Skip to main content
x
የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድር የተገኘለት የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የግል ሎጂስቲክስ ኩባንያዎችን እንዲያካትት ተጠየቀ
የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ መኰንን ከኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሳላሃዲን ከሊፋ በጥናቱ ላይ ሲነጋገሩ

የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድር የተገኘለት የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የግል ሎጂስቲክስ ኩባንያዎችን እንዲያካትት ተጠየቀ

ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ብድር በ138 ሔክታር መሬት ላይ የማስፋፊያ ግንባታዎች እንደሚካሄዱበት የሚጠበቀው የሞጆ ደረቅ ወደብ፣ የግል የሎጂስቲክስ የዕቃ አስተላላፊዎችን ማሳተፍ የሚያስችሉ ግንባታዎች እንዲያካትት ተጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የጋራ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ፋሲሊቲዎች እንዲገነቡ የሚዘረዝር የጥናት ውጤቱን ማክሰኞ ኅዳር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ባቀረበለት ጥያቄ መሠረት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (World Food Program-WFP) ላለፉት አምስት ወራት ያካሄደውን የጥናት ውጤት ይፋ ያደረጉት አቶ አማን ወሌ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብን ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃውን ያሟላ ማዕከል ወይም ሀብ እንዲሆን ለማድረግ ያስፈልጋሉ ያሏቸውን በርካታ ፋሲሊዎች፣ የግሉን ዘርፍ በማካተት መገንባት እንዳለባቸው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዴሚ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበር (አያታ) እንዲሁም የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበር ፌዴሬሽን (ፊያታ) የተመሰከረላቸው ኢንስትራክተር አቶ አማን ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ በሞጆ እንዲገነባ የሚታሰበው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከቀረጥ ነፃ የኢኮኖሚ ዞን፣ እንዲሁም የወጪ ንግድ ማስተናገጃ ዞን (ኤክስፖርት ፕሮሰሲንግ ዞን) እንዲኖር ማድረግ ከሚታሰቡት መካከል ይገኙበታል፡፡

የጋራ አገልግሎት ፋሲሊቲው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደር ቢሆንም፣ የግሉ ዘርፍ ግን ፋሲሊቲዎቹን በሊዝ ወይም በኪራይ መልክ የሚገለገሉበትን ዕድል እንዲያመቻች ይጠበቃል ያሉት አቶ አማን፣ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የሚሰጠው የቦንድ መጋዘን (በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2007 የተጠቀሰው ቦንድ የጉምሩክ መጋዘን በሚል ነው) ለግሉ ዘርፍ የተገደበ ተሳትፎ የሚፈቅድ እንደ መሆኑ መጠን፣ ከዚህም ባሻገር የግሉ ዘርፍ በመልቲ ሞዳል (በአንድ ሰነድ ሁሉም የጉምሩክ፣ የባንክና ሌሎች መጠይቆች የሚስተናገዱበት) ሥርዓት ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎትና አቅም ያለው በመሆኑ፣ መንግሥት እንዲህ ያሉትን ዕድሎች እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሰላሃዲን ከሊፋ በበኩላቸው፣ መልቲ ሞዳልን ጨምሮ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍበትን በር እንዲከፍት ጥያቄ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ መንግሥት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመልቲ ሞዳል ሥርዓት ውስጥ የሚሳተፉ አሥር አቅም ያላቸው የግል ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ያቀረበውን ሐሳብ፣ ማኅበሩ ግን በመላ አገሪቱ ብቃት ያላቸው ኩባንያዎችን የሚያሳትፍ መሥፈርት እንዲያወጣ መንግሥትን መጠየቁን አቶ ሰላሃዲን አስታውሰዋል፡፡ ለዚህም የመንግሥትን ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በሞጆ ደረቅ ወደብ በሐሳብ ደረጃ የቀረበው የጥናት ውጤት ካካተታቸው በርካታ የጋራ አገልግሎት መስጫ ፋሲሊቲዎች መካከል ከውጭ የሚገቡ እንደ ማዳበሪያ፣ የድንጋይ ከሰል፣ እህልና የመሳሰሉት ጭነቶች በግሉ ዘርፍ የሚስተናገዱባቸው ፋሲሊቲዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ብረትን ጨምሮ የማሽነሪ፣ የጭነት ተሽከርካሪዎችና ሌሎችም ከባድ ጭነቶች የሚስተናገዱባቸውና የመገጣጠሚያ ማዕከል ለገቢ ዕቃዎች ማስተናገጃነት ከሚታሰቡ ፋሲሊቲዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በወጪ ንግድ መስክ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍባቸው ከተጠየቁና በሞጆ ደረቅ ወደብ ውስጥ መገንባት አለባቸው ከተባሉት ውስጥ የባዶ ኮንቴይነሮች ማከማቻ ቦታ፣ ዕቃዎችን በኮንቴይነር ማሸጊያ፣ የቡና ማስተናገጃ ማዕከል፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎች ማስተናገጃ፣ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት የወጪ ንግድ ማዕከል፣ በቶሎ የሚበላሹ እንደ አትክልትና አበባ ያሉ ምርቶች የሚስተናገዱባቸው የማቀዝቀዣ መጋዘኖችና ሌሎችም የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍባቸው በሐሳብ የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የጥናት ውጤቱ በቀረበበት ወቅት ከተነሱ በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ያስፈልጋሉ የተባሉትን ፋሲሊቲዎች ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ ነው፡፡ ለማስፋፊያ የተገኘው የ150 ሚሊዮን ዶላር ብድርን ጨምሮ መንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማሳተፍ፣ ተጨማሪ ብድር በማፈላለግ ወይም ከራሱ በጀት ማስፋፊያውን መገንባት የሚችልባቸውን አማራጮች የጠቀሱት አቶ ሰላሃዲን፣ ማኅበራቸው ያቀረበው ሐሳብ አንድ ዘመናዊ የደረቅ ወደብ ሎጂስቲክስ ሃብ ማሟላት የሚገባውን ፋሲሊቲዎች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት የግሉ ዘርፍ በሎጂስቲክስ ዘርፉ እንዲሳተፍ የማድረግ ፍላጎት አለው፡፡ ይሁንና ለማቃለል የገበያ ተጠቃሚነት ወይም የፖሊሲ ማሻሻያ ጥያቄዎችን ከማቅረብ ባሻገር፣ የግል ኩባንያዎች በአገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ችግር ለመፍታት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ 

በመጪው ዓመት ግንባታው ሊጀመር እንደሚችል ለሚጠበቀው የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መቋቋሙ ታውቋል፡፡ የዲዛይን፣ የአዋጭነትና መሰል ጥናቶች ሊካሄዱ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም የባለሥልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡