Skip to main content
x
ትውፊታዊው ሩጫ

ትውፊታዊው ሩጫ

የዛሬ 17 ዓመት ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በተሳታፊዎች ቁጥርና በሚያበረክተው ማኅበራዊ አስተዋጽኦ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ይህ ታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው ባሻገር ብዙዎችን በአንድ መድረክ የሚያሰባስብ የመዝናኛ ትውፊት እየሆነ መምጣቱ በሩጫው የሚሳተፉም ሆነ ሌሎች የሚስማሙበት ሆኗል፡፡

ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ በዘንድሮው ዓመት ክንውኑ አዳዲስ አሸናፊዎችን ያስገኘ ከመሆኑ ባሻገር፣ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሁለት ተሳታፊዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የግለሰቦቹ ኅልፈተ ሕይወት ምክንያት እየተጣራ ቢሆንም፣ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ጠንከር ያሉ ልምምዶችን መከወን አስፈላጊ እንደሆነ ጠቋሚ ክስተት ተደርጎም ተወስዷል፡፡

በተለይ ከውድድሩ መከናወን ከቀናት በፊት ልምምድን አጠንክሮ ከመሥራት ባሻገር በቂ ዕረፍት ማድረግና ሌሎች ሰውነትን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብ፣ ዋነኛው ነገር መሆን እንደሚኖበት የእነዚህ ሁለት ግለሰቦች ሕይወት ማለፍ አስተማሪ እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ነገሮች ላይ አተኩሮ በመሥራት ይህን የአገሪቱን አንዱ መገለጫ እየሆነ የመጣውን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር መዝናኛቱን ጠብቆ እንዲቀጥልና ለኅብረተሰቡ ጤናም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት፣ ተሳታፊዎችም ጊዜ ወስደው ልምምድ እንዲያደርጉና ጤናቸውን ጠብቀው በየዓመቱ ለሚደረገው ለዚህ የሩጫ ድግስ ደርሰው መታደም ይችሉ ዘንድ የስፖርት ማዘውተርን ጠቀሜታ አዘጋጆቹ ቀደም ብለው በማስተማር ዘርፈ ብዙ ግብ ሊያሳኩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ በርካታ ናቸው፡፡

ኬንያዊቷ የኢሊምፒክ የዓለም ሻምፒዮኗ ቪቪያን ቼይሪዎት በክብር እንግድነት በተገኘችበት ውድድር በሴቶች ዘይኔባ ይመር (ንግድ ባንክ) በወንዶች ሰሎሞን በረጋ (ደቡብ) ያሸነፉ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 100,000 ብር ተሸልመዋል፡፡ የትግራይዋ ግርማዊት ገብረዝሄርና የመሰቦዋ ፎቴን ተስፋይ፣ የመሶቦው ሞገስ ጥዑማይና ዳዊት ፈቃዱ (በግል) ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል፡፡

ኅልፈተ ሕይወታቸው የተሰማው ሁለቱ እነማን ናቸው?

ለአዲስ አበባና አካባቢ ዓመታዊ ትውፊት እየሆነ ባለው ዓመታዊ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድ 44,000 ታዳሚዎችን አሳትፏል፡፡ ይሁንና ከተሳታፊዎቹ መካከል ኅልፈት ሕይወታቸው ማለፉ የተነገረላቸው ሁለቱ ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ከስፖርቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው ታውቋል፡፡

በቀድሞ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በ1951 ዓ.ም. ተወልደው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ምሥራቅ አጠቃላይ (የቀድሞው አስፋ ወሰን ኮምፕሬ ሄንሲቭ) ሁለተኛ ደረጃ መከታተላቸው የሚነገርላቸው አቶ መኰንን አምዴ ኅልፈታቸው ከመሰማቱ አስቀድሞ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በሰውነት ማጎልመሻ በ1971 ዓ.ም. በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ ከ1972 እስከ 74 ዓ.ም. በቦንጋ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሰውነት ማጎልመሻ መምህርነት ከዚያም ወደ ጅማ ከተማ በማቅናት በጅማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 1976 ዓ.ም. ድረስ በተመሳሳይ የትምህርት ክፍል አገልግለዋል፡፡ አቶ መኰንን ወደ ቀድሞ ሶቭየት ኅብረት በ1976 ዓ.ም. በማቅናት በሰውነት ማጎልመሻና ስፖርት አስተዳደር ለአምስት ዓመት ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪ (ኤምኤ) አግኝተው ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ መምህርነት፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በስፖርት ምርምርና ጥናት በማድረግ እስከ ኅልፈታቸው ድረስ በማገልገል ላይ እንደነበሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው ያስረዳሉ፡፡

ሌላው የቀድሞ ቦክሰኛ አቶ ፀጋ አያሌው ሲሆኑ፣ እሳቸውም በአዲስ አበባ አዋሬ ሠፈር በ1966 ዓ.ም. ተወልደው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ለቦክስ ስፖርት በነበራቸው ጽኑ እምነት በክለብ ደረጃ ለሕዝብ ማመላለሻ በ49 ኪሎግራም፣ ክብደት ምድብ ከዚያም ለባሕር ኃይል (መልሕቅ) ስፖርት ክለብ በዕድሜያቸው በተለያየ ኪሎ ግራም በአዲስ አበባና በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ሻምፒዮናዎች አሸናፊ መሆን የቻሉ፣ ከዚያም የአዲስ አበባ ምርጥ እስከመሆን ደረጃ በቦክስ የሚታወቁ ተወዳዳሪ እንደነበሩ ከሕይወት ታሪካቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡