Skip to main content
x

በአርሲ ነገሌ በግለሰቦች ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት ሲጠፋ ንብረት ወደመ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ከተማ ውስጥ በሁለት ጓደኛሞች አለመግባባት ምክንያት በተፈጠረ ግጭት፣ የሰው ሕይወት መጥፋቱና ግምቱ ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ንብረት መውደሙ ተገለጸ፡፡

የሪፖርተር ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት በአርሲ ነገሌ ከተማ ልዩ ስሙ 03 ጡረታ ሠፈር በሚባለው አካባቢ፣ ሁለት ጓደኛሞች ደረጀ ግሮሰሪና ሆቴል የሚባል መዝናኛ ውስጥ ይጋጫሉ፡፡ የሁለቱ ጓደኛሞች ግጭት እየጠነከረ በመምጣቱ፣ የግሮሰሪው ባለቤት ሊገላግሉ በመሀል ሲገቡ ታጥቀውት የነበረ ሽጉጥ ባርቆ አንደኛውን መግደሉን ምንጮች ተናግረዋል፡፡  

ለመገላገል ገብተው ሕይወት ያጠፉት የግሮሰሪው ባለቤት እጃቸውን ለፖሊስ የሰጡ ቢሆንም፣ የአካባቢው ወጣቶችና ነዋሪዎች በመደራጀት ዓርብ ኅዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ግሮሰሪውን በእሳት ማቃጠላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም በአካባቢው የሚገኙ ሱቆች፣ ቡቲኮች፣ ምግብ ቤቶችና የደረሰ እህል እየለዩ ሲያቃጥሉ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ረብሻውና ጉዳቱ እየጨመረና ወደ ሌላ እየተስፋፋ ስለነበር፣ ከሻሸመኔና ከሌሎች አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ፖሊሶች ሥፍራው መድረሳቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ስለደረሰው ጉዳትና ስላለበት ሁኔታ ሪፖርተር ዓርብ ማምሻውን በስልክ ያነጋገራቸው የአርሲ ነገሌ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብርሃም ግጭቱ የሁለት ጓደኛሞች ቢሆንም፣ መስመር አልፎ መሄዱንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡

ኅትመት እስከገባንበት ኅዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ድረስ የመከላከያ ሠራዊትና ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል በአካባቢው ስለደረሰ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደነበር ኢንስፔክተሩ አክለዋል፡፡

የአርሲ ነገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ቱሉን ሪፖርተር አነጋግሯቸው ችግሩ መከሰቱን የሰሙ ቢሆንም፣ እሳቸው ከአካባቢው ርቀው ሥልጠና ላይ በመሆናቸው ምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ስላላወቁ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡