Skip to main content
x
‹‹የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን የሚመርጡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ክለቦች መሆን አለበት››

‹‹የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን የሚመርጡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ክለቦች ብቻ መሆን አለበት››

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ

በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የስፖርትና የኦሊምፒክ ተቋማት ለዘመናት በሰጡት ሁለገብ አገልግሎት ይታወቃሉ፤ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት፣ የቴኒስና የእግር ኳስ ሊግ ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ መርሕ መሠረት 1960 .. ዳግም ሲደራጅ በዋና ጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ 1960 እና 1968 .. 6ኛውና 10ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን በማዘጋጀት ረገድ በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች አባልነት ብዙ እገዛዎችን አድርገዋል፡፡ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አማካሪ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አማካሪ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቶ ፍቅሩ በቀዳሚው ሕይወታቸው ከእግር ኳስ ተጫዋችነታቸው በኋላ የስፖርት አስተማሪ ሆነውም ነበር፡፡ ከበረኝነታቸው ጋር በተያያዘ በቃል ግጥምም ያገኙት ውዳሴም፣

‹‹ዳኛው አዳልቶ ቢሰጥ ሪጎሬ

እንቅ አርጎ ያዛት ያ ፍቅሩ ኪዳኔ›› የሚል እንደነበር በአንድ የታሪክ ማስታወሻ ሠፍሯል፡፡ ከዚያም 1949 .. በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ በመሆን ከስታዲየም የስፖርት ፕሮግራምችንሬዲዮ ጭምር ማሠራጨት መጀመራቸው ይነገራል፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ባሕር ማዶ ከተሰደዱ በኋላ ከሙያው ሳይርቁ በእንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ የሚዘጋጅ ኢንተርኮንቲኔንታል መጽሔት መሥራችና ዋና አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡ እነአበበ ቢቂላ በተካፈሉበት የሮም ኦሊምፒክ ጨዋታዎች (... 1960) አጋጣሚም የኦሊምፒክ ታሪክን አሳትመዋል፡፡ የቅርብ ሥራቸውም ከራሳቸው ሕይወት በመነሳት በጉለሌና በፒያሳ (አራዳ) ዙርያ ታሪክ ጠቀስ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ስፖርትና ኦሊምፒክ በቅርበት የሚከታተሉ እንደመሆናቸው፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ያላቸውን ምልከታ አስመልክቶ  ከሚኖሩበት ፈረንሣይ  በአራት ነጥቦች ዙሪያ ለሪፖርተር በኢሜይል የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ስለኢትዮጵያ ስፖርት

ከበርካታ ዓመታት ጀምሮ የአገራችን ስፖርት ምስቅልቅሉ ሲወጣ እያየን ከርመናል፡፡ ይሻሻላል የሚል ጉጉትም ነበረን፣ በበኩሌ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችንም በማነጋገር ለውጥ ያስከትላል የሚል እምነትም ነበረን፡፡ ስፖርቱም እንደ ሌሎቹ የድርጅት አወቃቀሮች ዘር ላይ የተመሠረተ ስለሆነ በሞያና በችሎታ ሳይሆን በክልል የተመረጡ ሰዎች ፌዴሬሽኖቹንና ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ተረክበው መቀለጃ አድርገውታል፡፡

‹‹መሬቴን ሲያርሱበት አያለሁ ዝም ብዬ

 ዘር ሳይዙ ማረስ ምን ያደርጋል ብዬ›› በማለት የተረተው የአገሬ ሰው ተስፋ ስለቆረጠ ነው፡፡ እውነትም የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ድርጅት ሆንዋል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ደካማነት የባለሙያዎች መጥፋት የመሪዎቹ የስፖርት አስተዳደር ችሎታ ማነስ ተደማምሮ ዝብርቅርቁ የወጣ ፌዴሬሽን አድርጎታል፡፡

ስለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ

በጣም የሚያሳዝነው ኢትዮጵያ ለሌሎች አገር ምሳሌ የነበረች፣ ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስ የአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንቦችን ያረቀቀው ይድነቃቸው ተሰማን ያፈራች አገር የፊፋና የካፍ መሳቂያ መሆንዋ ነው፡፡ አቶ ይድነቃቸው ከፈረንሣይ ፉትቦል ፌዴሬሽን ከፓሪስ ያመጣቸውን ሰነዶች በሙሉ በአማርኛ ተርጉሞ ታትሞ ከተበተነ በኋላ ሕዝቡ ደንቦቹን በደንብ እስኪረዳ ድረስ ለብዙ ዓመታት መመሪያዎቹ በፈረንሣይኛና በአማርኛ ነበር የሚታተሙት፡፡ ይህም ማለት የሕግንና ዴሞክራሲን የበላይነት ለማስረዳት ነው፡፡ የትርጉም ችግር ቢፈጠር የፈረንሣዩ ሰነድ በዋናነት ይወሰዳል ማለት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፊፋና ካፍ ያወጡትን መመሪያ ስንኳን የሚያነብ ስለጠፋ እያንዳንዱ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል የራሱን ጥቅም በማስቀደም ሕጉን ሁሉም በፊናው በመተርጐም ለፊፋ በመጻፍ አገራችንን ሲያዋርዱ ተገንዝበናል፡፡ ከዚህ በቀር እርስ በራሳቸው እየተደባደቡ ሥነ ምግባር የማናውቅ፣ ባህል የሌለን ጨዋነት ያነሰን ሕዝብ አስመስለውናል፡፡ ከመሃከላቸው ካፍ ድረስ በጠባይ ማነስ ክስ የቀረበባቸው አባሎች አሉ፡፡ እነኝህ ሰዎች ለኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ምሳሌ ሊሆኑ የማይችሉ በስፖርት ዓለም ውስጥ ሥፍራ የሌላቸው ለምርጫ መቅረብ የማይገባቸው ናቸው፡፡

ስለፌዴሬሽኑ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት

ለምሳሌ ለምርጫ የሚቀርቡትን የሚወስኑና የሚወክሉ ክልሎች ናቸው፡፡ ማለትም የክልል እግር ኳስ ፌደሬሽኖች፡፡ ማነው እነኝህን የክልል ፌዴሬሽኖችን የመሠረተው፣ የሚቆጣጠረው? በመሠረቱ የአገሪቱን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባሎችን መምረጥ የሚችሉ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ክለቦች ብቻ መሆን አለበት፡፡ ካስፈለገ በድምፅ አሰጣጥ ላይ ፕሪሚዬር ሊግ 3 ድምፅ፣ ከፍተኛ ሊግ 2 ድምፅ፣ ብሔራዊ ሊግ 1 ድምፅ ብሎ መወሰን ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ተመራጮቹ በክለቦች የተመለመሉ፣ እግር ኳስ የሚወዱ በነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱ፣ ወጣቶችን የሚደግፉ ራሳቸውን የቻሉ ጨዋ ሰዎች መሆን አለባቸው እንጂ፤ ገና ለገና በቴሌቪዥን እታያለሁ የሠፈር ሰውም ያየኛል፣ በጋዜጣም ላይ ፎቶግራፌ ይወጣል ብሎ በሙስና በር አስከፍቶ የሚመረጠውና ለራሱ ጥቅም የሚሯሯጠው መሆን የለበትም፡፡

ለፊፋ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ለመሆን የሚወዳደር ሁሉ በድርጅቱ ኤቲክስና መልካም አስተዳደር ማለትም የሥነ ምግባር ኮሚቴ ተመርምሮ ካለፈ ነው፡፡ ወደፊት ካፍም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ወይም የስፖርት ሚኒስትሮች በዚህ ዘዴ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ አገራችን ንቁና ተቆርቋሪ የስፖርት ሚኒስቴር፣ የስፖርት ኅብረተሰብና የሥነ ምግባር ኮሚቴዎች ባለመኖራቸው ነው፣ ከዚህ ቀደም ሚኒስትር ዴታው የኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ከሆነ በኋላ ነው ሁሉም ነገር የከሸፈው፡፡ በዓለም ውስጥ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፣ የስፖርት ሚኒስትር ዴታ የኮሚቴ አባል ሲሆንና የኦሊምፒክ ኮሚቴውን ፕሬዚዳንት ተከትሎ ጉብኝት ሲሄድ፡፡ የፌዴሬሽኑና የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚተች፣ የአገራችንን ሴቶች የሚያዋርድ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አሁን እንደሰማሁት ግን ውክልና ሰጥቶት የነበረው የትግራይ ክልል ውክልናውን ሰርዟል አሉ፡፡ ይኼም አስመስጋኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ሥነ ምግባር የሌለው ሰው መሆኑን ማስረጃ ነው፡፡ አገራችን በዕውቀታቸው የበለፀጉ በልዩ ልዩ መስክ የሠለጠኑ ጨዋ ሰዎች ያፈራች ስለሆነ ልክ እንደ ጥንት ጊዜ ብዙ አገልጋዮች ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ተገቢው ዘርና የፖለቲካ ፓርቲው አባል ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ መታወቂያቸውም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ የዚህ የእግር ኳስ ጭቅጭቅ ከተፈጸመ በኋላ የኦሊምፒክ ኮሚቴውን ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ ሁለት ደብዳቤዎች ለካፍ ጽፎ ከላከ በኋላ ምንም ደብዳቤ አልተላከም ብሎ መዋሸት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ  አንዱ ተወዳዳሪ ስለ ጠቅላላው ጉባዔው ሁሉ ነገር ተሟልቷል ብለህ ጻፍ ብሎ ባዘዘው መሠረት ለፊፋ መጻፍ ስህተት ነው፡፡ ይህ ሰው ከፌዴሬሽኑ በአስቸኳይ መሰናበት አለበት፡፡ አለበለዚያ ቤቱን ያፈርሳል፡፡

ኢትዮጵያን ከማዋረዳቸው በላይ አፍሪካን መሳቂያ ያደረጉት ሰዎች የቋንቋ ችግር ስላለባቸው ሼክስፒርም ስላኮረፋቸው፣ ፊፋ የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ደንቦች ተመልክቶ ያጐደለውን በማሟላት ምርጫ ለማካሄድ ተገቢ የሆኑት ኮሚቴዎች እንዲሰየሙ አድርጎ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ዕርዳታውን ያበረክታል፡፡ ከፊፋና ከካፍም ታዛቢዎች እንዲገኙ ያደርጋል፡፡ ለማንኛውም ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ መንግሥትም የስፖርቱን ጉዳይ ለፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ካልሆነ በቀር ችላ ያለው ይመስላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቆሙት፣ በስፖርት አስተዳደሩም መስክ ሞያተኞች ኃላፊነቱን መረከብ ካልቻሉ ቀለጥን ማለት ነው፡፡ ለክለቦቹ የመምረጥ መብታቸው ቢመለስ ከመሃላቸውና ከአካባቢያቸው ከደጋፊዎቻቸው ውስጥ ዕጩዎች ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በመሠረቱ በዓለም ደረጃ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በክለቦች የሚመራ ነው፡፡ ክልል የሚሉት ነገር የለም፡፡ ለማስታወስ ያህል የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ በ1941 ዓ.ም. የተመረጠው የሚቀጥለው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ከበደ ገብሬ (በኋላ ሌተና ጄኔራል) ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር አዛዥ፣ በኮንጎ ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግሥታት ጦር አዛዥና የአገራችን የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ)፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል አበበ ደገፋ (ከፈረንሣይ ሚሊቴር አካዴሚ የተመረቁ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩ) ዋና ጸሐፊ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የፌዴሬሽኑ መሥራች፤ ገንዘብ ያዥ ሻምበል በኋላ ጄኔራል ወልደዮሐንስ ሽታ (ኮሪያና ኮንጎ የዘመቱ የጦር አዛዥ) የኮሚቴ አባሎች አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ የጎማ ቁጠባ ፋብሪካ ያቋቋሙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ፕሬዚዳንት (የአቶ አብነት ገብረመስቀል አጎት)፣ አቶ ሰሎሞን አብርሃ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ሻለቃ ኃይሌ ባይከዳኝ (በኋላ ሌተና ጄኔራል፣ ሻለቃ ጋሻው ዘለቀ በኋላ ጄኔራል፣ ሻለቃ ዓለሙ ግዛው፣ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን (ስዊድን) ሙሴ ዲሚትሪ ስጎሎምቢስ (ግሪክ)፣ ሙሴ ቩሴኪስ (ግሪክ)፣ ሙሴ ናልዲ (ጣልያን)፣ ሻለቃ ኤስካንሶን (ስዊድን) ነበሩ፡፡ በምርጫው የተካፈሉት ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቀይ ባህር ክብር ዘበኛ፣ ጦር ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ መስፍነ ሐረር፣ ጤና ጥበቃ፣ ኦሊምፒያኮስ፣ አራራት፣ ፎርቱቲዶ፣ የእንግሊዝ ጦርና የህንድ ነበሩ፡፡ በዚያን ዘመን ፌዴሬሽኑ መነቃነቂያ ስላልነበረው በሻምበል ወልደዮሐንስ ሽታ አማካይነት የክብር ዘበኛ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ በጃንሜዳ ለፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት የሚሆን አንድ ክፍልና አምስት መቶ ብር ብድር፣ እንዲሁም አንድ ተላላኪ ድጋፍ ሰጥተው ነው፣ አቶ ይድነቃቸው የረዥም ዓመታት አገልግሎቱን የጀመረው፡፡ በእኛ ዘመን በፌዴሬሽኑ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ብዙ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች አገልግለዋል፡፡ ለምሳሌ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ አቶ ማሞ ታደሰ፣ አቶ (በኋላ ዶ/ር) ሥዩም ሐረጎት፣ አቶ አብተው ገብረየሱስ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኰንን፣ አቶ ሰይፉ ማህተመሥላሴ፣ ልጅ ካሳ ወልደማርያም፣ አቶ መብዓሥላሴ ዓለሙ፣ አቶ አብዱላሂ ሙጫ፣ ኮሎኔል ሰሎሞን ከዲር፣ ጄኔራል ወልደሥላሴ በረካ፣ ጄኔራል ያዕቆብ ገብረልዑልን የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ ለብዙ ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ኮሎኔል ታምራት ይገዙ የከፋ፣ የቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛቶች አስተዳዳሪ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂነር መኰንን ሙላት ናቸው፡፡ ኮሚቴዎች ውስጥ ካገለገለት ውስጥ ዶ/ር ያየህራድ ቅጣው፣ ዶ/ር ብርሃኔ ገብራይ፣ አቶ ላቀው አሰፋ፣ እንዲሁም ከ30 ዓመታት በላይ በምክትልና በዋና ጸሐፊነት ፌዴሬሽኑን ያገለገለው አቶ ካሳ ገብረጊዮርጊስ ጭምር አሁንም አዲስ አበባ የሚኖሩና የእግር ኳስ ሁኔታ ቅዠት የሚመስላቸው ታዛቢዎች ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውድድር ደረጃ 

በጥንት ጊዜ የትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ውድድር በጣም የተወደደ ነበር፡፡ ዕሮብ ዕሮብ የአዲስ አበባ ተማሪ በሙሉ ቡድኖቹን ለመደገፍ በእግሩ አገር ሲያቋርጥ ይታያል፡፡ ፀጥታ አስከባሪው ቦይስካውቶች ነበሩ፡፡ ለአንደኛ፣ ለሁለተኛና ለትንንሾቹ ሦስተኛ ቡድኖች ትጥቅ የሚያቀርበው ትምህርት ሚኒስቴር ነበር፡፡ ኃይለኛ ቡድኖች የተፈሪ መኰንን፣ ተግባረ ዕድ፣ መድኃኔዓለም፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ቀኃሥ) ሁለተኛ ደረጃ ኮተቤ፣ ሊሴ ገብረማርያምና ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቶች ነበሩ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ብቻ ሳይሆን በክብር ዘበኛ (መኩሪያ)፣ ጦር ሠራዊት (መቻል)፣ አየር ኃይል (ንብ)፣ ፖሊስ (ኦሜድላ) ቡድኖች ውስጥ ይጫወቱ የነበሩት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተመለመሉ፣ በየአካዴሚው ይሠለጥኑ የነበሩት ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይጫወትበት የነበረው የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ቡድን የጦር ሠራዊቱን መቻልን አሸንፏል፡፡ የትምህርት ቤት ስፖርት ድራሹ ከጠፋ ቆይቷል፡፡ ልጆቹም የሚጫወቱበት የሠፈር ሜዳ ከተወረሰ ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ለጊዜው ያለው መጫወቻ ሥፍራ ባቡር መንገድ (አስፋልት) ላይ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶች መጫወቻ ሥፍራ እየተመናመነ ተጨማሪ ክፍሎች ተሠርቶበታል፡፡ ታዲያ የአገራችን ወጣቶች በየትኛው ሜዳ ላይ ተጫውተውና ሠልጥነው ነው ለብሔራዊ ቡድኖች የሚሰለፉት? ፊፋና ካፍ ለወንድና ሴት ወጣቶች የሚያዘጋጇቸው ውድድሮች አሉ፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ በስንቱ ነው የተካፈለችው? ፌዴሬሽኑ ስለ ወጣቶች ያስባል ወይ? ስለ ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ለሚያወራ መሪ ልጆቻችንን አሳልፈን እንሰጣለን ወይ? የአገራችን ስፖርት እንዲስፋፋ ከተፈለገ ወጣቶቹ በስፖርት ተኮትኩተው ማደግ አለባቸው፡፡ ስለዚህም የትምህርት ቤቶች ስፖርት እንዲጠናከር የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎቹ በየመንደሩ እንዲኖሩ ልክ እንደ ጥንቱ የጉለሌ፣ የቀበና፣ የአባ ኮራን፣ የመርካቶ፣ የለገሃር፣ የካዛንቺስ ቡድኖች ሕይወት ዘርተው እንዲጫወቱ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ከ60 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ቅዳሜ ቅዳሜ በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የቦክስ ምሽት፣ እሑድ እሑድ ጧት ቢስክሌት እሽቅድድም፣ ከቀትር በኋላ በጃንሜዳ የፈረስ ግልቢያ፣ የሞተር ቢስክሌት እሽቅድድም፣ ካምፖሎጆ የእግር ኳስ ውድድር የሚታይበት ዘመን ነበር፡፡ ታዲያ አሁን መሻሻል ሲገባን ወደኋላ የቀረነው  ለምንድነው? መሪ ስለጠፋና በዳበሳ ብቻ የሚንቀሳቀስ ስለበዛ ነው፡፡ ስለ እግር ኳስ ቡድኖች ስናወራ አሠልጣኞች፣ ዳኞች፣ ሐኪሞችና ወጌሾች ሁሉ እንደሚያስፈልጉ ግልፅ ነው፡፡ የአሁኑ ፌዴሬሽን አሠልጣኞች እንደ ሸሚዝ የሚቀይር ነው፡፡ ለመሆኑ በየትኛው የቴክኒከ ዕውቀታቸው ነው፣ አሠልጣኝ ለመተቸትና ለመሳደብ ወይም ለመደባደብ የሚሞክሩት? በፊፋና በካፍ ዘንድ ተፈትነው የተመዘገቡ አሠልጣኞች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአገሪቱ የሚበቁ የወንድና የሴት አሠልጠኞች ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም አርቢትሮች በእነኚህ ዘመን ከነበሩት አርቢትሮች መካከል አቶ ሥዩም ታረቀኝ፣ እ.ኤ.አ. በ1968 ሜክሲኮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ብራዚል ናይጄሪያ (3-3) በሩብ ፍፃሜ  ጃፓን ፈረንሣይ (3-1)፣ በመጨረሻም የፍፃሜ ግማሽ ቡልጋሪያ ሜክሲኮን (3-2) ያጫወተ ነው፡፡ እነ አየለ ተሰማ፣ ደነቀው መንግሥቱ፣ ደመቀ አባተ በአፍሪካ የታወቁ ዳኞች ነበሩ፡፡ አሁን ባምላክ ተሰማ ብርታት መኖራችን ይታወቃል፡፡ ፊፋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ የአርቢትሮች ኮርስ ያዘጋጀው እ.ኤ.አ. በ1954 አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ እኔም ተካፋይ ነበርኩ፡፡ ይህንን ሁሉ መንገድ አቋርጦ የተገነባው የእግር ኳስ ጨዋታ ቀልቡ የጠፋው በመጨረሻም ለአገሬ ስፖርት ዕድገት የምመኘው የእግዚአብሔርን ምርቃት ነው እንጂ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ አይደለም፡፡