Skip to main content
x

‹‹ቁርጡን ንገሪኝ . . . ››

በአያሌው አስረስ

አፈሩን ገለባ ያድርግለት፣ አፅቁን ያለምልምለትና ‹‹ቁርጡን ንገሪኝ›› ከጥላሁን ገሠሠ ተወዳጅ ዘፈኖች የአንዱ ርዕስ ነው፡፡ የጽሑፌን ርዕስ የተዋስሁት ከእርሱ ነው፡፡ መንግሥት ቁርጡን ሊናገርባቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች አሉ፣ ሁለቱን እንሆ፡፡

 በአሁኑ ጊዜ አምስቱ ክልሎች ማለትም ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልል የየራሳቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከፍተዋል፡፡ በተጨማሪ በብሔራዊው ጣቢያ በተያዘላቸው ጊዜም ፕሮግራማቸውን እያቀረቡ ነው፡፡ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝና የሐረሪ ክልሎች እንዳቅማቸው በብሔራዊው ጣቢያ ፕሮግራማቸውን ያቀርባሉ፡፡ ጎጆ የወጡ ክልሎች መውጣት ላልቻሉት ወለሉን ለምን አያሠፉላቸውም የሚል ጥያቄ እግረ መንገድ ማንሳት ተገቢ ሆኖ ይታየኛል፡፡ የሚሰማ ማግኘት እንደ ሰማይ ቢርቅም፣ ይህን ማድረጉ ‹‹ቅድሚያ ወደኋላ ለቀሩ ክልሎች  ይሰጣል›› የሚለው መፈክር አፈር በልቶት ከሚቀር ማስታወሱ ስለማይከፋ ነው፡፡

      ዋልታና ፋና የፓርቲ ናቸው፣ አይደሉም? የሚለው ጥያቄ ማሟገቱ ሳይረሳ፣ እነሱንም ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በባለሀብቶች የሚተዳደሩ ዘጠኝ የንግድ (ዓለማዊ) ወደ ሰላሳ የሚጠጉ መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ራሳቸውን በዋናነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረሱ ናቸው፡፡ ሁሉም የሚያሠራጩት ሳተላይት ተጠቅመው በመሆኑ፣ ሊከታተላቸው የሚችለው የሳተላይት መቀበያ ገበቴ (ዲሽ) መትከል የቻለ  ድህነት የከፋ ጥላውን ያልጣለበት ወገን ነው፡፡

      ልጅ ሚካኤል የተባለ ተረበኛ እነዚህም በዝተው ታይተውት በአንድ የወግ ፕሮግራሙ ላይ፣ ‹‹አገሩን የወረረው የታሸገ ውኃና ቴሌቪዥን ነው፤›› ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡

      በነገራችን ላይ ተራቢ (ኮሜዲያን) ቀልድ አዋቂ፣ ማሳቅ ማፍነክነክ የሚችል ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ጨዋታ አዋቂ ማለትም ነው፡፡ ጨዋታ አዋቂ ሰው ደግሞ ለሰሚው አዕምሮ የሚኮሰኩስ፣ ለጀሮ የሚቆረፍድ ቃል ሳይጠቀም እያዋዛ አጥንት ሰብሮ የሚገባ ቁም ነገር የሚናገር ማለት ነው፡፡ በዚህ ተራቢው ተስፋዬ ካሳ የሚታወስ ሰው ነው፡፡ ብንረሳ ብንረሳ፣ ‹‹አንተስ በደህና ቀን አብደሃል . . . ›› የሚለውን ጨዋታውን  አንረሳለትም፡፡

      ወደ ቴሌቪዥን ጉዳይ እንመለስ፡፡ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የንጉሡንና የደርግን ዘመን ጨርሰን፣ ከኢሕአዴግ ዘመን ሃያ ስድስቱን ለገፋን ለእኛ፣ የዘላቂነታቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ዓይነቱን ዕድል ማግኘት ‹‹ምሥጋና ለእናንተ›› ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ መንግሥት ግን የምሥጋናው ባለድርሻ አይሆንም፡፡ ተመሥጋኞቹ በድፍረት የሚመጣውን ለመሸከም ራሳቸውን ያዘጋጁት ወገኖች ናቸው፡፡ እሱማ መመሥገን ቢፈልግ ኑሮ መንገዱን ግጥም አድርጎ በግራኝ ቁልፍ  አይቆልፍበትም ነበር፡፡ አቶ ግራኝ ደብረ ማርቆስ ላይ የራሳቸው የግል ፈጠራ የሆነ የበር ቁልፍ በማምረት የሚተዳደሩ ሰው ነበሩ፡፡

      የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3.2 የፌዴራሉ መንግሥት ዓርማ ከሚወክላቸው አንዱ፣ የሃይማኖቶች በአንድነትና በእኩልነት መኖር ነው፡፡

      መንግሥት የእኔ የሚለውና የተለየ ጥበቃ የሚደረግለት ሃይማኖት እንደሌለ በአንቀጽ 11 ላይ የተደነገገ ሲሆን፣ መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ እጁን መክተት እንደማይችል ተገልጧል፡፡

      በሌላው በኩል ደግሞ በአገሪቱ በማንኛውም አካባቢ ለየትኛውም የኅብረተሰብ  ክፍል እየተሰበኩ ያሉ እምነቶች የየአማኙ የግል ጉዳይ ቢሆኑም፣ የእምነቱ ተከታዮች ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው ሊያከብሩትና ሊጠበቁት የሚገባ፣ ሊከበርላቸውና ሊጠበቅላቸው ግድ የሚሆን በሕግ የታወቀ ሰብዓዊ መብት አላቸው፡፡

      የየሃይማኖቱ ተከታዮች በሰውነታቸውና ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ሕገ መንግሥቱ ከሚጠብቅላቸውና ከሚያከብርላችው መብቶች አንዱ የሐሳብ ነፃነት ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፤›› በማለት በማይደበዝዝ ቀለም አሥፍሮት ይገኛል፡፡

      በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይም፣ ‹‹የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸውን የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ፤›› በማለት ለሃይማኖታቸው አገልግሎት እስከ ከፍተኛው የመደራጀት መጠን፣ መደራጀት እንደሚችሉ ተረጋግጦ ይገኛል፡፡

      ‹‹ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብ ደኅንነትን፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶችና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል፤›› በማለት (አንቀጽ 27፣2) በመብቱ ላይ ገደብ ሊጣልበት እንደሚችልም ሕጉ ያሳውቃል፡፡

      ነገሩ ከሌላው ጫፍ ሲታይ፣ ሃይማኖት በቋንቋና በሌሎችም መንገዶች የሚገለጽ አንድ ራሱን የቻለ ሐሳብ እንደሆነ መረዳትም አይከብድም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል . . . ›› ከሚለው አንፃርም፣ ሃይማኖት አንድ ዓይነት የሐሳብ ክፍል በመሆኑ በሕጉ ጥበቃ እንዳገኘ መረዳት ቀላል ነው፡፡

      ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ሃይማኖትን ለማስተማር የሚያስፈልጉ ድርጅቶችን ማቋቋምና መምራት በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደ ነው፡፡ የዛሬ የማስተማር ሥራ እንደ ትናንቱ አስተማሪና ተማሪ ፊት ለፊት ተገናኝተው፣ በዛፍ ሥር፣ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰፊ አዳራሽ የሚካሄድ ብቻ አይደለም፡፡ በፈጣን ለውጥ ላይ ያለው ቴክኖሎጂ የማስተማርንም ሥራ ለፈጣን ለውጥ ዳርጎታል፡፡ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭት አዲሶችና ዋናዎቹ ተመራጭ ዘመናዊ የማስተማሪያ መንገዶች ሆነዋል፡፡ ዓለም በስፋት እየሠራበት የሚገኝ መንገድም ነው፡፡

      በብሮድካስት አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን መብትና ግዴታ በግልጽ መወሰን ያስፈልጋል በማለት፣ መንግሥት የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅን በ1999 ዓ.ም. አውጥቷል፡፡ አዋጁ የወጣው መንግሥት የ1997 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ከፈጠረበት መደናገጥ ባልወጣበትና ባልተረጋጋበት ጊዜ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

      አዋጅ ቁጥር 533/1999 ከወጣባቸው ምክንያቶች አንዱ በአዋጁ መግቢያ ላይ፣  ‹‹የብሮድካስት አገልግሎት በሕገ መንግሥት የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመምረጥና የመመረጥ የመሳሰሉትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት፤›› ነው ተብሎ ተገልጧል፡፡

      በዚህ አዋጅ የተቋቋመው የብሮድካስት አገልግሎት ባለሥልጣን ፈቃድ ከሚሰጥባቸው ውስጥ ሁለቱ፣ በሳተላይት አማካይነት የሚሠራጭ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የብሮድካስት አገልግሎቶች ናቸው፡፡

      ሆኖም ይህን አገልግሎት ለሕዝብ መስጠት ፈልገው ፈቃድ ቢጠይቁ የማይፈቀድላቸው በአዋጁ በአንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 3 እና 4 ክልከላ የተጣለባቸው አሉ፡፡ እነሱም የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በፓርቲዎች ላይ የተጣለው ገደብ ከፓርቲዎች አልፎ የፓርቲ መሪዎችንና የአመራር አባላቱን (ግለሰቦችን) የጨመረ፣ የፓርቲ የአመራር አካል በመሆናቸው ምክንያት ብቻ እንደ ማንኛውም ዜጋና ባለሀብት በብሮድካስት አገልግሎት ሥራ እንዳይገቡና ሀብት እንዳያፈሩ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሠማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፤›› የሚለውን በሕገ መንግሥት የተሰጠን መብት የገፈፈ ነው፡፡ በጥሩ አማርኛ ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣ፣ የሕገ መንግሥቱ ማፍረሻ አዋጅ ነው ብሎ መግለጽም ይቻላል፡፡

      ሃይማኖታዊው የኤልሻዳይ የቴሌቪዥን አገልግሎት ከለንደን ማሠራጨት ከጀመረ በኋላ፣ ከአገር ውስጥ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም እሱን ተከትለው የየራሳቸውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ጀምረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ ሠልፉን ተቀላቅላለች፡፡ የእስልምናና የካቶሊክ የእምነት ተቋማት ከዳር ቆመው ሲታዘቡ የሚኖሩ አይመስልም፡፡ ነገ የሌሎችን ጫማ ተከትለው ከመስመሩ ይገባሉ፡፡ አዋጁ  ቀድሞ ተጥሷልና ተው ተመለሱ ለማለት የማይቻል ይሆናል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ሚናቸው እየጎላ መምጣቱ መወሳት አለበት፡፡ በሕዝብ ውስጥ የፈጠሩትና የሚፈጥሩት ተደማጭነት ተቃሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህም መንግሥት ፈጥኖ መልሰ መስጠት አለበት፡፡ የብሮድካስት አዋጁ ይሻሻላል? ወይስ አይሻሻልም? መንግሥት ከሕዝብ የነጠቀውን መብት ለሕዝብ ይመልሳል? ወይስ አይመልስም? ወይስ መንግሥት አሁን የገጠመው ውጥረት እስኪረግብ ጠብቆ የተመቸ ጊዜ ላይ ሲደርስ፣ ‹‹እስከ አሁን ከሕግ በላይ ቆይታችኋል በቃችሁ፤›› ብሎ ማሠራጨት እንዲያቆሙ ያደርጋል? 

ይህ ደግሞ በዚያን ጊዜ እነሱ ሕዝባዊ መሠረት ስለሚያበጁ መንግሥትን በሕዝብ ዘንድ የተጠላ ስለሚያደርገው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይሆናል፡፡ ስለዚህም ዛሬ መንግሥት ቁርጡን መንገር አለበት፡፡

ከቴሌቪዥን ጋር አብሮ የሚነሳ፣ መንግሥት ሊያየው የሚገባ ጉዳይም አለ፡፡ የቴሌቪዥን ዓመታዊ ግብር፡፡ እኔ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹እኛ የመጨረሻዎቹ›› ከሚላቸው አንዱ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእየዕለቱን ፕሮግራም በበራሪ ወረቀትና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እያወጣ እያስተዋወቀ ተመልካች ለማግኘት በሚማስንበት ጊዜ ጥሩ ተመልካች ነበርኩ፡፡ ዓመታዊ የቴሌቪዥን ግብር በዚያን ጊዜ እንዲታወጅ ያደረገው  ጣቢያው በራሱ ገቢ ለመተዳደር ስለማይችልና መንግሥትም መሉ በጀቱን ችሎ  ለማሠራት አቅም ስላልነበረው እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ቴሌቪዥን ከማስታወቂያ አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠር ዓመታዊ ገቢ የሚሰበስብና ተርፎት ለመንግሥት ፈሰስ የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ ጣቢያው ወርቅ በአካፋ የሚዝቀው አርሶና ጎልጉሎ ሳይሆን፣ አድማጭና ተመልካች አለኝ ስለሚልና አለውም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ጥያቄው የጣቢያው የገቢ ማስገኛና መነገጃ የሆኑት ተመልካቾች እንደገና ለጣቢያው እንዴት ግብር ከፋይ ይሆናሉ? ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ክልሎችም የየራሳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ ሌሎችም የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም አሉ፡፡ ኢቢሲ አስገባሪ እንደሆነ የሚቀጥለው በምን መመዘኛ ነው? 

ይህ ከሃምሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረ አዋጅ ከዓመታት በፊት መሻር የነበረበት ቢሆንም፣ ዛሬም እየተጎተተ እያገለገለ ነው፡፡ አዋጁ ጊዜ ያለፈበት ከዘመኑ ጋር መሄድ የማይችል ነው ብሎ እንዲሻሻል ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው ክፍል ላይኖር ይችላል፡፡ ነገም እየተጎተተ ይቀጥል ይሆናል፡፡ መንግሥት የእሱንም ቁርጡን ሊነግረን ይገባል፡፡

‹‹ቁርጡን ንገሪኝ›› አለ ጥላሁን፣ መንግሥት ሆይ አንተም ቁርጡን ንገረኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡