንዳይፈርስ የነበራቸው ሐሳብ በካሳ ኃይሉ በሚመራው የመሳፍንት ቡድን የነበረውን ሙግት እስቲ የዘውዴ ረታን (የኤርትራ ጉዳይ፣ 427) አንብቡልኝ፡፡     

መስፍናዊ ሥርዓት ከዚያ የሥልጣኔ ማማ እያሽቆለቆለ ለረዥም ምዕተ ዓመታት አውርዶ አውርዶ ወደ ውርደት ቢያሸቀነጥረንም፣ አውሮፓዊያን አፍሪቃን ለመቀራመት ያደረጉትን ጉዞ በማደናቀፍ ነፃነታችንንና ማንነታችን ጠብቀን እንድንቆይ ያስቻሉንን መሪዎች ማመስገን ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አገራችንን ለማዘመን ባደረጉት ጥረት በአስቸጋሪ ሁኔታ ሆነው ሳይሸሹ ወይም እጃቸው ሳይስጡ ሽጉጣቸውን የጠጡ የአይበገሬነት ምልክት የሆኑትን አፄ ቴዎድሮስን፣ ተደጋጋሚ የውጭ ጠላቶቻችን በማሸነፍ በመጨረሻም እንገታቸው በመስጠት የመስዋዕትነት ዓርማ የሆኑትን አፄ ዮሐንስን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መርተው ወሳኝ የሆነውን ድል ዓደዋ ላይ በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይታቀብ፣ ለአፍሪካም ሆነ ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት እንድንሆንና እኛ ኢትዮጵያዊን የአካል ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ነፃነትን እንድንጎናፀፍ ያበቁትን አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ መንግሥታዊ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ ያለው መንግሥት የሚለውን አስተሳሰብ የሚከተሉ ፅንፈኞች ስለኢትዮጵያዊነት ብዙ የሚለፈልፉ ቢሆንም፣ ፋቅ ቢደረጉ ሁሉን ትተው ለተወለዱበት የቀድሞ ጠቅላይ ግዛት ይሠለፋሉ፡፡ ተጨማሪ ፋቅ ሲደረጉ ደግሞ ለተወለዱበት አውራጃና ወረዳ ሌላውን በማንኳሰስ አንገታችን እንሰጣለን ብለው የውሸታቸውን ዘራፍ ይላሉ፡፡ (ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕዴግ ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡