Skip to main content
x
ለባለቤቶቹ ጥያቄ እጁን የሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

ለባለቤቶቹ ጥያቄ እጁን የሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የሴት አመራሮችን ለኃላፊነት በማብቃትና የተለያዩ ደንብና መመርያዎችን በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ኅዳር 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በአራራት ሆቴል በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ በኦሊምፒክ ለጥቁር አፍሪካውያት በፈር ቀዳጅነቷ የምትታወቀው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉን የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት እንድትሆን በሙሉ ድምፅ ተቀብሏታል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከወር በፊት መደበኛውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በቢሾፍቱ ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በተደረገው መደበኛ ጉባዔ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሚመራባቸው የተለያዩ መመርያ ደንቦች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ያቀረባቸው አጀንዳዎች፣ በዋናነት ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

 የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጨምሮ ሌሎች በአገሪቱ የተለያዩ ስፖርቶችን እንዲያስተዳድሩ የተቋቋሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ መዋቅራዊ ይዘታቸው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ በክልሎች ውክልና ላይ የተመሠረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ አደረጃጀት ውክልናው በሙያዊ ብቃት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛል፡፡

      ይህንኑ ጥያቄ በማንሳት የእግር ኳስና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም የብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ትልቁ የሥልጣን አካል ተደርጎ በሚጠቀሰው ጠቅላላ ጉባዔ በአመራርነት ሙሉ በሙሉ በወንዶች የበላይነት እንዲሁም ለሁለቱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ደግሞ በባለቤትነት የሚጠቀሱት ክለቦች በድምፅም ሆነ በአመራርነት ተሳትፎ ሳይኖራቸው መቆየቱ የችግሩ አንድ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡

      በአትሌቲክሱ እስከ አራራቱ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉበዔ ድረስ ክለቦች ምንም ዓይነት ድምፅ ሳይኖራቸው ቆይቷል፡፡ በእግር ኳሱ  ግን አንድ አንድ ድምፅ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ ይሁንና ፌዴራላዊ የሥርዓት አወቃቀርን መነሻ የሚያደርጉ ሁለቱን የከተማ አስተዳደር ጨምሮ የክልል ፌዴሬሽኖች ክለቦች በየክልሎቻቸው ካልሆነ ቀጥታ ድምፅ ሊኖራቸው አይገባም በሚል በተለይም አዳጊ ክልሎች አሁንም ድረስ አሠራሩን በጽኑ በመኮነን ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ገብቶ የቆየው አትሌቲክሱ፣ በጠቅላላ ጉባዔው የድምፃቸው ጉዳይ ክለቦቹ ባሰቡት ልክ ባይሆንም ይሁንታ እያገኘ የመጣ ይመስላል፡፡ በአራራት ሆቴል በተደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ካስተላለፈው ውሳኔ በተጨማሪ ከአምስት ክለብ በላይ ያላቸው ክልሎች በጠቅላላ ጉባዔ ሁለት ሁለት ድምፅ እንዲኖራቸው ወስኗል፡፡

ምንም እንኳ ክለቦች በጉባዔ የሚኖራቸው ሚና በዚህ መልኩ ቢጠናቀቅም፣ ቀደም ሲል በዚሁ ጉዳይ የተቃውሞ ድምፁን ሲያሰማ የቆየው የኦሮሚያ ክልል ክለቦች ከሁለት በላይ ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል፣ የለም ክለቦች በጉባዔ ድምፅ ሊኖራቸው አይገባም በሚል ከሚቃወሙት ክልሎች ጋር ውሳኔውን ተቃውሞታል፡፡

ክለቦች በጉባዔ ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል፤ አይገባም ከሚለው የክልሎች እሰጣ ገባ ጎን ለጎን የጉባዔውን ሙሉ ድጋፍ ባገኘው ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣቱ ሒደት በአብዛኛው በጉባዔው ይሁንታ ያገኘ ነበር፡፡

የጉባዔውን ሙሉ ድጋፍ ያገኘው የሴቶች አመራርነት ሰጪ ጉዳይ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የአባል አገሮች ፌዴሬሽኖች እንዲተገብሩት ከሚጠይቃቸው አሠራሮች አንዱና የመጀመርያው ነው፡፡

እንደ አይኤኤኤፍ ከሆነ፣ ሴቶች በማናቸውም የስፖርት ተቋማት ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባው የአመራር ሰጪነት ሚና ቢያንስ 30 በመቶ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ መሠረት አሁን ባለው አካሄድ ሴቶችን ለዚህ ኃላፊነት በማብቃት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በአስቸኳይ ጉባዔው ከተመረጡት ሁለት የሴት አመራሮች ማለትም ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ከኦሮሚያና ወ/ሮ ፎዚያ እድሪስ ከአፋር ክልል ከተመረጡት በተጨማሪ በአትሌቶች ተወካይነት በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የተካተተችው መሠረት ደፋርን ጨምሮ ሦስት ሴቶች በፌዴሬሽኑች የኃላፊነት ቦታ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡