Skip to main content
x

የኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲ›› እና ‹‹ማዕከላዊነት›› የመጨረሻ ምዕራፍ

በአይተን ጂ.

የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከቆየባቸው 27 ዓመታት ባለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠሙት ፖለቲካዊ ችግሮች በጥልቀትና በውስብስብነት አስቸጋሪዎቹ ይመስሉኛል፡፡ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ኅብረተሰባዊ ጥያቄዎችን ባነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቃውሞና ተያይዞ በተፈጠረ ሁከት ዜጎች ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ለፍተው ደክመው ያፈሩት ንብረት ወድሟል፡፡ አገሪቷም ለአሥር ወራት ያህል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ቆይታለች፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘዋል፣ የዜጎች የፀጥታ ሥጋት ጨምሯል፣ አገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

ገዥው ፓርቲና መንግሥት የችግሩን መንስዔ ተረድተን የማስተካከያ ዕርምጃ እንወስዳለን በማለት ጥልቅ ተሃድሶ አድርገናል ቢሉም፣ ለተቃውሞ ምክንያት የነበሩት ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ተመልሰዋል ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ እንኳን ከግብር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጨምሮ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሚነሳ ተቃውሞ ሥጋትና ውጥረት ተፈጥሯል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ወደ ሁከት በተቀየሩ ተቃውሞ ሠልፎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተባባሰው ግጭት ምክንያት፣ እስካሁንም ድረስ ጥልቀቱን ያልተረዳነው አስደንጋጭ ጥፋት ተፈጽሟል፣ የአገሪቱንና የሕዝቦቿን ደኅንነት ሥጋት ውስጥ የሚጨምር ሁኔታ ታይቷል፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን የሚገዳደሩና የመንግሥትን መዋቅር ጭምር በመገልገያነት እስከ መጠቀም ድረስ የደረሱ የሙስና ኔትወርኮች እንዳሉ መንግሥት ራሱ አምኗል፡፡

የኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲ›› መቀጠል ይችላል?

ኢሕአዴግ እስካሁን የመጣባቸው የአሠራር መንገዶች፣ የፖለቲካ አካሄዶችና ውስጣዊ ድርጅታቸው ባህል የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ ተንትኖ፣ ለተከሰቱት ጉዳዮች ተገቢ ምላሽ በመስጠት አገሪቷን ወደ መረጋጋት ለመመለስ እንደከበደውና ድርጅቱ መሠረታዊ ለውጦችን ካላደረገ ችግሩን ለመፍታት እንደሚቸገር ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ ይኼንን ጉዳይ በጣም ወሳኝ የሚያደርገው ደግሞ የተደራጁና በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከፖለቲካ ድርጅቱ ትዕዛዝና ፈቃድ ውጪ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንና ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ ተቋማት፣ ከድርጅቱ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ የፀጥታና የፍትሕ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ለወቅቱ ሁኔታ የሚመጥን መፍትሔ መስጠትና ይህንን ፈታኝ ጊዜ ማለፍ ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ህልውና ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡

በመሠረቱ ለ22 ዓመታት ያህል ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ተግብሬያለሁ የምትል አገር ሰላምና ህልውና በመሪ ድርጅቷ ላይ መንጠልጠሉ በራሱ የውድቀቱ ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት ሊፈጥራቸው የሚችሉ ግጭቶች፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በተለያዩ የኅብረተሰብ መደቦች ዘንድ የሚፈጥሯቸው ተቃርኖዎች እየታወቁ፣  ይኼንን ሥጋት በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ሥርዓቶችና መንገዶችን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በበቂ ሁኔታ ሳይገነቡ ቀርተዋል፡፡ ከእነዚህ መንገዶችና ሥርዓቶች ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል አለመጎልበትና የጠንካራ ተቋማት አለመገንባት ዋነኞቹ የውድቀቱ መገለጫዎች ናቸው ብዬ አምናለው፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊነት የሚለውን አቅጣጫ እከተለላሁ ሲል በተቃውሞ ከተነሱበት ጥያቄዎች አንዱ፣ እንዴት ልማታዊ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡ በተለይም ሥርዓቱ በተሞከረባቸውና ስኬት ባገኘባቸው አገሮች (ሲንጋፖርን፣ ጃፓንና ሎሎችንም ማንሳት ይቻላል) የአገሮቹ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አምባገነን መንግሥታት እንደነበሩ በማንሳት ብዙዎች ሞግተው ነበር፣ አሁንም ይሞግታሉ፡፡ ድርጅቱ ግን እንደ ኢትዮጵያ ላለች በዴሞክራሲ ዕጦት ምክንያት ለዘመናት በቆዩ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች ውስጥ ለቆየች አገር፣ የሃይማኖትና የብሔር ብዝኃነት መገለጫዋ ለሆነች አገር ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ሲከራከር ቆይቷል፡፡ ሊበራል የሚባል ሕገ መንግሥት በማፅደቅ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በመቀበል፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትንና ሌሎችንም ተራማጅ ሊባሉ የሚችሉ ሕጎችን አፅድቋል፣ የዴሞክራሲ ተቋሟትን አቋቁሟል፡፡

ይሁንና ብዙዎች በኢሕአዴግ ጽሑፍና ንግግር ውስጥ ያለው ዴሞክራሲና በተግባር መሬት ላይ ያለው ዴሞክራሲ ለየቅል መሆናቸውን ይስማማሉ፡፡ ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን አርነት ዴሞክራሲ ሳይሆን ልማታዊ የሚለውን ዴሞክራሲ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ድርጅታዊ ማዕከላዊነትና የኢኮኖሚ ዕድገት እሳካለ ድረስ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ዴሞክራሲ በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በመቃኘት በራሴ መንገድ እተረጉማለሁ፣ በራሴ መንገድ እተገብራለሁ በማለት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫዎች የሆኑት ትንንሽ መብቶችና ነፃነቶች እንኳን በአብዛኛው ለይስሙላ የተቀመጡና በታሪክ ደረጃ ብቻ እንዲገኙ ተደርገዋል፡፡

በተለይም ከሃያ ዓመታት በላይ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ለኖረ ማኅበረሰብ የማይመጥን ደረጃ ላይ የሚገኝ የዴሞክራሲ ባህል እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ በትንሹ የዴሞክራሲ ባህል ባለበት አገር የተለያየ አቋም ያላቸው ቡድኖች ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበት፣ የሚከራከሩበት መድረክ በቀላሉ ያገኛሉ፡፡ ዜጎች ያለ መሳቀቅ መንግሥትን ይሞግታሉ፡፡ መንግሥት ሥራዬ ብሎ ትልቅ ትንሽ ሳይል የሚተቹትንና የሚቃወሙትን ሲያሳድድ፣ ሲያሸማቅቅና ሲያጠፋ አይታይም፡፡ ሕጎችና ተቋማት የኅብረተሰቡን መብት ለማረጋገጥ ሳይሆን የተቃውሞ ድምፆችን ለማጥፋት በተግባር ላይ ሲውሉ አይታዩም፡፡ ኅብረተሰቡም የሐሳብ ልዩነትን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናል፡፡ ከዘረኛው ጋር ዘረኛ ከፅንፈኛው ጋር ጽንፈኛ አይሆንም፡፡ በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ውይይት ስለሚኖር አሉባልታና ሐሜት ብዙ ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ይሁንና አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከዚህ እጅግ ተቃራኒ መሆኑን ማንም ምክንያታዊ ሆኖ ጉዳዩን የሚከታተል ሰው ይጠፋዋል ማለት ከባድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን እስኪያሳስባቸው ድረስ የአገሪቱ ወጣት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ አቋም ሳይሆን፣ በስሜት የሚነዳና ጽንፈኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ መግለጫቸው እንዳሉት መንግሥት መረጃ የመስጠት እጥረት ስላለበት ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቱ በፖለቲካና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በነፃነት የሚወያይበትና የሚቀራረብበት ምኅዳር እንዳይኖር ድርጅቱ ሆን ብሎ በመሥራቱ ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ የወጣት ማኅበራትና አደረጃጀቶች በድርጅት አባላትና አመራሮች መወረራቸው፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንኳን ያሉ አደረጃጀቶች ድርጅታዊ እንዲሆኑ ሲደረግ ይህ እንደሚከሰት መታሰብ ነበረበት፡፡

የመንግሥት ሚዲያን የፕሮፓጋንዳ ማሽን በማድረግ፣ በግል ሚዲያው ላይ ከተለያየ አቅጣጫ ጫና በመፍጠር አቅም እንዳይኖረውና ራሱን ሳንሱር እንዲያደርግ በማድረግ፣ የሐሳብ ብዝኃነት በሠለጠነ መንገድ የሚስተናገድበት ምኅዳር ጠቧል፡፡ በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ ውይይት የማድረግ፣ የመከራከር፣ ሙስናን የመዋጋትና መንግሥትን የመሞገት ዕድል እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ በተለይም የማኅበረሰባዊ ሚዲያ በተስፋፋበት በዚህ ጊዜ ኅብረተሰቡ በማስረጃ ላይ ከተመሠረተ ውይይት ይልቅ፣ በሐሜትና በአሉባልታ የተሞላ ሐሳብ ቅድሚያ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ የሚመስሉ ጥያቄዎች እንኳን ሲቀርቡ ልሂቃኑ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያይና ተቀራርቦ ሰላማዊ መፍትሔ ላይ እንዳይደርስ አድርጎታል፡፡ በሥርዓቱ የተፈጠሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንኳን የሐሳብ ብዝኃነትን የማይቀበሉ፣ በሐሳብና አቋም የተለዩዋቸውን ሰዎች በኃይል እስከ ማጥቃትና አብሮ ለመሥራት ሳይሆን ለመጠፋፋት የሚዶልቱ ሆነዋል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ኢሕአዴግ እንደሚለው ወደ አውራ ፓርቲ ሥርዓት ተቀይሯል፡፡ በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር አሁን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም ኢሕአዲግ እደራደራቸዋለሁ የሚላቸው፣ በቂ ሊባል የሚችል የሕዝብ ውክልና የሌላቸውና ለአገሪቱ ችግሮች የሚመጥን ቁመናና አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን የተረጎመበት መንገድና እሱንም ለመተግበር ያወጣቸው ፖሊሲዎችና ተግባራት ቀጥታ ውጤት ነው፡፡ 

ሌላው የኢሕአዴግ ዴሞክራሲ የፈጠረው አደጋ ኅብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ፣ ተገቢና ሕጋዊ ምላሽ የሚሰጡ አገልጋይ ተቋማት አለመኖር ወይም መዳከም ነው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱን ልማታዊ አደርጋለሁ በሚል ፈሊጥ ፖለቲካዊ ከተደረገ በኋላ፣ ልማታዊም ብቁም ሳይሆን እንደቀረ የራሱ የኢሕአዴግ ግምገማ ያሳያል፡፡ ‹‹ልማታዊ›› ቢሮክራሲው ውስጥ ያለው ብልሹ አሠራርና ሙስና ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኖብኛል እያለ ነው፡፡ የሕዝብን የፍትሕ ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉ የፍትሕ ተቋማት፣ ለድርጅቱ ሳይሆን ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆኑና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አክብረው የሚንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎችና ከሙስና የፀዳ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በመመናመናቸው ኅብረተሰቡ ለችግሮቹ ከእነዚህ የመንግሥት ተቋማት መፍትሔ አገኛለሁ የሚለው እምነቱ እንዲቀጭጭ አድርጎታል፡፡  ስለዚህም ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ችግሩን ተቋሞችን በመጠቀም ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ በተቃውሞና በአመፅ  ለማሳካት መሞከርን  ይመርጣል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሚመሩት ድርጅት ውስጥ ስለዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መዳከም ተጠይቀው፣ የማይገረሰስ የኢሕአዴግ መርህ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወት በነበሩት የመጨረሻዎቹ ዓመታት ድርጅቱ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ሳይሆን፣ አንድ ማዕከላዊ ዕዝ ያለው ፓርቲ ይመስል ነበር፡፡ ማዕከሉ ከአባል ድርጅቶቹ በላይ ጠንካራ ነበር፡፡ ውሳኔዎች በማዕከል ይወሰናሉ፣ ፖሊሲዎች ይቀረፃሉ፣ የአፈጻጸም መመርያዎችና አቅጣጫዎች ከማዕከል ይሰጣሉ፡፡ ክርክርና ውይይት በፓርቲው የላይኛው አመራር ዘንድ ይኖርና በተዋረድ ይሰርፃል፡፡ አራቱ አባል ፓርቲዎችና በውሳኔው ሒደት ጭራሽ ተሳታፊ የማይደረጉት አምስት ክልሎችን የሚያስተዳድሩ አጋር ድርጅቶችም ጭምር በየክልላቸው የተወሰነውን ያስፈጽማሉ፡፡ አፈጻጸማቸውም ከፍተኛ ቁጥጥርና ግምገማ ይደረግበታል፡፡

ይህ መርህ ፓርቲው የሚወስናቸውን ውሳኔዎች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ከማስፈጸም አንፃር ጠቃሚ ቢሆንለትም ድርጅቶቹ ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ ጉዳዮች፣ ችግሮችና ነባራዊ ሁኔታዎች ቅድሚያ ከሚሰጡ ይልቅ ለድርጅቱ ውሳኔ ቅድሚያ እንዲሰጡና ተገዥ እንዲሆኑ በማድረግ ከሕዝባቸው ጋር ለመራራቃቸውና አንዱ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይሁንና በተለይም ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሦስት ተያያዥ ጉዳዮች እንደተዳከመ ማየት ይቻላል፡፡

አንደኛው ምክንያት መርሁ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ጋር ቀጣይነት ባለው ተቃርኖ ውስጥ ያለ መሆኑ ነው፡፡ መርሁ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ ያገኙትን ያልተማከለ አስተዳደር የመመሥረትንና ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የመስጠት መብትን ነጥቋቸው ቆይቷል፡፡ እስካሁንም ድረስ ይህ መርህ ለመተግበር የቻለው ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ሳይሸረረው ቀርቶ ሳይሆን፣ ክልሎችና ብሔራዊ ድርጅቶች ይኼንን ለመጠየቅ የሚያስችል ቁመና ስላልገነቡና ማዕከሉም ጠንካራ ስለነበረ ነው፡፡

የአገራችንን ፖለቲካ የሚከታተሉ ምሁራንና ተንታኞች ይህ የድርጅቱ መርህ ሕገ መንግሥታዊ ፌደራሊዝሙን እንደሚጎዳው በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ የአገሪቱን የበላይ ሥልጣን የያዙ የኢሕአዴግ አባል የፓርላማ አባላት እንኳን ለዚህ መርህ ስለሚገዙ፣ ከሚወክሉት ሕዝብ ጥቅምና ሕገ መንግሥቱ እንደሚያስገድዳቸው ከህሊናቸው በላይ ለድርጅቱ ውሳኔ ተገዥ እንዲሆኑ ይገደዳሉ፡፡ መርሁ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ቀርቶ ያልተማከለ አስተዳደር ካላቸው አገሮች እንኳን በእጅጉ የጠነከረ ማዕከላዊነት ሲተገብር በመቆየቱ፣ ሥርዓቱ እንዳይፈተሽና ችግሮች ሲገጥሙ የሚፈቱበት ሥርዓትና ልምድ እንዳይዳብር አድርጓል፡፡

በተለይም በኦሮሚያ ክልል እንደታየው ህዝቡ ተቃውሞ ማንሳትና ሕገ መንግሥቱ ሙሉ ለሙሉ በተግባር እንዲውል መጠየቅ የጀመረ ጊዜ፣ ቢፈለግም ባይፈለግም የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ከራሱ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሳይቀር ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ አዲሱ የኦሮሚያ አመራር ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት መወሰኑን በተደጋጋሚ በአደባባይ መግለጹ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም በሕግ እንዲደነገግ እንቅስቃሴ መጀመሩና ሌሎችንም በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት በራሱ ለመተግበር የሚያደርገው ጥረት፣ ይህ መርህ ከውስጥም ጭምር ቀጣይነት ያለው ጥያቄ ውስጥ እየገባ መሆኑን ያሳያል፡፡

ሁለተኛው  ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰቱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና እንቅስቃሴዎች ምክንያት አንዳንዶች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ከማዕከላዊ ድርጅቱ ይልቅ ለሕዝብ ጥያቄዎች ቅድሚያ ለመስጠት መሞከራቸውና ይኼንንም በአደባባይ መግለጻቸው ነው፡፡ በተለይም ኦሕዴድና ብአዴን ይህንን ሲያደርጉ ለማየት ተችሏል፡፡ ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም አልነበረም ሊባል በሚችል ሁኔታ ያለ ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በክልሎቻቸው ላይ በነፃነት ውሳኔ የመስጠት እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎችም ከኅብረተሰቡና ከሚቃወሟቸውም ሰዎች ጭምር ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ምንም አንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚያ እንደማይመለከቱት ቢገልጹም፣ በክልሎቹ የሚታዩትን የሥራ አጥነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ችግሮች ለመፍታት የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ጥምረት ድርጅቶችን ለማቋቋምና በተለይም በኦሮሚያ ክልል የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት ተብለው የተጀመሩት ተግባራት ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው፡፡

ለነገሩ የክልል መንግሥታት ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ቅድሚያ መስጠታቸው መኮነን ያለበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራሊዝም ያወጀች አገር ያልተማከለ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ጭምር በተቻለ መጠን የመንግሥትን ሥልጣን ተደራሽነት ወደ ታች በማውረድ ለኅብረተሰቡ ሕይወት መሻሻል በቅርብ እንዲተጉ ማድረግ፣ ለሚወክሉት ክፍል ጥቅም እንዲከራከሩ ማስቻል የተሻለ እንደሆነ ይታመንበታል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊና ችግሮች ባሉበት አገር በየደረጃው ያለው መዋቅር ችግሮችን በራሱ አቅም እንዲፈታ ማድረግ ካልተቻለ አስቸጋሪ እንደሚሆን የሌሎች አገሮች ልምድ በግልጽ ያሳያል፡፡   

ሦስተኛው ምክንያት የማዕከላዊው የኢሕአዴግ አመራር መዳከም ነው፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኢሕአዴግ ሐሳቦችን የሚያፈልቅና ችግሮችን በቶሎ የሚፈታ ግለሰባዊም ሆነ የቡድን አመራር ማግኘት እንደቸገረው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አሁን ያለንበት የፖለቲካ ቀውስ በአግባቡ ሳይፈታ ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ባህሪውን እየቀያየረ መቀጠሉ ለዚህ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱ እንዳመነው ከላይኛው አመራር ጀምሮ በሙስና ኔትወርክ በተተበተቡና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ቅድሚያ በሚሰጡ አመራሮች ተሞልቷል፡፡ ይኼንን ችግር ለመፍታት ከፍተኛው ኃላፊነት ያለባቸው የድርጅቱ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን በምሬት ሲናገሩ መስማት፣ የችግሩን ጥልቀት ብቻ ሳይሆን ለመቆጣጠር ከባድ እንደሆነባቸው ማሳያ ይመስለኛል፡፡ 

የመጨረሻው ምዕራፍ

በመሠረቱ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መሸርሸሩና በጊዜ ሒደትም መቅረቱ ድርጅቱ ካልተዋሀደ በስተቀር የሚቀር ነበር ብዬ አላስብም፡፡ ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ አገሪቱ ይበልጥ ሳትተራመስ ከመውጣት አንፃር ደግሞ የመርሁ መሸርሸር ጎጂ ሳይሆን ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲያውም መርሁ ተፈጥሯዊ የመሞቻ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት ኢሕአዴግና ብሔራዊ ድርጅቶቹ የሚያስተዳድሩት ኅብረተሰብ፣ ልሂቃኑ እንዲሁም አባላቶቻቸው ሳይቀሩ በብዙ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ አገሪቷ ባሳለፈቻቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ምክንያት አሠላለፋቸው፣ ፍላጎታቸውና ውግንናቸው መሠረታዊ በሚባል ሁኔታ በሒደት ተለውጧል፡፡ ድርጅቱ ከእነዚህ ለውጦች ጋር ለመራመድ እንዲያስችለው ከዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ወጥቶ፣ አባል ድርጅቶቹ ለሚወክሉት ኅብረተሰብ ጥቅም የሚከራከሩና ለሕዝቡ ቅርብ የሆኑ እንዲሆኑ የሚያስችል መርህ ቢቀበል የሚያዋጣው ይሆናል፡፡ ሙስናን ለመዋጋትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመገንባትም ለጊዜው የሚመጥን መርህ ከመቀበል ውጪ አማራጭ ያለው አይመስለኝም፡፡

እንዲያውም ኢሕአዴግ ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርጅቱ ውስጥና አስተዳድረዋለሁ በሚለው ኅብረተሰብ ውስጥ ከተከሰቱ ለውጦችና መነቃቃቶች አንፃር፣ እንደ ቀድሞው የሚተገበር ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ለመመለስ ይችላል ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባትም ጠንካራ መሪ ቢያገኝ እንኳን ያንን መመለስ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ እንደዚያ ለማድረግ ቢሞከር ምናልባት ድርጅቱ ወደ መፈራረስ ያመራ ይሆናል እንጂ፣ ጠንካራ ማዕከላዊነትን መልሶ ይተገብራል ማለት አዳጋች ነው፡፡

ስለዚህም ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን የተገበረበት መንገድና የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት መርሆዎች በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ይኼንን ለውጥ በቅጡ መረዳት፣ መተንተንና ለዚህ የሚመጥን ፖሊሲና አሠራር መፍጠር ይኖርበታል፡፡ በቀጣይ ዓመታት ክልሎች የበለጠ እየተጠናከሩ የሚወጡበት፣ የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የሚፈቱበት፣ የራሳቸውን ቁመና የሚያዳብሩበት ባህልና አሠራር መመቻቸት አለበት፡፡ ማዕከላዊ የግንባሩ አመራር ሚናውን በመከለስ በፌዴራሉ መንግሥት ሥራና በድርጅት ደረጃም በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ ቅራኔዎችን የማስማማት ሚና በይበልጥ መጫወት ይኖርበታል፡፡ ይኼንን ለማድረግ ግን በተለይም ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ቋሚ መርህ ሳይሆን ሲያስፈልግ የሚሻሻልና የሚቀየር መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በተጓዳኝ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማጠናከር ደግሞ ወደፊት የሚፈጠሩ ቅራኔዎችንና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ እንዲስተናገዱ ያስችላል፡፡ የፖለቲካ ቀውስን እንደ አጋጣሚ በመቁጠር ተገቢ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ አለመሆን፣ ሥልጣንን ብቻ ሳይሆን አገርን ዋጋ እንደሚያስከፍል ስንት ተስፋ ተጥሎባቸው በቀውስ ከታመሱ አገሮች ልምድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡