Skip to main content
x

ኢትዮጵያዊነት በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያብባል - ይዘምናልም

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

(ክፍል ሁለት)

ባለፈው ሳምንት ዕትም ጸሐፊው ማንነትን፣ የወል ማንነትን፣ የማንነቶች ብዝኃነትን፣ የማንነት ቅራኔዎችን፣ ብሔርተኝነትና አገራዊነትን፣ የኢትዮጵያዊነት እንቆቅልሽን፣ የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካን፣ ወዘተ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በዚህኛው ዕትም ደግሞ ሁለተኛውንና የመጨረሻቸውን ክፍል ያስነብቡናል፡፡

  1. አግላይ ብሔርተኝነት

ብሔርተኝነት የአንድ ማንነት የጋራ ንዋታዊ ጥቅምና እሴቶች በውስጥ የሚንፀባረቁበት ከውጭ ደግሞ መለያ በሚሆንበት ታሪክ፣ መንፈስ፣ ስሜት ብቻ ሳይሆን እውነታ (Objective) ምክንያቶች ያሉትና የሚያድግ፣ የሚሻሻል፣ የሚዘምን ፖለቲካዊ አይዲዮሎጂ ነው፡፡ ይኼ በዓለም ደረጃ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መገለጫዎች ያሉት ክስተት አግላይ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ማንኛውም ኅብረተሰባዊ ማንነት፡፡ ለንፅፅር እንዲበጀን በመጀመርያ ዴሞክራሲያዊ ብሔርነተኝነትን እንይ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርነተኝነት ስንል የጋራ ንዋታዊ ጥቅምና እሴቶች እንዳሉ ሁሉ፣ በውስጡ የተለያዩ ንዋታዊ ጥቅሞችና እሴቶች እንዳሉ ተቀብሎ አቃፊና አሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ በአንድ ብሔር ውስጥ ገበሬ፣ ላብ አደር፣ ባለሀብት፣ ምሁር፣ ወዘተ ያሉ ማንነት በመኖራቸው እነሱም የየራሳቸው ንዋታዊ ጥቅምና የአስተሳሰብ ብዙኃነት ያላቸው መሆኑን የሚቀበል ነው፡፡ በብሔር ውስጥም አንድነትና ልዩነትን የሚያስተናግድ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋርም በጋራ መስተጋብር ያዳበሩት ታሪክ፣ ባህል፣ አስተሳሰብ ያለ መሆኑን ተቀብሎ በተለይ አሁን ባለው ዓላማዊ ሁኔታ ተባብሮ በአንድነት ካልሆነ በስተቀር ንዋታዊ ጥቅሞቻችንን እሴቶችን የማሳደግ የመጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ደኅንነቱም አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ተረድቶ አንድነትን የሚመኝ፣ ለአንድነት የሚታገል ግን በእኩልነት የተመሠረተ አስተሳሰብ ነው፡፡ አግላይ ብሔርተኝነት ስንል በውስጡ ያለውን አንድነትና ልዩነት የማይቀበል፣ ስለዚህም አንድ የብሔር አባባል (Narrative) ይዞ ልክ እንደ ጠቅላይና አግላይ ኢትዮጵያዊነት አንድ ሕዝብ፣ አንድ ብሔር፣ አንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ወዘተ የሚል ነው፡፡ የ‹አንድ ልብ› አባባል የሚከተል ነው፡፡ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያለውን የጋራ ታሪክ፣ ባህል መስተጋብር የሚክድ የሚያስታውሰው ከሆነም በጎውን ደብቆ የተፈጸሙትን በደሎች ብቻ እያንሸራሸረ የሚኖር አስተሳሰብ ነው፡፡ አግላይ በመሆኑ በውስጡም ልዩነት የማይቀበል በመሆኑ ብሔራዊነትን የሚሸረሽር እንጂ የሚያጠናክርም አይደለም፡፡

አግላይ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ በተለያየ መንገዶች ይገለጻል፡፡ ኢትዮጵያችን የጋራ እሴቶች እንደ ሌሏትና የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብርና ማኅበራዊ ገጽታ እንዳልነበረና በምኒልክ ዘመን የተገጣጠመች በጎ ገጽታዋን በመደበቅ፣ አገር በመመሥረት ሒደት ያጋጠሙትን ግፎች ብቻ በማስጮህ አገሪቷ የአንድ መሪና ተከታዮቹ አድርገው እንድትታይ ያደርጋሉ፡፡ ነፃነት በዋጋ የማይገመት (Priceless) መሆኑን ዘንግተው፣ ለሰው ልጅ ማንነት ያለውን ትርጉም በማሳነስ በጋራ ቅኝ ገዢዎችን ያሳፈርንበትን የጥቁር ሕዝቦች አለኝታ የሆነውን የአንድነት ማንነት ያንኳስሳሉ፡፡ ከላይ የተገለጹት የፈጠራ ሥራዎችና የተደነቁ ታሪካዊ ቅርሶቻችንን ኅብረተሰቡ እንዳያውና የጋራ እሴቶችን እንዳይንከባከብ ያደርጋሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሁላችን ፈቃድና መተማመን የምትገነባ አገር መሆንዋን በመቃወም፣ ልሂቃኑ የራሳቸውን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ በሕዝቡ ውስጥ መሠረታዊ ቅራኔ እንዳለ በማስመሰል ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ‹‹የብሔሬ ልጅ ይብላኝ›› አስተሳሰብ በመያዝ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በምንገነባት አገር፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገል የምናደርገውን ትግል ለማደናቀፍ የብሔር ከለላ ይጠቀማሉ፡፡ አግላይ ብሔርተኞች የራሳቸውን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ብትዘፈቅም አይገዳቸውም፡፡

የተፈጥሮ ሀብትና የድሮ ታሪክ ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ወሳኝ ባልሆነበት ዓለማዊ ሁኔታ የተትረፈረፈ ሀብት አለን? ወይስ ታሪክ አለን? በማለት ራሳቸውን አጉልተው ሌላውን አሳንሰው ያያሉ፡፡ ዋናው ኃይል የሰው ሀብት መሆኑንና የ100 ሚሊዮኖች ሀብት ለሁሉም ሕዝቦች በጣም ጠቃሚ መሆኑን ይዘነጋሉ፡፡ አግላይና ጠቅላይ ኃይሎች ብሔርና ብሔረሰቦችን ሲያንኳስሱና ማንነታቸውን ሲያበሳብሱ፣ አግላይ ብሔርተኞች ደግሞ ግብረ መልሱ እነሱ የመጡበትን ማኅበረሰብ ማውረድ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አግላይና ጠቅላይ ኢትዮጵያዊነትና አግላይ ብሔርተኝነት እየተመጋገቡ አገሪቱ የጀመረችውን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ጉዞ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ኅብረተሰባዊ አቅማችን ሰብስበን ወደፊት እንዳንራመድ ይከፋፍሉናል፡፡ ወደ ኋላ ይጎትቱናል፣ በማያባራ ጦርነት እንድንኖርም የተቻላቸውን ያህል ይሞክራሉ፡፡

ኢሕአዴግ ጠቅላይና አግላይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን ለአደጋ እያጋለጠ ነው

ባለፉት 25 ዓመታት በኢሕአዴግ መሪነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባፀደቁት ቻርተርና ሕገ መንግሥት እየተመሩ በአገሪቱ በአጠቃላይ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የግለሰብና የቡድን መብቶች በተወሰነ ደረጃ በመረጋገጡና በተገኘው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት ኢትዮጵያዊነት መለምለም ጀምሮ ነበር፡፡ የአገራችን ሰላም ለሌሎች አርዓያና የሚደርስላቸው ሆኖ ነበር፡፡ ድርቅ ረሃብ መሆኑ ያቋረጠበት፣ በዓለም ውስጥ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካረጋገጡ አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆን ጀምራ ነበረ፡፡ አሁን እየተከማቸ በመጣ ብሶት ባለፉት ሦስት ዓመታት ሰላሟ እየተረበሸ የመጣች አገር ሆናለች፡፡ በዚህ ከቀጠለ ልማቷ ይጓተታል አገሪቱም ወደ አላስፈላጊ ግጭቶችም ትሄዳለች፡፡

በኢሕአዴግ አምባገነንነት ምክንያት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ነው፡፡ ጠቅላይና አግላይ በመሆኑ ካለ ኢሕአዴግ መስመር ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው የሚለው አስተሳሰብ ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያገል ሆኗል፡፡ ፀረ ዴሞክራሲ በመሆኑ ምናልባት ከሰባት ሚሊዮን አባላቱ (በዓላማ የተሠለፉ ከሆነ) ጋር ሆኖ ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን አግልሏል፡፡ በሥሩ ያሉ አጎብዳጅ ‹‹ምሁራን›› ከምሁርነት ወሳኝ አቅም የተገለሉ ሆነዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን እንደ ፀጋ ስለማይቀበል የተደራጁትን (የእውነት ተቃዋሚዎች) አግልሎ የፖለቲካዊ ተቃውሞ ማዕከሉን ወደ ዳያስፖራ ልኮታል፡፡ ግጭትም እያስከተለ ነው፡፡ ከድርጅቱ በአስተሳሰብ የሚለዩትን ታዋቂ ሰዎችና አርቲስቶች ጠላት፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ወዘተ በማለት ያገላል፡፡ ከኅብረተሰብ የሚያገኘውን አቅም አጥቶ በአንድ እጁ የሚያጨበጭብ ሆኗል፡፡ በአይዲዮሎጂና በፖለቲካዊ ቀውስ ስለተዘፈቀ ኢሕአዴግ በቅርፅ (Form) እንጂ በይዘቱ (Content) አለ ወይ የሚያሰኝ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ጥርነፋ ብሎ በሚጠራው ግን በአምባገነናዊ ጥርነፋ መሠረት የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊ ሕይወት በመግደል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትንና መጠላለፍን በማጎልበት አባሎችንም እያገለለ ነው፡፡ ይኼ ውስጣዊ አሠራር ድርጅቱን በማኮላሸት ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ዘፍቆታል፡፡ ሁሉም ከአንድ ማዕከል እንዲፈስ በማድረግ ለፌዴራል ማዕከሉና ለክልሎች የተሰጠውን ፖለቲካዊ ሥልጣን በመዘባረቅ ‹‹Organized System Of Irresponsibility›› የሚሉት ዓይነት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የፌዴራልና የክልሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ወዘተ የራሳቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት አግኝተው እንዳይንቀሳቀሱ በአምባገነናዊ አሠራር ጠፍሮ ይዞታል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱም ብቃት በሌላቸው አባላቱ በመሞላቱና የጥርነፋ አሠራሩ ሽባ አድርጎታል፡፡ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተመሳሳይ በተለይ ኢቢሲ የብዝኃነትና የህዳሴ ድምፅ ነኝ ብሎ ‹ቢፎግርም›፣ የጠቅላይና አግላይነት ቀንደኛ ማሠሪያ ሆኗል፡፡ ጠቅላላ ሥርዓቱ አግላይና ጠቅላይ ሆኗል፡፡

ህዳሴ፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር የመሳሰሉት ጉዳዮች ኢሕአዴግ እንደፈለገ የሚቀልድባቸው ቃላት ስለሆኑ፣ ትምክህተኝነትና ጠባብነት የሚሉትን አባባሎች ለመጠቀም አልፈለግኩም፡፡ እንደ ማንኛቸውም ፀረ ዴሞክራቲክ አባባሎች መሸፈኛ ስለሆነ ይቀፋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ትምክህትና ጠባብነት ከውጭ ጠላት ወራሪ የማይተናነስ ጠላት ነው ተባለ፡፡ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ነው የሆነው፡፡ በእኔ አመለካከትም በእርግጥ ትምክህትና ጠባብነት ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች በገበሬው፣ በላብ አደሩ፣ በባለሀብቱ፣ በምሁሩ፣ በሴቱ፣ በወጣቱ፣ በሽማግሌው፣ በፓርቲዎችና በሌሎች አደረጃጀቶች ነው ሰፍረው የሚገኙት፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱት ፅንፈኞችም (ጠላት ሊሆኑ የሚችሉት) በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ኋላቀርነት ተጠቅመው እያጮሁ አገር ለማበጣበጥ መሞከራቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ ፅንፈኞች አይቀየሩም፡፡ ስለዚህ ዋናው ፍልሚያ በሕዝቦች ውስጥ ያለውን ኋላቀር አስተሳሰብ ለማሳመን መታገል ነው፡፡ አግላይና ጠቅላይ (ትምክህትና ጠባብነት) የሕዝቦች ንዋታዊ ጥቅሞችንና እሴቶችን የሚፃረሩ ናቸው፡፡ በሕዝቦቸ ውስጥ የሚገኝ የሕዝቦችን ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ አሜኬላ!! ሕዝቦች ሲገነዘቡት የማይጠቅማቸው በመሆኑ ያስወጉዱታል፡፡ ሕዝቦች በእነዚህ ኋላቀር አስተሳሰቦች ተጠቂ የሚሆኑት እጅግ የከፋ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድባብ ሲኖር ነው፡፡ ፅንፈኞችም በሕዝቦች ውስጥ ያለውን ሥጋት፣ ጥርጣሬ፣ ውዥንብርና ንዴት አቅጣጫ በማስቀየር ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲፋጅ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ዋናው ችግርና ዋናው ጠላት ድህነትና ፀረ ዴሞክራሲ ድባብ ነው፡፡ በዋናነት ገዢዎች ሥልጣናቸውን በኃይል ለመጠበቅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ዋናው ችግራችን ፀረ ዴሞክራሲ ስለሆነ በሁሉም መልክ በዋናነት በአመራር ያለውን እንታገለው እንደማለት፣ ልክ እንደ ጽንፈኞች አቅጣጫ በመቀየር የሌለ ጠላት ፈጥሮ ወደ ጦርነት ገብቷል፡፡ ትምክህትና ጠባብነት የሚሉት ጠላት፡፡ የጠላት ፍለጋ ዥዋዥዌ በመሞት ላይ ያለ ሥርዓት ምልክት መሆኑን ግንዛቤ ይያዝልኝ፡፡ የዚህ ጠንካራ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ሰለባ ከሆኑት መካከል በወቅቱ አነጋጋሪ የሆነውን የሙዚቃው ንጉሥ ቴዲ አፍሮን እንየው፡፡ ቴዲ ስለሰላም፣ ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት በተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ቢሆንም ተቀባይነት ያገኘ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በአንድ በኩል የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ወኔ የሚቀሰቅስ ኢትዮጵያዊነትን ሲያቀርብ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነትን የሚያቆሽሽ፣ አግላይና ጠቅላይ (ከላይ እንደገለጽኩት) አመለካከት ያለውን ኢትዮጵያዊነትን ያራምዳል፡፡ ለእኔ ቴዲ በተቃርኖ የተሞላ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚያራምደው፡፡ እሱ በድፍረትና ማንነቱን በጠበቀ (መንግሥትንና ፅንፈኛው ዳያስፖራን) ሳይፈራ የመሰለውን አቋም እያራመደ ስላለ ትልቅ ክብር አለኝ፡፡ በርከት ያሉ አርቲስቶች ለጥቅም ሲሉ የመንግሥትንና የፅንፈኛውን ዳያስፖራ ጫማ ለመላስ በሚንቀሳቀሱበት አገር እንደ ልዩ ሀብት መታየት ይገባው ነበር፡፡ ታዋቂ ሰውን ከማስፈራራት፣ ከማገድና ከመከልከል ይልቅ በነፃነት ሐሳቡን ቢያቀርብ፣ ተቃርኖ አለን የሚሉም ቢቀላቀሉትና ሕዝቦች የሚቀበሉት ኢትዮጵያዊነት በውይይት ቢጎለብት እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ክልከላና ማፈን የአዲሱ ኢትዮጵያዊነት ባህሪ አይደለም፡፡ የተለየ ሐሳብ ከሚፈራ መንግሥት ይገላገለን!!

ኢሕአዴግ ‹‹ተሃድሶ›› ይበለው ‹‹ጥልቅ›› ከምሩ ከሆነ አግላይነትና ጠቅላይነትን ነበር መታገል የነበረበት፡፡ በአመለካከት፣ በአደረጃጀት፣ በአሠራር፣ ወዘተ ከዴሞክራሲ ጋር የሚፃረሩትን በማስተካከልና ሕዝቡን በመስማት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን በማክበር፡፡ ይኼ ከፍተኛ የሕዝብ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ያባከነው “ጥልቅ ተሃድሶ” ከፖለቲካው ሙስና ወደ ጥልቅ ፖለቲካዊ ሙስና ተሸጋገረ፡፡ ከተሃድሶ አኳያ የሚታይ ፍንጭ ያለው ከኦሕዴድ ይመስላል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ተፅዕኖ ያመጣውም ይመስላል፡፡ ‹‹ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ…›› በሚል መጣጥፌ የመሰለኝን ያብራራሁ ይመስለኛል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ሆርን አፌርስ ከሚባለው ዌብ ሳይት (Horn Affairs) የተቀነጫጨበ ላካፍላችሁ፡፡

‹‹ከ27 ዓመታት በኋላ በምንም መመዘኛ ደርግ ይኼን አድርጓል፣ ኃይለ ሥላሴ ይኼን አድርጓል፣ እኛ ይኼን አድርገናል ብለን የምንነግድበት ሸቀጥ በእጃችን የለም›› (ስርዝ የእኔ)

‹‹እርግጥ ነው ንግግራችን ትልቅ ነው፡፡ ከይቅርታ ጋር ምላሳችንን አርዝመን ብዙ ተናግረናል፣ የምላሳችንን ያህል እጃችን ሊደርስ አልቻለም፡፡ የችግሩን ሥፍራ አላየንም፣ አልነካንም፣ አልወጋንም…›› (ስርዝ የእኔ)

‹‹እኛ በዕውቀታችን ሁሉ ነገር አሟልተን አይደለም አገር እየመራን ያለነው፡፡ በዕውቀት መታገዝና መረዳት አለብን፡፡ በአዲስ ሐሳብና ጥናት መደገፍ አለብን›› (ስርዝ የእኔ)

‹‹አጭር ዕድል ነው የሰጠን እንጂ ሕዝቡ ሰላም አይደለም፣ ዕድል ሰጥቶናል የመጨረሻ ዕድል፡፡ (ስርዝ የእኔ)

‹‹… መሥራት ያለብንን ሥራ ሠርተን ብንገኝ ኖሮ ሕዝቡ ለምን ያኮርፋል? ለምን ይነሳብናል? ለምን ይቆጣል? ማመስገን ሲገባው ስላልሠራን ነው፣ ይኼ አያጠያይቅም፡፡ የቤት ሥራችንን ስላልሠራን ነው›› (ስርዝ የእኔ)

አዲሱ አመራር በቅርቡ ባህር ዳር ድረስ ዘልቆ ከአማራ ክልል መስተዳድር ጋር በመሆን የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ለማጉላት የተደረገው እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ ትርጉም ስላለው፡፡ በሌሎች አዋሳኝ ክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በተለይ ለሶማሌ ክልል ጊዜ መስጠት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ወንጀል በተፈጸመበት ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍርድ ከማቅረብ ጎን ለጎን የሕዝቦችን አንድነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ ሕዝቦችን የሚያጣላ ሦስተኛ ወገን ለመፈለግ በአንዳንድ ወገኖች የተደረገው ችግሩን ውጫዊ (Externilization) እንደሆነ ማስመስል ግን አደገኛ ሙከራ ነው፡፡ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንድነት እንዳይኖር ወሳኝ ዕንቅፋት የሚሆኑት በውስጥ ባሉት ሊሂቃን ውስጥ ያለው ጠቅላይና አግላይ አመለካከትና ተግባር ነው፡፡ የታሪካችን አሻራ ብቻ ሳይሆን ከፊታችን የተደቀኑትን መሠረታዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በጠቅላይና በአግላይ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ ነው ሕዝቦችን የሚያፋጀው፡፡

ተስፋ እየጣልንበት ያለው አዲሱ የኦሕዴድ አመራር ዋናው የመጀመርያ ተግዳሮት ግን የኦሮሞን ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሠረት አድርጎ፣  ቁሳዊ ጥቅሞቹንና እሴቶቹን ማስጠበቅ ሲችል ነው፡፡ በእዚህ ከተሳከለት ብቻ ነው በኢትዮጵያ ደረጃ አመራር ለመስጠት የሚችለው፡፡ የኦሮሞ ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠበቀው በዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊነት ስለሆነ፣ በጠቅላይነትና በአግላይነት የሚመሠረት አንድነት ፈራሽ ነው፡፡  አቶ ለማ መገርሳና በዙሪያቸው ያሉት ጎልማሳ ምሁራን ለኢትዮጵያዊነት መሠረት፣ ስለአዲሱ ኢትዮጵዊነትና የሕዝቦች አንድነት ሲናገሩ ሕገ መንግሥቱን በሚገባ የሚያውቁ፣ በዕምነት ለማራመድና ተግባራዊ ለማድረግ ከኢሕአዴግ ውስጥ ብቅ ያሉ አመራሮች እየተፈጠሩ ነው እንዴ የሚያሰኝ ነው፡፡ በተግባር መረጋገጥ ያለበት ቢሆንም፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የጥርጣሬው ጥቅም (The Benefit of the Doubt) እና ሂሳዊ ድጋፍ (Critical Support) በመስጠት ከጎናቸው መሠለፍ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ጭፍን ድጋፍና ከብሔሬ ካልሆነ ብሎ ማኩረፍ ለሁላችንም አይጠቅመንም፡፡ ከመሀል ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምድ አመራር ብቅ በሚልበት ጊዜ ዘረኝነት የማያጠቃን ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ቢያንስ የእውነት መሆኑን እያረጋገጥን ስንሄድ ሙሉ ድጋፋችንን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ክልሎች የሚማሩበት ሁኔታ በመፍጠር በጋራ ልማትን፣ ሰላምንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን መገንባት ይገባናል፡፡

በ1984 ዓ.ም. ያጋጠመኝን ላካፍላችሁ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ተመድቤ ስለነበረ ከብዙ ምሁራን ጋር ስለአገራችን ሁኔታ ብዙ ጊዜ እናወራ ነበር፡፡ ደርግ በመወገዱ ሁሉም ደስታቸውን ይገልጹ ነበር፡፡ ስለቻርተሩ ስናወራ የመገንጠል ሥጋት እንዳላቸው ቢገልጹም በይዘቱ ይስማሙ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ግን በማይገባኝ ጉዳይ ያልተዋጠላቸው ነገር እንዳለ ግን ይሰማኝ ነበር፡፡ አንዱ ወዳጄ ሲነግረኝ የተወሰኑት የማይቀበሉት ቻርተሩን በቁምነገሩ ሳይሆን፣ አቀንቃኙ የኢሕአዴግ ኮር ወያኔ (ከትግራይ) በመሆኑ ነው አለኝ፡፡ ለማመን አቃተኝ፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት ብዙ ይናገራሉ፣ ያለቅሳሉ፣ እዬዬ ይላሉ፡፡ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ቢሆኑም መሪዎች ከአማራ ካልሆኑ የማይቀበሉ ናቸው፡፡ የዳያስፖራው ፅንፈኛም የእነዚህ ተቀጥያ ነው የሆነው፡፡ አይ ዘረኝነት!! ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ የሚያወጣ ዋና ሐሳብ ከየትኛው ይምጣ፣ በእውነት ኢትዮጵያዊያን ነን የምንለው መሠለፍ የሚያምርብን ይመስለኛል፡፡ ሕወሓትና ብአዴን፣ እንዲሁም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ተራማጅ አመራር ለመስጠት በማይችሉበት ወቅት በአክሱም፣ በላሊበላ፣ በጎንደር፣ ወዘተ ሥልጣኔዎችና በትጥቅ ትግል በነበረ ሚና እየተኮፈስን መኖር ለጥፋት ካልሆነ ለልማት አይሆንም፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ዘርን ማዕከል ያደረገ የሚመስል ጥቃት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲታይ፣ የእነ አቶ ለማ አመራር በንግግር ነው እንዴ የቀረው የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ተገቢ ሥጋትና ጥያቄ ነው፡፡ የክልሉ መስተዳድር ሁኔታውን በአስቸኳይ መቆጣጠርና ወንጀለኞችን ወደ ፍረድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ገና በጅምር ያለ እንቅስቃሴ ስለሆነ ተራማጅ ሐሳቦች ያለው አመራር ቢኖርም፣ በየደረጃው ያለው አመራር ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ኃይል እስኪሆን ድረስ ጊዜ መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡ በዚያ ላይ በአዲሱ አመራር ተራማጅነት ሥጋት የገባቸው ኃይሎችም እንቅፋት ቢፈጥሩ የምንጠብቀው ነው፡፡ የኦሮሚያ አመራር የኦሮሞ ሕዝብ ዕድል ሰጥቶናል እንዳለው ሁሉ፣ እኛም በ1966 ዓ.ም. የልጅ እንዳልካቸው መኰንን ካቢኔ ‹‹ፋታ ስጡኝ›› ዓይነት ጊዜ መግዣ ሳይሆን፣ የሚወሰዱዋቸውን ዕርምጃዎች እያየን በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚያካሂዱትን ዴሞክራሲን የማስፈን ሒደት እየመዘንን ጥንቁቅ ድጋፋችን መስጠት የሚገባን ይመስለኛል፡፡

  1. ወሰን ከሌለው የሕዝቦች መብት የሚቀዳ መሠረት ያለው ኢትዮጵያዊነት

ማንነታችንን እንደ ብዝኃነታችን ሰፊ አድርጎ የመተርጎም ነፃነት የሚሰጥ ሕገ መንግሥት አለ (ኖላዊ መልዓከ ድንግል (Horn Affairs))፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተሟላ የሕዝቦች መብቶች መሠረት አድርጎ፣ እነዚህን መብቶች ከማረጋገጥ ውጪ ሌላ ተግባር የሌለው መንግሥት የሚያቋቁም ሕገ መንግሥት አለን፡፡ ዋናው መመዘኛ የሕዝቦች መብቶችን መሠረት ያደረገ ኢትዮጵያዊነት በቀጣይነት የሚገነባ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መግቢያውን በሚገባ በማንበብ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ምን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹን ልጥቀስ፡፡

‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ አገራችን የራሳችን አኩሪ ባህል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት አገር በመሆንዋ፣ ያፈራውን የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፣ መጪውን የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤›› ይላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ትውልድ አግላይና ጠቅላይ ጽንፍ አመለካከትን ወግድ ብሎ ይኼ ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ትጣራለች፡፡

በጠንካራ ክልሎች ኢትዮጵያችን ትለምልም

ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚኖሩት በክልሎች ነው፡፡ ልማትና ዴሞክራሲ የሚገነባውና ሰላም በዋናነት የሚረጋገጠው በእነዚህ ክልሎች የሚደረግ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፈቃዳቸው የሰጡትን ሥልጣን ተጠቅሞ፣ እነሱ መሥራት የማይችሉትን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየሠራ ክልሎችን ማጠናከር ማለት፣ የጋራ እሴቶቻቸውን የማጎልበትና የአንድነት ተምሳሌት የመሆን ጭምር ነው፡፡ አገራችን የምትለማው ሁሉም ማንነቶች እንደ አቅማቸው በተሟላ መንገድ በግንባታው ያለ ምንም ገደብ ሲሠለፉ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለውን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረጉ ማንነቶች፣ እንቅስቃሴዎች፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ብሔርተኝነት፣ ሃይማኖቶች፣ መደቦች፣ ፆታዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎችና ሁሉም በሕግ መሠረት መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግዴታቸውን እየተወጡ በሚያደርጉት ሁለንተናዊ ትግል ነው ኢትዮጵያ የምትለመልመው፡፡ የተወሰኑ አካላት ብቻ አብዛኛውን ጎናችንን በልተው ሰላምና ልማት ማረጋገጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሕዝቦች በሁሉም ዓይነት አደረጃጀት (የሌላውን መብት ሳይነኩ በሕግ መሠረት) መሠለፍ ሲችሉ ነው አገራችን በከፍተኛ ፍጥነት የምታድገው፡፡ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ዲያሌክቲካዊ ቁርኝት አላቸው ማለት፣ ያለ ልማትና ዴሞክራሲ ሰላም እንደማይኖር ሁሉ ያለ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ በጭራሽ የማይታሰቡ ናቸው፡፡ በእኔ አመለካከት ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን መሠረት ያደረገ ደልዳላ ክልላዊ መንግሥት መኖር ኢትዮጵያዊነት ህያው እንዲሆን መሠረት ይጥላል፡፡ ሕዝቦች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቀጥታ የሚገናኙት በቀጭን ገመድ ነው፡፡ ወይም ግንኙነቱ የላላ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ብሎም የሕግ የበላይነት ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲሰፍን፣ ልማት ሲፋጠን፣ ሰላም ሲደላደል እውነተኛ ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ወሳኝ ዕርምጃ ተወስዷል ማለት ነው፡፡ ፖለቲካዊ መብቶቹ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶቹ የተሟላና ደኅንነቱ የተጠበቀ ወጣት ከኢትዮጵያ ውጪ ሌላ አያልምም፡፡

አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለው አግላይ ብሔራዊነት የተስፋፋው ብሔር ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመመሥረቱ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን የተሳሳቱ ይመስሉኛል፡፡ ቅድመ 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ በነፃነት ድርጅቶች ጦርነት ስትናወጥ የነበረችው፣ ደርግ ብሔር ተኮር የሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት ይከተል ስለነበረ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ጠቅላይና ኢዴሞክራቲክ ፌዴራል መንግሥት መኖሩና ልፍስፍስ የክልል መንግሥታት በመኖራቸው ነው፡፡ በምፅዋት የሚተዳድሩ ክልሎች ተይዞ ለሁሉም ነገር አንጋጦ ወደ አዲስ አበባ በማየት ሁሉም ችግሮች ከወደ ፌዴራል እንደሚመጡ አድርገው በመጮህ ኢትዮጵያዊነትን ይሸረሽራሉ፡፡ ጠንካራ ክልል የሕዝቡን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጠብቅ በመሆኑ፣ ሕዝቡም በራሱ የሚተማመንና ሕገመንግሥቱ ያወቀለትን ሥልጣን በሚገባ የሚጠቀም፣ ፌዴራል መንግሥቱ የጠቅላይነት ባህሪ ሲያሳይ በጊዜው የሚያስተካክል መሆን ይገባዋል፡፡ እኛ ጥሩ ብንሠራም ፌዴራል መንግሥት እየቀጣን ነው የሚል ልፍስፍስ ክልል፣ የገዥው ፓርቲ አባል ሆኖ እዚያ ሳይታገል አድልኦ አለ እያለ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጋጭ አጎብዳጅ ክልል ወዘተ፣ አለ፡፡ ብሔር ተኮር ፌዴራል ሥርዓት እንደ ማንኛውም የአስተዳደር ዘይቤ ችግሮች ሊኖሩት ቢችሉም (ፍፁም የሚባል ሥርዓት የለምና)፣ ለ26 ዓመታት ላገኘነው ሰላምና ልማት መሠረታዊ ንጣፍ አስቀምጧል፡፡ የዴሞክራሲ ችግር ሲኖር ነው የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ውስጥ የሚገባው፡፡

ለእኔ ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት አያስፈልግም ማለት ብሔር ብሔሮች የሉም፣ ወይም ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር አይፈልጉም እንደ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መደበላለቅ በሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መርሐ ግብሮች የብሔሮች ማንነት ጠፍቷል ማለት አይደለም፡፡ እንኳን የእኛ መስፍናዊ ሥርዓት ከልማት ጠፍሮ ያስቀራትና በጣም ዝቅተኛ የሆነ ታህታይ መዋቅር (Infrastructure) ያላት አገር፣  በኢንዱስትራላይዜሽን አብዮት ያለፉና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተካኑ በጣም የረቀቀ የኮሙዩኒኬሽንና የትራንስፖርት ሥርዓት ያላቸው እንደ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ቤልጅየም፣ ስፔን፣ ወዘተ ባሉ አገሮች ብሔሮች ማንነታቸውን እየተጠናከረ እንጂ እየተዳከመ አልሄደም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬና ነገ›› ቁጥር 3 (2008፡90-91) አሰፋ እንደሻው ስለብሔርተኝነት ህልውና እንዲህ ይላል፡፡

‹‹ዛሬ ማንም፣ የትም ያለ ዜጋ ሁሉ ብሔርና ብሔረሰብን እንደ ቋሚ መገልገያዎች አድርጓቸዋል፡ (አናውቅም አልሰማንም፣ አንቀበልም፣ አሻፈረን ከሚሉት በጣም አነስተኛ ክፍሎች በስተቀር)›› ቀጥሎም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ ጥንቅር በተለይ ብሔረሰባዊ ክፍፍል በዓለም ላይ የተለየና አስቸጋሪ ተደርጎ ይናፈሳል፡፡ የትም አገር የሌለና ለውድቀቷ የሚያመቻች ነው ብለው የሚያምኑ በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን የብሔረሰቦች ህልውና ሰዎች ባሻቸው መልክ የሚፈጥሩትና ቀጥቅጠው የሚሠሩት ክስተት አይደለም››

በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ብሔረሰቦች በሚመለከትም እንዲህ ይላል፡፡

‹‹የአፄ ቴዎድሮስ ዝርያዎች የሆኑት ቅማንቶች ጠፉ፣ አማራው ውስጥ ገብተው ቀለጡ ከተባለ ከስንት ዓመታት በኋላ እንደገና ለማንሰራራት መሞከራቸው ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ባለሥልናት እኩይ ቁስቆሳ የተነሳ አድርገው፣ የጥያቄያዎችን ተገቢነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉት በርካታ ናቸው፡፡ ባለሥልጣናት ቆሰቆሱ፣ አልቆሰቆሱ ቅማንትነታቸውን መነሻ አድርገው የራሳቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና አስተዳደር በጃችን እናስገባለን ቢሉ ምንድነው ጥፋቱ? አንድ ሰው ኩናማ ነው ሌላ አፋር ነው ወዘተ ብሎ ማመልከት በሬ ቀንድ አለው፣ ላም ጡት አላት፣ ሰዎች በአብዛኛው ሁለት እጅ አላቸው ከሚሰኘው ትረካ የሚለይ አይደለም፤›› በማለት ብሔረሰቦችን ህልውና ይገልጻል፡፡ ብሔሮች በየጊዜው እየፈረሱና እየተገነቡ (De-Constructed And Constructed) የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ተነፃፃሪ ነፃነታቸውና ህልውናቸው አላቸው፡፡ ከ50 ዓመት በፊት የተጻፈላቸው ብሔርና ብሔሮች ከ1983 ዓ.ም. በፊት ‹‹ነፃ አውጪ›› ድርጅት የነበራቸውና በ1987 ዓ.ም. በሚገባ የተደራጀ ብሔር ብሔረሰቦች የሉም፣ አልሰማሁም የሚል ድንቁርናና ድርቅና ምን ይባላል? በድሮ መኖር፣ ወይም ቆሞ ቀር አመለካከት ማለት ይኼ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ያወቀላቸውን መብቶች ተጠቅመው በተወሰነ መልኩ ማጣጣም ቢጀምሩም፣ በጠቅላይ ፌዴራል መንግሥት በመነጠቁና ልፍስፍሶቹ የክልል መንግሥታት መከላከል ስላልቻሉ፣ አሁንም ፌዴራሊዝሙ ከዚህ በላይ ይለጠጥልን የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሕዝቦች ፈቃድ የታወጀ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እስኪ ይሁን ተብሎ ሕዝበ ውሳኔ ቢደረግ የለም ብሔር ተኮር የፌደራል ሥርዓቱን አንፈልገውም፣ እንደ ብሔር በራስ መተዳደር በዝቶብናልና ይቀነስልን፣ ኢትዮጵያዊ ባህልና ቋንቋ እንጂ የራሳችን የሚዳብር ቋንቋና ባህል የለንም የሚሉ ይመስላችኋል? ኢትዮጵያዊነት የሚፈካው የብሔር ብሔረሰቦች መብት በተሟላ መንገድ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ጠንካራ ክልሎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ሥጋት የሚሆን ከሆነ ኢትዮጵያ አንድ አጉራ ዘለል የጦር አበጋዝ ጠፍጥፎ እንደሠራትና በቀላሉ እንደምትፈርስና እንደምትበተን ማሰብ ኢትዮጵያን ማሳነስ ነው፡፡ ወይም ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ ‹‹የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት›› በሚል በሆርን አፌይርስ ‹‹ይህች አገር ደግሞ በሁላችን ፈቃድና መተማመን የምትገነባና እየተገነባችም የምታብብ አገር ናት፡፡ ነሸጥ ያደረገው በአንድ ጀንበር ተነስቶ የሳላት ወይም የሚስላት ንግርትም አይደለችም፤›› የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን መሠረት አድርገን የኢትዮጵያችንን እንደ አዲስ እንገንባ ነበር፡፡ የዛሬና የወደፊት ቁልፍ እሴታችን ማንነታችንና ነፃነታችን በዴሞክራሲ ባህላችን ይወሰናልና፡፡ ዓለማየሁ ተረዳ (2008)፣ ‹‹… ጠቀመም ጎዳም ነባር እሴቶቻችን ማፍረስ ቀላል ነው፡፡ ምትክ የሚሆኑ አዳዲስ እሴቶች መፍጠር ግን ከባድ ነውና ልታስቡበት የሚገባ ይመስለኛል፤›› እንዳለው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕዴግ ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡