Skip to main content
x
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን  የኋልዮሽ ጉዞ

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኋልዮሽ ጉዞ

ከማሚኮ

ብዙዎቻችን ብሔራዊ ፓርኮች ለዱር እንስሳት ጥበቃ ብቻ የተቋቋሙ ይመስለናል፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን የባለሥልጣኑም ሰዎች እንደዛ የሚያስቡት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፓርኮቻችን የተከለሉት ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ ነው የሚለው አስተምህሮ ብዙ መድረኮች ላይ ስለምናደምጥ፡፡

ለፓርኮቻችን መውደቅም አንደኛው መነሻ ይኼ አስተሳሰብ ነው፡፡ ፓርኮቻችን ከዱር እንስሳ መጠለያነት በላይም የእኛም የሕይወት እስትንፋስ መሠረት ናቸው፡፡

ለአብነት የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ብንወሰድ፣ ከባሌ ሰንሰለታማ ተራራዎች ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት ከ40 በላይ ወንዞች ይመነጩበታል፡፡ እነዚህ ወንዞች ከእኛም አልፈው ለጎረቤት ሶማሊያ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የኑሮ መሠረት ሆነዋል፡፡

የመልካ ዋከናና የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የእነዚህ ወንዞች ውጤት ናቸው፡፡ እነዚህ ወንዞችና ደን በመኖራቸው ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ወንዞቹንም በመጠቀም በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ፓርኮቻችንን በመጠበቅ አገራችን የምትከተለውን የአረንጓዴ ልማት ስኬታማ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም ከካርበን ሽያጭ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ሌላ አማራጭ ይሆናል፡፡

ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የኅብረተሰባችን ክፍል የባህል ሕክምና ተጠቃሚ ነው፡፡ ለመድኃኒት የሚሆኑ በርካታ ዕፀዋት የሚገኙት በብሔራዊ ፓርኮችና በጥብቅ ሥፍራዎች ውስጥ ነው፡፡ በዚህ በኩል የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ይጠቀሳል፡፡

እናም ብሔራዊ ፓርኮች የዱር እንስሳ መኖሪያ ብቻ ሳይሆኑ የሕይወታችን መሠረት የሆኑት ውኃና ንፁህ አየር ምንጭ ከመሆናቸው ባሻገርም ሁሉ ነገራችን እየሆነ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጪያ የሆኑት ወንዞች መሠረት ናቸው፡፡

ፓርኮችን ለራሳችን ብለን ስንጠብቅ የዱር እንስሳቱ ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ እናስችላቸዋለን፡፡ ‹‹በአንድ ጠጠር ሁለት ቅል›› እንዲሉ፡፡ ለካ የለመዳችሁት፣ ‹‹በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ፤›› የሚል አባባል ነው፡፡ ለምንድነው ሁለት ወፍ ቀርቶ አንድ ወፍ የሚገደለው? አንድን ወፍ ለማየት ቱሪስት ስንት አገር አቆራርጦ ይሄዳል፡፡ እኛ ለልጆቻችን በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ እንግደል እያልን እናስተምራለን፡፡ ‹‹በአንድ ጠጠር ሁለት ቅል፤›› ብንል ምን እናጣለን?

እናላችሁ በአንድ ጠጠር ሁለት ቅል እንዲሉ የተፈጥሮ ሀብታችንን ከመጠበቃችንም ባሻገር የዱር እንስሳዎቻችንን ለቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ በማድረግና በስፖርታዊ አደን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ይችላሉ፡፡ ባሌ ፓርክም አይደል ያለነው የባሌ መለያ የሆነው የደጋ አጋዘን (ኒያላ) ከአረጀ በኋላ ለስፖርታዊ አደን የሚሸጠው 15 ሺሕ ዶላር ነው፡፡ በአሁኑ ምንዛሪ ስንመታው ከ400 ሺሕ ብር በላይ ማለት ነው፡፡ እና የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ የማስተዳደር አቅሙ ኖሮን ብንጠቀምበት ለእኛ አይደለም ለሌላ አገር አንተርፍም?

ስለ ብሔራዊ ፓርኮቻችን ምንነት ይህን ያህል ካልኳችሁ እነዚህን ብሔራዊ ፓርኮች ለማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ይህን ስያሜ ከመያዙ በፊት በተለያዩ ስያሜዎችና አደረጃጀቶች አፈር ልሶ የተነሳ ተቋም ነው፡፡

ስለ እውነት ለመናገር አሁን የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ብዙ ሊያሠራው፣ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችለው ቢሆንም፣ መንጃ ፈቃድና ዕውቀት የሌለው ሰው የሊሙዚን መሪ ቢጨብጥ የት መሄድ ይችላል? የቢሮውን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ስብሰባ አሳዳጅ አመራር ዕጣ ፈንታው ሆኗል፡፡

የተቋሙ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› የሚባለው የኢትዮጵያ የደንና ዱር አራዊት ጥበቃ ድርጅት ተብሎ በሚጠራበት ወቅት ነበር፡፡ ወቅቱ የደርግ ሥርዓት በመሆኑ ወደ ፓርኮች ዝር ማለት በራስ ላይ እንደ መፍረድ የሚያስቆጥር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ፓርኮቹ ህልውናቸው ተጠብቆ ታፍረውና ተከብረው እንደነበር ይነገራል፡፡ ይሁንና በኃይልና በጉልበት እንጂ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲጠበቁ ባለመደረጉ የመንግሥት ለውጥ በሚመጣበት ወቅት ለከፍተኛ ጉዳት ተጋልጠዋል፡፡

በወቅቱ ግን ፓርኮቹ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደነበሩ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ለቅኝት (Patrol) ማድረጊያ ድርጅቱ የራሱ አውሮፕላን ነበረችው፡፡ በተለይ ኦሞ ፓርክ በየብስ ግንኙነት ለማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ አውሮፕላኗ ለሠራተኞች ደመወዝና ሬሽን (መቁነን) በማመላለስ ጉልህ ሚና ነበራት፡፡

እንደው ነገርን ነገር ያነሳዋልና የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በዚያ ውጥረት ውስጥ ሆነው ብሔራዊ ፓርኮቻችንን ይጎበኙ ነበር አሉ . . .፡፡ ባሌ ፓርክ ውስጥ እርሳቸው ሲመጡ የሚያርፉበት ክፍል እንዳለ እኔ ራሴ ተመልክቻለሁ፡፡ እናላችሁ በ1973 ዓ.ም. አካባቢ ኦሞ ፓርክን ለመጎብኘት በሔሊኮፕተር ይሄዳሉ፡፡ በአየር ላይ ሆነው የቦታውን ስፋት የተመለከቱት የወቅቱ ግብርና ሚኒስትር ይህን ሁሉ ቦታ ይዘን ሕዝባችን ለምን ይራባል? ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ሊቀ መንበሩም ወደ ፓርኩ ኃላፊ ዞር ብለው ምላሽ ይጠብቃሉ፡፡ የፓርኩ ኃላፊ አቶ ለይኩን አቡኔ አሁንም በሕይወት አሉ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ጓድ ሊቀመንበር አገራችን የመሬት ችግር የለባትም፡፡ ዋናው ችግር የማኔጅመንት ነው፤›› ሲሉ ይመልሳሉ፡፡ ሊቀመንበሩም ወደ ሚኒስትሩ ዞር ብለው የወጣቱን ኃላፊ ምላሽ በአዎንታ ጭንቅላታቸውን በመወዝወዝ ተቀበሉ፡፡

የኢትዮጵያ የዱር አራዊት ድርጅት ስመ ገናናና በጦር መኮንኖች የሚመራ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ከተጎዱት ተቋሞቻችን መካከል ብሔራዊ ፓርኮቻችን ይጠቀሳሉ፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥቱን መሠረት ካስያዘም በኃላ አብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርኮች ወደ ክልል አስተዳደሮች ሲሄዱ የፌዴራሉም ተቋም በግብርና ሚኒስቴር ሥር በመምርያ ደረጃ እንዲወርድ ተደረገ፡፡

እነሆ አፈር ልሶ ተነስቶ ዛሬ አቅም ያለው፣ ግን በአቅሙ ደረጃ መሪ ያላገኘ ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ ብሔራዊ ፓርኮች ወደ ክልል በተላለፉበት ወቅት ሁለት ገጽታዎች ታይተዋል፡፡ በአብዛኞቹ ክልሎች ፓርኮቹ ምንም ለውጥ ያላሳዩበት፣ ይልቁንም ቁልቁል የተንደረደሩበት ሁኔታ ነው የታየው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልል የሚገኙ ፓርኮች በተሻለ ደረጃ የክልሎቹ መንግሥት ትኩረት መስጠታቸው ይታያል፡፡ በተለይ የስሜን  ብሔራዊ ፓርክ ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የመሰረዝ ሥጋት ውስጥ ለማውጣት ካለፉት 15 ዓመታት በፊት ጀምሮ በቅርብ እንደማውቀው የአማራ ክልል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ለስኬት እንዲደርስ በማድረጉ ከማንም በላይ ሊመሰገን ብቻ ሳይሆን፣ በአርአያነትም ለሌሎች ክልሎች ማሳያ ሊሆን ይገባል፡፡

ባለሥልጣኑ በአዲስ መልክ ሲደራጅ በክልሉ የሚገኙትን የስሜን ብሔራዊ ፓርክና የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ወደ ፌዴራል በመሄዳቸው ፓርኮቹ በክልሉ መንግሥት ሲተዳደሩ በነበረበት ደረጃ ትኩረት አለማግኘታቸውን ኃላፊዎቹ በአንድ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡ የስሜን ብሔራዊ ፓርክም ከመሰረዝ ሥጋት የወጣው ክልሉ ሲያስተዳድረው በባለቤትነት ለዓመታት በቁርጠኝነት በመሥራቱ እንጂ በባለሥልጣኑ ሥር ቢሆን ኖሮ እንደማይሳካ በቅርብ ያሉ ባለሙያዎች አስምረው ይናገራሉ፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ ደንና የዱር እንስሳት ባለሥልጣን ወደ ፌዴራል የሄዱትን ፓርኮች ወደ ክልሉ ለማስመለስ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ በእርግጥም ከዚህ በፊት ከነበራቸው መልካም ሥራ የአማራና የትግራይ ክልል ፓርኮቹን በባለቤትነት ቢያስተዳድሩ ውጤታማ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡ እንደ አገርም አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ የተሻለ ይዞታ ያላቸው ፓርኮች የሚገኙት በእነዚህ ሁለት ክልሎች ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

ኢዱልጥባ ምን እየሠራ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት ፓርኮቹ እየጠፉ እንጂ ለውጥ የሚታይባቸው አይደሉም፡፡ ጥር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የዱር እንስሳ በአውሬዎች ሲበሉ›› በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አቅርቤላችሁ ነበር፡፡ በወቅቱም እንስሳቱን ከአውሬዎች ለመታደግ የሚመለከታቸው አካላት የወሰዱትን ዕርምጃ ማክበር እፈልጋለሁ፡፡

ተቋሙን በአዲስ መልክ ለማደራጀት የተጀመረው ጥረት መልካም ቢሆንም፣ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን የውስጥ ሠራተኞች በምሬት ሲገልጹ፣ እኛም በውጭ የታዘብነው አለ፡፡ ከዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪ ከቦታቸው ከተነሱት ኃላፊዎች አንዱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ነው፡፡ በምትኩም ሌላ ኃላፊ ይመደባል፡፡ አዲስ የተመደበው ኃላፊ ገና ሥራ ሳይጀምር ኃይለኛ የኮሪደር ወሬ ይናፈሳል፡፡ “ሰውየው ኃይለኛ ነው፣ ለአለቃ የሚመች አይደለም፣ ይታገላል፣ ወዘተ” በስፋት ይናፈሳል፡፡ ይህን ወሬ እንዲናፈስ ያደረገው ከቦታው የተነሳው ኃላፊ ነው የሚል ወሬ ነገሮች ከተቀየሩ በኋላ ሰምቻለሁ፡፡ ከቦታው የተነሳው ኃላፊ ይህ ወሬ እንዲናፈስ ያደረገው ንግድ ሚኒስቴር እንደ ተመደበ ስላወቀ ነው አሉ፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ ደቡብ ክልል አብረው የካቢኔ አባልና ሁለቱም የቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በወቅቱም በነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ለሚዲያ መግለጽ የሚከብደውን የግለሰቡን ሰብዕና በማጋለጥ ከኃላፊነቱ እንዲባረር ካደረጉት የካቢኔ አባላት ቀንደኛው በመሆናቸው አሁንም እርሳቸው በሚመሩት ሚኒስቴር መመደብ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቱን ስለሚያውቁ ቀናት አያሳድሩኝም በማለት እንደሆነ ሁለቱንም በቅርበት የሚያውቋቸው ይገልጻሉ፡፡ እናም ያለው አማራጭ አዲስ የተመደበውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ላይ ለአለቃ አስቸጋሪ መሆኑን በማስወራት አዲሱ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርን በማሸበር የጀመረው ሥራ አለ በሚል ሰበብ እንዲያስቀሩት ይማፀናል፡፡ ‹‹ከማያውቁት መልአክ . . . ›› እንዲሉ ዋና ዳይሬክተሩ በራሳቸው መተማመን ሲገባቸው ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ተደጋጋሚ ደብዳቤ በመጻፍ በቦታው እንዲቆይ ያደርጋሉ፡፡

ለባለሥልጣኑ አንዱ ውድቀት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቃትና አቅም ያለው የኮሙዩኒኬሽን ሰው መመደብ ሲገባ ከጌዲኦ ዞን አስተዳዳሪነት በኋላም ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቱ ተገምግሞ የተባረረን ሰው መደበቂያ ማድረጉ ተቋሙን ብቻ ሳይሆን ድርጅቱንም ለትዝብት የሚዳርግ ነው፡፡ በጳጉሜን 2008 ዓ.ም. በተደረገ የድርጅት ግምገማ አባላት በሕግ ይጠየቁልን ካሏቸው ሦስት ከፍተኛ አመራሮች በቁጥር አንድ የተቀመጠው ይኼው ግለሰብ ነው፡፡ እስከ አሁን ምንም ዕርምጃ ሲወሰድ አላየንም፡፡

ይህ ግለሰብ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ በነበረበት ወቅት በክልሉ ከፍተኛ ተወዳጅ የሆነውንና የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች በጉጉት የሚሳተፉበትን ‹‹የሺ ኮኮቦች ፌስቲቫል›› እስከ አሁን እንዲዘጋ ያደረገ ነው፡፡ የሺ ኮኮቦች ፌስቲቫል የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ ለማቀራረብና ባህላቸውን ለማሳደግ ‹ዘ ክርስቲያን ሰን ፈንድ› የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ጉጌ በተባለ አገር በቀል ድርጅት የሚቀርብ ነበር፡፡ ጉጌ የተባለውን ድርጅት ምክንያት በመፍጠር በማፍረስ ገንዘቡን ወደ ቢሮው ቀጥታ ፈሰስ በማስደረግ ቢሮው እንዲያዘጋጅ ያስደርጋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ቢሮው ባዘጋጀው ፌስቲቫል ከፍተኛ ምዝበራ በመካሄዱ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ዝርዝሩን ከግምገማው ውጤት ማየት ይቻላል፡፡ ይህ ፌስቲቫል በተከበረ በሁለተኛው ወር ይህ ግለሰብ በግምገማ ከቢሮ ኃላፊነቱ ይባረራል፡፡ ለወራት ያለሥራ ቤቱ ከቆየ በኋላ አሁን አምባሳደር የሆኑት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር በኔትወርክ ወደ ዱር እንስሳ ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሊያመጡት ቻለ፡፡

የበግ ለምድ ለብሰው ለድርጅት ተቆርቋሪ መስለው ሕዝብን እያማረሩ ባላቸው ኔትወርክ የሚሽሎኮለኩ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ኢሕአዴግ ጠንካራ አቋም ካልያዘ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የመጣ ሰው ነው ለውጥ ያመጣል ብለን የምንጠብቀው? 

ለባለሥልጣኑ ሌላው መሰናክል አሁን ባለው አደረጃጀት ደሴት ሆኖ መቀመጡ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው፡፡ ባለሥልጣኑና ሚኒስቴሩ  ከመነሻው በቋንቋ አይግባቡም፡፡ ሲቀጥል አሁን ብሔራዊ ፓርኮቻችን የከብት መዋያ በመሆናቸው የሚጎበኙ ሳይሆኑ የአድኑኝ ጥሪ ላይ ናቸው፡፡ መዳን የሚችሉት ደግሞ በባለሙያ ሲታገዙ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ በቋንቋ ሊግባባና የተሻሉ ባለሙያዎችን በዝውውር እንኳን ሊያገኝና ሊመጋገብ የሚችለው ለአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ተጠሪ ሲሆን ነው፡፡ አደረጃጀቱን ለማስተካከል ጥናቶች እየተደረጉ ነው የሚል ወሬ ከሰማን ዓመታት ቢቆጠሩም ተግባር ግን አይተን አናውቅም፡፡ ባለሥልጣኑ አሁን ባለበት እንዲቆይ የሚፈልጉና ያሉበትን ወንበር እንደ ርስት ይዘው መቆየት የሚፈልጉ ግለሰቦች መኖራቸው ይነገራል፡፡ ግለሰቦች ነገ ያልፋሉ፡፡ አገር ግን ትቀጥላለች፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኃልዮሽ ጉዞም አንድ ቦታ ሊቆም ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡