Skip to main content
x
ትምህርት ዓይነ ስውርነቴን ወደ በጎ አጋጣሚ የቀየረልኝ ቁልፍ ነው

ትምህርት ዓይነ ስውርነቴን ወደ በጎ አጋጣሚ የቀየረልኝ ቁልፍ ነው

በየትነበርሽ ንጉሤ

የአምስት ዓመት ልጅ ሆኜ ነበር ዓይነ ስውር የሆንኩት፡፡ ለቤተሰቦቼ እጅግ አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ ባደግኩበት ገጠራማ መንደር የነበረው  ድንጋጤ ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም በዚያች መንደር ዓይነ ስውር ለመሆኔ ሰበቡ የእግዜር ዕጣ ወይም ደግሞ አንዳች እርግማን እንደነበር ነው የታመነው፡፡

በመንደርተኞቹ ዓይን እንደኃጢአተኛ መቆጠር ብቻ ሳይሆን ያለኝን ዋጋና ስፍራም ጭምር ነበር ያጣሁት፡፡ የአንዲት በገጠር የምትኖር ሴት ልጅ ዕጣ ፈንታ ማግባትና ለቤተሰቦቿ ጥሎሽ ረብጣ ማስገኘት ነው፡፡ እናም እኔን ማንም ወንድ ሊያገባኝ እንደማይፈልግ እርግጥ ነበር፡፡

ይህ ፍፁም የመሰለ መጥፎ ዕጣ በሕይወቴ ለትልቁ መልካም አጋጣሚ በር ከፈተልኝ፡፡ እናቴና አያቴ በልጅነቴ ለባል ሳይሆን ለትምህርት አጩኝ፡፡ ከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ሻሸመኔ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወደሚገኝ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ላኩኝ፤ እኔም ትምህርትን የሙጥኝ አልኩ፡፡

ከከፍል ጓደኞቼ ከፍተኛውን ውጤት የማስመዘግበው እኔ ሆንኩ፡፡ ጓደኞች አፈራሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ገብቼም በኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ ሴት ዓይነ ስውራን የሕግ ባለሙያዎች መካከል ሆንኩኝ፡፡

ዛሬ ላይ ላይት ፎር ዘ ወርልድ ለተባለ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እየሠራሁ ለአካል ጉዳተኞች መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምፄን እያሰማሁ እገኛለሁ፡፡

የግል ታሪኬ ደስ የሚልና አነቃቂ ቢሆንም ምን ያክል ያልተለመደ እንደሆነና መታደል የታከለበት እንደሆነ ሰዎች ልብ እንዲሉት እፈልጋለሁ፡፡ ለበርካታዎች በደሃ አገር ለሚኖሩ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘትና ትምህርት ቤት መሄድ ይዞት የሚመጣውን መልካም አጋጣሚ ማግኘት እጅግ እጅግ ከባድ ነው፡፡

ይህን በቁጥር ማስረጃ አስደግፎ ማስረዳት ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ከአካል ጉዳተኞች ጋር የተያያዙ መረጃዎች ማግኘት ሌላው ትልቁ ችግር ነውና፡፡ ሆኖም  በአዳጊ አገሮች የሚኖሩ 32 ሚሊዮን የሚጠጉ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ትምህርት ቤት እየሄዱ እንዳልሆነ ይገመታል፡፡ ይህ ቁጥር ከስዊድን ሕዝብ አጠቃላይ ብዛት ሦስት እጥፍ በላይ ነው፡፡

በተለይ ደግሞ በገጠር ለሚኖሩ አካል ጉዳተኛ ልጃገረዶች ሕይወት እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ከሴትነታቸው ጋር አካል ጉዳታቸው ሲጨመር ሊያልፉት የሚገባቸው መሰናክልና እንቅፋት በእጅጉ ብዙ እና አታካች ነው፡፡ ሁሌም በሕይወት ሠልፍ ውስጥ ከመጨረሻዎቹ መጨረሻ የሚገኙት አካል ጉዳተኛ ሴቶች ናቸው፡፡ የእነርሱን ታሪክም በደንብ አጥርቼ አውቀዋለሁ፡፡ ቤት ውለው ታናናሽ ወንድምና እህቶቻቸውን እንዲንከባከቡ የሚወሰንባቸው እኒሁ ሴቶች ልጆች ናቸው፡፡

እነርሱን በአግባቡ ለማስተማር የሚረዱ ግባዓቶች የሉንም በሚል እና ሌላም ምክንያት ‹‹መስማት የተሳናቸውንና ዓይነ ስውራን ተማሪዎችን አንቀበልንም›› በሚል ከትምህርት ቤት ደጃፍ የሚመለሱት ወላጆች የእኒሁ ሴቶች ወላጆች ናቸው፡፡ ክራንች አሊያም ደግሞ ዊልቼር በማጣት ወደ ትምህርት ቤት የሚወስደውን ወጣ ገባና ምቹ ያልሆነ  መንገድ ማቆራረጥ ያልቻሉት እኒሁ ሴት ልጆች ናቸው፡፡

በእፍረትና መሸማቀቅ አሊያም ሊደርስባቸው ከሚችል መደፈርና የኃይል ጥቃት ለመጠበቅ በሚል በቤተሰቦቻቸው ከቤት እንዳይወጡ በር የሚዘጋባቸው እኒሁ አካል ጉዳተኛ ሴት ልጆች ናቸው፡፡

በአዳጊ አገሮች አካል ጉዳተኛ ልጆች የሚደርስባቸው መገለል ደረጃውና ዓይነቱ የከፋ ነው፡፡ ይኸው ማግለልም የመንግሥታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን የማሳካቱን ጥረት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ጉዳዩ ሊሰጠው የሚገባውን ያህል ትኩረት እያገኘ አለመሆኑ ያሳስባል፡፡

በዓለም ዙሪያ አካል ጉዳተኞች ከአንድ ቢሊዮን በላይ ብንሆንም ከፖለቲካው፣ ከመገናኛ ብዙኋኑ ከንግድ ተቋማትና ከሥራዎች እንድንገለል መሆኑ እንደሌለን ያክል እንድንቆጠር አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ዲሴምበር 3 ቀን ማለትም ኅዳር 24 ቀን በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ቀን ድምፃችንን ለማሰማት እጅግ ጠቃሚ ቀን የሚሆነው፡፡

በአካል ጉዳተኛ ልጆች ላይ የሚደርሰው መገለል ሊቆም ይገባል፡፡ ሁሉም ሕፃናት እኩል የትምህርት ዕድል ሊያገኙ ይገባል፡፡ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው አካል ጉዳተኞችም ድንቅ ሥራ ሠርተው ማሳየት ይችላሉ እያልን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ልንናገር ይገባል፡፡

አንድ ነገር ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ልሞክር፡፡ ምንም እንኳ እኔ ባልፍበትም በተለይ አካል ጉዳተኞች ለብቻቸው ለማስተማር የሚቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ለችግሩ መፍትሔ እንዳልሆኑና ያንንም እንደ መፍትሔ እያቀረብኩ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ፡፡ እነዚህ ‹‹ልዩ›› ትምህርት ቤቶች ለሁሉም ተደራሽ አይደሉም፡፡ ከገንዘብም አንፃር  አዋጭነታቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደ መንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መረጃ እነዚህ ልዩ ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን አካተው ከሚያስተምሩ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነፃፀሩ በአሥራ አምስት  እጥፍ ውድ ናቸው፡፡

የመጨረሻ ግባችን ከልዩ ትምህርት ቤቶች ይልቅ ሁሉም ልጆች፤ ወንዶችም ሴቶችም፣ አካል ጉዳተኞች ሆኑም አልሆኑ በአንድ ክፍል ውስጥ እኩል የሚማሩበት የአካቶ ትምህርት ሥርዓትን መፍጠር ሊሆን ይገባል፡፡ አካታች የትምህርት ሥርዓት የአካል ጉዳተኞች መገለል እንዲያበቃ ለማድረግና ከትምህርት ቤት ውጭ ያሉ ሕፃናትን ቁጥር በእጅጉ ለመቀነስ የሚያስችለን ሁነኛ መንገድ ነው፡፡

ሆኖም በቅርብ ይፋ የሆነው ‹‹ኮስቲንግ ኢኪውቲ›› የተሰኘ ጥናት የሚያሳየው ለአካቶ ትምህርት ማስፈፀሚያ ከመንግሥታት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች፣ እንደ አውሮፓ ኅብረትና ‹‹ግሎባል ፓርተነርሺፕ ፎር ኢጁኬሽን›› ያሉ የረዥም ጊዜ የአካቶ ትምህርት ደጋፊዎችም ጭምር የሚመድቡት ገንዘብ እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ነው፡፡

እነዚህ የለውጡ አቀጣጣይ መሆን የሚገባቸው ተቋማትና አካላት የበጀት አመዳደባቸውንና ቅድሚያ ስለሚሰጡት ጉዳይ በድጋሚ ማሰብ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡

በአዳጊ አገሮች የሚገኙ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ወጣት አካል ጉዳተኞች  ለመማርና ተቀጥረው ለመሥራት ፈቃደኞች ቢሆኑም ይህን ማድረግ በሚጠይቀው ውድ ዋጋ ምክንያት ፈቃዳቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡

ነገር ግን እንደባንግላዴሽ፣ ካምቦዲያ፣ ህንድ፣ ኔፓልና ፊሊፒንስ ያሉ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው በአካል ጉዳተኞች ትምህርትና ሥልጠና ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት አዋጭነት ጉዳት ለሌለባቸው ተማሪዎች ከሚፈሰው ሙዓለ ንዋይ አዋጪነቱ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ ይበልጣል፡፡

ስለሆነም ዋነኛ ለጋሽ ተቋማት ከትምህርት ጋር ለተያያዙ ፕሮግራሞች ለሚሰጡት በጀት አካታችነትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ቢወስዱ ከፍተኛ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች መንግሥታት ለትምህርት የሚይዙትን በጀት ለመጨመር ቢስማሙና ትምሀርት ቤቶቻቸው ሁሉ አካታችና ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ አካል ጉዳተኛ ልጆች ከትምህርት ክፍሎች እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ቢፈጥሩ ትልቅ እመርታ ልናይ እንችላለን፡፡

አካል ጉደተኛ ልጆች እኩል የሆነ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ብናደርግ ምን ያህል አቅም እንደምንፈጥር አስቡት እስቲ? እኔ ትምህርት ቤት መሄዴን እንደ ዕድለኝነት እቆጥረዋለሁ፡፡ ቀጣይ ትውልድ የሆኑት አካል ጉዳተኛ ልጃገረዶችና ሴቶች ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ትምህርትን ለጥቂቶች ብቻ እንደሚሰጥ ልዩ ዕድል ሳይሆን እንደ መሠረታዊ መብታቸው የሚቆሙለት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዋ የትነበርሽ ንጉሤ በላይት ፎር ዘ ወርልድ የአካል ጉደተኞች ጉዳዮችና ፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪ፣ እንዲሁም የራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት 2017 ሎሪየት ተቀብለዋል፡፡  ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡