Skip to main content
x
‹‹ዘመቻ ፍቅር ለኢትዮጵያ አንድነት››

‹‹ዘመቻ ፍቅር ለኢትዮጵያ አንድነት››

‹‹ውድ ልጆቼ… መቼም ታሪክ ይቅር የማይለው፤ ለስርየትም የማይመች ስህተት መሥራቴ ይታወቀኛል፡፡ ጥሬዋን ቆርጥሜ ያደግሁባትን ሀገር መበደሌ አንሶ፣ እናንተን ልጆቼን ለዚህ አሰቃቂ መከራ ያደረስኳችሁ እኔ ራሴ ነኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ከአሁን በኋላ እንደገና የአንድ ሰው ዕድሜ ቢጨመርልኝ እንኳ እናንተን መካስ አልችልም፡፡ ኢትዮጵያን ግን የተጋረጠባትን ታሪካዊ እንቅፋት በማስወገድ በትንሹም ቢሆን ልክሳት ወስኛለሁ፡፡ እናም ከአሁን በኋላ እኔን አትፈልጉኝ፡፡ ይልቅ የአያቶቻችሁን የነራስ አሉላ አባነጋን ሀገር… ኢትዮጵያን አጥብቃችሁ ፈልጓት፡፡ ይህን ደብዳቤ አንብባችሁ እንደጨረሳችሁ ወደ ውጪ ስትወጡ በተጠንቀቅ የሚጠብቃችሁ ልዩ መኪና አዘጋጅቼላችኋለሁ፡፡ መኪናው ውስጥ ያለው ሰውዬ ያዘዛችሁትን ሁሉ ያደርግላችኋል፡፡ እኔ ግን ወደ ታላቁ ጦርነት ከትቻለሁ፡፡ ወደ አርማጌዶን፡፡ መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ፡፡››

ይህን ዐውደ ንባብ የያዘው ‹‹ተልዕኮ አርማጌዶን›› የተሰኘው የተስፋጽዮን ጋሻነህ መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹ዘመቻ ፍቅር ለኢትዮጵያ አንድነት›› የሚል ንኡስ ርዕስ ያለው መጽሐፉ እውነታን በልቦለድ አስተሳስሮ የቀረበበት፣ በታዋቂው ቀዶ ሐኪም ነፍስኄር ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ታሪክ ላይ ተመሥርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊና ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ያሉ ገጽታዎች ከታቦተ ጽዮን ጋር ተሳስሮ የቀረበበት መጽሐፉ፣ መቼቱን ከኢትዮጵያ ኤርትራን ጨምሮ ባሕር ማዶ ባሉ አገሮች አሜሪካን አካትቶ ይዟል፡፡ በ‹‹ዘመቻ ፍቅር›› እንደተገለጸውም፣ ‹‹ስለዚህ አዲሱ ታቦታችን ፍቅራችን ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በንቃት የምንጠብቀውም ይህን የከበረ ሕግ የተጻፈበትን ልባችንን ነው፡፡ ፍቅር ባለበት ሁሉ መልካምነት፣ ይቅርታ፣ አንድነት አሉና፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ደግሞ አንድነት ጥያቄ ሆኖ ሊነሳ አይችልም! ለዚህ ነው ተልዕኮ አርማጌዶን ከታቦት ያለፈ ምስጢራዊ ዓላማ ያለው መሆኑን የታሪካችንን መጽሐፍ ለማንበብ ዕድሉን ያገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊገነዘቡልን የሚገባው፡፡››

መጽሐፉ 232 ገጽ ሲኖሩት ዋጋውም 69.99 ብር ነው፡፡

የሁለት የፍልስፍና መጻሕፍት ምረቃ

በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የፍልስፍና መምህር የሆኑት አቶ ፀሓዬ ይኄይስ ያዘጋጇቸው ‹‹የፍልስፍና መግቢያ›› እና ‹‹ዝኽረ ሶቅራጠስ የመጀመርያው የፈላስፋ ሰማዕት ሕይወትና ፍልስፍናዊ አስተምህሮ›› መጻሕፍት መሰንበቻውን ለኅትመት በቅተዋል፡፡

ፕሌቶ የጻፈውን ዝኽረ ሶቅራጠስ እንደተረጎሙት አቶ ፀሐዬ መቅድማዊ አገላለጽ፣ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቃለሉትና የተቀሩበት ሌሎች የፕሌቶ ጽሑፎች ከ2300 ዓመታት በፊት የተጻፉ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ከተጻፉት ዘመን ጀምሮ በጥንታዊው፣ በመካከለኛው፣ በሕዳሴውና በዘመናችንም አስተሳሰብ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተፅዕኖአቸውን ሊያሳርፉ የቻሉ ዘመን ያልሻራቸው ‹‹ዕፁብ ድንቅ›› ጽሑፎች ናቸው፡፡

‹‹አየህ፣ እኛ የምናድግ ፍጡሮች ነን፡፡ በቀጣይ የመሆን ሒደት ላይ ያለን ቢያንስ ለማርጀት! ግን ደግሞ በተስፈኝነት ወደተሻለ በመሆን ሒደት ላይ ነን፤ የበለጠ ለመማር፣ የበለጠ ክህሎት ለመደለብ፣ የበለጠ ለመብሰል ብሎም ብልህ ለመሆን፤›› የሚል ኃይለ ቃል በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን የሠፈረው ‹‹የፍልስፍና መግቢያ›› ላይ ነው፡፡

በደራሲው መግቢያ እንደተጻፈው ዋነኛ ተልዕኮው የያዘውን ርዕሰ ጉዳይ መሠረታዊ ፍቺ መግለጽ ነው፡፡ በሰባት ዐበይት ምዕራፎች የተከፈለው መጽሐፉ ቅድመ ነገርን፣ የፍልስፍና ምንነትን፣ ፍልስፍና እና ፍልስፍናዊ ሕይወትን፣ የፍልስፍና ጥያቄዎችን፣ የፍልስፍና ታሪካዊ አነሳስና ዕድገት፣ ፍልስፍናዊ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም ዐበይት የፍልስፍና ዘርፎች ተገልጾበታል፡፡

ሁለቱ መጻሕፍት ረቡዕ ኅዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. አስኮ በሚገኘው ካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍና እና የነገረ መለኮት ተቋም ከረፋዱ 5 ሰዓት እንደሚመረቁ ታውቋል፡፡

የሁለት የፍልስፍና መጻሕፍት ምረቃ

 

 ‹‹የማያልቅ አዲስ ልብስ››

‹‹የማያልቅ አዲስ ልብስ›› የበቃሉ ሙሉ የግጥም ስብስብ ሲሆን፣ ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ተመርቆ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹ብራና እና ወናፍ›› የተሰኘ የግጥም መድብል አሳትሟል፡፡ አዲሱ መጽሐፍ በ49 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

‹‹የማያልቅ አዲስ ልብስ››

 

ዐውደ ርዕይ

ዝግጅት፡- ‹‹ቢካም ኤ በተርፍላይ›› በሚል የአዕምሮ ዝግመት ባለባቸው ሠዓሊያን የተዘጋጁ ሥዕሎች ይታያሉ፡፡

ቀን፡- ከኅዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሕዝብ እይታ ክፍት ይሆናል

ቦታ፡- አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ