Skip to main content
x

‹‹ከአንበሳ መንጋጋ ማን ያወጣል ሥጋ?››

  • ዕውን አዲሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች መዳፍ ተላቋል?

በታገል ጎበዜ

      የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም.  የናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ሲካሄድ፣ በአክሲዮን ማኅበሩ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ  ትዝብቱን እንደሚከተለው ይገልጻል፡፡

      ከዛሬ 58 ዓመት በፊት የወጣው የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ‹‹አንቀጽ 352፡፡ ስለአነስተኛ ባለአክሲዮኖች መብት፡፡ ልዩ ልዩ የሆነ ብዙ የባለአክሲኖቸ ክፍል ሕጋዊ ሁኔታቸውም የተለያየ ያሉ እንደሆነ፣ ለአስተዳደር ምክር ቤት ቢያንስ አንድ እንደራሴ እንዲመርጡ ለእያንዳንዱ ክፍል የማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ያረጋግጥላቸዋል፤›› ይላል፡፡ ካለይ ስለተገለጸው የሕግ አንቀጽ የእንግሊዘኛው ትርጉም  እንዲህ ይላል፡-

‹‹Art. 352. - Rights of a minority. Where there are several groups of shareholders with different legal status, the articles of association shall provide for each group to elect at least one representative on the board of directors››.

ብሔራዊ ባንክ ይህን ሕግ ተከትሎ በገንዘብ ድርጅቶች የዳይሮክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ የአነስተኛ ባለአክሲዮኖችን መብት እንዲያስከበር፣ በሕጉም መሠረት የየድርጅቶቹ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሻሻል እንዲያደርግ ‹ተቆርቋሪ ጠቋሚዎች›› በእንግሊዝኛው አጠራር ‹‹Whistleblowers›› የሚባሉት፣ ለባንኩ የበላይ አስተዳደር ግልጽ ደብዳቤ በማቅረብና በተለያዩ ጊዚያትም በጋዜጦች ላይ አስተያየቶችን በመጻፍ የገንዘብ ደርጅቶች ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በቡድናዊ ስሜት እየተነሳሱ፣ ደርጅቶቹን ለግል ጥቅማቸው ብቻ እንዳያውሏቸው አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ከማሳሰብና አቤቱታ ከማሰማት አልቦዘኑም፡፡

ባለሀብቶች አገራችንን በኢኮኖሚያዊና በኅብረተሰባዊ ልማት ለማሳደግ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ፣ ብሎም ድርጅቶቹን በማደራጀት ረገድ የተጫወቱትና ወደፊትም የሚጫወቱት ሚና የሚደነቅና ከበሬታም የሚቸረው መሆኑ ሳይካድ፣ የገንዘብ ደርጅቶች ዋነኞቹ ‹ባለቤቶች›› ለባንኮች ገንዘብ አስቀማጮች (Depositors)፣ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ የመድን ውል ባለቤቶች (Policyholders) ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለአክሲኖቹ በብቸኝነት የየድርጅቶቹ ባለቤቶች አለመሆናቸውን ሲረዱት አይስተዋልም፡፡ የሁሉም አገሮች መንግሥታት ከሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ በተለየና በተቀናጀ መንገድ የገንዘብ ደርጅቶችን በቅርብና በጥልቀት የሚቆጣጠሩበት ምክንያት፣ የዋነኛ ባለድርሻ አካላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን መረን የለቀቁ የገንዘብ ደርጅቶች በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከል ነው፡፡

ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በንግድ ሕጉ መሠረት የአነስተኛ ባለአክሲዮኖችን መብት ሳያስከበር ላለፉት 16 ዓመታት በዝምታ ከርሞ፣ ባለፈው የ2009 ዓ.ም.  የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ግልጽነትን የተላበሰ ለማድረግና ለመልካም አስተዳደር ዋነኛ መርሆች አጽንኦት ለመስጠት የጥቆማና የምርጫ አሠራር ደንብ በማውጣት፣ ለአንድ ዓመት በዝግጀት ተከርሞ በያዝነው 2010 ዓ.ም. አፈጻጸሙ ተጀምሯል፡፡

የንግድ ሕጉ ‹‹ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች›› እና ‹‹አነስተኛ ባለአክሲዮኖች›› ብሎ በሁለት ጎራ ከፍሎ ያስቀመጣቸውን ባለአክሲዮኖች ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ባወጣው ደንብ ‹‹በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጠቅላላው የተፈረመ ካፒታል ውስጥ ሁለት በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሆነውን ድርሻ የያዘን ሰው ወይም ደርጅት ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮን (Influencial shareholder)›› እንዲሁም ‹‹በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጠቅላላው የተፈረመ ካፒታል ከሁለት በመቶ ወይም ከዚያ በታች አክሲዮን የያዘን ሰው ወይም ደርጅት በከፍተኛ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆነ ባለአክሲዮን›› በማለት ግልጽ የሆነ ስያሜ ሰጥቷል፡፡ በተጫማሪም ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት መሥፈርትና ስብጥር፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ የአስመራጭ ኮሚቴው ደንብና አሠራር፣ የቦርድ  ዕጩዎች ጥቆማ፣ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት፣  ወዘተ.›› በሚሉ  ርዕሶች  በደንቡ ውስጥ ዝርዝር መመሪያ ወጥቷል፡፡

እንግዲህ፤ ብዙ ገንዘብና የሰው ኃይል ለአንድ ዓመት ያህል ፈሶበት ሲለፋበት የከረመው ከላይ የተጠቀሰው ደንብ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን እንዳሰበው፣ ግልጽነትን የተላበሰና ለመልካም አስተዳደር ዋነኛ መርሆች አጽንኦት የሰጠ ሳይሆን አያሌ  ህፀፆችና ጉድለቶች የሞሉበት በመሆኑ ከዚህ ቀጥሎ ጥቂቶቹን  ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡

  1. ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴው›› ጊዜው በመጠናቀቅ ላይ ካለው የዳይሬክተሮች ቦርድና ከተፅዕኖ ፈጣሪ  ባለአክሲዮኖች ነፃ ነበር ማለት ይቸግራል፡፡  ይህም አመለካከት ስህተት ነው ከተባለ  ‹‹የአስመራጭ ኮሚቴው›› ከጉድለት በፀዳ መንገድ የተመረጠ መሆኑን ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ለባለአክሲዮኖች ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል፡፡
  2. ከብዙ ዓመታት ልምድ እንደሚታወቀው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ስብሰባ ‹‹ዓመታዊ የድጋፍ  ሠልፍ›› እንጂ ግልጽ በሆነ መንገድ የኩባንያውን የሥራ ክንዋኔዎች  አብዛኛው የባለአክሲዮን ክፍል ይረዳዋል ለማለት ይቸግራል፡፡ ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ ለሦስት ወይም ለአራት ሰዓታት በሚደረግ ጉባዔ፣ ይልቁንም በዕለቱ ጉባዔተኛው ወደ ስብሰባ አዳራሽ  ሲገባ በተበተኑለት የቴክኒክ፣ የሒሳብ፤ የኦዲተሮችና ሌሎች  ሪፖርቶች አብዛኛው የኩባንያው ባለአክሲዮን ሙሉ በሙሉ ተረድቷቸውና  በቂ ግንዛቤም ጨብጦባቸው ውሳኔ ሰጠባቸው ቢባል ለይስሙላ ካልሆነ በቀር፣ ሚዛን የሚደፋ ሀቅ አይደም፡፡ ባለአክሲዮኖች ተዘጋጅተውበትና አስበውበት በጉባዔዎች ላይ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ‹‹ቁልፍ የክንዋኔዎች መግለጫዎች›› (Key Figures and Facts) የንግድ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ከጉባዔ መጥሪያ ደብዳቤዎች ጋር  ለባለአክሲዮኖች ሊደርሷቸው ይገባ ነበር፡፡ በቀድሞ ጊዜ ሰነዶች ለጉባዔተኛው ከመጥሪያ ጋር ይደርሳሉ፡፡  ዛሬ  በምን ምክንያት ልምዱ  እንደቀረ አይታወቅም፡፡
  3. ‹‹በቦርድ አባልነት ለመመረጥ ፈቃደኛ የሆኑና የኢንሹራንስ ኩባንያውን ጥቅሞች ከሁሉ በተቻለ ለመስጠትና እንዲሁም የኩባንያውን ሥራ የሚመሩና የሚቆጣጠሩ፣ የመሪነት ብቃት ያላቸውን ዕጩዎች ያቀርባል፤›› በማለት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በግልጽ የሰጠውን ኃላፊነት አሰመራጭ ኮሚቴው ተወጥቷል ምክንያቱም አስመራጭ ኮሚቴው የዕጩዎችን ጥቆማና ምርጫ በጥራት እንዳላካሄደ መረዳት የሚቻለው የዕውቀትና የክህሎት ስብጥሩን  አላመቻቸም፡፡ መልሰው የተመረጡት በአብዛኛው በወንበሩ ላይ የነበሩት የቦርድ አባላት ሲሆኑ፣ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ሰነዶችን በሚመረምርበት ጊዜ ምርጫው ኩባንያውን በብቃት ለመምራትና ለመቆጣጠር የሚችሉ አዳዲስ ዕውቀቶችና ክህሎቶች እንዳልተሰባጠሩበት ሊገነዘበው ይችላል፡፡ ይልቁንም ከተጠቋሚዎች መካከል ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና የአስተዳደር ብቃት ያላቸው ምሁራን ጥቆማውን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ለመረዳት ኮሚቴው ያደረገው ጥረት አይታወቅም፡፡ በደንቡ መሠረት በዕጩነት ለመቅረብ ሙሉ ፈቃደኝነት አስፈላጊ መሆኑ ባይካድም፣ የተጠቋሚዎች ቁጥር ደንቡ ከሚያዘው ቁጥር አንሶ ሲገኝ አንዳንድ  ተጠቋሚዎችን ለማግባባትና ጥቆማውን እንዲቀበሉት ማድረግ የአስመራጭ ኮሚቴው ዋነኛ ኃላፊነት ነበር፡፡ ከታጩት ባለአክሲዮኖች መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም የቅርብ ደርጅቶች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው የሠሩና በተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች መካከል የነበረውን የእርስ በርስ ግጭትና ሽኩቻ ስለሚያውቁ፣ እንደገና ወደዚህ ዓይነቱ አታካራ ለመመለስ ስላልፈልጉ ሊሆን  ይችላል፡፡ ምክንያቱም ካለፉት ጥቂት ዓመታት በፊት በጥቅም ግጭት የኩባንያው ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች እርስ በርሳቸው ሲወነጃጀሉና ከፊሎቹ  በከፊሎቹ ላይ ተነሳስተው ጉዳዩ ፍርድ ቤት የደረሰ እንደነበር ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን  የተሰወረ አይደለም፡፡
  4. ከተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮንና ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆኑ ባለአክሲዮኖች ጎራዎች የተመረጡት የዳይሬክተሮች ቦርድ ተመራጮች ከዝምድና፣ ከሎሌነትና ከሌሎች ዓይነት ንክኪዎች የፀዱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ‹‹በድርጅታዊ አሠራር›› ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖችና ተባባሪዎቻቸው ድምፃቸውን እርስ በርስ እንደተደጋገፉበት ግልጽ ነው፡፡ በወንበሩ ላይ የሚገኙት የቦርድ አባላትም እንዲሁ፡፡ ስለሆነም ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ግልጽነትንና የመልካም አስተዳደር መርሆችን ለማስፈን የቀየሰውን የተስፋ ጭላንጭል የዚህ ዓይነቱ የውስጥ ለውስጥ ትግግዝ አጨልሞታል፡፡ የሌሎች አገሮች ‹‹የደርጅት መልካም አስተዳደር (Corporate Governance)›› ደንቦች ‹‹በዘመድ አዝማድ፣ በአቻ በጋብቻ፣ በጌታና ሎሌና ሌሎችም ዓይነት ንክኪ ላላቸው ሰዎች›› ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች ለቦርድ አባልነት የሰጧቸው የምርጫ ድምፆች ሕገወጥ ናቸው፡፡ በአገራችን በአዋጅ ቁጥር 746/2004 አንቀጽ 12  መሠረት ‹‹. . . .ማንኛውም ሰው ብቻውንም ሆነ ከባለቤቱ ወይም ዕድሜያቸው 18 ዓመት በታች ከሆኑ በአንደኛ ደረጃ ከሚዛመዳቸው ሰዎች ጋር በመሆን፣ ከማናቸውም መድን ሰጪ የተፈረመ ካፒታል ከአምስት በመቶ በላይ አክሲዮን ሊይዝ አይችልም፤›› በማለት  አክሲዮኖችን የመያዝ ገደብ ጥሏል፡፡ ለምን ቢባል? አንድ ባለሀብት በዘመድ አዝማድ ስም አክሲዮኖችን እንዳያግበሰብስ ለመከላከል ነው፡፡ ታዲያ ‹‹ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ባለአክሲዮን ለዘመድ አዝማዶቹና ለሎሌዎቹ የምርጫ ድምፁን ቢያፈስላቸው ሰዎቹ 18 ዓመት ስለሞላቸው፣ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን እንዳሰበው ‹‹በድርጅት መልካም አስተዳደር›› (Corporate Governance) አንፃር ግልጽነትን ማላበስና ለዋነኛ መርሆቹም አጽንኦት መስጠት ነውን? ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በንግድ ሕጉ መንፈስ የባለአክሲዮኖችን የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብጥርስ በአግባቡ አደላደልኩ ማለት ይችላል?  ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ይህ ኢፍትሐዊ ደርጊት እንዳይተገበር  መከላከል ኃላፊነቱ አይደለምን?
  5. የኩባንያው የሰው ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መሄዱንና ከኩባንያው ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን በመግለጽ የቦርዱ ሰብሳቢ ከሪፖርታቸው ቀጥለው ለጉባዔተኛው ተናግረዋል፡፡ የኩባንያውን የሰው ሀብት ለማልማትና ኩባንያው የራሴ ነው በሚል ወኔና አስተሳሰብ፣ ብሎም በታማኝነትና በሀቀኝነት ሊያገልግል የሚያችል የሰው ኃይል አስተዳደር ስትራቴጂ መቀየስና ተግባራዊ የሚደረግበትንም ምክረ ሐሳብ በጥናት ተደግፎ ለውሳኔ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ እንዲሁ በደረቁ ለውይይት መቅረቡ ከጉንጭ አልፋነት አልዘለለም፡፡ የድርጅት ሠራተኛን ትጋትና ታማኝነትን ለመማረክ  የሠራተኛ ማነቃቂያና መበረታቻ ዘዴዎች ወሳኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ በድርጅት ውስጥ አድልኦ፣ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም፣ ሙስናና ሸፍጥ፣ ወዘተ. መንሰራፋት ሠራተኞችን በአግባቡ ለማስተዳደር አደገኛ እንቅፋቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በድርጅት ውስጥ ካሉ ትጉህና ታማኝ ሠራተኞችን ይዞ ለማቆየት ስለማያስችሉ  በአስቸኳይ መወገድ እንዳለባቸው የሰው ኃይል ልማት ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡
  6. በአክሲዮን ማኅበር ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የአክሲዮኖች ዝውውር መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አክሲዮኖች ከማን ወደ ማን እንደተዘዋወሩና ሌሎችን መረጃዎች የያዘ ሰንጠረዥ ለጉባዔተኛው ተበትኖ ነበር፡፡ በሰንጠረዡ ላይ አክሲዮኖቹን ያዘዋወሩት ባለአክሲዮኖች ስም ለምን ተገለጸ? ወደፊትም በዚህ መልኩ መቅረብ የለበትም የሚል ሐሳብ ከጉባዔተኛው መካከል አንድ ባለአክሲዮን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ሐሳቡ አዋጅን የሚፃረር በመሆኑ  የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በመልስ ማስተካከል ነበረባቸው፡፡ ለምን አክሲዮን የሚያዛውረው ሰው ስም እንዳይገለጽ እንደተፈለገ አይታወቅም፡፡  የአክሲዮን አዛዋሪም ሆነ የሚዛወርለት ሰው ስምና አድራሻ፣ ስምምነት ሳይገለጽ ዝውውሩን የሚያፀድቀው ባለሥልጣን እንደማይቀበለው ግልጽ ነው፡፡ የመድን ሥራን ለመደንገግ  በቁጥር 746/2004 የወጣው አዋጅ አንቀጽ 11  ከንዑስ አንቀጽ (2) እስከ (5)፡፡ ማንኛውም መድን ሰጪ ብሔራዊ ባንክ በሚወስነው መሠረት የባለአክሲዮኖችን ስም ዝርዝርና ድምፅ የመስጠት መብታቸውን የሚያሳይ የአክሲዮን መዝገብ ይይዛል፡፡ በዚህ መዝገብ ውስጥ የሠፈረ ማንኛውም የአክሲዮን ዝውውር አክሲዮኖችን ባስተላለፈውና በተላለፈለት ሰው መካከል አክሲዮኖችን የማስተላለፍ ሕጋዊ ስምምነት ስለመኖሩ፣ እንዲሁም የአክሲዮኖቹ ስም ባለቤትነት ስለመዘዋወሩ የመጨረሻ ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
  7. ማንኛውንም ሰው ተደማጭነት ያለው ባለአክሲዮን ሊያደርግ የሚችል የአክሲዮን ዝውውር በአክሲዮን መዝገብ ከመመዝገቡ በፊት በብሔራዊ ባንክ መፅደቅ አለበት፡፡ (5) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) የተመለከተው የአክሲዮን መዝገብ በመድን ሰጪው መደበኛ የሥራ ሰዓት ሕዝብ ያለ ክፍያ ማየት በሚችልበት ሁኔታ በመድን ሰጪው ዋና መሥሪያ ቤት ይቀመጣል ይላል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኩባንያውን ካፒታል ጠቅላላ ጉባዔው ሊያሳድግ ይችላል፡፡ ነገር ግን አጠያያቂው ነገር ተጨማሪ ካፒታሉን ባለአክሲዮኖች እንዴት ይከፋፈሉት የሚለው  ነው፡፡ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲኖች የሚቀርበው ሐሳብ እንተለመደው በአክሲዮን ይዞታችን ልክ በተመጣጥኖ  (Proportionately) ይከፋፈል የሚል ነው፡፡ በጸሐፊው አስተያየት ይህ የክፍፍ መንገድ  ኢፍትሐዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች ከተጨማሪው አክሲዮን የአንበሳውን ድርሻ ሲያገኙ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ላልሆኑት ባለአክሲዮኖች የሚተርፋቸው ፍርፋሪ ነው፡፡ የተመጣጥኖ ዘዴ ላለው ይጨመርለታል በሚለው መርህ መሠረት ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖችን ሲጠቅም፣ አነስተኛ ባለአክሲዮኖችን አይጠቅምም፡፡ ባለፉት ዓመታት የኩባንያው አጠቃላይ ዕድገት የተገኘው የሁሉም ባለአክሲዮኖች ገንዘብ ይነስም ይብዛ አንድላይ ሆኖ የተሠራበት ሲሆን፣ ካፒታል ሲያድግ በተለይ የአነስተኛ ባለአክሲዮኖች ድርሻ እንዲሻሻል ለማድረግ ፍትሐዊ የሆነ የክፍፍል ዘዴ ሊቀየስ ይገባል፡፡ የአነስተኛ ባለአክሲዮኖችን መብት የሚያስከብር እንደራሴ በዳይሬክተሮች ቦርድ ላይ መወከል  ያስፈለገው ለእንዲህ ዓይነቱ አድልኦ መፍትሔ ለመሻት ነበር፡፡
  8. በዕለቱ በተካሄደው የባለአክዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ አዳራሽ ውስጥ ጸሐፈው የተቀመጥኩት ከወደ ኋላ በነበሩ ወንበሮች ሲሆን፣ አጠገቤ አንድ አዛውንት ባለአክሲዮን ተቀምጠው ነበር፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚለው ቃል በተደጋጋሚ በጉባዔተኛው ሲነሳ ስለሰሙ ግራ ተጋብተው ኖሮ ወደ እኔ ዞር አሉና ‹‹ስማ እንጂ እነዚህ ሽብር ፈጣሪዎች በኩባንያችን ውስጥ ጉቡብን እንዴ?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‹‹የለም እነሱ አልገቡም አልኳቸውና እነዚህ እርስዎ የጠቀሷቸው ሽብር የሚፈጥሩት በአገር፣ በሕዝብና እንዲሁም በመንግሥት ላይ ነው፡፡ የኩባንያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሚባሉት ግን በከፍተኛ ገንዘብ አክሲዮኖችን የገዙና ኩባንያውን እኛ በፈለግነው መንገድ እናስተዳድረው በማለት በአነስተኛ ገንዘብ እንዳቅማቸው አክሲዮን የገዙ ሰዎችን መብት የሚጨቁኑ ናቸው፤›› ብዬ መለስኩላቸው፡፡

ወዲያው አጠገባቸው የነበሩ  ባለአክሲዮን ተነስተው፣ ‹‹አብዛኞቻችን ባለአክሲኖች እንግሊዝኛ የማንበብ ችሎታ የለንም፡፡ ለምን በአማርኛ ተተርጉሞ አልተሰጠንም?›› ብለው ሲጠይቁ፣ ሌሎችም ባለአክሲዮኖች ሐሳባቸውን ደግፈው በጥያቄው ላይ አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ ጉባዔው ለጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ አንድ የአማርኛ ጽሑፍ የተበተነ መሆኑ ባይካድም፣ በዳይሬክተሮች ቦርድ ላይ የከፍተኛና የአነስተኛ ባለአክሲኖች ስብጥር መኖር እንደዚህ ያሉትን የቸልተኝነት ተግባራት ለማስወገድ ይረዳል፡፡ በቅርቡ ‹‹እንዘጭ እንቦጭ›› በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ መጻፉን በወሬ ደረጃ ሰምቻለሁ፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ደርጅቶች በመልካም አስተዳደራቸውና የሥራ አመራራቸው በየጊዜው ‹‹እንዘጭ እንቦጭ›› ከማለት ተሻሽለው፣  ለአገርና ለሕዝብ መስጠት የሚገባቸውን እጅግ ጠቃሚ አገልግሎት በጥራትና በስኬት መስጠት የሚችሉበትን ቀን  ጸሐፊው በጣም ይናፍቃል፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡