Skip to main content
x
የመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥን በሚያጓድሉት ላይ ተጠያቂነትን የሚያመጣው ሥልት

የመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥን በሚያጓድሉት ላይ ተጠያቂነትን የሚያመጣው ሥልት

በሳምንቱ ከታዩ ክንውኖች ውስጥ መንግሥት በመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ መስክ ከለጋሾች ጋር ያካሄደው ግምገማ አንዱ ቢሆንም፣ ከዚሁ ጋር የሚገናኘውና የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው የአጋርነት ማዕቀፍ የተሰኘ ፕሮግራም ኩታ ገጠም ሆኗል፡፡

የዓለም ባንክን ጨምሮ ከበርካታ ለጋሽ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍ እየታገዘ በሚያስፈጽማቸው የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ መስኮች የተመዘገቡ ለውጦችን በገመገመው መድረክ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደርና የግዥ ሒደት፣ የኢንፎርሜሽን ሥርዓት፣ የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓትና ሌሎችንም ተመልክቷል፡፡

ጤና እንዲሁም ከትምህርት ባሻገር፣ በመጠጥ ውኃ፣ በሳኒቴሽን፣ በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታና በሌሎችም የአገልግሎት መስኮች የነበሩ አቅርቦቶች ከማክሰኞ ኅዳር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ የገመገመው የመንግሥትና የለጋሾች የጋራ መድረክ ካስተናገዳቸው መርሐ ግብሮች ውስጥ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባቀረበው የዳሰሳ ጥናት ውጤት ይገኝበታል፡፡

ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ያካሄደውን የሥነ ሕዝብና የጤና መስክ የዳሰሳ ጥናት ካመላከታቸው ነጥቦች መካከል የትምህርት፣ የጤና እንዲሁም የንፁህ መጠጥ አቅርቦትና መሰል ነጥቦች ይገኙበታል፡፡ በአገሪቱ የተሻሻለ ንፁህ የመጠጥ ውኃ የሚያገኘው ሕዝብ ቁጥር 65 በመቶ እንደሆነ ያመላከተው ስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከዚህ ውስጥ 57 በመቶው የገጠሩ ነዋሪ ሲሆን፣ ከከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ግን 97 በመቶው የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንደሚያገኝ አረጋግጧል፡፡

በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ ከፍተኛ ጉድለት የታየበት የግልና የአካባቢ ንፅህና ወይም የሳኒቴሽን አቅርቦት ነው፡፡ በኤጀንሲው ጥናት መሠረት የአገሪቱ የሳኒቴሽን ሽፋን ስድስት በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በየሜዳው የሚፀዳዳው ሕዝብ ብዛት 32 በመቶ ሲሆን፣ የተሻሻሉ የሳኒቴሽን አቅርቦቶች ጉድለት 53 በመቶ ደርሷል፡፡ እንደ መፀዳጃ ቤት ያሉ አገልግሎቶችን በጋራ የሚጠቀመው ሕዝብ ብዛት ዘጠኝ በመቶ እንደሆነ የሚያሳየው ጥናት፣ በገጠር ደረጃ የተሻሻለ አቅርቦት ማግኘት ያልቻለው ሕዝብ 56 በመቶ እንዲሁም በከተማ ደረጃም 43 በመቶ እንደሚሸፍን አመላክቷል፡፡

በጤና ረገድ የሕፃናት ሞት እየቀነሰ በመምጣት በሕይወት ከሚወለዱና ከአምስት ዓመታቸው በፊት ለሞት ከሚዳረጉ 1,000 ሕፃናት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚሞቱት ቁጥራቸው 67 እንደሆነ፣ ይህም ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት ከተመዘገበው የ88 ሕፃናት ሞት ቁጥር አንፃር መቀነሱን አሳይቷል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት በተደረገው ጥናት መሠረት የሟች ሕፃናት ቁጥር 166 እንደነበር የኤጀንሲው የጥናት ሪፖርት ያሳያል፡፡ ይሁንና በጤና ባለሙያዎች ታግዘው የሚለወዱ እናቶች ቁጥር 28 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ያሳየው ይኸው ጥናት፣ 42 በመቶው የወሊድ አገልግሎት በልምድ አዋላጆች እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

የልምድም የሕክምናም አገልግሎት ሳያገኙ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 15 በመቶ ሲሆን፣ በሐኪሞች ዕገዛ የሚለወዱ እናቶች ብዛት ስድስት በመቶ፣ በነርሶች ወይም በአዋላጅ ነርሶች ታግዘው የሚወልዱት እናቶች ቁጥር 20 በመቶ ሆኗል፡፡ በጤና ተቋማት ከሚወለዱ እናቶች ዝቅተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡት ክልሎች አፋርና ሶማሌ ሲሆኑ፣ 15 እና 18 በመቶ እንደ ቅደም ተከተላቸው አስመዝግበዋል፡፡ 

በትምህርት ረገድም በአገሪቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የመጀመያ ደረጃ ትምህርት ከሚያጠናቅቁ ወንዶችና ልጃገረዶች መካከል ዝቅተኛውን ውጤት ያሳዩት የአፋርና የሶማሌ ክልሎች፣ እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት አሳይቷል፡፡ በአፋር ክልል የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ የቻሉት 19.13 በመቶ፣ በሶማሌ 26.82 በመቶ ሲሆኑ፣ በድሬዳዋ ደግሞ 38.36 በመቶ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ አካባቢዎች ልዩ እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ደረጃ ማለትም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ባለው ዕርከን ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሁሉም ተማሪዎች፣ ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ ለማለፍ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ማቀዱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ለመጪዎቹ ሦስት ቀናት የሚገመገመው የአገሪቱ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ስለታዩ መሻሻሎችና ችግሮች የሚመክረው የጋራ መድረክ፣ ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ትኩረት የሚደረግባቸውን አቅጣጫዎችም ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የዓለም ባንክን ጨምሮ በርካታ መንግሥታት ድጋፍ የሚሰጡበት የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መንግሥት ከሚያራምዳቸው ትልልቅ ፕሮግራሞች መካከል እንደሚመደብ ለጋዜጠኞች ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ፣ በቅርቡ ለዚሁ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ከዓለም ባንክ ጋር የ600 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት እንደተፈረመ አስታውሰዋል፡፡ መንግሥትም ከራሱ በጀት ይህንን ያህል ገንዘብ ለፕሮግራሞቹ በመመደብ እንደሚሠራ የጠቆሙት አቶ አድማሱ፣ በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር በኩል ከግምጃ ቤት የሚወጣ ገንዘብ እንደመሆኑ መጠን፣ በበጀት አጠቃቀምና ትግብራ ላይ የሚፈጸም የሙስና ተግባር እምባዛም መሆኑንና ለጋሾቹ በውጤት ላይ ተመሥርተው ፋይናንስ የሚለቁ በመሆናቸውም ጭምር፣ የበጀት ፍሰቱን ተዓማኒ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ያሉት ውጤቶች የተመዘገቡበት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት፣ በስታትስቲክስ ኤጀንሲና በተቋማቱ መካከል የመረጃ መጣረስ የታየበት ነበር፡፡ ከየመሥሪያ ቤቶቹ ከቀረበው የመረጃ ስብጥር ውስጥ በተለይ በጤና ጥበቃና በኤጀንሲው መካከል ጉልህ የመረጃ ልዩነቶች ተስተውለዋል፡፡ ጤና ጥበቃ በወሊድ መቆጣጠሪያ ሥርጭትና አጠቃቀም፣ በሕፃናት ክብካቤ፣ ቅድመ ወሊድና ድኅረ ወሊድ የሕክምና ክትትል፣ በክትባት አቅርቦትና በመሳሰሉት አገልግሎት መስክ ያቀረባቸው መረጃዎች ከስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃዎች ጋር መጣረስ ታይቶባቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል በአገር አቀፍ ደረጃ የወሊድ መቆጣጠሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ71 በመቶ እንደጨመረ ሚኒስቴሩ ሲገልጽ፣ ኤጀንሲ ግን ዘመናዊውም ሌሎች የእርግዝና መከላከያዎችን ጭምር የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር ከ36 በመቶ እንደማይልጥ አሳይቷል፡፡

ምንም እንኳ የመረጃው አለመናበብ የታየው በአብዛኛው ከየዘርፍ መሥሪያ ቤቱ በሚመጣው የመረጃ ጥራት ችግር ምክንያት መሆኑ ቢጠቀስም፣ አንዳንዶቹ መረጃዎች ላይ የታየው ለውጥ ግን ከተሠራው ሥራ ጋር እንደማይዛመድ አቶ አድማሱ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ ከዚህ ቀደም የንፁህ ውኃ አቅርቦት ሽፋን ከ80 በመቶ በላይ እንደደረሰ ሲነገር ቢቆይም፣ በጥናት በተረጋጠው መሠረት ግን ከ65 በመቶ ያነሰ ነው፡፡ ይህ በመረጃው ጥራት ላይ እንጂ በንፁህ ውኃ አቅርቦትም ሆነ በሌላውም መሠረታዊ አገልግሎት መስክ የተሠራው ሥራ ለውጡ ወደ ታች ስለመቀነሱ የሚያመላክት እንዳልሆነ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የዓለም ባንክ ኅዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የአራት ዓመታት የአጋርነት ማዕቀፍም እንዲህ ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን አካቶ ብቅ ያለ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ተጠያቂንነት ከማኅበራዊ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ጋር አቀናጅቶ እንደሚያስኬድ የሚጠበቀው ይህ የባንኩ የአጋርነት ማዕቀፍ፣ የመንግሥት ተቋማት ፋይናንስና በጀት ነክ መረጃዎችን ለሕዝብ ማቅረብ፣ ግልጽ ማድረግና ማሳወቅን ብቻም ሳይሆን፣ ሕዝቡም የፋይናንስ ግልጽነትን፣ የግዥና የበጀት አመዳደብ፣ የወጪና ገቢ አስተዳደሮችን የሚያውቅባቸውን ስልቶች ይዞ ብቅ ማለቱን ይተነትናል፡፡

የአጋርነት ማዕቀፉ መንግሥት በአምስት ዓመት ውስጥ ከሚያከናውናቸው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦች ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተነገረለት የዓለም ባንክ የአጋርነት ማዕቀፍ ሰነድ፣ በመንግሥት በኩል ከዚህ ቀደም የታዩ ድክመቶችን፣ የተመዘገቡ እንደ ማኅበራዊ ሴፍቲኔት ያሉ ዋቢ ተሞክሮዎችን በመተንተን ያቀርባል፡፡