Skip to main content
x
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ አንድ የመንገድ ግንባታ ውል አልፈጸመም

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ አንድ የመንገድ ግንባታ ውል አልፈጸመም

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ሲያከናውነው ከነበረው በተለየ፣ በ2010 በጀት ዓመት አንድም የመንገድ ግንባታ ውል ሳይፈጽም የበጀት ዓመቱ ታጋመሰ፡፡

ባለሥልጣኑ በቀደሙ ዓመታት እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ድረስ የመንገድ ግንባታ ውላቸው ይፈጸማል ካላቸው ፕሮጀክቶች፣ ቢያንስ አንድ ሦስተኛውን የግንባታ ውላቸውን ይፈጽም ነበር፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ግን እንደ ቀደሙት ዓመታት አዳዲስ የግንባታ ውሎችን ሳይፈጽም መዘግየቱ አዲስ ነገር ሆኗል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ ወገኖች እንደሚገልጹት፣ ባለሥልጣኑ እስካሁን የግንባታ ውሎችን ሳይፈጽም የዘገየበት ምክንያት ከገንዘብ እጥረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ መንግሥት ግንባታዎችን ለማቀዛቀዝ ካለው ፍላጎት አንፃር ሊታጠፉ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው ይላሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ግን የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የግንባታ ስምምነቶች ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ሳይካሄዱ የዘገዩት የግዥ ሒደቱ ጊዜ በመውሰዱ ነው ይላል፡፡

በ2009 በጀት ዓመት እስከ ሁለተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ድረስ (ስድስት ወራት) በአጠቃላይ ስምንት የመንገድ ግንባታዎች ውላቸው ተፈጽሞ እንደነበር የጠቆሙ አስተያየት ሰጪዎች ግን፣ ችግሩ ግልጽ ባይሆንም ይኼን ያህል መዘግየቱ በበጀት ዓመቱ ግንባታቸው ይጀመራሉ ከተባሉ መንገዶች ውስጥ ተግባራዊ የማይሆኑ መኖራቸውን የሚጠቁም ነው ይላሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሪፖርተር ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በበጀት ዓመቱ ይፈረማሉ ተብለው የተያዙት የመንገድ ፕሮጀክቶች የግዥ ሒደታቸው የተጀመረው በዚሁ በጀት ዓመት በመሆኑ ጊዜ ወስዷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ይፈረማሉ የተባሉት ፕሮጀክቶች የግዥ ሒደታቸው ደግሞ እስከ አራት ወራት የሚጠይቅ በመሆኑ ጨረታ ተካሂዶ ከሥራ ተቋራጮች ጋር ውል ለመፈጸም ባይቻልም፣ አሁን ግን የአንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች የጨረታ ሒደት እየተጠናቀቀ በመሆኑ ከታኅሳስ 2010 ዓ.ም. በኋላ የኮንትራት ውላቸው መፈረም እንደሚጀምር የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡ 

ግንባታቸው ይጀመራል የተባሉት መንገዶች በሙሉ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ይፈረማሉ ተብሏል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ግንባታቸውን ለማስጀመር በዕቅድ የያዛቸውና በዚሁ መሠረት በጀት ያስፈቀደላቸው ፕሮጀክቶች 69 ናቸው፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ አስፈጽማቸዋለሁ ላላቸው አጠቃላይ ክንውኖቹ የተፈቀደለት በጀት 46 ቢሊዮን ብር መሆኑ አይዘነጋም፡፡